FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Monday, October 21, 2013

ከእሁድ እስከ እሁድ

(የሳምንቱ አጫጭር ዜናዎች ከተለያዩ ምንጮች)

bole1


ማንን እንመን ?
ኢህአዴግ ሶማሌ፣ ትህዴን “ኢትዮጵያዊያን ናቸው” ይላል
በቦሌ ክፍለ ከተማ በቤት ውስጥ ፈነዳ በተባለው ፈንጂ ህይወታቸው እንዳለፈ የተገለጸው ሁለት የሶማሌ ዜጎች እንዳልሆኑ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ትህዴን/ አስታወቀ። በፈንጂው የሞቱት ሁለት ሰዎች ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ ስማቸውም “ምክትል ኢንስፔክተር ሞላ መላኩ የተባሉ የፖሊስ አባልና አቶ ሞገስ አስቻለው የተባሉ ሲቪል ናቸው” ሲል የገለጸው ትህዴን የሟቾቹ ስም በመታወቂያ መረጋገጡን አመልክቷል። የመታወቂያውን ቅጂ ግን በገጹ አላተመም። ከአደጋው ጋር በተያያዘ በስፍራው ታይታችሁዋል በሚል በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መታሰራቸውን ያመለከተው ዜና የሶስት ሰዎችን ስም ይፋ ያደረገው ኦክቶበር 19 ቀን 2013 ነው።
በሌላ በኩል ኦክቶበር 16 ለንባብ የበቃው ሪፖርተር ጥቅምት 3 ቀን 2006 ዓ.ም. በቦሌ ክፍለ ከተማ ሩዋንዳ ማዞሪያና ቦሌ ሚካኤል መግቢያ አካባቢ በቦምብ ፍንዳታ ሕይወታቸው ያለፈው ሁለት ሶማሊያውያን ሽብርተኞች መሆናቸውን ማረጋገጡን፣ የፌዴራል ፖሊስ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡
የአንድ ግለሰብ ሰርቪስ ቤት ተከራይተው ከነበሩት ሶማሊያውያኑ መካከል፣ አንደኛው ከ20 ቀናት በላይ የቆየ ሲሆን፣ ሌላኛው ፍንዳታው ከመድረሱ ከሁለት ሰዓታት በፊት የደረሰ መሆኑን ግብረ ኃይሉ ማረጋገጡን አስረድቷል፡፡ ሽብርተኛ የተባሉት ሶማሊያውያኑ ካፈነዱት ቦምብ በተጨማሪ መጠናቸው ያልተገለጸ ቦምቦችና አንድ ሽጉጥ ከሁለት ካርታ ጥይት ጋር መገኘቱን፣ የፈንጂ ማቀጣጠያና የአደጋ መከላከያ ጃኬቶች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማሊያና ቀበቶዎች መገኘታቸውም ተገልጿል፡፡ከሶማሊያውያኑ ጋር ቀጥታ ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሦስት ተጠርጣሪዎችና የቤቱ አከራይ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄባቸው መሆኑንም ግብረ ኃይሉ አክሏል በማለት ዘግቧል። አዲስ አድማስ በበኩሉ ከዚህ በታች ያለውን ዜና አስነብቧል
የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጐቹ ራሳቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ አስጠነቀቀ
ባለፈው እሁድ በቦሌ ሚካኤል አካባቢ ከደረሰው ፍንዳታ ጋር ተያይዞ ሁለት ተጨማሪ የፍንዳታ ጥቃት ለማድረስ አልሸባብ የተሰኘው የሶማሊያ ቡድን እንደዛተ የገለፀው የአሜሪካ ኤምባሲ፤ የዛቻው ተአማኒነት ባይረጋገጥም በኢትዮጵያ የሚገኙ አሜሪካዊያን ጥንቃቄ እንዳይለያቸው አሳሰበ፡፡Bomb-Blast-Addis
የኢትዮጵያና የናይጄሪያ ቡድኖች ግጥሚያ በሚካሄድበት ሰዓት ጥቃት ለመፈፀም ሲዘጋጁ የነበሩ ሁለት ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ሲሆን በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት በማወጅና ሽብር ለመፈፀም በመዛት የሚታወቀው አልሸባብ “ድርጊቱ በኔ አባላት የተፈፀመ ነው” ብሏል፡፡
