FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Saturday, October 19, 2013

የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጐቹ ራሳቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ አስጠነቀቀ

አልሸባብ የፍንዳታ ጥቃት ለማድረስ ዝቷል

ባለፈው እሁድ በቦሌ ሚካኤል አካባቢ ከደረሰው ፍንዳታ ጋር ተያይዞ ሁለት ተጨማሪ የፍንዳታ ጥቃት ለማድረስ አልሸባብ የተሰኘው የሶማሊያ ቡድን እንደዛተ የገለፀው የአሜሪካ ኤምባሲ፤ የዛቻው ተአማኒነት ባይረጋገጥም በኢትዮጵያ የሚገኙ አሜሪካዊያን ጥንቃቄ እንዳይለያቸው አሳሰበ፡፡
የኢትዮጵያና የናይጄሪያ ቡድኖች ግጥሚያ በሚካሄድበት ሰዓት ጥቃት ለመፈፀም ሲዘጋጁ የነበሩ ሁለት ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ሲሆን በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት በማወጅና ሽብር ለመፈፀም በመዛት የሚታወቀው አልሸባብ “ድርጊቱ በኔ አባላት የተፈፀመ ነው” ብሏል፡፡
አልሸባብ በቦሌ ሚካኤል ለተከሰተው ፍንዳታ ሃላፊነት እንደሚወስድ በትዊተር እንዳስታወቀ ኤምባሲው ጠቅሶ ባሰራጨው ማሳሰቢያ፤ በፒያሳና በቸርችል ጐዳና አካባቢ የፍንዳታ ጥቃት ለመፈፀም እንደዛተም ገልጿል፡፡
በቦሌ ሚካኤል በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ በተከሰተው ፍንዳታ ሁለት የሶማሊያ ተወላጆች መሞታቸውን የገለፀው ፖሊስ፤ ከሟቾቹ አንዱ የኢትዮጵያ ማሊያ በመልበስ ከኳስ ተመልካቾች መሃል የፍንዳታ ጥቃት ለመፈፀም እየተዘጋጀ እንደነበር ጠቁሟል፡፡
ለጥቃት የታሰበው ፈንጂ እዚያው ፈንድቶ ነው ሁለቱ አሸባሪዎች የሞቱት ብሏል - ፖሊስ፡፡ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል፤ የፍንዳታው ፈፃሚዎች አልሸባብ መሆናቸውን ተጠይቀው ገና አልተረጋገጠም ብለዋል፡፡
የፀረ ሽብር ግብረ ሃይል ጉዳዩን እየመረመረ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ሽመልስ፣ ግብረ ሃይሉ የደረሰበት ውጤት ጊዜውን ጠብቆ ይፋ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment