FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Saturday, October 19, 2013

ዜጎችን እያቀጨጨ የሚፈረጥም መንግስት… ብዙ አይራመድም ስንት እድሜ ይኖረዋል?

ዜጎችን እያቀጨጨ የሚፈረጥም  መንግስት… ብዙ አይራመድም ስንት እድሜ ይኖረዋል?
የውጭ ንግድ ፈቅ አላለም፤ ባለበት ደንዝዞ ቆሟል - የንግድ ሚኒስቴር መረጃ።
የግል ኢንቨስትመንት ተዳክሟል፤ ድርሻው በግማሽ ቀንሷል - የIMF መረጃ።
የአገሪቱ የባንክ ብድር፣ 90% ወደ መንግስት ይሄዳል - የአለም ባንክ ሪፖርት።
“ትልልቅ ፕሮጀክቶች በውጭ ምንዛሬ እጥረት እየተቀየዱ የሚሄዱበት እድል ሰፊ ነው” … የኤክስፖርት ገቢ መዳከሙን በመግለፅ ይህን የተናገሩት የንግድ ሚኒስቴር ሃላፊዎች ናቸው። ያሳስባል፣ እውነታቸውን ነው። ነገር ግን፣ ትልቁና አሳሳቢው ነገር፣ የመንግስት ፕሮጀክቶች መስተጓጎላቸው አይደለም። የውጭ ንግድ መዳከም፣ ጠቅላላ በአገር ኢኮኖሚና በዜጎች ኑሮ ላይ ተጨማሪ ችግር እንደተደቀነ የሚጠቁም ምልክት ነው። ደግሞስ፣ የመንግስት ገናናነት እየገዘፈ፣ የግል ኢንቨስትመንት እየቀጨጨ፣ እንዴት ጥሩ ውጤት ይገኛል ብሎ መጠበቅ ይቻላል?
አሳዛኙ ነገር፣ መንግስት ራሱን በራሱ ጠልፎ እየጣለ መሆኑን አለመገንዘቡ ነው። መንግስት “የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ” ውስጥ የዘረዘራቸውን ትልልቅ ፕሮጀክቶች ለማሳካት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስፈልገዋል። ግን ምን ዋጋ አለው? ዋነኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ የሆነው የግል ኢንቨስትመንት እየቀጨጨ የመጣው፣ “በእድገትና ትራንፎርሜሽን እቅድ” ሳቢያ ነው። ተግባራዊ የተደረጉ የመንግስት እቅዶች፣ የኤክስፖርት ገበያውንና የውጭ ምንዛሬ ምንጮችን እንዴት እየጎዱ እንደሆነ ለማሳየት እሞክራለሁ።
በእርግጥ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ የሚስተጓጎል ፕሮጀክት የለም ብለዋል። የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በጭራሽ አይጓተትም ያሉት ጠ/ሚ ኃይለማሪያም፣ ሌሎቹ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ደግሞ በውጭ ብድር የሚካሄዱ በመሆናቸው የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደማያሳስብ ለመግለፅ ሞክረዋል።
እንዲያም ሆኖ፣ ከኤክስፖርት የሚገኘው ገቢ የታሰበውን ያህል እንዳልተሳካ አልካዱም። ቢሆንም፣ ይህንን ጉድለት የሚሸፍን ነገር ተገኝቷል። ከተለያዩ ምንጮች ወደ ኢትዮጵያ የተላከው የውጭ ምንዛሬ ከተጠበቀው በላይ ሆኗልና። ለነገሩ፣ በየአገሩ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በየአመቱ የሚልኩት ገንዘብ ቀላል አይደለም። በአመት ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ እየላኩ ነው። ከኤክስፖርት ከሚገኘው ዶላር ይልቅ፣ ከዳያስፖራ የሚመጣው በልጧል። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለቤተሰብና ለዘመድ የሚልኩት ገንዘብ መጨመሩ ጥሩ ነው። ነገር ግን፣ የኤክስፖርትን ጉድለት ይሸፍናል በሚል የሚያፅናና አይደለም - በእጅጉ የሚያሳስብ እንጂ።
ከሳምንት በፊት ጠ/ሚ ኃይለማሪያም፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት የመንግስት ፕሮጀክቶች እንደማይስተጓጎሉ ቢገልፁም፤ ከምር ሳያሳስባቸው የቀረ አይመስለኝም። በዚያው ሳምንት የንግድ ሚኒስቴር ሃላፊዎች ከክልል መስተዳድር ተወካዮች ጋር ተሰብስበው የተነጋገሩበት ዋና ርዕሰ ጉዳይ፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው። ወደ ውጭ የሚላኩ የእርሻና የፋብሪካ ምርቶች፣ በጥራትና በብዛት እየቀረቡ አይደለም በማለት የተናገሩት የንግድ ሚኒስቴር ሃላፊዎች፣ “ትልልቅ ፕሮጀክቶች በውጭ ምንዛሬ እጥረት እየተቀየዱ የሚሄዱበት እድል ሰፊ ነው” በማለት አሳሳቢነቱን ገልፀዋል።