አልሸባብ በቦሌ ሚካኤል ለተከሰተው ፍንዳታ ሃላፊነት እንደሚወስድ በትዊተር እንዳስታወቀ ኤምባሲው ጠቅሶ ባሰራጨው ማሳሰቢያ፤ በፒያሳና በቸርችል ጐዳና አካባቢ የፍንዳታ ጥቃት ለመፈፀም እንደዛተም ገልጿል፡፡
በቦሌ ሚካኤል በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ በተከሰተው ፍንዳታ ሁለት የሶማሊያ ተወላጆች መሞታቸውን የገለፀው ፖሊስ፤ ከሟቾቹ አንዱ የኢትዮጵያ ማሊያ በመልበስ ከኳስ ተመልካቾች መሃል የፍንዳታ ጥቃት ለመፈፀም እየተዘጋጀ እንደነበር ጠቁሟል፡፡
ለጥቃት የታሰበው ፈንጂ እዚያው ፈንድቶ ሁለቱ አሸባሪዎች መሞታቸውን ፖሊስ ተናግሯል፡፡ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል፤ የፍንዳታው ፈፃሚዎች አልሸባብ መሆናቸውን ተጠይቀው ገና አልተረጋገጠም ብለዋል፡፡ የፀረ ሽብር ግብረ ሃይል ጉዳዩን እየመረመረ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ሽመልስ፣ ግብረ ሃይሉ የደረሰበት ውጤት ጊዜውን ጠብቆ ይፋ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡
40/60 ቤት ክፍያ ያጠናቀቁ የህብረት ስራ ማህበር ሊሆኑ ነው
የቤት ባለቤት ለመሆን ሙሉ ክፍያ ያጠናቀቁ የ40/60 ተመዝጋቢዎች በመኖርያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበር ወደ ተነደፈው ፕሮግራም እንዲዛወሩ የአዲስ አበባ አስተዳደር ማግባባት ጀመረ፡፡ በ40/60 ፕሮግራም የተመዘገቡ የተሻለ ገቢ ካላቸው ነዋሪዎች መካከል ክፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሚጠበቅባቸውን ሒሳብ መቶ በመቶ መክፈላቸው ይታወቃል፡፡ ይህንን ያጤነው 40 60የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እነዚህን መቶ በመቶ የከፈሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማግባባት ወደ መኖርያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ፕሮግራም እንዲዛወሩ ለማድረግ ጥረት መጀመሩን ሪፖርተር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሥር የሚገኘው የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማደራጃ ጽሕፈት ቤት ምንጮች ጠቅሶ ይፋ አድርጓል።
በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም 81,257 ነዋሪዎች መመዝገባቸውና በሦስቱም የመኖርያ ቤቶች (10/90 እና 20/80) ፕሮግራሞች የተመዘገቡ ነዋሪዎች 2.5 ቢሊዮን ብር መቆጠባቸው ይታወቃል፡፡ የእነዚህን ቤቶች ግንባታ ለማስጀመር መንግሥት ተጨማሪ 7.5 ቢሊዮን ብር እንደመደበ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሐሙስ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጸዋል::

አንደበት
“ኢትዮጵያነቴን ይዤው ወደ መቃብር እሄዳለሁ”  አቶ ተስፋ ገ/አብ የቡርቃ ዝምታ ጸሀፊ
ቀደም ብዬም ተናግሬያለሁ። ማንም ሊከለክለኝ አይችልም። ማንም ሊሰጠኝ አይችልም። አገር ውስጥ እንዳልገባ ልከለከል እችል ይሆናል። የልብ ስሜቴን መንጠቅ የሚችል አንድም ሰው የለም። ይህንን ስሜቴን ነው ባጭሩ ማነገር የምፈልገው።ማንም አይቻለውም። ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቼ ሚሊዮኖች አሉ።በተለያዩ ምክንያቶች አገር ቤት መግባት አይችሉም። ከጥቂት ጊዜያት  በሁዋላ ግን እንደጎርፍ ነው ወደ አገራችን የምንገባው።ይህንን ነው ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው። / አበባ ይበተንለታል/ ለከለከሉኝ ክፍሎች ማን ነው ያ ከልካይ በመሰረቱ? ከየት ነው የመጣው? ያ ሰው ምን አደረገ ለአገሪቱ?እኔ የቢሾፍቱ ልጅ ነኝ። ኢትዮጵያዊ ነኝ። ይህንን መከልከል የሚችል ማንም የለም።ይዤው ወደ መቃብር እሄዳለሁ። እስከመጨረሻው … (ተስፋዬ ከኢካድኤፍ የመወያያ መድረክ ጋር ካደረገው ቃለ መጠይቅ የተወሰደ)
ከሰነዱ ከተገኙት መረጃዎች መካከል ተስፋዬ በእጁ የጻፈው ይህ መረጃ ይገኛል፡-
“ኢትዮጵያዊያን የኤርትራ ታሪክ በትክክል እንዲያውቁ ይረዳል። ይህም በአዲሱ የኢትዮጵያ ትውልድ አእምሮ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል እንዳልነበረችና እንደማትሆንም የአመለካከት ዘር መዝራት ያስችለኛል። ለዚህ ሥራም የናንተ መ/ቤት ሆነ ህገደፍ (ሻዕቢያ) ሰነዶችን እንድመለከት በመፍቀድ ያግዘኝ ዘንድ እመኛለሁ። እነዚህ መጻሕፍትን ጽፌ እስከምጨርስ ሁለት ዓመት ይፈጅብኛል። ቢያንስ በቢሮና በጽሕፈት መሣሪያዎች እንዳልቸገር ብደረግ እመኛለሁ።” …tesfaye hand written
“በኤርትራ ጉዳይ፣ በሻዕቢያ አላማዎችና አሰራሮች፣ እንዲሁም ኢሳያስን በተመለከተ ያለኝ በጣም ግልጽ ነው። ከነሙሉ ችግራችን ኤርትራ በትክክለኛው ሃዲድ ላይ እየተጓዘች ነው ብዬ አምናለሁ። የሚታረሙ ነገሮች ካሉ ዋናው ጉዞአችን ሳይነካ እየተስተካከለ ሊሄድ ይችላል ብዬ አምናለሁ። የምጽፈውም ሆነ የምሠራው ይህን መሠረት ያደረገ ነው።” …
“አሻግሬ ስመለከት በርቀት ሰማያዊ ተራሮች ይታየኛል። ከተራሮቹ ስር ያለው ለጥ ያለ የእርሻ ሜዳ የአባቴ አገር ነው።” …
“ይህን ታሪክ እጽፈዋለሁ: 3 ተከታታይ መጽሐፍ ሊወጣው ይችላል። ባህረነጋስያን በመጀመር የኤርትራን ታሪክ እጽፈዋለሁ። የሻቢያን የትግል ታሪክ እጽፈዋለሁ። ይህም ኢትዮጵያዊያን ስለኤርትራ ተገቢውን ሃቅ እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል። በዚህ መጽሐፍ ጠላት አፈራለሁ። ቢሆንም ግን እጽፈዋለሁ። ስለዚህ ከአሁኑ ፍንጭ መስጠቱ ጠቃሚ ነው። በተቃውሞ የምጽፍ የሚመስላቸው ስለሚኖሩ እስከዚያው ድረስ ይዝናኑበት። ኤርትራ ለመመለሴ ምክንያት ይሰጥልኛል።”
በኦጋዴን የነዳጅ ጉድጉድ ቁፋሮ ተጀመረ
ኒው ኤጅ የተሰኘው የእንግሊዝ ኩባንያ በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኦጋዴን ቤዚን፣ ኤልኩራን በተባለ ሥፍራ የነዳጅ ጉድጓድ ቁፋሮ ጀመረ፡፡ ኒው ኤጅ በኦጋዴን ብሎክ ሰባት፣ ስምንትና አዲጋላ በተባለ ድሬዳዋ አቅራቢያ በሚገኙ የነዳጅ ፍለጋ ቦታዎች አፍሪካ ኦይል ከተሰኘ የካናዳ ኩባንያ ጋር በነዳጅ ፍለጋ ሥራ የተሰማራ ኩባንያ ነው፡፡
ኩባንያው ኤልኩራን በተባለ በሶማሊያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ አካባቢ የነዳጅ ጉድጓድ ቁፋሮ ጀምሯል፡፡ogaden-main
ታማኝ የዜና ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያው የመቆፈሪያ ማሽኑን ተክሎ የቁፋሮ ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ሳለ የቁፋሮ ባለሙያዎች በማሽኑ ላይ የቴክኒክ ችግር በማግኘታቸው የቁፋሮ ሥራውን ሳይጀምሩ አዘግይተውታል፡፡ ባለሙያዎቹ በማሽኑ ላይ ያገኙትን የቴክኒክ ችግር አስወግደው የቁፋሮ ሥራውን ባለፈው ሳምንት መጀመራቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
