በስደት አገራቸውን ለቀው የወጡ ሰዎች ያለመሰለል መብት አላቸው። በህግም የተደነገገ ነው። ከለላ የሰጣቸውም አገር ይህንን የመከላከልና የመቃወም ግዳጅም አለበት። ከለላ ያገኙ ስደተኞችም ሆኑ ከለላ እንዲሰጣቸው ያመለከቱ ወገኖች ስለመሰለላቸው ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ ከቻሉ ህጉን ጠቅሰው የመከራከር መብት አለቸው። ለመብታቸው ሲከራከሩ በመደራጀት ቢሆን ይበልጥ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ አውሮፓ በስደት ያሉ ቀድሞ የውጪ ጉዳይ የዲያስፖራ ኢንጌጅመንት ዳይሬክቶሬት ዲፓርትመንት ኤክስፐርት ይናገራሉ።
እኚሁ ሰው እንደሚሉት ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ በአቶ መለስ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የተቋቋመው ይህ ዲፓርትመንት ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለወቅቱ የውጪጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን ሪፖርት ያቀርብ ነበር። በጁላይ 2003 ስድስት አባላትን በመያዝ የተቋቋመው ዲፓርትመንት “ብዙሃን አድፋጭ” ዲያስፖራ ወይም “silent majority” የሚባሉትን ለመማረክና በስደት ውጪ አገር የሚኖሩትን የተቃዋሚ ድርጅት ዋና ደጋፊዎችንና አመራሮችን የሚከታተል ቻፕተሮች አሉት።
የአገዛዙ ደጋፊ ለሚባሉት ዲያስፖራዎች የቀረጥ ነጻ መብት በመስጠት፣ መሬት በማደል፣ በማህበራት በማደራጀት ቢቻል መታወቂያ በመስጠት፣ “ለአገር ግንባታ ደጋፊ ማድረግ” በሚል ሽፋን በያሉበት አገር ከኤምባሲ ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ በማድረግ የተዘረጋው መዋቅር የአውሮፓውን የክትትል ስራ በግንባር ቀደምትነት እንዲመራ የመደበው የብራስልስ ኤምባሲን ነው። በቤልጂየም ኢትዮጵያ ኤምባሲ ካውንስለር በመሆን የሚያገለግሉት የቀድሞው የህወሃት ታጋይ ይህንኑ የአውሮፓ የክትትል ቻፕተር እንደሚመሩት የሚያስረዱት የቀድሞ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰራተኛ የቻፕተሩን ጠርናፊ “አቶ መለስ በታመሙበት ወቅት ብራስልስ ሆነው አስፈላጊውን ሁሉ ሲያደርጉ የነበሩ የስርዓቱ ታማኝ ሰው ናቸው” ሲሉ ይገልጹዋቸዋል።
በጥቅማ ጥቅም ዲያስፖራ ውስጥ ሆነው የክትትል ስራ በመስራት በያሉበት አገር ካለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር ግንኙነት በመፍጠር ስርዓቱን የሚያገለግሉ ስለመኖራቸው በውል የሚናገሩት እኚሁ ሰው “ስርዓቱን ሸሽተው ጥገኛነት የሚጠይቁ ኢትዮጵያውያን ስለ አገዛዙ የሚሰጡት መረጃ ስለሚያንገበግባቸው ዲያስፖራው ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ ለማኮላሸት ከፍተኛ በጀት ይመደባል። በዚሁ በጀት እጅግ ቀረቤታ ላላቸው ደጋፊዎቻቸው በሚኖሩበት አገር ተራ የጉልበት ሰራተኛ የሚያገኘው ክፍያ ተሰልቶ ይከፈላቸዋል” በማለት አገሩን፣ ቤተሰቡን፣ ንብረቱን፣ ቤተዘመዱን ጥሎ የሸሸውን ዜጋ እየተከታተሉ ሪፖርት ስለሚያቀርቡት ክፍሎች ይናገራሉ።
ሰፊ ማብራሪያ ያቀረቡት እማኝ የኢህአዴግ ደጋፊዎች የልማትና ድጋፍ ማሰባሰቢያ መድረኮችን በማመቻቸት ታማንነታቸውን እንደሚያሳዩ የሚገልጹት የቀድሞ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ባልደረባ “ይህ አሰራር የተኮረጀው ከቻይና ነው። የተለያዩ አገር አሰራሮችና የደህንነት መዋቅሮች የተጠኑ ቢሆንም የ ቻይናው የተመረጠው ለስራውና ኢህአዴግ ለሚፈልገው አደረጃጀት አመቺ ሆኖ በመገኘቱ ነው” ሲሉ የመዋቅሩን ተፈጥሮ ያስረዳሉ።
ከሳምንት በፊት በኖርዌይ ስታቫንገር፣ ዛሬ ኤፕሪል 28/2013 ደግሞ በኦስሎ ስለተካሄደው የቁጣ ተቃውሞ አስተያየት የሰጡት እኚሁ ሰው “ኢህአዴግ ሊገለኝ ነው በማለት ሸሽተው ጥገኝነት የጠየቁ ወገኖች ከመንግስት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም። ሊኖራቸውም አይችልም ማስረጃ በማሰባሰብ ጉዳዩን ወደ ህግ ማቅረብ ይቻላል” ባይ ናቸው።
“ተሰደን አገር ለቀን ወጣን። አገራችን እንዳንኖር ተደረግን። በስደት በምንኖርበት አገር ድረስ መጥተው ገንዘብ ሊጠይቁን ማሰባቸው ይገርማል። እንደዚህ ገንዘብ የተጠሙበት ምክንያት ምን ይሁን? ኢህአዴግ አገሬ እንዳልኖር አደረገኝ፣ ህይወቴ አደጋ ላይ ነው በሚል ከለላ የጠየቀ ሰው እንዴት መንግስት ደጅ ይቀርባል። ይህ እኮ ህገወጥ ነው። ወንጀል ነው። ከለላ የሰጠው አገርም ሆነ ዋናው የስደተኞች ህግ አይደግፈውም” በሚል አንድ ጥግ ይዘው የሚነጋገሩና የሚወያዩም አጋጥመውኛል።
መከላከያው አክራሪንና አልሸባብን ይደመስሳል በሚል የማይነጥፍ ገበያ አላቸው። መሬት ይሸጣሉ። ንግዱን ተቆጣጥረውታል። ኢንቨስትመንቱን በጃቸው አድርገውታል። አስመጪና ላኪነቱን የግላቸው አድርገውታል። ባዕድ ሃይል የማያደርገውን የከፋ ተግባር እንመራዋለን በሚሉት ህዝብ ላይ ይፈጽማሉ። አገሪቱን በዘርና በጎሰኝነት አስተሳሰብ መርዝ በክለው እርስ በርስ እያጫረሱ ምድሪቱን የበቀል ቡቃያ አድርገዋታል። ታዲያ እነዚህ ሰዎች በየትኛው ሞራላቸው ነው ስደት የሚለበልባቸውን ዜጎች ሰብስበው ገንዘብ የሚጠይቁት? የሁሉም ጥያቄ ነው።
በተጠቀሰው ቀን ለአባይ ግድብ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ለማካሄድ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ አጭር የስልክ መልዕክት (የኤስ ኤም ኤስ) ጥሪና በተለያዩ አደረጃጀቶች ጥሪ ተበትኖ ነበር። ኦስሎ የሚኖሩ የስርዓቱ ሰለባዎች ራሳቸውን አደራጅተውና ግብረኃይል አቋቁመው በስብሰባው ለመገኘት ዝግጅታቸውን አስቀድመው እንዳከናወኑ በስፍራው የነበሩ ለጎልጉል ዘጋቢ አመልክተዋል።
እንደተባለው ጠዋት ረፈድ ፈድ ሲል በስቶኮልም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰው ስብሰባውን ለመምራት ወዳጆቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ያዘጋጁት መድረክ ላይ ለመቀመጥ Radisson Blue Scandinavia Hotel ሲደርሱ የጠበቃቸው ሌላ ነበር። በስብሰባው ለመገኘት የሚያስችል “የዜግነት” መብት ያላቸው ወገኖች ስብሰባውን ለመካፈል ጠየቁ። “አትገቡም” ሲባሉ ተቃውሟቸውን ከቁጣ ጋር አሰሙ። ባለስልጣኑ ማሽላ እያረረ ይስቃል እንደሚባለው ፈገግታ በማሳየት በምሬት በሚወርደው የተቃውሞ ቃል መገረፋቸውን ለመደበቅ ሞከሩ። ንዴታቸውን ለመደበቅ ሲታገሉ ጭራሹኑ ስብሰባውን ማድረግ በማይችሉበት ደረጃ ተቃውሞው ስለጨመረ ለአባይ ግድብ ብር ለማሰባሰብ የተወጠነው የኦስሎው ውጥን ስታቫንገር እንደሆነው ተኮላሸ። ፖሊስ ስብሰባው ሊካሄድ እንደማይችል አረጋገጠ።