ከአመት አመት የኤክስፖርት እድገት እየተዳከመ መምጣቱን የሚክድ ይኖራል ብዬ አልገምትም። አሁን ደግሞ፣ ከነጭራሹ ቅንጣት እድገት አልታየም። እንዲያውም የኤክስፖርት ገቢ ቀንሷል። በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ከተዘረዘሩት “ግቦች” ጋር ሲነፃፀርማ፣ በእጅጉ ወደኋላ ቀርቷል። የእቅዱ ግማሽ ያህል እንኳ አልተሳካም።
በእቅዱ የመጀመሪያ ዓመት በ2003 ዓ.ም፣ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የነበረውን የኤክስፖርት ገቢ በአንድ ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ (3 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ) ቢታሰብም፣ የእቅዱ 75 በመቶ ብቻ ነው የተሳካው። ቀላል እድገት ነው ማለቴ አይደለም። 2.75 ቢሊዮን ደርሷል። በቀጣዩ ዓመት ግን፣ እድገቱ ተዳክሟል። በ“ኦሪጅናሉ” እቅድ መሰረት፣ የኤክስፖርት ገቢ በ2004 ዓ.ም ወደ አራት ቢሊዮን ዶለር የሚጠጋ ይሆናል ተብሎ ነበር የታሰበው። በተግባር የተገኘው ገቢ ግን 3.15 ቢ. ዶላር ነው። ከመነሻው አመት ጋር ሲነፃፀር በሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ገቢ ለማግኘት ቢታቀድም፣ በተግባር የተገኘው እድገት 1.2 ዶላር ገደማ ነው። እናም እቅዱ 60 በመቶ ብቻ ነው የተሳካው ማለት ይቻላል።
አሁንም ኦሪጅናሉን እቅድ ካስታወስን፣ በ2005 ዓ.ም ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የኤክስፖርት ገቢ ለማግኘት ታስቦ እንደነበር እናያለን። በተግባር የተገኘው ውጤት ደግሞ 3.1 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው። የአመት አመት እድገቱ ተዳክሞ ከመቆሙም በላይ፣ የኋሊት መንሸራተት ጀምሯል። በ2002 ዓ.ም ከነበረው መነሻ አሃዝ ጋር ስናነፃፅረው፣ በሦስት ቢሊዮን ዶላር የላቀ እንዲሆን ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ያህል ብቻ ነው የተሳካው። የእቅዱ 37% ብቻ ማለት ነው። ከአመት አመት የስኬቱ መጠን እየቀነሰ መሆኑን የምታስተውሉ ይመስለኛል።
ዘንድሮም የኤክስፖርት ገቢ ከሰባት ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ይሆናል ተብሎ በእድገትና ትራንስፎርሜሽ እቅዱ ውስጥ ተጠቅሷል። ሃሙስ እለት የወጣው የአይኤምኤፍ መግለጫ እንደሚያመለክተው ግን፣ የኤክስፖርት ገቢው 3.6 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይሆናል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።
እንግዲህ አስቡት፤ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅዱ ላይ የሰፈረው፣ በ2002 ዓ.ም ሁለት ቢሊዮን ዶላር የነበረውን የኤክስፖርት ገቢ፣ በ2006 ዓ.ም በአምስት ቢሊዮን ዶላር ይጨምራል የሚል እቅድ ነው። በእውን ይታያል ተብሎ የሚጠበቀው ጭማሪ ግን 1.5 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው። የእቅዱ 33% ብቻ መሆኑ ነው።
የእቅዱ ስኬት ከአመት አመት እየቀነሰና እየተሸረሸረ የመጣው አለምክንያት አይደለም። የእቅዱ መዘዝ ከአመት አመት እየጨመረና እየተደራረበ ስመጣ ነው። ‘መዘዝ’ ስል፣ ያልታሰበና ያልተጠበቀ መመዝ ማለቴ አይደለም። በደንብ ታስቦበታል። ከዚያም አልፎ፣ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ በይፋ ተዘርዝሯል። በአምስት አመታት ውስጥ በአገሪቱ ከሚካሄዱ የኢንቨስትመንት ስራዎች ውስጥ 67 በመቶ ያህሉ በመንግስት ፕሮጀክቶች፣ 33 በመቶ ያህሉ ደግሞ በግል ኢንቨስትመንት እንደሚሸፈን በ“እቅዱ” ውስጥ ተጠቅሷል። በሌላ አነጋገር፣ የመንግስት ፕሮጀክቶች፣ ከግል ኢንቨስትመንቶች በእጥፍ እንዲበልጡ ነው የታቀደው።