የሚቆፈረው ጉድጓዱ ጥልቀት 2,800 ሜትር እንደሆነና የቁፋሮውን ሥራ ለማጠናቀቅ ሦስት ወራት ያህል እንደሚፈጅ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከሦስት ወራት በኋላ በጉድጓዱ ውስጥ ነዳጅ መኖርና አለመኖሩን የሚጠቁም የሙከራ ሥራ እንደሚሠራ ታውቋል፡፡
አፍሪካ ኦይል በቅርቡ በድረ ገጹ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ከኒው ኤጅ ጋር በመተባበር በኦጋዴን ላይ አተኩሮ እንደሚሠራ ገልጿል፡፡
አፍሪካ ኦይል በኤልኩራን የነዳጅ ክምችት እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ መገኘቱን ጠቅሶ፣ አሁን በሚቆፈረው ጉድጓድ በአካባቢው የሚገኘውን የነዳጅ ክምችት መጠን ለማወቅ እንደሚቻል አስታውቋል፡፡
‹‹በኤልኩራን ነዳጅ መኖሩ ይታወቃል፡፡ አሁን ዋናው ሥራ የሚሆነው በሚቆፈረው ጉድጉድ ውስጥ የነዳጅ ፍሰት እንዲከሰት በማድረግ በአካባቢው የሚገኘውን የነዳጅ ክምችት መጠን ማወቅ ነው፤›› ምንጮች ተናግረዋል።
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፔትሮሊየም ባለሙያዎች በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ቴኔኮ የተባለ የአሜሪካ ኩባንያ በኤልኩራን በቆፈረው የመጀመሪያ የነዳጅ ፍለጋ ጉድጓድ የተፈጥሮ ዘይት ፍሰት ማግኘቱን አስታውሰው፣ በወቅቱ ኩባንያው ክምችቱ በቂ አይደለም በሚል ትቶት ሄዷል ብለዋል፡፡ አክለውም አሁን ባለው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው አፍሪካ ኦይልና ኒው ኤጅ በኤልኩራን ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ ክምችት ሊያገኙ እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ዜናው የሪፖርተር ነው።
በናይጀሪያ ድጋፍ ሰበብ አፈ-ጉባኤና ወታደሮች ሞቱ
በኢትዮጵያ እና በናይጄሪያ የእግር ኳስ ጨዋታ በጋምቤላ ክልል ኚኝኛግ ወረዳ በደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የወረዳው አፈጉባኤ እና ወታደሮች እንደሞቱ ምንጮቼ ነገሩኝ ሲል አዲስ አድማስ ጋዜጣ በቅዳሜ እትሙ አስታውቋል። ጋዜጣው የአደጋውን መጠንና የጉዳቱን ስፋት ለማረጋገጥ ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካለት በመጠቆም ባተመው ዜና ችግሩ የተከሰተው ጋምቤላ ክልል መሆኑን አመልክቷል።
soccerየደቡብ ሱዳን አዋሳኝ በሆነችው የኚኝኛግ ወረዳ ባለፈው እሁድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ከናይጄሪያ አቻው ጋር በአዲስ አበባ ስቴዲየም ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ባደረጉት ወቅት፣ የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን በማሸነፉ ደስታቸውን በጭፈራ በመግለጽ ላይ በነበሩ እና በድርጊቱ በተቆጡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች መካከል ግጭት ተፈጥሮ የኚኝኛግ ወረዳ አፈጉባኤና ከሁለት በላይ ወታደሮች እንደሞቱ ታውቋል።
