FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Saturday, October 5, 2013

“አንድነት” ፓርቲ የአዲስ አበባ አስተዳደርና ፖሊስን እከሣለሁ አለ

“አንድነት” ፓርቲ የአዲስ አበባ አስተዳደርና ፖሊስን እከሣለሁ አለ
የ3 ወሩ ህዝባዊ ንቅናቄ “ዋጋ የተከፈለበት” ነው ብሏል

ባለፉት ሶስት ወራት “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚል መሪ ቃል የመጀመሪያ ዙር ህዝባዊ ንቅናቄ ሲያደርግ የቆየው አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ፤ ባለፈው እሁድ የማጠቃለያ ሰልፉን ሲያደርግ ደርሶብኛል ላለው የሞራልና የንብረት ጉዳት የአዲስ አበባ አስተዳደርና ፖሊስን በህግ እንደሚጠይቅ አስታወቀ፡፡ አንድነትና 33ቱ ፓርቲዎች ከትላንት በስቲያ በአንድነት ፅ/ቤት በሠጡት መግለጫ፤ የህዝባዊ ንቅናቄ ማጠቃለያ ሰልፉን መስከረም 19 አዲስ አበባ ላይ ለማካሄድ እንደምንችል የሚያረጋግጥ የእውቅና ደብዳቤ የከተማ መስተዳደሩ የከንቲባ ፅ/ቤት ቢሰጣቸውም፣ በእጅ አዙር ሠልፉ በመስቀል አደባባይ እንዳይደረግ መከልከላቸውን፣ ከህግ ውጪ በፀጥታ ተቋማት አካባቢ ሰልፉ እንዲከናወን መገደዳቸውንና ቅስቀሣ እንዳይደረግ መታገዳቸውን አመልክተዋል፡፡
ፖሊስም ህገ መንግስቱንና ህዝቡን መጠበቅ ሲገባው “ለመቀስቀስ፣ ፖስተር ለመለጠፍና በራሪ ወረቀቶችን ለማሠራጨት ፈቃድ ያስፈልጋል፣ ትዕዛዝ አልደረሠንም” በማለት ህገ መንግስታዊ መብቶችን ጥሷል ያሉት ፓርቲዎቹ፤ የአንድነትን ሊቀመንበር ጨምሮ 101 አባላትን ከማክሠኞ እስከ እሁድ ማሠሩንም ገልፀዋል፡፡ “ፖሊስ ለህግ የበላይነት መቆም ሲገባው በድብቅ ለተሠጠው ትዕዛዝ ተገዢ በመሆኑ ጉዳዩን ለህግ እናቀርባለን” ብለዋል - ፓርቲዎቹ፡፡ የፓርቲው አመራር አባል አቶ አስራት ጣሴ በተለይ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ቃለምልልስ፤ ስለ ሠላማዊ ሠልፍና ህዝባዊ ስብሠባ ማድረግ የወጣው አዋጅ “ማንኛውም ሠላማዊ ሠልፍ ወይም ህዝባዊ የፖለቲካ ስብሠባ በጦር ሃይሎች፣ በጥበቃ እና የህዝብን ሠላምና ደህንነት በሚቆጣጠሩ የመንግስት የስራ ክፍሎች አካባቢ 300 ሜትር ክልል ውስጥ ሊደረግ አይችልም” እንደሚል ጠቅሠው፤ የአዲስ አበባ መስተዳደር የአዋጁን አንቀፅ በመጣስ፣ እነዚህ ተቋማት በሚገኙበት ጃንሜዳ እንድንሰባሠብ ሊያስገድደን ሞክሯል ብለዋል፡፡ ፓርቲው ያቀረባቸውን ዘጠኝ ያህል አማራጭ ቦታዎች በመከልከል አዋጁን በጣሠ መልኩ በጃንሜዳ አድርጉ የሚል ትዕዛዝ ማስተላለፉ ከፍተኛ የህግ ጥሠት መሆኑን የጠቀሱት አቶ አስራት፤ ፓርቲው ያቀረባቸውን አማራጭ ቦታዎች ገምግሞ አለመፍቀዱም ሠላማዊ ሠልፍ የማድረግ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌውን የጣሠ በመሆኑ በአስተዳደሩ ላይ ክስ እንመሰርታለን ብለዋል፡፡
ፓርቲው በፖሊስ ተቋማት ላይ የሚያቀርበው ክስ የተሻሻለውን የፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ መሠረት አድርጐ ነው ያሉት አቶ አስራት፤ አዋጁ የህዝብን የፖለቲካ ግንዛቤ ማዳበር፣ የፓርቲውን አላማ ለህዝብ ማስረፅ እንዲሁም ዜጐች በሃገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሣትፎ እንዲኖራቸው መቀስቀስ… የፖለቲካ ፓርቲ የዕለት ተዕለት ተግባራት መሆናቸውን እንደሚገልጽ ጠቅሰው፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ አዋጁን በመጣስ በዚህ ሠላማዊ ሠልፍ ብቻ ከ100 በላይ ሠዎችን አስሯል ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መኪና፣ ሞንታርቦና ጀነሬተር የመሣሠሉትን የፓርቲው ንብረቶችን ያለ አግባብ ስላገደ፣ በሁለቱም የመብት ጥሰቶች እንከሳለን ብለዋል፡፡ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳየች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል ከእሁዱ ሠላማዊ ሠልፉ በኋላ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሠጡት መግለጫ፤ “ፓርቲው ባካሄደው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ በሽብር ወንጀል ተከሠው የተፈረደባቸውን ግለሠቦች አቋም ማንፀባረቁና ማወደሱ የህግ መዘዝ ያመጣል፤ ፓርቲው ለሚመጣው የህግ መዘዝ ዝግጁ መሆን አለበት፡፡” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
አቶ አስራት የአቶ ሽመልስ ከማልን መግለጫ በተመለከተ ሲናገሩ፤ “የህግ ጥሠት የፈፀሙት የመንግስት አካላት ስለሆኑ መከሠስ ያለባቸው እነሡ ናቸው፤ ከዚያ የተረፈው ዝም ብሎ ማስፈራራት ነው፤ እኛ ግን በሃገራችን አንፈራም፣ ልንፈራም አይገባም” ብለዋል፡፡ ከሠኔ 12 ቀን 2006 ጀምሮ እስከ መስከረም 19 ቀን 2006 በቆየው የሶስት ወር ህዝባዊ ንቅናቄ ፓርቲው በጐንደር፣ በደሴ፣ በባህር ዳር፣ በአርባ ምንጭ፣ በጅንካ፣ በአዳማና በፍቼ አባሎቹ እየተደበደቡና እየታሠሩም ቢሆን የተቃውሞ ሠልፎቹን ማካሄዱን ጠቅሶ፤ በመቀሌና በባሌ ሮቤ ጫናውን መቋቋም ባለመቻሉ ሣይካሄድ መቅረቱን አመልክቷል፡፡ በከፍተኛ ጫና ውስጥ ታልፎ የተደረገው ህዝባዊ ንቅናቄ የእስር፣ የድብደባ፣ የሞራል ጉዳትና የንብረት ማጣት ዋጋ የተከፈለበት እንደሆነ ፓርቲው አስታውቋል፡፡

http://www.addisadmassnews.com

No comments:

Post a Comment