ድሮ እንደዚያ አልነበረም። ኢህአዴግ ስልጣን በያዘባቸው የመጀመሪያ አመታት፣ ከመንግስት ፕሮጀክቶች ይልቅ የግል ኢንቨስትመንት ድርሻ ይበልጥ ነበር - (የግል ኢንቨስትመንት 70 በመቶ የመንግስት ደግሞ 30 በመቶ)። መንግስት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን እገነባለሁ ቢልም፣ ቀስ በቀስ የግል ኢንቨስትመንት ድርሻ እየቀነሰ፣ በተቃራኒው የመንግስት ፕሮጀክቶች ድርሻ እየጨመረ መጥቷል። የዛሬ አስር አመት ገደማ ነው፣ የሁለቱ ድርሻ እኩል የሆነው (ሃምሳ በመቶ - ሃምሳ በመቶ)። የዚህን ጊዜም ነው፣ በመላው ዓለም ወደ ሶሻሊዝም ያዘነበሉ ናቸው ከሚባሉ አምሳ አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ የተገለፀው።
የቁልቁለት ጉዞው ግን በዚሁ አላቆመም። አይኤምኤፍ ሀሙስ እለት ባሰራጨው ዘገባ እንደገለፀው፣ የግል ኢንቨስትመንት ድርሻ ወደ 25 በመቶ እንደወረደና የመንግስት ፕሮጀክቶች ድርሻ 75 በመቶ እንደደረሰ ይገልፃል። በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ከተጠቀሰውም በላይ የከፋ መሆኑን ተመልከቱ። እንዲህ አይነት የመንግስት ገናናነት፣ በብዙ አገራት ውስጥ የለም። በእጅጉ ሶሻሊስታዊ የኢኮኖሚ አካሄድን ከሚከተሉ ሶስት የዓለማችን አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ሆናለች የተባለውም በዚህ ምክንያት ነው። ነፃ ገበያ እንዲህ ነው እንዴ?
የመንግስት ፕሮጀክቶች ድርሻ እያበጠ፣ የግል ኢንቨስትመንት ድርሻ እየተደፈጠጠና እየቀጨጨ የመጣው፣ በተለያዩ ምክንያቶች ቢሆንም፣ ትልቁና ዋናው ሰበብ ግን ከባንክ ብድር ጋር የተያያዘ ነው። የባንክ ብድሮች ከአመት አመት ከግል ኢንቨስትመንት እየራቁ ወደ መንግስት ፕሮጀክቶች እንዲጎርፉ ተደርጓል። ከ20 አመታት በፊት፣ ከግማሽ በላይ የባንክ ብድሮች ለግል ኢንቨስትመንትና ለግል ቢዝነሶች የሚውሉ ነበሩ።
ግን ብዙም ሳይቆይ የባንክ ብድር አቅጣጫው ተቀይሮ፣ ወደ መንግስት ድርጅቶችና ፕሮጀክቶች መጉረፍ ጀመረ። በ2003 ዓ.ም፣ ከባንኮች አዲስ ብድር ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ ለመንግስት ድርጅቶችና ፕሮጀክቶች እንደተሰጠ የሚገልፀው የአለም ባንክ ሪፖርት፣ ከዚያ ወዲህ ባሉ አመታትም የግል ድርጅቶች የሚያገኙት ብድር ይበልጥ እየቀነሰ እንደመጣ ያትታል። አሁን፣ ከባንኮች ብድር ውስጥ 90 በመቶ ያህሉን የሚወስዱት የመንግስት ድርጅቶችና ፕሮጀክቶች ናቸው። State Owned Enterprises are increasingly absorbing domestic banking sector credit. In the six-month period from June 2011 to December 2011, 71 percent of new loans were directed towards public enterprises. This share increased to 89 percent during the second half of 2012. A substantial share of the available foreign exchange is similarly diverted towards public investment. (የአለም ባንክ ሪፖርት Ethiopia Economic Update II፡ Laying the Foundation for Achieving Middle Income Status፡ June 2013 … ገፅ 24)
በዚህ መልኩ፣ ለግል ኢንቨስትመንት የሚውል የባንክ ብድር እየተንጠፈጠፈ፣ የግል ኢንቨስትመንት እየቀጨጨ ሲሄድ፣ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እየቀነሰ መምጣቱን ምኑ ይገርማል? ከሞላ ጎደል በሸቀጦች ኤክስፖርት የሚገኘው ገቢ፣ በግል ድርጅቶችና ኢንቨስትመንቶች አማካኝነት የሚመጣ ነዋ። ታዲያ፣ መንግስት ራሱን በራሱ ጠልፎ አልጣለም ትላላችሁ? በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ የተዘረዘሩትን ትልልቅ ፕሮጀክቶች ለማከናወን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስፈልገዋል። ነገር ግን፣ “እቅዱ” ራሱ፣ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ የሆኑ የግል ኢንቨስትመንቶችን የሚደፈጥጥና የሚያቀጭጭ ነው።

http://www.addisadmassnews.com

No comments:

Post a Comment