ችግሩ እንደተፈጠረ ከፌደራልና ከክልል የተውጣጡ ባለስልጣናት ቦታው ድረስ በመሄድ የማረጋጋት ስራ መሥራታቸውን ምንጮቻችን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ የክልሉ ፕሬዝዳንት ሁኔታው ለማየት ወደ ስፍራው የሄዱ ሲሆን ስለ ጉዳዩ ፕሬዝዳንቱን በስልክ ለመጠየቅ ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡
መምህራን የስራ ማቆም አድማ አደረጉ
በደቡብ ክልል በጋሞጎፋ ዞን በጨንጫ ወረዳ የሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤት መምህራን ለአባይ ግድብ ማሰሪያ በሚል ከደሞዛቸው ላይ ገንዘብ መቆረጡን ተከትሎ ካለፉት 3 ቀናት ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ኢሳት ጥቅምት 7 ቀን 2013 ዓ ም ባሰራጨው ዜና አመለከተ።
የጨንጫ ፣ ጭነቶ፣ ጦሎላ፣ ጨፌ፣ ጺዳ እና ቱክሻ ትምህርት ቤቶች መምህራን በአድማ ላይ መሆናቸውን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ተማሪዎች ቤታቸው ለመቀመጥ ተገደዋል። የወረዳው እና የዞን መምህራን ማህበር ከመምህራኑ ጋር በመሆን አድማውን እያስተባበሩ ሲሆን፣ አድማው ወደ ሌሎች ትምህርት ቤቶች እና አካባቢዎች ሊዛመት እንደሚችል መምህራኑ ተናግረዋል።strike
መምህራን “ደሞዛችን በግድ መቆረጡ አንሶ፣ እኛ በጠየቅነው ቀርቶ ባልጠየቅነው ወር ለምን ይቆረጥብናል ” በማለት አድማውን እንደ ጀመሩ አንድ መምህር እንደገለጹለት ያመለከተው ኢሳት መምህራን የአንድ አመት ደሞዛቸውን ከተቆረጠ በሁዋላ፣ ከመስከረም ጀምሮ ደግሞ ሁለተኛውን ዙር ማስቆረጥ ጀምረዋል ያለው ኢሳት የኢትዮጵያ መንግስት መምህራን ለአባይ ግድብ ማሰሪያ በፈቃዳቸው ከደሞዛቸው እንዳስቆረጡ በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱንም አስታውሷል።
ዓለምአቀፍ ጠበቆች የኢትዮጵያን ባለስልጣናት ለፍርድ ለማቅረብ እንቅስቃሴ ጀመሩ
በወጣት አብዱላሂ ሁሴን አማካኝነት በኢትዮጵያ የኦጋዴን ክፍል የተፈጸመውን የጦር ወንጀልና የሰብአዊ መብት ጥሰት ፊልም የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም በስዊድን ቁጥር አንድ ቴሌቪዥን በትናንትናው እለት መቅረቡን ተከትሎ አለማቀፉ ጠበቆች ጉዳዩን ወደ አለማቀፍ ፍርድ ቤት ለመውሰድ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ኢሳት በጥቅምት 5 ቀን 2005 ዜናው አስታወቀ።
ogdenወጣት አብዱላሂ ለኢሳት እንደገለጸው ፊልሙ ከተላለፈ በሁዋላ ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን የሰጡት ሲሆን፣ ስቴላም የተባሉ የ አይ ሲ ጄ ጠበቃ ጉዳዩን ፍርድ ቤት እንደሚያቀርብ በሬዲዮ ይፋ አድርገዋል። የስዊድን የጦር ወንጀል ኮሚሽን ፍርድ ቤትም ማስረጃዎችን በመመርመር ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ከወጣት አብዲ ጋራ ቀጠሮ ይዟል። ጠበቆቹ ጄኔቫ ካለው አይሲጄ እና ከሌሎችም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ጉዳዩን ወደ አለማቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ለመውሰድ እንደሚሞክሩ ኢሳት አመልክቷል።
