FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Wednesday, September 4, 2013

የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ተከሰሱ!!

(ሠዓሊ አምሳሉ ገብረኪዳን አርጋው)




ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን
አዲስ አበባ
አመልካች፡-  ሠዓሊ አምሳሉ ገብረኪዳን አርጋው
ጉዳዩ፡- በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ (በአየር ሞገድ በሚሰራጩ የብዙኃን መገናኛዎች) በፖለቲካዊና በሕገወጥ መመሪያዎች የመደመጥ ወይም የመስተናገድ ዕድል ስለመነፈግ
mediaበአየር ሞገድ የሚደመጡ የብዙኃን መገናኛ ወይም በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ የሚለቀቁ ዘፈኖች በአንድ ነጠላ ርእሰ ጉዳይ ላይ ማለትም በጾታዊ ፍቅር ላይ ብቻ ማተኮር እና ከያኔያኑም ቀድሞ ከነበረን የኪነት አትኩሮት በተቃራኒው ሀገርን ወደፊት ሊያራምዱ የሚችሉ፣ ትውልድን የሚቀርጹ ማለትም ሥነ-ምግባሩን ሥነ-ልቦናውንና ሰብእናውን የሚያንጹ ስንት ቁምነገሮች እያሉ ይህንን ርእሰ ጉዳይ ብቻ ያውም አንጋዶ ማለትም ከግብረ-ገባዊ አመለካከት አንጻር ትክክል ባልሆነ አቅጣጫ ሙጥኝ ብሎ መቅረት አገራችን ድሀ እና ልማት የጠማት ሀገር ከመሆኗ አንጻር ከኪነት ልታገኘው የሚገባትን ጥቅም ማግኘት አለመቻሏ እንደዜጋ ቢያስከፋኝ እና ቢያሳስበኝ ችሎታዬ በፈቀደልኝ መጠን ሰብአዊ ልማት ላይ ያተኮረ፣አሳሳቢና ትኩረት በሚሻ ርእሰ ጉዳይ ላይ ማለትም አንዳንድ ሴቶቻችን ምን አንዳንድ? አሁንማ ስፍር ቁጥር አላቸው እንዴ! ብቻ እነዚህ ሴቶች በፋሽን ሽፋን ክቡሩን ገላቸውን አራቁተው የሴትን ልጅ ክብርና ማንነት በሚያዋርድና በሚያረክስ ሁኔታ ወይም ከእርቃን ያልተናነሰ አለባበስ መጠቀማቸው የሚያስከትለውን አደጋ የሚገልጽ፣ የሞራል (የግብረ-ገብ)፣ የሎጂክ (የአመክንዮ)፣ የአይደንቲቲ (የማንነት) ጥያቄዎችን በማንሣት ከሀገርና ከሕዝብ ወይም ከትውልድ ጥቅም አንጻር ለማየት የሚሞክር፣ ትርፍና ኪሳራን የሚያሳይ፣ ኃላፊነት እንዲሰማን የሚመክር ባጠቃላይ ትውልድ ቀረጻ ላይ ያተኮረ እንደዘፈኖቻችን አዝማች የማይደጋግም አዝማች በመደጋገም ፋንታ ሊባሉ የሚገባቸውን ቁም ነገሮች የሚል ይህንን ሁሉ አድርጎ ከአብዛኞቹ ዘፈኖቻችን ባነሰ የደቂቃ ቆይታ ማለትም በአምስት ደቂቃ ከአርባ አምስት ሰከንድ የሚያልቅ ዘፈን ደርሼ ወይም አዘጋጅቼ ይሄንን ሰብአዊ ልማት ላይ ካተኮሩ ሥራዎቼ ቁ.1 ብዬ በመሠየም  ጥር 2004ዓ.ም አዲስ አበባ ለሚገኙ ለየነጋሪተወጉ እና ለየመዝናኛ ዝግጅት አዘጋጆች ከሁለቱ በስተቀር ለሁሉም አድዬ ነበር፡፡ ቁጥር 2ቱን ደግሞ አሁን ወጣቱን የሀገር ተስፋ የሆነውን ሀገር ተረካቢ ትውልድ ብላሽ ወይም ከንቱ እያደረገው ባለውና የሀገርን ተስፋ የማምከን ከባድ ሥጋት ላይ በጣለው በሱስ ላይ ያተኮረ በማድረግ ሱሰኝነትንና የሚያስከትለውን አደጋ ወይም ውድቀትና የሰብእና ዝቅጠትን የሚያሳይ፣ እንደዚህኛው ሁሉ ጠንካራ የሎጂክ (የአመክኒዮ)፣ የሞራል (የግብረ-ገብ) ጥያቄዎችን እያነሣ ከዜግነት ግዴታ፣ ከሀገር እና ከሕዝብ ጥቅም አንጻር የሚፈትሽ፣ ማንነታችንን መለስ ብለን እንድናስብና እንድንጠብቅ የሚያደርግ ዘፈን ከዚህኛው በመቀጠል ለሕዝብ ጆሮ ለማብቃት አዘጋጅቼ ነበር፡፡ በሰብአዊ ልማት ላይ ወይም በትውልድ ቀረፃ ላይ ያተኮርኩበት ምክንያት 1ኛ/ ሰብአዊ ልማትን ወይም ትውልድ ቀረጻን ያላስቀደመ ልማት ስለ ልማት በቂ ግንዛቤ ያለማግኘት ችግር ያለበት እና በአረም የመመለስ ዋጋን የሚያስከፍል በድቡሽት ወይም በአሸዋ ላይ ቤትን እንደመሥራት ነውና ከዚህም የተነሣ የልማት እንቅስቃሴ ግቡን እንዳይመታ ይደርጋልና ነገራችን ሁሉ የእናቧይ ካብ የእቧይ ካብ እንዳይሆን በመሥጋቴ 2ኛ/ ደግሞ ከላይ እንደገለጽኩት ከአንድ ነጠላ ርዕሰ ጉዳይ ውጪም ሊተኮርባቸው የሚገቡ ብዙ ርእሰ ጉዳዮች እንዳሉ በማንሣት ለማሣየት ሁለተኛው ምክንያቴ ነው፡፡
ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ የብዙኃን መገናኛዎች ይህን የሰጠኋቸውን ዘፈን  አንዳቸውም እንኳን አየር ላይ ሊያውሉት ወይም ሊያጫውቱት ሳይችሉ ወይም ሳይፈቅዱ ቀርተዋል፡፡ አንድ ሁለት የመዝናኛ ዝግጅት አዘጋጆች ዘፈኑን ሊለቁት ሲሞክሩም በሬዲዮ ፕሮግራሞች ወይም ዝግጅቶች ተቆጣጣሪዎች ተከለከሉ፡፡ የሬዲዮ ጣቢያዎችና የመዝናኛ ዝግጅቶች አዘጋጆች ዘፈኑን አየር ላይ ለመልቀቅ ያልፈለጉባቸው ወይም ያልቻሉባቸው ምክንያቶች ሦስት ናቸው፡፡
  1. የሴቶችን ነገር በትችት መልክ ስለሚያነሣ ዘፈኑን ለማስደመጥ የብሮድካስት ባለሥልጣን ሕግ ይከለክለናል የሚል ሲሆን
  2. በተለይ በመዝናኛ ዝግጅቶች አዘጋጆች የሚሉት የእኛ አድማጮች ብዙዎቹ ሴቶችና ሕፃናት ናቸውና ይህንን ዘፈን ብናስደምጥ አድማጭ ያርቅብናል ወይም ያስከፋብናል ከገበያ ውጭ ያደርገናል ሲሉ
  3. የሴቶች ጉዳይ ክስ ያቀርብብናል የሚሉ ናቸው፡፡
የገረመኝና ያሳዘነኝ ነገር የተከበረ የባሕል፣ የወግ፣ የሞራል(የግብረ-ገብ) ድንጋጌዎቻችንን በመናድ ትውልድን የሚያስቱና ወደ አልሆነ አቅጣጫ የሚነዱ እንስሳዊ የወሲብ ባሕልን ማለትም ከአንድ በላይ የፍቅር ግንኙነትን የሚሰብኩና የሚያበረታቱ ፣ትዳር መመሥረትን ግቡ ያላደረገ ግንኙነት ፈጥሮ ወሲብ መፈጸምን ብቻ መጨረሻ ግባቸው የሆነና ይሄንንም የሚሰብኩ፣የጠንካራ ማኅበረሰብ መሠረት የሆነውን ተቋም ክቡሩን ትዳርና ሊጠበቅለት የሚገባውን አካላዊና መንፈሳዊ ንጽሕና ጨርሶ እንዲዘነጋ እንዲጠፋም የሚያደርጉ ባጠቃላይ የጥፋት መልእክቶችን ያዘሉ ለሀገርም ሆነ ለትውልድ ፋይዳ የሌላቸውን ዘፈኖችን ሲለቁ ወይም ሲያጫውቱ ምንም የማይመስላቸውና ተጠያቂነት የማይሰማቸው ሰዎች አልሚ ፣አንቂ፣ መካሪና ገሳጭ ትውልድን የሚያንጽ ዘፈንን ለመልቀቅ ወይም ለማስደመጥ ግን ትንሽም እንኳ ተነሣሽነት ያጡና ጨርሶ ፍላጎት የሌላቸው ሆነው ማየቴ ነው፡፡
እንደሚመስለኝ በእነዚህ ሰዎች ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ አለ፡፡ የብሮድካስት(የስርጭት) ባለሥልጣን ያወጣውን ሕግ በቅጡ እንዳልተረዱት ይሰማኛል፡፡ በበኩሌ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ጠቃሚ እሴቶቻችን እንዲጠበቁ እንዲከበሩ የሚያሳስቡና የተሳሳቱትንም ግብረገባዊ በሆነ መንገድ የሚመክሩ፣ የሚገስጹና የሚያስተምሩ ዘፈኖችን እንዳይደመጡ ብሎ ይከለክላል ብዬ ለማመን እቸገራለሁ፡፡ የእኔ ዘፈን ደግሞ ከዚህ ውጪ ያደረገው ምንም ነገር እንደሌለ ከማመልከቻዬ ጋር አያይዤ ያቀረብኩትን የዘፈኑን ሲዲና የግጥሙንም ወረቀት በማድመጥና በማንበብ መረዳት ይቻላል፡፡ እኔ ይህንን ዘፈን ያዜምኩት ለመደመጥና የግፍ ገንዘብ ለማግበስበስ ዳሌሽ፣ ባትሸ፣ተረከዝሽ ወዘተ… ብዬ ተቅለስልሼ መዝፈን አቅቶኝ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ይሄ ለሀገር እና ለሕዝብ ወይም ለትውልድ ምን ይጠቅማል? ምንስ ይፈይዳል? ማንንስ ያንጻል? ያልገባኝ ነገረ ቢኖር እነዚህ ሰዎች ከሀገር እና ከትውልድ ጥቅም ይልቅ ጥቂት የነበሩ ነገር ግን እያደር እጅግ እየበረከቱ የመጡ በመንስኤነትም የሚያስከትሉት ጥፋት ሊነገር ከሚችለው በላይ የሆኑ የአፈንጋጭ እኅቶች ጥቅም እንዴት ሊበልጥባቸው እንደቻለና እንደሚያንገበግባቸውም ነው፡፡
በዘፈኑ ላይ ለመግለጽ አንደሞከርኩት ብዙ እኅቶቻችን ፋሽን ነው እያሉ ከእርቃን ያልተናነሰ አለባበስና ከባሕላችንና ከወጋችን ከሃይማኖታችንም ጋር የሚጋጭ ወይም ውጭ የሆኑ የአልባሳት ዘመነኝነት(ፋሽን) ፉክክር ውስጥ መውደቃቸውና በአደባባይ መታየታቸው በየትምህርት ተቋማቱ ማለትም ከመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ካሉ ሕፃናት እኅቶች ጀምሮ እስከ ዩንቨርሲቲ ያሉ ሴቶች እኅቶቻችንን ሕልማቸውን ለሚያጨናግፉ ለምን ለምን ዓይነቶች ውስብስብ ችግሮች እንደዳረጋቸው፣ በአስገድዶ መድፈር ወንጀልና ለወሲብ ብዝበዛ ወንጀሎች የሚያበረክተው ቀጥተኛ የሆነ አሉታዊ አስተዋጽኦ፣ ለኤች አይቪ ሥርጭት መስፋፋት የሚፈጥረው አሉታዊ አስተዋጽኦ ድምር ውጤቱም ሀገርን ለሞት ሊዳርግ የሚችል መሆኑ በግልጽ እያየነውና እየሰማነው ያለነው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ ምን ያህል አሳሳቢና አንገብጋቢ እንደሆነ ላንረዳ እና ላንገነዘብ የምንችልበት ጤነኛ ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡
እስከማውቀው ድረስ በዘፈኑ ላይ ለተጠቀሰችው ገጸባሕሪ /ካራክተር/ ዓይነት ሴት ጥበቃ የሚያደርግ ወይም ከለላ የሚሰጥ ሕግ ወይም አዋጅ ማለትም ሴቶች እንደፈለጉ ሆነው ይውጡ የፈለጉትን ዓይነት አለባበስ ይጠቀሙ የሚል ወይም የሚፈቅድ ሕግ ወይም አዋጅ የለም፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ዓይነት በሆነበት ሁኔታ ማንም መብቴ ነው መብቴ ተነካ ብሎ ያልተሰጠውን ወይም ያልተደነገገለትን መብት ሊጠይቅ የሚችልበት እኔን እና የእኔን ቢጤ ወይም የእኔና የእኔን የመሰለ ዘፈንን ያስደመጠን ነጋሪተ-ወግ ሊከስ የሚችልበት አካሄድ ሊኖር አይችልም፡፡ በአንጻሩ ግን እኔ እንዲህ ዓይነት ዘፈን በመሥራቴ ሕግ ይደግፈኛል ያበረታታኛል፡፡ ሕግ ስል የተጻፈ ሕግ ብቻ ማለቴ አይደለም፡፡ ያልተጻፉ ነገር ግን ገዢ የሆኑ የባሕል፣ የወግ፣ የሞራል (የግብረገብና) የሃይማኖታዊ ሕግጋቶችም ጭምር እንጂ፡፡
እስከሚገባኝ ድረስ የሴቶች ጉዳይ መ/ቤት የሀገራችንን ሴቶች ኢኮኖሚያዊ ወይም ጥሪታዊ ሰብአዊና ግብረገባዊ መብቶቻቸውን ለማስጠበቅና ለማስከበር የሚሠራ መ/ቤት እንጂ በተቃራኒው ሴቶች የሞራል (የግብረ-ገባዊ) ጥያቄን ረግጠው ራሳቸውን እንዲያረክሱ ማንነታቸውን እንዲያዋርዱ ክቡሩንና ጽዱውን ባሕልና ወጋቸውን እንዲያጎድፉ፣ ቅዱስ ሃይማኖታቸውን እንዲያስተሀቅሩ በውጤቱም ሀገር በድህነቷ ላይ ዘርፈ ብዙ ውጥንቅጥ ችግሮች ላይ እንድትዘፈቅ ለማድረግ፣ የክብረነክ እሴቱ መውደቅ የማይሰማው፣ የጽዱ ባሕሉና ወጉ መጉደፍ የማይገደው፣ የቅዱስ ሃይማኖቱ መስተሀቀር የማይደንቀው በአጠቃላይ ለማንነቱ ደንታ የሌለው ትውልድ ለመፍጠር ወይም ለማፍራት የሚሠራና የተቋቋመ መሥሪያ ቤት አይመስለኝም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ ዓላማቸው ከላይ እንደገለጽኩት ከሆነ እኔ እንዲያውም እነሱ ለዚህ ሥራዬ ያልተቆጠበ ድጋፋቸውን ሊሰጡኝ እንደሚችሉ ነው የሚሰማኝና የምገምተው፡፡ ዓላማችን አንድነውና የሚሠሩት ሴቶቻችንን ከተለያዩ አሰናካይ ችግሮች፣የቆዩም ሆኑ አዳዲስ ዘመን የሚፈጥራቸውን ኋላ ቀርና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በመታደግ ብቁ ዜጋ ለማድረግ እስከ ሆነ ጊዜ ድረስ፡፡
እንደሰማሁት ከሆነ በእነዚህ ዓይነት ሰበቦች ማለትም በሴቶች ጉዳይና በብሮድካስት በባለሥልጣን እየተሳበበ ለሕዝብ ጆሮ ሳይበቁ የቀሩ ወይም እንዳይደመጡ የተደረጉ ግብረገባዊ ዘፈኖች የትየሌሌ ናቸው፡፡ ሁኔታው መቼም እጅግ የሚገርምና ድርጅቶቹንም የሚያስገምት፣የሚያሳማ፣ሌላ ዓላማ ያላቸው የሚያስመስል፣ የመብትና የግዴታን የጥፋትና የልማትን ልዩነቶች መረዳት የተቸገሩ የሚያስመስል ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ብንጠቅስ የአንድ አዝማሪ ዘፈን “መቀነቱ መልካም የተሰጠሽ ላንቺ፤ለጠየቀሽ ሁሉ ዝም ብለሽ አትፍቺ፡፡” የሚል ስንኝ የነበረውን ዘፈን አይሆንም ተብሎ ይህ ከላይ የተጠቀሰው ስንኝ ተቆርጦ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ የኤልያስ ተባበልን ተይ ተመለሽ በሏት የሚለው ዘፈንም እንዲሁ እንዳይተላለፍ ተደርጓል፡፡ ብዙ ዘፈኖች የአየር ሽፋን እንዳያገኙ ካገኙም ስንኞቻቸው ተቆርጠው እንዲቀርቡ የሚያደርጉበት አንድ ሌላም አደገኛ ምክንየያት አለ ለሳሌም በሕዝብ ዘንድ እጅግ ለመወደድ የበቃው የብርሃኑ ተዘራና የማዲንጎ አፈወርቁ “ሰላም ያገር ሰው ወይም አንበሳው አገሳ” የተሰኘው ዘፈን “ይሄን ሰው አማራ ‰ረ የሚለው ማን ነው” እያለ የሚወርደው አዛማች “ቢለያም ቋንቋው ደማችን አንድ ነው” እስከሚለው ድረስ ተቆርጦ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ ነው ዘፈኑ በቴሌቪዥን(በምርዓየ-ኩነት) እና በሬዲዮ(በነጋሪተ-ወግ) መታየቱና መደመጡ አንዲቀጥል የተደረገው፡፡ የብዙኃን መገናኛዎቹ ይሄንን ያደረጉበት ምክንያት ገዥው ፓርቲ(ቡድን) ከሚያራምደው ፖለቲካዊ(እምነተ-አስተዳደራዊ) አቋም ጋር የማይስማማ የሚቃረን ስንኝ ስለሆነ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ገዥው ፓርቲ ይሄንን ሊያደርግ የሚችለው ምንም እንኳን ሕጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ ማቋቋም አይችሉም ብሎ የከለከለ ቢሆንምና ገዥው ፓርቲ ግን ራሱ የደነገገውን ሕግ በመጣስ የራሱ ልሳናት የሆኑ የብዙኃን መገናኛዎች ያሉት በመሆኑ እነኝህን ዘፈኖች ከያዝኩት ፖለቲካዊ አቋም ጋር አይጣጣሙም ወይም ተቃርኖ አላቸው ብሎ ሽፋን መከልከል የሚችለው በራሱ በግሉ የብዙኃን መገናኛዎቹ እንጅ በመንግሥት ወይም በሕዝብ የብዙኃን መገናኛዎች ላይ ይሄንን ማድረግ የሚችልበት ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አልነበረም፡፡ ድርጊቱ ሕገ ወጥና ወንጀልም ነው፡፡ ምክንያቱም የመንግሥት (የሕዝብ) የብዙኃን መገናኛዎች ያለአንዳች አድልዎ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚነሡ ሁሉንም አስተሳሰቦች ፖለቲካዊም(እምነተ-አስተዳደራዊም) ቢሆኑ እንዲያስተናግዱ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ተጥሎባቸዋልና፡፡
በሌላም በኩል ከገዥው ፓርቲ የተለየ አቋምና አስተሳሰብ የሚያንጸባርቁ ፓርቲዎችም ሆኑ የኪነት ሥራዎች ያሏቸው ከያኔያን (አርቲስቶች) በሕዝብ(በመንግሥት) የብዙኃን መገናኛዎች ሐሳባቸውን ያለ አንዳች ሳንሱር(ቅድመ-ምርመራ) በፃነት ለሕዝብ የማስደመጥ፣የማንጸባረቅ፣የማንሸራሸር፣የመስተናገድ ሕገመንግሥታዊ መብት አላቸው፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ እየሆነ ያለው ግን ፈጽሞ ከዚህ ተቃራኒው ነው፡፡ እንዲያው ለምሳሌ አንዲት ጠቀስኩ እንጅ ፈጽሞ ተቀባይነት በሌላቸው ሕገ ወጥ ተግባራት መብታቸውን አተው ሽፋን የተነፈጋቸው የኪነት ሥራዎች የትየለሌ ናቸው፡፡ ታዲያ ይሄ ተግባር ራሱ ላወጣው ሕግ የሚገዛ “መንግሥት” ከሌለ ምን ማድረግ ይቻላል? ተብሎ ብቻ የሚተው በደል ነውን? በወረቀት ላይ ጥሩና ጠቃሚ መብቶችን አስፍሮ በተግባር ግን ፈጽሞ ተቃራኒው ተግባር እንዲደረግ ማድረግ ከከባድ የማጭበርበር ወንጀል የከፋ ወንጀል አይደለምን?
ይሄ “መንግሥት” ከፍተኛ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሚጠይቀውን የመንግሥትነትን ያህል ቦታ ይዞ ራሱ ላወጣው ሕግ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ለእንድ ቀንም እንኳ ተሥተዳድሮበት አለማወቁ እጅግ አሳፋሪና የመጨረሻው የዘቀጠ ሰብእና መገለጫ፣ ቆሻሻና ወራዳ ታሪክም ነው፡፡ ይሄንን ተግባር እንደ ብልጠትና ብልህነት የሚቆጥርና የሚያደንቅ ሰውም ሌላ ምንም ዓይነት የሕክምና ማረጋገጫ ሳያስፈልገው ጤነኛ አለመሆኑን ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ የተማርኩ ነኝ የሚል ከሆነም እንደገና ይመለስ እና ሀ ብሎ ፊደል ይቁጠር።  ከባዱና አስቸጋሪው  ሆኖ ለመገኘትም ፈታኙ ነገር ቀናነቱ እንጅ ክፉነቱ አይደለም፣ትክክለኝነቱ እንጅ ስሑትነቱ አይደለም፣ ገንቢነቱ እንጅ አፍራሽነቱ አይደለም፣ማኅበራዊነቱ እንጅ ግለኝነቱ አይደለም፣ እውነተኛነቱ እንጅ ሐሰተኛነቱ አይደለም፣ንጹሕነቱ እንጅ ቆሻሻነቱ አይደለም፣ ዐዋቂነቱ እንጅ ድንቁርናው አይደለም፣ ቅድስናው እንጅ እርኩሰቱ አይደለም ወዘተ. ፡፡
ወደቀደመው ሐሳብ ልመለስና በእነዚህ የብዙኃን መገ“—­ች ትውልድን ወደ አልሆነ አቅጣጫ የሚነዱ አንዳች ቁምነገርና ፋይዳ የሌላቸው ዘፈኖች እንደፈለጉ በነጻነት የሚታዩና የሚሰሙ የሚደመጡ ከሆነ ሲሆን ሲሆን ኃላፊነት የሚሰማን ከሆነ እንደዚህ ዓይነት ዘፈኖች እንዳይደመጡ መደረግ ነበረባቸው፡፡አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት መደመጥ አለባቸው ከተባለ ግን  ይልቁንም መካሪና ገሳጭ አስተማሪ የሆኑቱ ሌላው እንኳ ቢቀር በተመሳሳይ መልኩ እኩል ዕድል እንዴት ሊሰጣቸው አይገባም? አድማጭና ተመልካችም የሚበጀውንና የሚመርጠውን እንዲሰማና እንዲመለከት እንዴት መብት ወይም ዕድል አይሰጠውም? ይህ ካልሆነ ደግሞ አፈንጋጮቹ ዘፈኖች እንዳይተላለፉ የማይደረገው ለምንድንነው? ምዕራቡ ዓለም አንጻራዊ በሆነ መልኩ የሰው ልጆች መብት በየዓይነቱ የተከበረበትና የሚጠበቅበት የዓለም ክፍል እንደሆነ ይነገራል፡፡ በሚዲያቸውም (የብዙኃን መገናኛዎቻቸውም) አንድ ዘፋኝ ስለ አንዲት ገጸባሕሪ ዘልፎና አንቋሾ ቢዘፍን ጉዳዩ የዚያች ገጸባሕሪ ሆኖ ይቀራል እንጂ ነገሩ ተጠምዝዞ በአጠቃላይ የሴቶች ጉዳይ ተደርጎ አይታሰብም፡፡ እኛ ታዲያ ከእነሱ የበለጠ መብት ጠባቂና አስጠባቂዎች ሆነን ነው? ወይስ የመብት ምንነቱ አልገባን ሆኖ? ፡፡ የግለሰብ መብት ማለት ምን ማለት ነውን?  የግለሰብ መብት ሊጠበቅና ሊከበር የሚገባው ወይም ያለበት እስከምን ድረስ ነው? አንዲት አፈንጋጭ ሴት መብቴ ነው የሚለውን ቃል ስለተናገረች ብቻ መብቷ ይሆናል ወይ? በበኩሌ የግለሰብ መብት መብት ሆኖ ሊከበር የሚገባው የቡድን ጥቅማችንን እስካልተጋፋ ፣ እስካልጣሰ ወይም እስካልተገዳደረ ጊዜ ድረስ ብቻና ብቻ ነው፡፡ ይህ የዲሞክራሲ (የበይነ-ሕዝብ) ሥርዓት አንኳር አስተሳሰብ ነው፡፡ እኛ የሰው ልጆች ተፋቅረንና ተሳስበን በአንድነት ለመኖር የቻልነው ሳንነጋገር የተስማማንባቸው በባሕልና በወግ ሥርዓቶች ጥበቃ የሚደረግላቸው የጋራ ጥቅሞች ስላሉን ነው፡፡ እነኚህ የጋራ ጥቅሞች ባይኖሩ ኖሮ የሰው ልጆች በአንድነት በኅብረት ወይም በጋርዮሽ የመኖር ዕድል ባላገኘን በተበተንን እንደ አራዊትም በሆንን ነበር፡፡ የጋራ ጥቅም ሥርዓት ለአንድ ማኅበረሰብ የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ የጋራ ጥቅም ድንበር በአንዳንድ አፈንጋጮችና እንደሰው ስሜትን መጠበቅና መቆጣጠር በማይፈልጉ ወይም ባቃታቸው ሰዎች እንዲደፈርና እንዲጣስ ጨርሶ ልንፈቅድ አይገባም፡፡ የግል ጥቅም ወይም መብት ያለ የጋራ ጥቅም ወይም መብት ፋይዳ የለውም ብቻውንም  መቆም አይችልም፡፡ የጋራ ጥቅም ወይም መብትም ለ የግል ጥቅም ወይም መብት ካልተመቸ እርባና የለውም ብቻውንም መቆም አይችልም፡፡ ይህ እንዲሆን የፈቀድን ለታ ግን በአንድ ጀምበር ባይሆንም ረጅም በማይባል ጊዜ ግን እንናዳለን እንፈርሳለን እንበተናለን ሰብአዊነታችን ተቀይሮ የግብረገብና ሥነምግባር አጥር አልባ የሆነ ሌላ መጥፎ ቆሻሻ መገለጫ ወይም ማንነት ይኖረናል፡፡
ለሞራል ወይም ለክብረነክ ድንጋጌዎች ደንታ የሌላቸውና የብዙኃን መገናኛ ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅም አንጻር የሚጠይቀውን ብስለት ብቃትና አስተዋይነት ያልያዙ የሌላቸው ግለሰቦች የብዙኃን መገናኛውን መቆጣጠራቸው ጠንካራ አቋም ያላቸው በሚመስሉት በምዕራቡ ዓለም አንኳ ጠንካራ አቋም ያላቸውን መንግሥታቶቻቸውንም ሳይቀር የሞራል(የግብረ-ገብ) እሴቶቻቸውን እና ጠቃሚ ባሕላቸውን የሚያስጠብቁበትንና የሚንከባከቡበትን፣ ዘመን የወለዳቸውን መጥፎ ልማዶችን  ለመከላከል የሚችሉበትን አቅም ጨርሶ እንዳሳጧቸውና እንዳቃቷቸው ከባድ የራስ ምታት ፈተና እንደሆኑባቸውና እየተሸነፉ ከቀን ወደቀንም ከብዙ አቅጣጫ ብዙ ነገሮች እየተበላሹባቸው እንደ ሆነ ሁሉ የዚህ መጥፎ ተሞክሮ በሀገራችን እየታየ በመሆኑ ካለብን የአቅም ውስንነት ከሌሎቹም የተነሣ ይሄን አደጋ መቋቋም ጨርሶ አንችልምና  ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ከወዲሁ ነገሩ ከእጅ ሳይወጣና ሳያመልጥ አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ  ሊወሰድ እንደሚገባ አበክሬ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ጦር አውጆ ከሚመጣ ጠላት ይልቅ ይህ ችግር የከፋ ብሔራዊ አደጋ የመጋረጥ አቅም አለው እንደ መንግሥት ይሄንን መረዳት የግድ ይላል ይህ ካልሆነ ግን ጉዳዩ ሌላን ነገር ይጠቁማል፡፡ እኔ የግድ ስም እየጠራሁ የእነ እከሌ የእነ እከሌ ዝግጅቶች እያልኩ ይህንን ከላይ የጠቀስኩትን አደጋ በሀገር ላይ የጋረጡትን በመዘርዘር መግለጥ ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ የዚህ ባለሥልጣን መሥሪያቤት ሥራው እና ኃላፊነቱ (ማንዴቱ) ይሄው ነውና፡፡ ዞር ብሎ በብዙኃን መገናኛዎች ያለውን ሁኔታ ቢመለከት በቀላሉ ሊያገኘውና ሊረዳው የሚችለው ጉዳይ በመሆኑ፡፡
በዘፈኔ ላይ የተገለጸችው ገጸባሕሪ እንዴት ባለ መልኩ የቡድን ጥቅሞቻችንን አደጋ ላይ እንደጣለች ዘፈኑ ላይ ግልጽ ጥርት ባለ መልኩ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም የዚች ገጸባሕሪ ዓይነት ሰብእና ያላቸው ሴቶች እንደዚህ አይነቱን አለባበስ መጠቀም በጭራሽ መብታቸው ሊሆን አይችልም፡፡ መብቷ ነው ተብሎ የተደነገገበት የሕግ መጽሐፍም እስካሁን ድረስ የለም፡፡ ሊኖርም አይችልም፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ያልተጻፈና የሌለ ሕግ እየተጠቀሰ ገንቢ የሥነ-ኪንን ሥራዎችን መጣል ማፈንና ከያኔያኑንም ማሸማቀቅ ኢ-ሞራላዊና ኢ-ግብረገባዊ ሕገወጥም እንደሆነ በቦታው ላሉ ማለትም የብዙኃን መገናኛዎችን በኃላፊነት ተቆጣጥረው ላሉ የተዛባ እና የተንጋደደ አስተሳሰብ ላላቸው ግለሰቦች ሊነገራቸው ይገባል፡፡ ምንአልባት ምንም ያህል የሕግ እውቀት ላይኖራቸው ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ባይኖራቸውም እንኳ በተፈጥሯዊ ዕውቀት (in common sense) በቀላሉ ሀገርን የሚጠቅመው ትውልድን የሚያንጸው የቱ ነው?  የሚለውን አግባብ የሆነውንና መቼም ጊዜ ቢሆን ሊረሳ የማይገባውን አንገብጋቢ ጥያቄ ለራሳቸው ቢያነሡ ከእንደዚህ ዓይነት የተሳሳተና አደገኛ አካሄድ የመጠበቅ ዕድል ሊያገኙ በቻሉ ነበር፡፡
በመሆኑም የብሮድ ካስት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የብዙኃን መገናኛዎቹ የያዙትን አደገኛ አቅጣጫ ማለትም አድማጭ ያስከፋብናል በሚል ግብረ ገባዊ ዘፈኖችን የማይቀበሉና ዕድል የሚነፍጉ ከሆኑና አድማጭ ለማስደሰት ብለው ደግሞ የዚህን ተቃራኒ መልዕክት ያላቸውን ዘፈኖች የሚያስደምጡ ከሆነ ሕዝቡን ወዴት እየነዱት እየወሰዱት እንደሆነ በግልጽ እየታየ በመሆኑ ሳይዘገይ የአቅጣጫ ማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ጥቆማዬን አቀርባለሁ፡፡ የብሮድካስት(ስርጭት) ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በየብዙኃን መገናኛው ያለው መደናገርና ግራ መጋባት አለማወቅም ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ ተረድቶ ቅድሚያ ትኩረት (Primary Concern) በመስጠት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው ለማስገንዘብ በሚል እንደወረደ ስሜታዊነት በተንፀባረቀበት መልኩ ማመልከቻውን ጽፌዋለሁ፡፡ ለድፍረቴ ታላቅ ይቅርታ ሳልጠይቅ አላልፍም፡፡ ለችግሩም መፍትሔ እንደሚሰጠው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር
ሠዓሊ አምሣሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ይሄንን የአቤቱታ ማመልከቻ ጻፍኩና ሄድኩ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ወደ ተባሉት የመሥሪያ ቤቱ ባለሙያዎችም ገብቸ የክስ ማመልከቻውን ስሰጥ ጉዳዩ ምን እንደሆነ እንድነግራቸው ጠየቁኝ  ጉዳዩንም ከገጠመኝ ችግር ጋር አስረዳሁ፡፡ ባለሞያዎቹ ግን አይ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሚመለከተው ወይም የመመልከት ሥልጣኑ ያለው በብዙኃን መገናኛዎቹ ሽፋን ወይም ሥርጭት ባገኙ ጉዳዮች ላይ ለሚቀርቡ ቅሬታዎች ነው፡፡ ባልተሠራጩ ወይም ሽፋን ባላገኘ ጉዳይ ላይ ምንም ማለት አንችልም በብዙኃን መገናኛዎች ሥራ ላይ ጣልቃ እንደመግባት ይቆጠራል የሚል ምላሽ ሰጡኝና እዚያው ሳለሁ የክስ ማመልከቻየን መለሱብኝ፡፡ እኔም አይ ዘፈኔ እንዳይተላለፍ የተደረገው እኮ እናንተ አወጣቹሁት በተባለው ሕግ ምክንያት ነው፡፡ ምንም እንኳ ዘፈኑ ለሥርጭት ባይበቃም በእናንተ ሕግ ምክንያት ነውና ለሥርጭት እንዳይበቃ የተደረገው ጉዳዩን ልታዩት ይገባል የሚል መከራከሪያ አቀረብኩ፡፡ ባለሞያዎቹ ግን የተለየ ምላሽ አልነበራቸውም የብዙኃን መገናኛዎችን ይሄንን ዘፈን አስደምጡ ብለን ማዘዝ አንችልም፡፡ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በጉዳይህ ላይ ሊሄድ የሚችለው እዚህ ድረስ ነው፡፡
ከዚህ በተረፈ ግን ምናልባት በግላችን የምንሰጥህ ምክር ሊኖር ይችል እንደሆነ ዝርዝር ጉዳዩ ምን እንደሆነ እስኪ ንገረን አሉ፡፡ እኔም የዘፈኑን ግጥም በማንበብ ከብዙኃን መገናኛዎችና የመዝናኛ ዝግጅቶች አዘጋጆች የገጠመኝን ችግር በዝርዝር አጫወትኳቸው፡ ነገር ግን የእነሱም ማለትም ዙሪያዬን የከበቡኝ የሰባቱም ባለሞያዎች እምነት የተለየ አልነበረም፡፡ ከአንድ ሰዓት ተኩል ለበለጠ ጊዜ የአለባበስና መብትን በተመለከተ የከፊል እርቃን አለባበስ እስካላቸው ብሔረሰቦቻችን ድረስ በጥሩ ሁኔታ በመቃኘት እጅግ የጦፈና አስተማሪ ክርክር ካደረግን በኋላ ልዩነታችን በጣም ጠበበና ምን ወደ ማለት መጡ እሽ ይሁን ነገር ግን አፕሮችህን ማለትም ሀሳብህን ያቀረብክበትን መንገድ ቀይረው የሰው ልጅ ብዙ ጊዜ ተችተኸው ወይም ነቅፈኸው ልምከርህ ላስተምርህ ስትለው ተደማጭና ውጤታማ አትሆንም ስለዚህ ከዚህ የተለየ አካሄድ ብትጠቀም የሚል ሐሳብ አቀረቡ በምሳሌ እንዲያስደፉልኝ ጠየኳቸው፡፡ እነሱም ሐሳቡ እንዳለ ሆኖ አግባብነት ያለው አለባበስን እያደነክ ባሕላችንን እያመሰገንክ ከነቀፋና ከትችት የፀዳ ምክርህንም አስታከህ ብታቀርበው ውጤታማ ልትሆን  ትችላለህና ይሄንን መንገድ ብትጠቀም መልካም ነው፡፡ የሚል ሐሳብ አቀረቡ፡፡
እኔም ሐሳባቸው ጥሩ እንደሆነ ነገር ግን ከዚህ በፊት በዚህ አቀራረብ የተሠሩ በርካታ ዘፈኖች እንደነበሩ ነገር ግን ምንም ለውጥ ያላመጡ ከመሆኑም በተጨማሪ ጉዳዩን የምርጫ ጉዳይ እንዲሆን እንዳደረገው ማለትም ዘፈኔ እናንተ እንዳላችሁት “ይሄውልሽ እኅቴ የእኛ እኮ ባሕላችን ወርቅ ነው ምን የመሰለ ክብርን የሚጠብቅ የአለባበስ ባሕል አለን እና ይሄን አለባበስ ተጠቀሚ እባክሽ” የሚል ቢሆን አይ እኔ አይመቸኝም እሱ ለእኔ ኋላ ቀር ነው የእኔ ምርጫ ይሄኛው ነው ከማለት ውጭ አሃ ውነትህን ነው እኔ ስላላወኩ ነበር አትልም ምክንያቱም ሲጀመርም ይሄ ጠፍቷቸው አይደለምና የተራቆተ አለባበስ ወደ መጠቀም የሄዱት የሰለጠኑ መስሏቸው ፣ ለአፈንጋጭ የውስጥ ስሜታቸው እጅ በመስጠታቸው እና በተሳሳተ ግንዛቤ ነፃነታቸውን የተጠቀሙ መስሏቸው እንጂ፡፡ ይሄም በተደጋጋሚ በየብዙኃኑ መገናኛው አለባበስን በተመለከተ በተደረጉ ውይይቶች ላይ ተንጸባርቋል፡፡ በመሆኑም ነው ስለ ጉዳዩ በሁሉም የዕድሜ ክልል ያሉትን ሰዎች ስሜትና ፍላጎት በመጠየቅና ጥናት በማድረግ ለየትና ቆንጠጥ ባለ አቀራረብ የጉዳዩን ክብደት ሊያሳይና ሊያስገነዝብ በሚችል ደረጃ መልስ የሚያሳጡና የሚሹ አመክንዮአዊ ጥያቄዎችን በማስያዝ፣ ለራሷ የምትሰጠውን የሞራል(የግብረ-ገብ) ደረጃ እያደረገችው ካለችው ነገር ጋር እንድታገናዝብ የሚያደርግ፣ የግል ስሜቷን ብቻ እስካልተከተለችና ኃላፊነት የሚሰማት ብቁ ዜጋ እስከሆነች ጊዜ ድረስም እንከን የሌለበት የአለባበስና የአስተሳሰብ ባሕላችንን መጠቀም አማራጭ የሌለው መፍትሔ እንደሆነ እንድትረዳ ያደርጋል ባልኩት መንገድ ትችት ያለበትና አፋጣጭ ጥያቄዎችን የሚያነሣ፣ በየ ውይይት መድረኩ የተለያዩ የመከራከሪያ ነጥቦችን እያነሡ ክርክሩን በአሸናፊነት እንደተወጡ ስለሚያስቡና ካሸነፍን ወይም ሊያሳምኑን እስካልቻሉ ጊዜ ድረስ የምናደርገው ነገር ትክክል ነው የሚል አቋም ስላለ ያልታያቸውን ያልተረዱትን ነገር በማሳየት የጉዳዩን ክብደት አበክሮ ለማስገንዘብ ጠንከር ባለ አገላለጽ እነዚያ የመከራከሪያ ነጥቦቻቸው ባላሾችና የትም የማያደርሱ መሆናቸውን የሚያስገነዝቡ አመክንዮዎችን በመጠቀም ኃላፊነት እንዲሰማንና ከሁለት አንድን መምረጥ ስንመርጥም መልካሙን እንዲሆን የሚያሳስብ አካሄድ የተጠቀምኩት፡፡
