ከውጭ ሀገር የወልቃይት ጠገዴ ተወላጅ ኢትዮጵያዊያን
“ሰውን ሰው ውጦት” ይላሉ እናቶቻችን የእናትነትንና የወሊድን ምስጢር ሲገልፁ፡፡ በዚህ የፈጣሪ ህግጋት ተገዳ በምጥ የምትጨነቅን እናት፣ እህት፣ ወይም ሚስት በጭካኔ መኪና ላይ እንደ አልባሌ እቃ ተወርውራ ከእነ ፅንሷ ለሞት ስትዳረግ፤ ለአይን የሚያሳሱ የእግዚአብሔር ንፁሃን ህፃናት ተወልደው ከሚድሁበት ቀያቼው እንደ ትቢያ ታፍሰው በግፍ በመወርወራቸው እስትንፋሳቸው በጭንቅ ስትቋረጥ ፤ ክፉና ደጉን ለይተው የሚያውቁ(የማያውቁ አላልንም) ታዳጊ ወጣቶች ሃገሬ ከሚሏት መንደራቸውና ህይወቴና ሙያዬ ከሚሉት የትምህርት ገበታቸው በማን አለብኝነት ሲሳደዱ፤ አባወራዎች ሀገሬ ርስቴ ብለው ጫካ መንጥረው፣ የእባብና የጊንጡን ንክሻ ችለው፣ የጅብና የአንበሳውን ትግልና ንጥቂያ ተቋቁመው ከቆረቆሩትና ካለሙት ቀያቸው በልጆቻቸውና በሚስቶቻቸው ፊት እንደ ሌባ እየተገረፉ፣ እንደ መፃተኛ ሲዋከቡና ወደ ማያውቁት ስፍራ በገፍ ሲጋዙ ማየትና መስማት ይልቁንም ይህ ሁሉ ሰቆቃና ግፍ የሚፈፀምባቸው “ዐማራ” በመሆናችሁ ነው መባሉ ምንኛ ነብስያ ድረስ ያማል? እንደምን እንቅልፍ ይነሳል? እኮ ምን ያህልስ ያስቆጣል?
ወያኔዎች ታላቋን ትግራይ ለመመስረት ካደረባቸው ጽኑ ህመም በመነሳት በ1968ዓ.ም የትግራይ ማኒፌስቶ በመቅረጽ ከተነሱበት ግዜ ጀምሮ የጎንደርንና የወሎን ለም መሬቶችን በመቆጣጠር ሲጀመር በነዚህ አካባቢዎች ውስጥ ነዋሪ የሆኑትን ጎንደሬዎች በማፅዳትና በትግራይ ህዝብ በመተካት ይጠናከርና ማቆሚያው የጠፋች ወይም እጅግ ደካማ የሆነች ኢትዮጵያን በመፍጠር ይሆናል።
ይህን እኩይ ሴራ እውን ለማድረግ ወያኔ ከ1972ዓ.ም ጀምሮ ወደ ጎንደር ለም መሬቶች ወደ ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት በመዝለቅ ዘር ማፅዳቱን ቀጥሏል፡፡ ከዚያን ግዜ ጀምሮ እስከ 1983ዓ.ም ድረስ በነበረው የመከራ ጊዜ ብቻ ከ20,000 በላይ ንፁሃን ወገኖቻችን በህወሃት “ባዶ ስድስት” እየተባለ በሚታወቀው አሰቃቂ የመሬት ውስጥ እስር ቤት ታጉረው በግፍ ያለቁ ሲሆን፣ ከ70,000 በላይ ህዝባችን የህወሃት ወራሪ ቡድን በአካባቢው የሚፈፀመውን ግፍና መከራ በመሸሸት ለስደት ተዳርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚያ እጅግ ዘግናኝና ታሪክ ይቅር ከማይለው ሰቆቃ ማምለጥ ያልቻሉ ሴቶች፣ ህፃናትና፣ አረጋውያን ባድማ ጠባቂ በመሆን ቀጣዩን የህወሃት ግፍና መከራ ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡
የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር በትረ መንግስቱን ከጨበጠ በኋላም ቢሆን እስካሁኗ ደቂቃ ድረስ አንድን ዘር አጥፍቶ በሌላ የመተካት(Ethnic Cleansing) ወንጀል እየፈጸሙብን ይገኛል። በኃይልና በማናለብኝነት ርስታችንን ወደ ትግራይ ከመከለል፣ በብዙ መቶ ሺዎች የትግራይ ሰፋሪዎችን ከማስፈር፣ ሴት ልጆቻችንና እህቶቻችን በትግራይ ኮርማዎች ከማስወለድና ከማስደፈር፣ ልጆቻችን በአማርኛ እንዳይማሩ ከማገድና ከመከልከል፣ በየምክንያቱ ንብረታችንና ገንዘባችንን በመዝረፍ በድህነት አዘቅት ውስጥ እንድንገባ ከማድረግና የበይ ተመልካች እስከመሆን ድረስ ሲያደርሱን፤ በቅርቡም ለሱዳን በገፀ-በረከትነት ተሸልሞ ከተረፈው ዳር-ድንበራችን ወደ ሱዳን ድንበር አዋሳኝ ያሉትን ለም መሬቶች ከአርማጭሆ አውደራፊ እስከ መተማ ድረስ ለመቆጣጠር እንዲያመች ዐማራዎችን እያስለቀቁ የትግራይ ሰዎችን እያሰፈሩ እንዳሉ ገሃድ ሲሆን የሰሞኑን በጉራ ፈርዳና በቤንሻንጉል ክልል በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የዐማራ ተወላጆች የበረሃ በሽታን፣ የጊንጥና የእባብ ንክሻን ተቋቁሞ መሬቱን አልምቶ መጠቀም ሲጀምር ያፈራውን ሃብትና ንብረት ለመከወን ግዜ ሳይሰጠው እንደከብት በጅራፍ እየተነዳ ከገዛ አገሩ ሲባረር በብስጭትና በቁጣ እያየን ነው።
እንደ ወያኔዎቹ እኩይ አላማና እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የስነልቦና ዝግጅት ከሆነ ይህ በወገኖቻችን ላይ የሚፈፀመው ግፍ መከራና ሰቆቃ ከዚህ በከፋ ሁኔታ ይቀጥላል የሚል ግምት አለን። በዚህም መንገድ የሞተች ወይም ደካማይቱን ኢትዮጵያ እስክትፈጠር ድረስ የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር ተልእኮ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
እዚህ ላይ ያነሳናቸውንና ለማሳሰብ የፈለግናቸውን ሃገራዊ አደጋ ለማሳየት ይረዳን ዘንድ የቅርብ ጊዜ ታሪኮችን በማጣቀሻነት እናንሳ፡፡
የታሪክ ማጣቀሻ አንድ
የተከበሩ አቶ በድሩ አደም በምርጫ 97 ወቅት ሚያዝያ 30 ቅንጅት በጠራው የድጋፍ ሰልፍ ላይ አደረጉት የተባለው ንግግር ውስጥ “ወያኔን በካርዳችን ወደ መጣበት እንመልሰዋለን” አሉ ተብሎ የሃገሪቱ ብቸኛው በመንግስት የሚተዳደረው ኢቲ ሬድ/ቴሌቪዥንና በውጭ ሃገር የሚገኙ አፍቃሪ ትግራውያን ሚዲያዎች ቅንጅት ትግሬዎችን ወደ መጡበት ወደ ትግራይ እናባርራለን አሉ በማለት በትግሬዎች ላይ በከፈቱት የሃሰት የሽብር ዘመቻ ሀገር ምድሩን እንዲያ ሲያውኩ ዛሬ በተጨባጭ የ”አማራ” ተወላጆችን ወደ መጡበት የመመለስ መለሳዊ ራዕይ/ዘመቻ ሲተገበር ልሳናቸው መዘጋቱ የማፅዳቱ መሪና ወደ መጡበት የ“መመለስ” ሴራ የማን እንደሆነ በገሃድ ያጋለጠ ይመስለናል፡፡
ይህ “አማራ” ናችሁ እየተባለ በንፁሃን ወገኖቻችን ላይ የሚፈፀመው አረመኔያዊ ሰቆቃና ግፍ ለእኛ አንድን ታላቅ/ታናሽ የታሪክ ምዕራፍ መከፈቱንና በተለይም ዛሬ በህወሃት/ወያኔ ፊት አውራሪነትና በቤንች ማጂ፣ በጉምዝና በሽናሻ የበታች/የበላይ አስተዳደር ትርጁማንነት በጉራፈርዳ/ደቡብ እንዲሁም በማሻ/ቤንሻንጉል አካባቢ እየተፈፀመ የሚገኘው “ዐማራን የማፅዳት ዘመቻ” የአባቶቻችን ታላቋ ኢትዮጵያ በትግራይ “ምርጥ” ልጆቿ ወደ ተዘጋጀላት የእርድ ቁልቁለት እያመራች ለመሆኑ የመጨረሻ ደወል ይመስለናል፡፡
የታሪክ ማጣቀሻ ሁለት
የተከበሩት ፕ/ር አስራት ወልደየስ (አፈሩ ይቅለላቸውና) የዛሬ 20 ዓመት አካባቢ በሽግግሩ ወቅት ገና ህወሃትና ኦነግ ከፍቅራቸው ፅናት የተነሳ በአንድ የእንትን ሳህን ላይ አብረን ካልተቀመጥን እያሉ ሲያውኩና “ነፍጠኛ” በሚል የጅል ዘፈናቸው ሲያደነቁሩን በነበረበት ወቅት ለፍቅራቸው መገለጫ ይህንኑ “ዐማራ” የሚሉትን ህዝብ በበደኖና በአርባጉጉ እንደ በግ ሲያርዱትና ወደ መጣህበት ተመለስ እያሉ ሲያሳድዱት “የፍትህ ያለህ” እያሉ ሲጮሁና መጪውን አደጋ ሲያመላክቱ የኦሮሞ ህዝብ፣ በተለይም ልሂቃናቱ ልባቸው እንደ ፈርኦን ደንድኖ ነበር፡፡
በወቅቱ ሂደቱን ላስተዋለ ሁሉ መጪው ጊዜ ግልፅ ነበር፡፡ ይሃውም የኦሮሞን ህዝብ ከኢትዮጵያዊነቱና ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ከሆነው ከ“ዐማራ” ህዝብ በደም ከለዩት በኃላ ህወሃት/ወያኔዎቹ እያሳደዱ እንደሚያርዱትና እንደሚያግዙት እርግጥ ነበር፡፡ ለምንስ ቢሉ ህወሃት የአንድነትና የሉዓላዊነት ጠላት፣ የኢትዮጵያዊነትና የታላቅነት ፀር፣ እንዲሁም የትግሪያዊ ስግብግብ ታላቅነት ህልመኛ ነውና ነው፡፡ የተፈራው አልቀረም ዛሬ ልጇ በህወሃት/ኦህዴድ የዘረኝነት ሰይፍ ያልታረደባት፣ አልያም የሀገሪቱ እስር ቤቶች በሙሉ ወለጋ /አርሲን እስኪመስሉ ድረስ በእስር ቤት ያልተወረወረባት የኦሮሞ እናት አትገኝም፡፡ ውጤቱም ሆነ የተፈራውም ይሄው ነበር፡፡
የታሪክ ማጣቀሻ ሶስት
በቅርቡ ያው የተፈረደበት “አማራ”/የመሃል ሃገር ሰው ከክልላችን ይውጣልን በማለት እንደመቀጣጫ ከ9 ያላነሱ(ለጊዜው ቁጥራቸው ተዘንግቷል) ኢንጂነሮችንና የተለያዩ የመንገድ ስራ ባለሙያዎችን በስለት እንደበግ በማረድና የተቆራረጠ አካላቸውን በጆንያ በመክተት ወደ ቤተሰቦቻቸውና ወደ አካባቢው ነዋሪ በመላክ የአውሬነታቸውን ልክ የገለጡትና በኋላም እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸውን የ“ዐማራ” ተወላጆች በማፈናቀል የተጠናቀቀው የጋምቤላው ሰቆቃና ግፍ አንዱ ነበር፡፡ ታዲያ ህወሃትና የጋምቤላው መንግስት የጋምቤላን ህዝብ ከደጀኑ ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጋር እንዲያ ደም ካቃቡት በኋላ ዛሬ የዓለም አቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) በዘር ማጥፋት ወንጀልነት የመዘገበውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ አኝዋኮቹ በተራቸው እንዲያስተናግዱ ታሪክ ግድ ብሏቸዋል፡፡
እንግዲህ ከላይ በተከታታይ ከጠቀስናቸው ሶስት “የታሪክ ማጣቀሻዎች” በመነሳት ቀጣዩ “ባለ ሳምንት” ማን እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም፡፡ የደቡቡ ጉራፈርዳም ሆነ የቤንሻንጉሉ ማሻ “ዐማራ”ን በመጨረስና በማፈናቀል የሚጠናቀቁ ቢሆን ኖሮ የትግሉ አቅጣጫ አንድ ወጥ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን የህወሃት/ወያኔ አላማና የጎደፈ ታሪካቸው እንደሚያዘክረው ከሆነ፡ የመጨረሻ ውጤቱ አሁን ከምናየው በእጀጉ የተለየና የራቀ ነው፡፡ ይኃውም ቀጣዩ የአውሬው የጅምላ ፍጅት ሰለባዎች ደቡቦች/ቤንች ማጂዎችና ቤንሻጉሎች የመሆናቸው እውነታና አይቀሬነት ነው፡፡
ይልቁንም ዛሬ በጉራፈርዳና በማሻ አካባቢ በሚገኙ ንፁሃን ወገኖቻችን ላይ እየተፈፀመ ያለው ሰቆቃ የመጨረሻ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን እኛን አሞናል፡፡አስቆጥቶናል፡፡ በበኩላችን ዛሬ ለህመማችንም ሆነ ለቁጣችን ልክ የለውም፡፡ ምን አልባት በእነ ህወሃትና በደቡቦቹም ሆነ በቤንሻጉሎቹ መንደር የአንዳንድ ተራ ኢትዮጵያውያን በተለይም “ዐማራ” መቆጣት የዘወትር መሳለቂያና መደበሪያ ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ማን ያውቃል እኛም ነገ እልፎችን እናስከትል ይሆናል፡፡ የወገኖቻችንም እንባና ሰቆቃ ለአንዴና ለመጨረሻ ለማስቆም ለህወሃትና ለአጫፋሪዎቹ የወለድ አግድ ዋጋን ከፍለንም ቢሆን የምናስቆምበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም፡፡
ዉድ ኢትዮጵያዊያን ወገኖች ትላንትም ዛሬ በወልቃይትና በጠገዴ እንዲሁም በጋንቤላ በሌላም በሌላ… ዛሬም የትናቱ ቀጣይ በጉራፈርዳና በቤንንሻንጉል ዐማራ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመና እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጽዳት የወያኔ ዘመቻ ነገም በቀሪው ኢትዮጵያዊ ወገን ላይ እንደሚፈጽም መጠራጠር ያለብን አይመስለንም። ስለዚህም ከተጣለብን አፍዝዝ አደንዝዝ አዚም በመላቀቅ ነገ በእኔ በማለት ሀገራችን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችንን ለማዳን አሁኑኑ እንነሳ! በህወሃት/ወያኔ የዘር ማጽዳት ዘመቻ ገፈት ቀማሽ የሆነው እኛ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጅ ጎንደሬ ኢትዮጵያውያን ሀገርንና ወገንን ለማዳን በሚደረገው ትግል ግንባር ቀደም በመሆን የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁዎች መሆናችንን መግለፅ እንወዳለን!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
No comments:
Post a Comment