FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Wednesday, October 9, 2013

በትግራይ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ካምፕ ዓመጽ ተካሯል

እስካሁን ስድስት ሞተዋል፤ በርካታዎች ቆስለዋል!




አመጹ ከካምፕ ወደ ካምፕ እየተዛመተ ነው

በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ተመዝግበው በትግራይ-ኤርትራ ድንበር ዳርቻ በስደት ማቆያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ የኤርትራ ተወላጅ ስደተኞችና በኢህአዴግ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ተካሯል። የሰው ህይወት ማለፉና ነጻ እንቅስቃሴ መከልከሉ ተሰምቷል፤ እስካሁን ስድስት ሞተዋል፤ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ በርካታዎች ቆስለዋል።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውና በአውሮፓ ተቀምጠው ጉዳዩን የሚከታተሉ የጎልጉል ምንጮች እንዳሉት ኦክቶበር 5 ቀን 2013 ምሽት ላይ በትግራይ ማይ ዓይኒ ወረዳ በሚገኝ የስደተኞች ካምፕ የተቀሰቀሰው ረብሻና ተቃውሞ ወደ ሌሎች ካምፖችም ተዛምቷል። በተለይም በትላንትናው እለት ሽሬ አካባቢ በሚገኘው አድ ሃሪሽ ካምፕ የተነሳው ተቃውሞ ጋብ ሊል የቻለው ኢህአዴግ ሃይል በመጠቀሙ እንደሆነ ተመልክቷል። በዚህም የሃይል ርምጃ የቆሰሉ በርካታዎች እንዳሉ ተመልክቷል።
Mai-Aini-በአካባቢው ነዋሪዎችና ገለልተኛ ታዛቢዎች ባለመኖራቸው ጉዳዩ ይፋ ባይወጣም የተፈጠረው አለመግባባት በሁሉም የስደተኛ ካምፖች እንዳይቀጣጠል ከፍተኛ ስጋት አለ። የዜናው ምንጮች እንደሚሉት ኢህአዴግ ልዩ ክትትል በማድረግ በአካባቢው የነበረውን ነጻ እንቅስቃሴ ዘግቷል። ቁጥጥሩንም አጥብቋል። አሁን የተጀመረው ተቃውሞና ረብሻ ስደተኛ መስለው ካምፕ በተቀላቀሉ የሻዕቢያ ሰላዮች የሚቀነባበር እንጂ ሻዕቢያ ያማረራቸው የሚፈጽሙት እንዳልሆነ ኢህአዴግ በስፍራው ባሉ አመራሮቹ እየተናገረ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሱዳን የስደተኞች ካምፕ የሚኖሩ 30 ሺህ የሚጠጉ የኤርትራ ስደተኞች የስራ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ከውሳኔ መደረሱ ተሰምቷል። በዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ተቋምና በሱዳን መንግሰት መካካል በተደረገ ሰፊ ድርድር ስደተኞቹ ፈቃድ ለማግኘት የሚችሉበት አግባብ ላይ ተደርሷል። በቅርቡ በውሃ ላይ በደረሰ አደጋ ህይወታቸውን በሚያሳዝን መልኩ ያጡትን ዜጎች ተከትሎ በስደት ጣቢያዎች ለረዥም ጊዜያት የተቀመጡ የኤርትራ ስደተኞች ስራ የሚሰሩበትና ጉዳያቸው ባጭር ጊዜ የሚታይበት አግባብ ሊኖር እንደሚገባ እየተጠቆመ ነው። ከስደተኞቹ ወገንም ይህ ጥያቄ በተደጋጋሚ እየቀረበ ነው።
የሻዕቢያን አገዛዝ በመሸሽ ኤርትራን የሚለቁ ዜጎች በየጊዜው መበራከታቸው ያሳሰበው የኤርትራ መንግስት ለዜጎቹ መሰደድ የሲአይኤና የኢህአዴግ እጅ አለበት በማለት በተደጋጋሚ ክስ ማቅረቡ አይዘነጋም። ከኤርትራ በኩል እንዲህ ቢባልም ኢህአዴግ በቀጥታ ጉዳዩን አያስተባብልም። ይልቁኑም ኢህአዴግ ራሱን ከሻዕቢያ የሚሻል የዲሞክራሲ አባት አድርጎ ስለ ኤርትራ ተወላጆች መብትና ጥቅም ተካራካሪ አድርጎ ነው የሚስለው። ቀደም ሲል የረብሻውን መቀስቀስ አስመልክተን በፌስቡክ ገጻችን ባሰፈርነው ዘገባ የቆሰሉት አራት ስደተኞች ሲሆኑ ህክምና ቢደረግላቸውንም ሊተርፉ አለመቻላቸው ተጠቁሟል። ዜናውን ያቀበሉን ክፍሎች እንዳሉት ስደተኞቹ በወያኔ ደህንነቶችና ሰላዮች አንተዳደርም በማለት ያነሱት ጥያቄ መልኩ ሳይቀይር የዓለምአቀፉ የስደተኞች ኮሚሽን ጣልቃ መግባት እንዳለበት ያሳስባሉ:።
ቀደም ሲል የተነሳውን ረብሻ አስመልክቶ የሚከተለውን ዜና ጽፈን ነበር። እስካሁን ድረስ ከሻዕቢያም ሆነ ከኢህአዴግ ስለደረሰው ችግር የተሰጠ አንዳችም ፍንጭ የለም። (Photo: JRS)

የኤርትራ ስደተኞች በትግራይ ተቃውሞ አነሱ
“በኢትዮጵያ ደህንነቶች አንተዳደርም”