አውቃለሁ አፕሮቹ(አቀራረቡ) ፈሊጥ የጎደለው ነው ነገር ግን ያልተሞከረው ወይም ያልተሔደበትን የቀረን ብቸኛው አማራጭ ይሄው አካሄድ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ እስኪ የዚህኛውን አካሄድ ደግሞ እንሞክረው በማለት ነው የሚል ምላሼን ካቀረብኩ በኋላ ከፊሎቹ ዝምታን ሲመርጡ ከፊሎቹ ግን ከአድናቆት ጋር እስከ መጨረሻው ድረስ እንድቀጥልና እንዳላቆም በማሳሰብ ልሔድባቸው የሚገባኝን መሥሪያ ቤቶች በመንገርም ጭምር ድጋፍና ልሄድባቸው የሚገቡኝን ቦታዎች ጥቆማ  ሰተውኝ የጋለ ክርክራችን ተቋጨ፡፡ እኔም አመስግኜ ሥራ ስላስፈታኋቸውም ይቅርታ ጠይቄ ማመልከቻዬንም ይዤ ወጣሁ፡፡
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ከዚያም በመቀጠል እንደ ብሮድ ካስት ባለሥልጣን ሁሉ ማሳጫ ወደ ሆነው መሥሪያ ቤት አመራሁና የሚመለከታቸውን ሁለት የሥራ ኃላፊዎች አነጋገርኩ ከመጀመሪያው ጋር ስለ አለባበስ ሕጋችን ምን ይላል በሚለው ጉዳይ ላይ ሲሆን እርሳቸውም እንዲህ ልበሱ እንዲህ አትልበሱ የሚል ነገር የለም፡፡ ነገር ግን የሰዎችን ወሲባዊ ፍላጎት የሚቀሰቅሱ ማኅበረሰቡ ተቀብሎት ከሚኖረው ጥሩ ባሕልና ወግ ውጭ የሆኑና የሚቃረኑ ጸያፍ ድርጊቶችን በአደባባይ ማሳየት ወንጀል እንደሆነ መደንገጉን ገለጹልኝ ከዘፈኔ ዓተያይ ጋርም እያጣቀስን ጥሩ ውይይት አደረግን ኃላፊው ቀጠሉና ግን ለምን በሴቶች ላይ ብቻ አተኮርክ? ሲሉ ጠየቁኝ እውነት ነው ይሄኛው ዘፈን በሴቶች ላይ ብቻ ያተኮረ ነው እንደዚሁ ሁሉ በወንዶች ላይ ብቻ ያተኮረ ሱስን ርእሰ ጉዳዩ ያደረገ ዘፈን መጻፌንና አቅም በፈቀደልኝ ጊዜ ተቀናብሮ ለጆሮ እንደሚበቃ ስነግራቸው አሀ! ዘራፍ ብለህ ነዋ የተነሣኸው? ብለው ፈገግ አሰኙኝ፡፡
በመቀጠልም ከሌላኛው የሚመለከታቸው የመሥሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊ ጋርም እንዲሁ በቅድሚያ የጻፍኩትን ዘፈን በብዙኃን መገናኛዎች ዘንድ ያጋጠመውን ችግር ገለጽኩላቸው የዘፈኑን ስንኞችም አነበብኩላቸው እርሳቸውም መሥሪያ ቤታቸው በእንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ላይ በማንም ላይ ክስ አቅርቦ እንደማያውቅ ማንዴቱም (ኃላፊነቱም) እንዳልሆነ ገልጸው መክሰስ ቢኖርባቸው ኖሮ ግን በምርአየ ኩነት (ቴሌቪዥን) በሚታዩ ሴቶችን በእርቃን በሚያሳዩና ከሞራልና (ከግብረ-ገብ) ውጭ በሆኑትና መጥፎ ትምህርት በሚሰጡ የኪነት ሥራዎች ላይ ክስ ይመሠርቱ እንደነበር አብራሩ እኔም ከዚህ በፊት አንድ አትሌት በቃለ መጠይቁ ጊዜ አግባብ ያልሆነ ነገር ተናግሯል በሚል ክስ መሥርታቹሁበት እንደነበረ ይነገራል ስላቸው ይህንን ጉዳይ መ/ቤታቸው እንዳላደረገውና ድርጊቱም ፈጽሞ ትክክል እንዳልሆነ በጥሩ አገላለጽ ገለጹልኝ ታዲያ ማን አደረገው ስላቸው የሆኑ ቡድኖች ናቸው መጨረሻ ላይም አትሌቱን ወይም ሯጩን ይቅርታ አስጠይቀው ትተውታል ድርጊቱ ግን ትክክል ያልሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተሠራበት ያለው የአትሌቲክስን  ሕግ መሠረት ያላደረገና የሚቃረን መሆኑን በማብራራት ድርጊቱ ምን ያህል የተሳሳተ እንደነበር አብራሩ፡፡ እኔም ለነበረን ቆይታ አመስግኜ ትብብራቸው በፈለኩ ጊዜ ድጋፋቸውን እንዲሰጡኝ ጠይቄ ወጣሁ፡፡ የብዙኃን መገናኛዎቹ ግን ከዚህም በኋላ ለመታረም ባለመፍቀዳቸው ይሄንን ሁሉ ጉዳይ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ሕዝቡ ዓይቶ ይዳኘን ዘንድ ለንባብ አበቃሁት ስላንዛዛሁባችሁ ይቅርታ ያውም ብዙ ነገሮችን አስቀርቸ ለትዕግስታችሁ አመሰግናለሁ፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡

No comments:

Post a Comment