ቀደም ሲል ይፋ ከተደረገው በተጨማሪ አዳዲስ መረጃ የያዘው አዲሱ ፊልም “ልዩ ፖሊስ” እየተባለ በሚጠራው ሀይል የተፈጸመ የዘር ማጥፋት ወንጀልና የክልሉን ፕሬዚዳንት የተቸች አንዲት ሴት በኦበነግ አባልነት ስትፈረጅ የሚያሳይ መረጃ ተካቶበታል ። የክልሉ ፖሊስ ሀላፊ በእስር ላይ የሚገኙትን ሴቶች በመድፈር ብዙ ህጻናት በእስር ቤት ውስጥ መወለዳቸውን በፖሊሶች በራሳቸው ሲነገር የሚያሳይ ፊልም መካተቱትን ወጣት አብዱላሂ ገልጿል። ፊልሙ ” የዲክታተሮች እስረኞች” የሚል ርእስ ተሰጥቶታል።
ጉዳዩን በማስመልከት የአለማቀፍ የህግ ባለሙያዎች ኮሚሽን በእንግሊዝኛ ኢንተርናሽናል ኮሚሽን ኦፍ ጁሪስትስ ኮሚሽነር የሆኑት ስቴላ ጋርደ ለኢሳት እንደገለጹት የወንጀሉን ፈጻሚዎች ወደ ፍርድ ለማቅርብ የሚችሉትን ሁሉ እንደሚጥሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአለማቀፍ ወንጀል (ICC) ፈራሚ አገር ባለመሆኑዋ ማስረጃውን በቀጥታ ለፍርድ ቤቱ መላክ እንደማይቻል የገለጹት ኪሚሽነር ጋርደ፣ ይሁን እንጅ ሰቆቃን ለመከላከል የተቋቋመው ኮሚቴ (Committee Against Torture) ፈራሚ አገር በመሆኑ ጉዳዩን በዚሁ በኩል ለመከታተል እና የስዊድን ፖሊስ ምርመራ ጀምሮ እርምጃ ለመውሰድ እንዲችሉ ጥረት እንደሚያደርጉ ከኢሳት ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እንደገና በአዋጅ ሊቋቋም ነው
በሀገሪቱ በኮምፒውተር የሚሰሩ ማንኛውም የመሰረተ ልማት ተቋማትና የመረጃ አገልግሎት የኔትወርክ አውታሮች ላይ ከውጪና ከሀገር ውስጥ የኮምፒውተር ቫይረስን ጨምሮ በተለያየ መንገዶች የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲቻል ታስቦ የተቋቋመው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እንደገና በአዋጅ እንደሚቋቋም ኢሬቴድ ገለጸ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጀነራል ተክለብርሀን ወ/ዓረጋይ ረቂቅ አዋጁ ህግ ሆኖ ሲፀድቅም የሀገሪቱን የመረጃ ደህንነት ከማስጠበቅ ባሻገር የመንግስትና የግል የልማት ድርጅቶች ከሳይበር ወይም ከኮምፒውተር ጥቃት በመከላከል የሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ያስችላልም ማለታቸውን ዜናው አመልክቷል። ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም አዋጁ ኤጀንሲው የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን ቀድሞ በማወቅ እና በመከላከል እርምጃ እንዲወሰድ የመረጃ ማምረትና ተደራሽ የማድረግ ተግባራትን በአግባቡ እንዲወጣ እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡insa ethiopia
በተለይም ደግሞ አዋጁ ምስጢራዊ የሀገር ደህንነት መረጃዎችን እና የኢንዱስትሪዎችን ፣የባንኮችን ፣የቴሌኮሚኒኬሽን ፣የኤሌክትሪክ ሀይል ፣የመገናኛ ብዙሀንን ተቋማት እንዲሁም የግዙፍ ፕሮጀክቶች የኮምፒውተር ኔትወርክ አውታሮች ከሳይበር ጥቃት እንዲጠበቁ እንደሚያስችልም በውይይቱ ተብራርቷል፡፡ ድንበር የለሹ ይህ የኮምፒውተር ወንጀል አዲስ የሀገር ልዋላዊነት የጥቃት ምንጭ እንደሆነ የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህንንም ተግባር የሚፈጽሙ ግለሰቦች የሽብር ፣የፖለቲካ ፣የወንጀል ምክንያቶችን ጨምሮ የተለያዩ ዓላማዎች ይዘው የሚንቀሳቀሱ እንደሆኑ ኢሬቴድ አመልክቷል።
ኢንሳ ዜጎችን በማፈንና ኢህአዴግ ለስለላ የሚጠቀምበት ዋንኛ ማሽኑ እንደሆነ በተደጋጋሚ መገለጹ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment