FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Friday, October 4, 2013

“ኢህአዴግ፤ የምትቃወሙትንም እኔ ነኝ የምሰጣችሁ እንዳይለን” – ተቃዋሚዎች

“የኢህአዴግን የሥልጣን ዘመን አጭበርብረሃል” የሚል ወቀሳ ደርሶብኛል “ሥልጣን ለኢህአዴግ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው!” ውዲቷን ኢትዮጵያ ላለፉት 12 ዓመታት በርዕሰብሔርነት የመሯት (ወይስ መራቻቸው?) የ90 ዓመቱ አዛውንት ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፤ ከጥቂት ቀናትe100348138Ethiopia በኋላ ሥልጣናቸውን በአደራ ለሰጣቸው ኢህአዴግ አስረክበው ከቤተመንግስት በመውጣት ኢህአዴግ ወዳዘጋጀላቸው መኖርያ ቤት ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። “ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ይደረጋል” ሲባል ሰማሁ ልበል? ወይስ ጆሮዬ ነው? (ጆሮዬ በሆነ!) ለምን መሰላችሁ? መቼም እሳቸው ከሥልጣን አልወርድም ብለው ከኢህአዴግ ጋር ሙግት ሊገጥሙ አይችሉም። ይሄማ ውለታ ቢስ መሆን ነው። እናላችሁ —- “ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር” ከሚለው ይልቅ “ሰላማዊ የሥልጣን እርክክብ” ቢባል የተሻለ ሳይሆን አይቀርም የሚሉ ወገኖች አሉ። በነገራችሁ ላይ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በሥልጣን ዘመናቸው ከህመማቸው በቀር በሌላ በሌላው እድለኛ ናቸው ማለት ይቻላል። እንዴት ብትሉ—- ስንቱ ቱባ ቱባ የኢህአዴግ ሹማምንት በጋዜጠኞች ሲሞለጩና ሲተቹ፣ በፓርቲያቸው ሲገመገሙና “ሂሳችሁን ዋጡ” ሲባሉ፤ እሳቸው ግን ለ12 ዓመት እንደተከበሩ ኖረዋል። (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ!) የፕሬዚዳንቱ አማካሪ አቶ አሰፋ ከሲቶ፤ “ውጤታማና እድለኛ ናቸው” ያሉት ለዚህ ይሆን እንዴ? በእርግጥ አልተሳሳቱም፤ሰውየው እድለኛ ናቸው። ባለቀ ሰዓት ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባልሾመ አንጀታቸው የትችት መዓት አወሩዱባቸው እንጂ።
ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ ላይ ስለፕሬዚዳንቱ የ12 ዓመት የሥልጣን ዘመን አስተያየት የሰጡ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና ምሁራን በአንድ ድምፅ “ውጤታማ አልነበሩም” ብለዋቸዋል። እኔ ፕሬዚዳንቱን ብሆን (ምኞት እኮ ነው!) ምን እንደምል ታውቃላችሁ? “የእኔን እድል ይስጣችሁ” (እርግማን እኮ አይደለም!) “እንደእኔ ፕሬዚዳንት ሆናችሁ እዩት” ለማለት ነው። ልክ ነዋ! ኢህአዴግ በፕሬዚዳንትነት የሾመው ሰው ያለው ሥልጣንና ሃላፊነት የቱ ድረስ እንደሆነ ሳያውቁ እኮ ነው ተመቸን ብለው የሚናገሩት። ኢህአዴግ የሾመው ከኢህአዴግ ፍላጎት ውጭ ተዓምር እንዲሰራ መጠበቅ “ፌር” አይደለም። (በኢህአዴግ ደግሞ ትግል እንጂ “ተዓምር” መስራት አይፈቀድም!) ከፓርቲው አፈንግጦ ተዓምር ለመስራት የሚወራጭ ካለም የቀድሞው ፕሬዚዳንት የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ዓይነት እጣ ፈንታ ይገጥመዋል። ከቤተመንግስት ወጥቶ ጣራው የሚያፈስ የኪራይ ቤቶች ቤት ውስጥ ይገባል።
ይሄም ታዲያ እጁን ከፖለቲካ ሰብስቦ ከተቀመጠ ብቻ ነው። ነጋሶ ግን እጃቸውን ሰብስበው አልተቀመጡም። በግላቸው በምርጫ ተወዳድረው በማሸነፍ ፓርላማ ገቡ። ራሴ ባረቀቅሁት ህገመንግስት ውስጥ የሰፈረውን ፖለቲካዊ መብቴን ከማስወስድ የሚያፈስ ቤታችሁን ውሰዱልኝ አሉ። (“የነጋሶ መንገድ” በሚለው መፅሃፋቸው እንደነገሩን) በነገራችሁ ላይ ፕሬዚዳንት ግርማ “ውጤታማ አልነበሩም” የሚለውን የተቃዋሚዎች ትችት እየተቃወምኩም ሆነ እየደገፍኩኝ አይደለም። (“አይቻልም ወይ መኖር የማንም ሳይሆኑ” ያለችው ድምፃዊት ማን ነበረች?) እኔ ግን ጥያቄ አለኝ – በፕሬዚዳንቱ ላይ በተሰነዘሩት አስተያየቶች ዙሪያ። ፕሬዚዳንቱ ይሄን ሁሉ ዘመን ኖረው ኖረው ከቤተመንግስት ሊወጡ አንድ ሐሙስ ሲቀራቸው “ውጤታማ ነበሩ? አልነበሩም?” የሚለውን የጦፈ ሙግት ምን አመጣው? ምናልባት ኢህአዴግ አዲስ ለሚሾመው ፕሬዚዳንት ይጠቅም እንደሆነ እንጂ ለተሰናባቹ እኮ የሚተርፋቸው ፀፀት ብቻ ነው። (The damage is already done! አለ ፈረንጅ) እውነቱን ለመናገር— ተቃዋሚዎች ስለፕሬዚዳንቱ የሰጡት አስተያየት የድሮ ተረት ከማስታወስ ያለፈ ፋይዳ አለው ብዬ አላስብም (“ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” አሉ) የሚገርመው ደግሞ ከአስተያየት ሰጪዎቹ መሃል ጠንካራና ደካማ ጎኖቻቸው ወይም ስኬትና ውድቀታቸው ብሎ ከፋፍሎ ለማየት አንድ እንኳን የሞከረ የለም። ተቃዋሚዎቹ “የማርያም ጠላት” ያደረጓቸውን ያህል በፓርላማ የኢህአዴግ ደጋፊና ብቸኛው የግል ተመራጭ ዶ/ር አሸብርም እንከን የሌለባቸው ፍፁም ፕሬዚዳንት አድርገው ነው ያቀረቧቸው። (“ወልደህ ሳትጨርስ—”የሚለው ተረት ትዝ ብሏቸው ይሆን?) የፕሬዚዳንት ግርማ አማካሪ አቶ አሰፋ ከሲቶ እንኳን የቱንም ያህል መላዕክ ቢያደርጓቸው አይፈረድባቸውም (ሥራቸው ነዋ!) እኔ ተቃዋሚዎችን ብሆን ግን ትችቴን አንድም ኢህአዴግ ላይ አሊያም የፕሬዚዳንቱን ሥልጣን በገደበው ህገመንግስቱ ላይ ነበር የማነጣጥረው።
(“አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” አሉ!) እኔ የምለው ግን— ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ በፕሬዚዳንት ግርማ ላይ የወረደውን የትችት ውርጅብኝ ሰምቶ ይሆን? ከሩጫ በኋላ ፕሬዚዳንት የመሆን ፍላጎት አለኝ ስላለ እኮ ነው! (ፍላጎት ነው ምኞት?) በኋላ ከሚቆጨኝ ለአትሌታችን ምክር ቢጤ ጣል ባደርግለት ደስ ይለኛል። ለፖለቲካ ዲሲፕሊንና ልምምድ ብቻ በቂ አይደሉም። (ሩጫና ፖለቲካ ለየቅል ናቸው!) እንግዲህ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ባለፉት 12 ዓመታት ሰሩም ተባለ አልሰሩ በቅርቡ ከሥልጣናቸው ይሰናበታሉ። ከወር በፊት ይመስለኛል— ፕሬዚዳንቱ ከ“ሚት ኢቲቪ” አዘጋጅ ተፈራ ገዳሙ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ሲመረጡ የፍርሃት ስሜት አድሮባቸው እንደሆነ ጠይቋቸው፣ በመጀመርያው ጊዜ እንጂ በሁለተኛው ምንም ዓይነት ፍርሃት እንዳልተሰማቸው ገልፀው፣ለሦስተኛ ዙር በፕሬዚዳንትነት መቀጠል አለመቻሉ ትንሽ እንደሚያናድድ ተናግረዋል – በቀልድ መልክ። (ከአንጀታቸውም ሊሆን ይችላል!) ግን አያችሁልኝ— የኢህአዴግን ምስጢር ወዳድነት። እስካሁን እኮ ቀጣዩ ፕሬዚዳንት ማን እንደሚሆን ፍንጭ እንኳ አልሰጠንም። (ኢህአዴግ “ሰርፕራይዝ” ማድረግም ነፍሱ ነው አሉ!) እናላችሁ— ችግር የለም፤ ቀኑ ሲደርስ አዲሱን ፕሬዚዳንት በፓርላማ አቅርቦ ሰርፕራይዝ ይለናል – እንደ ልደት ስጦታ (ስጦታውስ ለኛ ሳይሆን ለተሿሚው ነው!) ባለፈው ሳምንት “ታጋይ ደከመኝ አይልም እንጂ ኢህአዴግ ድክም ብሎታል” በሚል ርዕስ ያቀረብኩትን ፅሁፍ ያነበቡ አንድ ደንበኛ ስልክ ደውለው እንዴት እንደወቀሱኝ አልነግራችሁም። ወቀሳው ምን መሰላችሁ? “የኢህአዴግን የሥልጣን ዘመን አጭበርብረሃል” የሚል ነው። በመቆርቆር ግን አይመስልም፤ “23 ዓመት አንቀጥቅጦ ገዝቶን እንዴት 21 ዓመት ብቻ ትላለህ? ሁለቱን የት ደብቀህለት ነው?” ነበር ያሉኝ።
እኔ እንኳን መደበቄ አልነበረም። ሁለቷ ዓመት የልምምድ ጊዜ ናት ብዬ ነበር የተውኳት (ለካስ ሂሳብ ማወራረድ ተጀምሯል!) እኔ ግን 30 እና 40 ዓመት የመግዛት ራዕይ ላለው ፓርቲ ገና ወገቡ ላይ ሆነን ሂሳብ መተሳሰብ ፋይዳው አልታየኝም። ባይሆን 30ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ሲገባ የሥልጣን ዘመኑን መቆጣጠር እንጀምራለን፤ አሁንማ ምን ተነካና። በነገራችሁ ላይ — ኢህአዴግ የሥራ ብዛትና ጫና ስላደከመው ከመውደቁ በፊት የአንድ ዓመት እረፍት ይውሰድ በሚል ያቀረብኩትን ሃሳብ አብዛኞቹ የኢህአዴግ አባላት ክፉኛ እንደተቃወሙትና እንዳወገዙት ሰምቻለሁ – “ታጋይ አይደክመውም” በማለት። ከዚህ ሃሳቤ የማልታቀብ ከሆነም በቅርቡ የተቃውሞ ሰልፍ ለመውጣት እንደዛቱብኝ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ሹክ ብለውኛል። ከሁሉም የገረመኝ ግን ምን መሰላችሁ? አንዳንድ የኢህአዴግ ካድሬዎች በእኔ ላይ ለሚደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ገና ካሁኑ መፈክሮች ማዘጋጀት መጀመራቸው ነው። (የሰልፍ ፈቃድ ሳያገኙ?) እስቲ ከመፈክሮቹ ጥቂቶቹን እንያቸው – “ኢህአዴግ ደክሞታል በሚል ማደናገርያ ሥልጣን በአቋራጭ መያዝ የህልም እንጀራ ነው!” “ሥልጣን ለኢህአዴግ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው!” “ኢህአዴግ አረፍ እንዲል የሚፈልጉት የኒዮሊበራል ተላላኪዎች ናቸው!” እኔ ግን እንደነሱ አይደለሁም።
ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ቀንደኛ አቀንቃኝ ስለሆንኩ በዛቻውም ሆነ በመፈክሮቻቸው ቅያሜ አላደረብኝም። እንደውም ያለውዝግብ የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ ካገኙ ከእነሱ ጋር ሰልፍ ለመውጣት ሁሉ አስቤአለሁ – ተቃውሞው በእኔ ላይ ቢሆንም። ከገዢ ፓርቲ ጋር ተቃውሞ ሰልፍ ማድረግ ምን ዓይነት ስሜት እንደሚፈጥር ማወቅ እፈልጋለሁ (ለጠቅላላ እውቀት እኮ ነው!) በዚያ ላይ ተቃዋሚዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚጠሩት በእያንዳንዱ ሰልፍ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ፈቃድ ክፍልና ከፖሊስ ጋር የሚጋቡትን እልህና ውዝግብ ሰበብ ለማወቅ እፈልጋለሁ። ኢህአዴግስ ተመሳሳይ ውዝግብና እልህ ውስጥ ይገባል ወይስ ነገሩ አልጋ በአልጋ ይሆንለታል? (የባለቤቱ ልጅ መሆኑ እኮ አልጠፋኝም!) ይሄን ሁሉ የመፈተሽና የማጥናት ፍላጎት አለኝ። ስፖንሰር ተደርጌ እኮ አይደለም። (የሃገሬ ጉዳይ አያገባኝም እንዴ?) ባለፈው እሁድ ሰማያዊ ፓርቲ በመስቀል አደባባይ ሰልፍ ለማድረግ ጠይቆ፤ ቦታው በኮንስትራክሽን ሥራ ላይ እንደሆነና “ለልማት ነው ቅድምያ የምንሰጠው” የሚል ምላሽ እንደተሰጠው ገልጿል።
በዚሁ ሰበብ ፖሊስ ከቢሮው ንብረቶች እንደወሰደበት እንዲሁም እሁድ እለት ሰልፉን ሊያካሂዱ ሲሉ መንገድ በመዝጋት ሰልፉን እንዳቋረጠባቸው ፓርቲው በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። አንድነት ፓርቲም በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጠይቆ፤ ሌላ አማራጭ ቦታዎች አቅርብ ከተባለ በኋላ ያቀረበው ሁሉ ውድቅ ሆኖ ሰልፉን ጃንሜዳ አድርግ እንደተባለ አስታውቋል። በዚሁ ሰሞን ሰላማዊ ሰልፍን የሚገድብ አዲስ መመሪያ ከአዲስ አበባ መስተዳድር መውጣቱን የሚናገሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ የተቃውሞ ሰልፉ የሚደረግበትን ቦታና ጊዜ የሚወስነው መስተዳድሩ እንደሆነ ጠቁመው፤ “አሁን የቀራቸው የምትቃወሙትንም የምንሰጣችሁ እኛ ነን” ማለት ብቻ ነው ሲሉ ክፉኛ አሽሟጠዋል። አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊ አዲስ ወጣ በተባለው መመሪያ ተናዶ ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ? “እንደዚያ ከሆነማ ለምን ሰልፍ የሚወጣውንም ህዝብ እነሱ አይመድቡልንም?” በአሁኑ ጊዜ ኢህአዴግ የተቃዋሚዎች ሰልፍ በጣም አስፈርቶታል የሚለው ይሄው የተቃዋሚ ደጋፊ፤ “በመኪና ለመቀስቀስ፣ ፖስተር ለመለጠፍ፣ በራሪ ወረቀት ለመበተን፣ ወዘተ— ለሁሉ ነገር አስፈቅዱኝ እያለ ነው፣ ለምን መፈክሮቹንም እሱ አያዘጋጅልንም” በማለት አዲስ የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ለገዢው ፓርቲ አበርክቶለታል። “እናም ኢህአዴግ በቅርቡ “ሰላማዊ ሰልፍ እናዘጋጃለን፣ የተቃውሞ አጀንዳዎችን እንቀርፃለን፣ ለሰልፍ የሚወጣ ህዝብ እንመለምላለን፣ በራሪ ወረቀቶችን እናዘጋጃለን፣ የተቃውሞ ሰልፍ ቅስቀሳ እናደርጋለን ወዘተ– የሚል ልዩ ማስታወቂያ በኢቴቪ ሲያስተላልፍ ልንሰማ እንችላለን” ብሏል – የተቃዋሚ ደጋፊው። (ግን ወዴት እየሄድን ይሆን? ለሁሉም የቀረበ ወቅታዊ ጥያቄ ነው!)

No comments:

Post a Comment