የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትምህርት አቆሙ
ኢሳት ዜና:-የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከአስተዳደሩ ጋር የብቃት መመዘኛ ፈተና ዙሪያ መግባባት ባለመቻላቸው ትምህርት ማቆማቸው ተሰማ፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ተግባራዊ እንዲደረግ ያስተላለፈው ውሳኔ በተማሪዎቹና በዩኒቨርሲቲው መካከል አለመግባባትን በመፍጠሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የዩኒቨርሰቲውም የአራተኛ ዓመት ተማሪዎች ግቢ ለቀው መውጣታቸውን ለኢሳት የሚደርሱ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ተማሪዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ የብቃት ማረጋገጫ እንዲወስዱ ሲጠይቃቸው ተማሪዎቹ በቂ የዝግጅት ጊዜ ይሰጠን ብለው በመጠየቃቸው አለመግባባቱ ተከስቷል፡፡ የብቃት ማረጋገጫ ፈተናውን ለመውሰድ በቂ ጊዜ ይሰጠን ብለን ብንጠይቅም ዩኒቨርሲቲው በአጭር ቀናት ውስጥ እንድንወስድ አስገድዶናል በማለት ተማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ ለሶስት ዓመት ያህል የተማሩትን ትምህርት በቂ ዝግጅት ሳያደርጉ በሁለት ቀናት ውስጥ የብቃት መመዘኛውን ውሰዱ መባሉ አግባብነት የሌለው ነው የሚሉት ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ግን ሙሉ ለሙሉ መፈተን እምቢ እንዳልን አስመስሎ በመግለጽ ላይ ነው ሲሉ ተማሪዎቹ ይናገራሉ፡፡
በተማሪዎቹና በአስተዳደሩ የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ ፌደራል ፓሊስ ያደረገውን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ተማሪዎች ግቢውን ጥለው መውጣታቸው ለኢሳት የደረሱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ በአምስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ በአክራሪነትና ፅንፈኝነት ዙሪያ ስልጠና ለመስጠት የተዘጋጀ ፕሮግራም ባለመግባባት መበተኑን ምንጮች ለኢሳት አስታውቀዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በአክራሪነት ዙሪያ ለመወያየት ፈቃደኝነታቸውን ማሳየት ባለመቻላቸውና ሙስሊም ተማሪዎች ለጁማ ሶላት መውጣት በመሞከራቸው በግዳጅ ወደ ስብሰባ እንዲሄዱ ተሞክሮ እንደነበር ታውቋል፡፡
No comments:
Post a Comment