ከበትረ ያዕቆብ
ለረጅም ጊዜ የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ አዘጋጅ ሆኖ ያገለገለዉና የጋዜጣዉ ህትመት ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ የኢቦኒ መፅሔት ዋና አዘጋጅ ሆኖ በመስራት ላይ የሚገኘዉ ጋዜጠኛና ብሎገር ብስራት ወልደ ሚካኤል ሰሞኑን በ4 የደህንነት ኃይሎች ታግቶ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እንደተፈፀመበት ተናገረ ፡፡ ድርጊቱ የተፈፀመዉ ባሳለፍነዉ ሰኞ (ነሐሴ 20 – 2005ዓ.ም) ከምሽቱ 2፡35 ላይ ከስራ ወደ ቤቱ በጉዞ ላይ እያለ ነበር፡፡
ብስራት ወልደ ሚካኤል እንደገለፀዉ ግለሰቦቹ ለ50 ደቂቃ ያህል ያገቱት ሲሆን ፤ ከአሁን በኋላ በየትኛውም ጋዜጣ ፣ መፅሔትም እንዲሆም ብሎግ ላይ ብትፅፍ በህይወትህ ላይ ፈርደህ ነዉ ሲሉ ዝተዉበታል፡፡ በመጨረሻም በጥፊ መተዉታል፡፡ ብስራት እንደገለፀዉ ከሰዎቹ መካከል አንዱ ሽጉጡን እየደጋገመ በማሳየት ሊያስፈራራዉ ሙከራ ያደረገ ሲሆን ፤ ሌላኛዉ ደግሞ እንዳይንቀሳቀስ ሴንጢ በሆዱ ላይ ደግኖበት ነበር፡፡ ጋዜጠኛ ብስራት አያይዞም “አቶ መለስ ዜናዊ አለዉ ከተባለዉ 3 ቢሊዮን ዶላር እና ልጁ ከታማችበት 5 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም የፀረ ሽብርተኝነት ህጉን በሚመለከት የፃፋኳቸዉ ፅሑፎች እንዳናደዷቸውና እንዳበሳጯቸው በንግግራቸው ይጠቃቅሱልኝ ነበር” ሲል ተናግሯል፡፡
“ይህን የጋዜጠኝነት ሙያየ ወድጄና ፈልጌ በመማር የገባሁበት እንጂ ተገድጄና ተመድቤበት የምሰራው አይደለም ፤ ከዚህም ሙያ ልወጣ አልችልም ” የሚል ምላሽ ሰጠኋቸዉ ሲል የተናገረዉ ጋዜጠኛ ብስራት ፤ አያይዞም ፀያፍ ስድብ እንደሰደቡትና ከወላጅ አባቱ ጋር በተያያዘ የተናገሩት አሳዛኝ ነገር እንደነበረ ጠቁሟል፡፡ አያይዞም “ከግለሰቦቹ መካከል አንዱን ልደታ ፍርድ ቤት በተለይም በሽብርተኝነት የተከሰሱትን የእነ አንዱዓለምንና እስክንድርን ጉዳይ ልዘግብ ስሄድ ሁሌም እዚያ የማላጣው ሰዉ ነበር” ብሏል፡፡
“ይህንን ሁሉ ወዲያው ሳሪስ ለሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ሄጄ ያሳወቅሁ ሲሆን ፤ ያኔ ተረኛ መርማሪ ፖሊስ የነበረው ኮንስታብል ጥላሁን ታዴ የተባለ ሰዉ ያንተ ጉዳይ ከበድ ስለሚል የጣቢያው ዋና ኢንስፔክተር አበበ አያሌው ሲመጣ ጠዋት ንገረው አለኝ፡፡ በሰዓቱ የሚተባበረኝ ፖሊስ ቢኖር ግን የገቡበትን አቅጣጫ ስላየሁ አጋቾቹን እናገኛቸው ነበር ፤ ግን በሰዓቱ ለሚቀጥለዉ ቀን ከመቅጠር በቀር የተባበረኝ አልነበረም፡፡” በማለት ጋዜጠኛ ብስራት ተናግሯል፡፡ አያይዞም “በነጋታው ማክሰኞ ጠዋት ነሐሴ 21 ቀን ዋና ኢንስፔክተር አበበን ለማናገር ወደ ጣቢያው ብሄድም አሁን የሉም ፣ ለስብሰባ ወጥተዋል ተብዬ ከሰዓት እንድመለስ ተነገረኝ፡፡ ከሰዓትም ስሄድ ተመሳሳይ መልስ ከተሰጠኝ በኋላ ለረቡዕ ነሐሴ 22 ቀን ጣዋት እንድሄድ ተነገረኝ፡፡” ሲል የገጠመዉን ዉጣ ዉረድ አስረድቷል፡፡
እንደሚታወቀዉ ሰሞኑን እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት በጋዜጠኞች ላይ መጠነ ሰፊ ዛቻና ማስፈራሪያ እየፈፀመ ይገኛል፡፡
No comments:
Post a Comment