የሻዕቢያን አገዛዝ በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱ የኤርትራ ተወላጆች “በኢትዮጵያ ደህንነቶች ስር አንተዳደርም” በሚል የተቃውሞ ድምጻቸውን በማሰማታቸው ግጭት መነሳቱ ተሰማ። የስደተኛ ካምፑ አስተዳደሮች “ሻዕቢያ ያሰረጋቸው ሰላዮች እንጂ እውነተኛ ስደተኞች ይህንን ጥያቄ አያነሱም” ማለታቸውን ከስፍራው ከነበሩ ለመረዳት ተችሏል።
ኦክቶበር 5 ቀን 2013 ማምሻውን በትግራይ ማይኒ ወረዳ “ማይ ዓይኒ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የተቀሰቀሰው ረብሻ ሲነሳ ስደተኞቹ ያሰሙት ቅሬታ “በወታደሮች አንተዳደርም፣ የካምፑ ሰራተኞች በሙሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው፣ የደህንነት ሰራተኞች ሊያስተዳድሩን አይገባም …” የሚሉ ሲሆኑ የጥያቄያቸው መደምደሚያ “በስደተኞች ድርጅት (UNHCR) ሰራተኞች እንተዳደር” የሚል ነው።
በተጠቀሰው ቀን ምሽት በጣሊያን ውሃ ላይ ሰጥመው ለሞቱ የኤርትራ ተወላጆች የሃዘን ስሜት ለማንጸባረቅ በተዘጋጀ የሻማ ማብራት ስነ ስርዓት ላይ ረብሻው እንደተነሳ የገለጹት የስፍራው የጎልጉል ምንጭ፣ ረብሻውን ተከትሎ ድንጋይና የተለያዩ ቁስቁሶች መወርወራቸውን አመልክተዋል።
ረብሻውን ለማስቆም ታጣቂ የወታደሮች ተኩስ መክፈታቸውን የገለጹት ክፍሎች አራት ስደተኞች መቁሰላቸውን ተናግረዋል። ረብሻው እስኪነጋ ድረስ መቀጠሉንም ጠቁመዋል። ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ረብሻው ስለመቆሙ የተባለ ነገር የለም።
የዜናው ምንጮች በካምፑ አስተዳደሮች በኩል ስለሚሰጠው ምላሽ ተጠይቀው “ሻዕቢያን አምልጠው ስደት ካምፕ በሰላም የደረሱ ስደተኞች በምንም መልኩ ተቃውሞ ሊያነሱ አይችሉም። ስደተኛ መስለው የተቀላቀሉ የሻዕቢያ የደህንነት ሰራቶች ናቸው ይህንን የሚያደርጉት” ሲሉ መስማታቸውን ተናግረዋል።
ከተባበሩት የስደተኞች ኮሚሽን በስደተኞች ስም የሚገባው ከፍተኛ ገንዘብ ይዘረፋል በሚል ውስጥ ውስጡን ቅሬታ እንደሚደመጥ የጠቆሙት እነዚህ ክፍሎች፣ ገንዘብን አስመልክቶ ስደተኞች ከሚያሰሙት ቅሬታ በላይ በሙስና ለተጨማለቀው ኢህአዴግ ለስደተኞች የሚላከው ገንዘብ መጠን እንዳሳሰበው ያስረዳሉ።
ስደተኞቹ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆናቸው ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚረዱዋቸው ወገኖቻቸው በባንክ የሚልኩላቸው ገንዘብ መብዛቱ ኢህአዴግን እንዳስጨነቀው ስለ አሰራሩ የሚያውቁ ክፍሎች አስረድተዋል። ከፍተኛ መጠን ያለው ብር ወደ ስደት ካምፖች የሚላከው “በትክክል ከዘመድ አዝማድ ወይስ ከሌላ?” የሚለውን ኢህአዴግ ማጥናት ከጀመረ መቆየቱን አመልክተዋል።
በማይ ዓይኒ ካምፕ ብቻ ከ4000 በላይ ስደተኞች እንደሚገኙ የሚገልጹት ምንጮች አብዛኞቹ የአስተዳደር ሰራተኞች የኤርትራ ዜግነት ያላቸው የኢህአዴግ ወዳጆች እንደሆኑ ቢገለጽም ስደተኞቹ ሊቀበሉት አልቻሉም። ተነሳ የተባለው ረብሻ በኢህአዴግና በሻዕቢያ መካከል ያለው ውጥረት በተካረረበት ወቅት መሆኑ ጉዳዩን እንዳያወሳስበው ስጋት አለ። አስተያየት ሰጪዎች አንደሚሉት ስደተኞቹ ኢትዮጵያ ምድር ቢገኙም የሚተዳደሩት በዓለም የስደተኞች ድርጅት ስር በመሆኑ ያለመሰለል መብታቸው የተጠበቀ ነው። እንደተባለው እየተሰለሉ ከሆነ አግባብ አይደለም ድርጊቱን ድርጅቱ ራሱ ያወግዘዋል ብለዋል።
በሌላ በኩል ግን የስደት ከለላ የሰጠችውን አገር ደህንነት በሚፈታተን መልኩ መንቀሳቀስ ሌላው ትልቁ የህግ ጥሰትይሆናል ሲሉ ተናግረዋል። ዜናውን አስመልክቶ ከኢህአዴግ ወገን እስካሁን የተባለ ነገር የለም። በኢትዮጵያ በተለያዩ የስደተኞች ካምፕና በአዲስ አበባ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የኤርትራ ተወላጆች መኖራቸው ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment