FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Sunday, October 27, 2013

የሂውማን ራይትስ ዋች የሰሞኑ ዘገባ

ለወያኔ ፋሽስታዊ ግፍና የውገን ሰቆቃ ምላሽ መስጠት ይገባል

በኤፍሬም የማነብርሃን
በዓለም ታዋቂው የሰብዓዊ መብቶች ሟጋች ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዋች (Human Rights Watch) ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ፡ የአፍሪቃ አንድነት ዋና ከተማ በምትባለው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የወያኔ መንግስት በኢትዮጵያውያን ላይ እያካሄደ ያለውን የግፍ ግፍ ለዓለም አጋልጧል፡፡ በዚች ደቂቃ ማዕከላዊ ፖሊስ ጣቢያ እየተባለ በሚጠራው የሰቆቃ ቦታ በንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ ለኢትዮጵያዊነት ፍቅርና ክብር በሌለው የወያኔ ወንጀለኛ መንግስት ይህ ነው የማይባል ወንጀል እየተፈጸመበት ይገኛል። በ”ሕጋዊ” መንገድ እንዲሰሩ “ተፈቅዶላችው” የሕዝቡን ሰቆቃ በመስማትና የሚፈጸመው ግፍና በደል እንዲቀርና በሰላማዊ መንገድ በውድ አገራችን ላይ ደሞክራሲ እንዲለመልም እየታገሉ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ፤ የወያኔ ፋሽስታዊ መንግስት በአንድ ወገን ዓለምን ለማታለልና ዲሞክራሲ እንዳለ ለማስመሰል ፓርቲ ማቋቋም ይቻላል ብሎ ካስወራ በኋላ፤ ከዓለም እይታ በስተጀርባ ግን ይህ ነው የማይባል ፋሽስታዊ ጭካኔ በንጹኅን ኢትዮጵያውያን ላይ እያካሄደ አንደሚገኝ የመብት ሟጋች ድርጅቱ አጋልጧል። እንዲህ ያለ ወንጀል በውዲቷ ዋና ከተማችንና በታላላቆች የሃይማኖት መጻሕፍት በቅድስናዋ ደጋግማ በምትጠቀሰው አገራችን ሲፈጸም እንዴት ዝም ብለን እናያለን? እያንዳንዱ እትዮጵያዊ ባለው ዐቅሙ ሊያደርግ የሚገባውን ለማድረግ ለምን አይረባረብም?
ይህ ግፍ በወገኖቻችን ላይ ሲፈጸምባቸው የቆየ መሆኑን ከሥርዓቱ ተጠቃሚዎች በስተቀር ሁሉም የሚያውቀው ቢሆንም፡ እንደዚህ በዓለም ደረጃ ታውቆ በግላጭና ቁልጭ ብሎ መነገሩ ወያኔ አትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን፤ ከአሁን በኋላ የዓለምን ሕዝብ ጭምር አያታለለ ሊቆይ እንደማይችል ያስገነዘብው ዪመስለኛል። ለዚህም የሂውማን ራይትስ ዋችን በሚቻል ሁሉ መርዳትና ምስጋናችንንም ማቅረብ ይገባናል።
በተጨማሪም እያንዳንዱ ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ “አሁንስ በቃ በጋራ እንኳን ምንም ማድረግ ቢያቅት በግሌ ማድረግ የሚገባኝን ማድረግ አለብኝ” ብሎ መነሳትና ይህንንም የግል ውሳኔ በስራ ለመተርጎም መወሰን አለበት፡፡ የግፉ አይነት፡ ብዛት፡ እና የጭካኔው መጠን ውስጣችንን የሚረብሽና ሰላምን የሚነሳ እንደመሆኑ መጠን፤ ይህን የውስጥ ንዴታችንን ወደ ወደተጨባጭ ትግል ለመቀየር በኢትዮጵያ ላይ ይግፍ መረቡን ዘርግቶ የተቀመጠውን ይሕን እርኩስ መንግስት ባለን ዐቅም ፊት ለፊት ተጋፍጠን “በዚህማ ልትቀጥል አትችልም ፡ይብቃህ እርኩስ ኃይል ይብቃህ“ ማለት መቻል አለብን።