በኖርዌይ ከሚታተሙትና ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ዜና ካሰራጩት መካከል፣ ቬጌ የሚባለው ጋዜጣ አስራ አንድ ሰዎች ህገወጥ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል በሚል መታሰራቸውን አስነበበ። በስፍራው ቁጣቸውን የገለጹ ወገኖች ሳያስፈቅዱ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል በሚል ጋዜጣው የእስሩን ምክንያት ፖሊስን ጠቅሶ አስፍሯል። በስፍራው የተገኙም ሆኑ የዚህ ሪፖርት አቅራቢ እንደታዘበው ዜጎች አስቀድመው የጠየቁት በስብሰባው ላይ እንሳተፍ የሚል የዜግነት ጥያቄ ነበር። በጥያቄያቸው መሰረት ወደ ስብሰባው ቦታ ለመግባት ሳይችሉ መከልከላቸው እንደ ዜጋ የሞራልና የማንነት ጥያቄ በመሆኑ ቁጣቸው ከስርዐቱ ተፈጥሮ ጋር ተዳምሮ የነደደ ነበር።
ከፍተኛ ቁጥር የነበረው የፖሊስ ሃይል አስራ ሁለት ተሽከርካሪዎችን አሰልፎ የቁጣውን ሰልፍ “ለመቆጣጠር” እንደቻለ፣ የሰለጠኑ ውሾችና ከሆቴሉ በቅርብ ርቀት ሄሊኮፕተርም ተዘጋጅቶ እንደነበር ቬጌ አስነብቧል። የጎልጉል ሪፖርተር ባሰባሰበው መረጃ አባይ ቢገደብ የሚጠሉ ወገኖች የሉም። ቅድሚያ ሊከናወኑ የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ግን ይስማማሉ። ቅድሚያ አፈናውና ያለ ህዝብ ውክልና በጠመንጃ ከህዝብ ጫንቃ ላይ መንሰራፋት ሊቆም ይገባዋል። የመብት ገደብም ሊቆም ግድ ነው። ይህ ሲሆን ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ገንዘብ የሌለው በጉልበቱ አድርግ የተባለውን ያደርጋል። አገርም በዜጎቿ ፍላጎትና እኩል ተሳትፎ ያለ ስጋት ትለማለች።
የታሰሩት ሰዎችን በተመለከተ ይህ ሪፖርት እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ ስለመፈታታቸው የተሰማ ነገር የለም። በሳምንት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ጠንካራ ሊባል የሚችል ተቃውሞ ያጋጠመው ኢህአዴግ፣ በኖርዌይ ተመሳሳይ ፕሮግራም ለማካሄድ ባይሞክር እንደሚሻለው ገለልተኛ ነን የሚሉ ወገኖች ተናግረዋል። አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ወቅት በኖርዌይ የገጠማቸው ተቃውሞ የከፋ እንደነበርና የመጡበትን ጉዳይ በወጉ ሳይጨርሱ መመለሳቸውን ያስታወሱት እነዚሁ ክፍሎች “አሜሪካ በዲቪ የተጓዙ ደጋፊዎች ሊኖሩ ይችላሉ። አውሮፓ ግን በትምህርት መጥተው የቀሩ ካልሆኑ በስተቀር ኢህአዴግ በግልጽ ሊደግፉት የሚችሉትን አባላት ለመግኘት አይቻለውምና አባይን እንደጀመረው ከቻይና ተበድሮ ቢያጠናቅቀው ይመረጣል” ብለዋል። ኢህአዴግ በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች፣ በሳዑዲ አረቢያ፣ በዱባይ፣ በደቡብ አፍሪካ ተመሳሳይ ተቃውሞ እንደገጠመው በተለያዩ ሚዲያዎች መዘገቡ የሚታወስ ነው። (ፎቶ: VG)
No comments:
Post a Comment