በአገሪቱ ዋና ከተማ መሃል ላይ እንዲሁም ስላልታወቀ ነው እንጂ በጣም በብዙ የአገሪቱ ከተሞችና መንደሮች ውስጥ ይህን የመሰለ የግፍ ግፍ እየተካሄደ እያለና ሕዝቡ የመከራ ገፈፉን እየቀመሰ ያለ መሆኑን ሁላችንም በልባችን እያወቅነው እንዴት ብለን ቁጭ እንላለን፤ እንዴትስ በልተን ጠጥተን እንውላለን አናመሻለን፤ እንዴትስ ተኝተን እናድራለን፤ እንዴትስ ቤተ ክርስቲያን አስቀድሰን፤ መስጊድ ተሳልመን ቤታችን እንገባለን፤ እንዴትስ አገር አለን ብለን ስለ አገር ዕድገትና ልማት እናወራለን፤ እንዴትስ ስለዚህ ወንጀለኛ መንግስት መልካምነት እንናገራለን።
ከሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ትንሽ ቀንጨብ አድርገን እንመልከት፡፡
“ በኢትዮጵያ ከ1997ቱ አወዛጋቢ ምርጫ በኋላ በሰላማዊ ተቃዎሞ ላይ የሚደረገው ጫና ተባብሷል። በማዕከላዊ ተይዘው ምርመራ የሚካሄድባቸው የመንግስት ተቃዋሚ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች … በተለይ በምርመራ ጊዜ ታሳሪዎቹ በጥፊ፣ በእርግጫ እንዲሁም በብትር እና በሰደፍ በተደጋጋሚ እንደተመቱ … ሰውነታቸውን ለህመም በሚዳርግ ሁኔታ እንዲሆኑና በተለይም እጆቻቸውን ከግድግዳ ጋር ታስረው እንዲንጠለጠሉ ተደርጎ ለረጅም ሰዓታት ያለማቋረጥ እንደሚደበደቡ ተናግረዋል። ከኦሮሚያ ክልል የመጣ አንድ ተማሪ ብቻውን ተነጥሎና በሰንሰለት ታስሮ ለበርካታ ወራት እንዲቆይ እንደተደረገ ተናግሯል፡፡ ‘ለመቆም ስሞክር እቸገራለሁ፡ ለመቆም ጭንቅላቴን፣ እግሮቼን እና ግድግዳውን መጠቀም ነበረብኝ ፡፡ ምግብ ስመገብ እንኳ በሰንሰለት ታስሬ ነበር። ስመገብ እጆቼ በፊት ለፊት በኩል እንዲታሰሩ ይደረጋል ስጨርስ ደግሞ መልሰው ወደ ኋላ ያስሩኛል።’”
እንግዲህ ይህ መረጃ በአጋጣሚ ሕዝብ ዘንድ ወሬው ሊሰማ የቻለው ከእስር ወጥተው ለወሬ ነጋሪነት የበቁ ሰዎች ስለተገኙ ነው። ክዚህ ጀርባ እንዲህ ያልታወቁ፡ በድብቅ በአገሪቱ ዙርያ በወያኔ ነፍሰ ገዳይ ቡድኖች በወገኖቻችን ላይ የሚፈጸሙ ስፍር ቁጥር የማይገኝላቸው ወንጀሎች እንዳሉ መገመት አያዳግትም። ቤት ይቁጠረው። የወንጀለኞቹ መሪ መለስ ዜናዊ በተገኘበት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ወርቅነህ ገበየሁ በደህነነት ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የተናገረውን ለመጥቅስ ወያኔ እንደ ልዩ የስራ ችሎታው አድርጎ የሚትቀምበት ዘዴ “በተቀናጀ ኦፐሬሽን ለረጅም ጊዜ ለመንግስት ሥጋት ሆነው የቆዩ ሰዎች እንዲወገዱ” ማድረግ መሆኑን ወርቅነህ በኩራት ሲገልጽ ሁሉም በስብሰባው የነበሩ የምክር ቤቱ አባላት ከመለስ ጭምር የዜናው አስፈሪነትና ከባድነት ለመቅጽበት እንኳን በመንፈሳችው ውል ሳይል ስብሰባውን ሲቀጥሉ ታይተዋል።
በቅንጅት መሪዎች በተልይ ደግሞ በእህት መሪያችን በወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተፈጸመውን ግፍና መከራ እንዲሁም በአሁኑ ውቅት በእስክንድር ነጋ፤ በአንዷለም አራጌ፤ ወዘተ በዚች ሰዓት የሚፈጸመውን ግፍና መከራ ሁሉም የሚያውቀው ነው ። በሞቱ የተገላገልነው መለስ ዜናዊና የወያኔ መንግስት በሃሰትና ውሽት ላይ የተመሰረተውን የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም በማሰብ፤ የቅንጅትን መሪዎችን ለዓመታት በእስር ቤት በማንገላታትና በማሰቃየት፤ በጨለማ ቤት ለወራት በማቆየት፤ ከጉልበትና ከማስፈራራት በተገኘ የሃሰት የእምነትቃል ላይ እንዲፈርሙ በማድረግ በኢትዮጵያ ሕዝብና በደጋፊዎቻቸው ዘንድ እነዲጠሉና የመሪነት ድጋፋቸው እንዲቀንስና እንዲናቁ ያደረጉትን ሙከራ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው ነው።
ይህ የወንጀለኞች መንግስት በኢትዮጵያ ላይ በመሳርያ ኃይል ከተፈናጠጠ በኋላ አገሪቱን በዘር መከፋፈሉ፤ አገሪቱን ያለባሕር በር ማስቅረቱ፤ ለምለም የአገሪቱን መሬቶች ለሱዳን አሳልፎ መስጠቱ፤ የአንድን አናሳ ብሔረሰብ አባላትን የኢኮኖሚው፡ የቢሮክራሲው፡ የሚሊታሪው፡ የፍርድ ቤቶች፡ የቤት ንብረትና መሬት ይዞታዎች የበላይ አስተዳዳሪና ባለቤት ወዘተ ማድረጉ፤ የአገሪቱን ብርቅዬ መምህራን ከዩኒቨርሲቲ ማፈናቀሉ፤ ሕዝብን ለምርጫ ካልወጣህ ካለ በኋላ መሸነፉን ሲያውቅ በዲሞክራሲ የተመረጡትን መሪዎች ማስገደሉ ማሰሩና ንጹሃን ወጣትና ህጻናትን መጨፍጨፉ፤ ሰሞኑን ደግሞ የወንጀለኛ ድርጅት አባል ካልሆናችሁ ስራ፡ እድገት አታገኙም ማለቱ ወዘተ አልበቃው ብሎ አስከፊ በሆኑት አሥር ቤቶቹ ውስጥ መሪዎችንና አዛውንቱን ለዚሕ ለሚዘገንን መከራና ሰቆቃ መዳረጉ ምን ያሕል ሕዝቡን የናቀ መሆኑን ያሳያል።
እንዲያውም ከሁሉም በላይ ደግሞ የሚያበሳጨው መንግስቱ ኃይለማርያምን በኢትዮጵያውያን ላይ ትልቅ በደል ሰርቷል እያለ የሚያብጠለጥለው የወያኔ መንግስት፡ ከመንግስቱ ኃይለማርያም በማያንስ ጭካኔ ከፖለቲካ ልዩነት በቀር ምንም ያልሰሩ ንጹሃንን ይህን ለመሰለ ስቃይና መከራ የዳረጋቸው መሆኑ ነው። በተጨማሪም በመንግስቱ ኃይለማርያም የተጀመረው የዚህ ለመከራ የተዳረገ ሕዝብ ፍዳ በዚህ ዘረኝነት ባሰከረው የወንጀለኞች መንግስት በጣም በተራቀቀ ድርጊት መቀጠሉ “ያገር ያለህ” ወደሚያስብል ነጥብ ላይ አድርሶናል።
በተለይ ደግሞ በዚህ ኢንተርኔት፡ ተዟዟሪ ስልክ፡ ሳተላይት ሬዲዮና ቴሌቪዥን እና በአጠቃላይ የሚዲያ ቴክኖሎጂ በዓለም በተንሰራፋበት ዘመን የወያኔ መንግስት ኢትዮጵያውያን የዚህ ዕድገት ሙሉ ተካፋይና ተሳታፊ እንዳይሆኑ አፍኖ፡ የዓለምን ሕዝብ ይሉኝታ ሳይፈራ የጭካኔና የግፍ መረቡን በአገሪቱ ላይ ዘርግቶ በማናለብኝነት አስከፊ ሴራውን ሲያከናውን ለብዙ ኢትዮጵያውያን “አሁንስ አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” የማያስብል ደረጃ የደረስን ይመስላል ። እስከመቼ ችለን ልናየውና የወያኔን የግፍ ቀንበር ተሸክመን ኑሮን መቀጠል እንደምንችል ማሰብና አስቸኳይ ውጤት ለማግኘት መረባረብ ይገባናል።
ይህን የሂዩማን ራይትስ ዋች ዘገባ ያነበብነውንና እንዲሁ እንደማንኛውም ዜና የምናልፈው መሆን የለበትም። ተጨባጭ የሆኑና የወንጀለኛው መንግስት እንዲሰማው የሚያስችሉ፤ ከባድ ያልሆኑ ነገርግን ተፈጻሚነት ሊያገኙ የሚችሉ፤ ሰላማዊ ዘዴና እርምጃዎች ላይ ተወያይተን በዝርዝር በማስቀመጥ በውጭ አገር ተቀማጭ የሆንነው ኢትዮጵያዊ ያን በስራ ልንተረጉማቸው ይገባናል። ለመነሻ፤ መወያያና መንደርደሪያ ያህል የሚከተሉት እነሆ።
1. ቢያንስ ለሶስት አለያም ለስድስት ወራትም ሆነ ለአንድ ዓመት የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንስላዎች ከኢትዮጵያውያን የሚያገኙትን ገቢ ለመቀነስ፤ እነደ ፓስፖርት የማሳደስ ቪዛ የማስመታት፤ የውክልና ሰነዶችን የማጻፍ፤ ቤትና መሬት ለማሰራትና ለመግዛት የሚከፈሉ ክፍያዎችን ወዘተ የሚጠይቁ ሥራዎችን ወደነዚህ የመንግስት አውታሮች ዘንድ ሄዶ ወይም በፖስት ቤት አማካኝነት ልኮ አለማሰራት።
2. ቢያንስ ለሶስት አለያም ለስድስት ወራትም ሆነ ለአንድ ዓመት በውጭ አገር በሚገኙ በግልጽ በወያኔ ካድሬዎች በሚንቀሳቀሱ ወይም የወያኔን ካፒታልና ቢዝነስ በሚያንቀሳቅሱ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ በማድረግ ምንም ዓይነት የዕቃ ግዢ ወይንም የገንዘብ ልውውጥ እንዲህ ካሉ ሰዎች ጋር ከማድረግ መቆጠብ። ይህንን ዐቀብ በምናካሂድበት ወቅት እንቅስቃሴው በዘር ላይ ያልተመሰረተና ያለበቂ ማስረጃ በአንድ ብሔር ተወላጆች ላይ ያላነጣጠረ እንዲሆን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። ወደዚያ ዓይነት የትግል አቅጣጫ ሊመሩ የሚፈልጉትን ግለሰቦች በሙሉ መምከርና ካልሆነም መገሰጽ ይገባል።
3. ቢያንስ ለሶስት አለያም ለስድስት ወራትም ሆነ ለአንድ ዓመት የመንግስት አውታር ለሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሆነ ሌሎች ባንኮች ገንዘብ ለሚያደርሱ እንደ ዌስተርን ዩኒየን የመሳሰሉ ወደ ወያኔ ካዝና የውጭ ምንዛሪ (ፎርን ኤክስቼንጅ) በሚያስገቡ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚላክ ገንዘብ አለመላክና የሚኖሩበትን አገር ሕግ ሳይጥሱ በሌላ ዘዴ አገር ቤት ለሚገኝ ወዳጅ ዘመድ ብር መላክ።
4. ቢያንስ ለሶስት አለያም ለስድስት ወራትም ሆነ ለአንድ ዓመት የወያኔን ዓላማ በግላጭ ከሚያስፈጽሙ የወያኔ ካድሬዎች ጋር በማንኛውም አጋጣሚ ድጋፋቸውን የሚሰጡት መንግስት በደምና ግፍ የተጨማለቀ መንግስት መሆኑን ባላሰልሰ በማስረዳት ላጭር ጊዜም ቢሆን ከጋራ ተሳትፎ ማግለል። ይህንን ዐቀብ በምናካሂድበት ወቅት እንቅስቃሴው በዘር ላይ ያልተመሰረተና ያለበቂ ማስረጃ በአንድ ብሔር ተወላጆች ላይ ያላነጣጠረ እንዲሆን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። ወደዚያ ዓይነት የትግል አቅጣጫ ሊመሩ የሚፈልጉትን በሙሉ መምከርና ካልሆነም መገሰጽ ይገባል።
5. ቢያንስ ለሶስት አለያም ለስድስት ወራትም ሆነ ለአንድ ዓመት በኢትዮጵያ አየር መንገድ አለመጠቀም። ወያኔ በአሁኑ ጊዜ የጭካኔና የግፍ ሥራውን ለማካሄድ ብዙ የገንዘብ ዐቅም ስለሚያስፈልገው ይህንን የገቢ ምንጩን መቀነስ ለትግላችን መፋጠን ይጠቅማል።
6. ወያኔ በኢትዮጵያ ውስጥ መልካም ሥራ እያካሄደ እንዳለ ሊናገሩ የሚፈልጉ ሞኝና ተላላዎች አገሪቱ በደም የተነከረችና የንጹሃን ሰቆቃ የሚጮህባት አገር እንደሆነች ባላሰለሰ በመንገር በእጅ አዙር የወያኔ ቱልቱላ ቃል አቀባዮች እንዳይሆኑ መምከርና የኢኮኖሚ ዕድገትም እውነትነቱም ሆነ ተፈጻሚነቱ ሊረጋገጥ የሚችለው የሰው ልጅ በሰውነቱ ሲከበርና ያች ሃገር የጥቂቶችና የዘረኞች ሳትሆን የሁሉ ኢትዮጵያዊያን በመሆኗ ጥቂቶች ዘረኞች የብዙዎችን መብት ረግጠው ላንተ እኛ ብቻ ነን የምናውቅልህ እያሉ የሚያናፍሱት ወሬ በሰለጠነው ዘመን ሊሰራና ሊቀጥል የማይችል ተራ ቱልቱላ መሆኑን እንዲገነዘቡ ማድረግ።
7. ወያኔ ሰሞኑን በዳያስፖራ የሚገኙትን የዋህ ኢትዮጵያውያን ገንዘባችውን ለመቀማት የያዘው ዘዴ “ኢትዮጵያ ውስጥ መሬትና ኮንዶ ለመሥራት ኢንዲያስችላችሁ 60/40 የሚባል ፕሮግራም ተዘጋጅቶላችኋል፤ 60 በመቶ (60%) በውጭ ምንዛሪ ካስቀመጣችሁ ቀሪዊን አርባ በመቶ (40%) በአነስተኛ ወለድ የሚከፈል ብድር አዘጋጅቼላችኋለሁ፤ ነገር ግን የውጭ ምንዛሪውን በቀጥታ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ገቢ ማድረግ ይጠበቅባችኋል” በማለት ኢትዮጵያውያንን በግፍ ቀንበሩ ለረጅም ጊዜ ሊይዝ የሚያስችለውን ሃብት ለመሰብሰብ ጥረት ኢያደረገ ስለሆነ ቢያንስ ለሶስት አለያም ለስድስት ወራትም ሆነ ለአንድ ዓመት ይህን ከመሰለ ለወያኔ የውጭ ምንዛሪ መሰብሰቢያ ማታለያ ዘዴ ውስጥ ከመውደቅ መቆጠብ።
እነኝህ ከላይ የተዘረዘሩት ምን መደረግ አለበት ለሚለው ጥያቄ መልስ ባጭሩ ለመስጠት የታቀዱ ናቸው እንጂ ሁሉንም ዘዴ አያካትቱም። የተለያዩ ኢትዮጵያውያን በዝርዝሮቹ ላይ ተጨማሪም ሆነ ማሻሻያ ወይም አዳዲስ ገንቢ ሃሳቦች ቢያቀርቡ ጥረታችን ውጤታማ ይሆናል የሚል ግምት አለኝ፡
የወያኔ የክፋት የጭካኔና የበደል ቀንበር አንድ ቀን ከኢትዮጵያውያን ጫንቃ ላይ ወድቆ ይፈጠፈጣል!!
የኢትዮጵያውያን ሰቆቃ የማለቂያው ቀን ሩቅ አይደለም!!
ውድ አገራችን ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!

No comments:

Post a Comment