FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Wednesday, September 4, 2013

ሰላማዊ ትግል በካዮች እና መከላከያ ምክሮች!

(ግርማ ሞገስ)

semayawi-party-protest-june-02


ህውሃት (መንግስት) ህዝብን የሚገዛበት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ አቅሙ ከሰማይ የሚወርድለት ወይንም በተፈጥሮው ከውስጡ የሚንጠፈጠፍለት ሳይሆን ከህዝብ የሚነጭለት ነው። ፖሊሱም፣ ደህንነቱም፣ የኢቲቪ ሰራተኛውም፣ የቃሊቲ አስተዳዳሪውም፣ የኢምባሲ ሰራተኛውም፣ ወ.ዘ.ተ. ከህዝብ የሚመለመሉ ናቸው። ለህውሃት በደሞዝ ክፍያ ያገልግሉ እንጂ የሰዎቹም ሆኑ የደሞዛቸው ምንጭ ህዝብ ነው። በግብር እና በሌሎች ምክንያቶች ከህዝብ የሚሰበሰብ ነው ደሞዛቸው። አሊያም በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ከውጭ በዕርዳታ፣ በብድር ወይንም በሌሎች ስምምነቶች የሚያገኘው ነው ደሞዛቸው። የፋብሪካ፣ የኢንዱስትሪ፣ የመገናኛ፣ የትራንስፖርት፣ የአየር መንገድ፣ የመድህን ሰራተኞች፣ የንግድ እና አገልግሎት ድርጅቶች ወ.ዘ.ተ. በሙሉ ስራ ቢያቆሙ ከህዝብ መንጭቶ ወደ ህውሃት የሚፈሰው ሃብት ብር ይቋረጣል። ህውሃት ለፖሊስ፣ ለደህንነት እና ለመሳሰሉት ሽብርተኛ ስልጣን ጠባቂዎቹ የሚከፍለው ደሞዝ ያጥረዋል። እነሱም ደሞዝ ካልተከፈላቸው አያገለግሉትም። ስለዚህ የህውሃት የፖለቲካ አቅም ይዳከማል። ብሎም አቅሙ ከምንጩ ይደርቃል ማለት ነው። በመጨረሻ ተርቦ ይሞታል ህውሃት። እንደምናስተውለው ከሆነ ከዚህ በፊት በፈጸማቸው ይቅርታ በማናደርግለት የተለያዩ የፖሊሲ ስህተቶች ላይ ህውሃት ዛሬም በቀጣይነት በህዝብ ላይ ተከታታይ መብት ረገጣዎች እና የኢኮኖሚ ቀውሶች እየፈጠረ ነው። ሰላማዊ ዜጎችን ሽብርተኞች እያለ ሽብርተኛው እራሱ መሆኑን ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ እያደረገ ነው። ህውሃት የፖለቲካም ሆነ የሞራል ብቃት እንደሌለው የኢትዮጵያ ህዝብ እያወቀ ነው። ባቡር ሃዲዱንም፣ ህንጻዎቹንም፣ መንገዶቹንም፣ ግድቦቹንም ህዝቡ እራሱ ለራሱ በራሱ የገነባል። ህውሃት አያስፈልገውም። ተቃዋሚውም ከምንጊዜውም የተሻለ በስሏል። ቀጣይነት ያለው ሳይኮሎጂያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፈርጆች ያሉት ሰላማዊ ትግል በማድረግ ላይ ይገኛል።
የሰላማዊ ትግል ማራመጃ መሳሪያዎች (በጠብ መንጃ ምትክ) በቁጥራቸው 200 ያህል ሲሆኑ በጸባያቸው ተዛማጅ እና ውስብስብ ናቸው። ይሁን እንጂ የአልበርት አነስታይን ሰላማዊ ትግል ምርምር ተቋም ባልደረቦች እነ ጅን ሻርፕ የመሳሰሉት የዘመናዊ ሰላማዊ ትግል የፖለቲካ ሳይንስ ጠበብቶች እነዚህን 200 ሰላማዊ ትግል ማራመጃ መሳሪያዎች ማጥናት እንዲቻል ለማድረግ በሶስት አብይ ክፍሎች ከፍለዋቸዋል። እነሱም (1ኛ) ተቃውሞ እና ማግባባት (Protest and Persuasion) ፣ (2ኛ) የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ትብብር መንፈግ (non-cooperation) እና (3ኛ) ጣልቃ መግባት (intervention) ይባላሉ። እስካሁን በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ሰላማዊ ትግል በ(1ኛው) ክፍል የሚመደብ ነው። ይሁን እንጂ ህውሃት (መንግስት) በተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በገበሬው፣ በሰራተኛው፣ በተማሪው፣ በእስረኛው፣ በነፃ ጋዜጠኞች፣ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አይግባ በሚል መርኽ እንከን የለሽ ሰላማዊ ትግል በማኪያሄድ ላይ በሚገኙት ኢትዮጵያውያን ሙዝሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ላይ የሚፈጽመው ወከባ፣ ድብደባ፣ እገታ፣ ግድያ ሰላማዊ ትግሉን ወደ (2ኛው) ደረጃ እንዲሸጋገር እየገፋው ነው።
የሆነው ሆኖ ሰላማዊ ትግል ውስብስብ ነው። በረጅም ማስተዋልን፣ በረጅም ማስላትን፣ የትግል ብስለትን፣ ትዕግስትን፣ ጀግንነት፣ ፅናትን ሁሉ ይጠይቃል። ያ ብቻም አይደለም። ሰላማዊ ትግል ከጀብዱኛነት ነፃ መሆንን፣ ለግል ስም እና ዝና ከሚደረግ ሽሚያ መራቅን፣ እራስን ሳይሆን ህዝብን የመንግስት ስልጣን ባለቤት በማድረግ ላይ ማተኮርን ይጠይቃል። ያ ብቻም አይደለም። የህውሃት ሰርጎ ገቦች ሰለባ አለመሆንን፣ ከቀረው ተቃዋሚ እኔ እሻላለሁ ከሚል ደካማ ስሜት መራቅን፣ ለክፍፍል ቀዳዳ አለመስጠትን እና የመሳሰሉትን ሁሉ ይጠይቃል ሰላማዊ ትግል። ያ ብቻም አይደለም። በሌሎች አገሮች ስለተደረጉ (የተሳኩም ያልተሳኩም) ሰላማዊ ትግሎች ተመክሮዎችን በስፋት እና በጥልቀት ማወቅም ይፈልጋል። ከእነዚህ ከተዘረዘሩት ውስጥ አንዱ ወይንም ሁለቱ ቢከሰቱ ወይንም ቢጓደሉ ሰላማዊ ትግል ይበክላል።
በምርጫ ጊዜም ብክለቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። የምርጫው ውጤት አንድ አምባገነን አውርዶ በአዲስ አምባገነን መተካት ወይንም ለመፈንቅለ መንግስት ቀዳዳ መክፈት እንዳይሆን አስፈላጊውን ፕላን ቀደም ብሎ ማስላት ያስፈልጋል። አሊያ በግብጽ ያየነው ሊከሰት ይችላል በኢትዮጵያ። የግብጽ ሰላማዊ ትግል የሙባረክን አምባገነን መንግስት ካስወገደ በኋላ በተደረገው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ አራት ግለሰቦች እንደተወዳደሩ እናስታውሳለን። በቅርብ ከስልጣን የወረደው ሞርሲ (ሃይማኖትን ከፖለቲካ ጋር የሚቀላቅለው) በምርጫ ያገኘው የህዝብ ድምጽ 12 ሚሊዮን ግድም ሲሆን የቀሩት ሶስቱ (ሃይማኖትን ከፖለቲካ የማይቀላቅሉት) ግለሰቦች ያገኙት የህዝብ ድምጽ ድምር 21 ሚሊዮን ግድም ነበር። ሶስቱ አርቆ ማየት ስለተሳናቸው፣ የግብጽን ህዝብ የመንግስት ስልጣን ባለቤት ማድረግን ከማስቀደም ፈንታ እራሳቸውን (ፓርቲያቸውን) በማስቀደማቸው በህብረት መቆም ተሳናቸው። ስለዚኽ ሶስቱ ያገኙትን የህዝብ ድምጽ ለሶስት ሲካፈሉት ሞርሲ አሸነፋቸው። ዛሬ ላይ ቆመን ሁኔታውን ወደ ኋላ ስንመለከተው ግብጽ አጭሩን የዴሞክራሲ መሸጋገሪያ ድልድይ የሳተቸው ያን ጊዜ ነበር ማለት ይቻል ይሆናል። ዛሬ እንደምናየው ግብጽ እረጅሙን መንገድ በመጓዝ ላይ ነች።
በተቃራኒው ከፍ ብለን ያነበብናቸው በምርጫ ጊዜ ሊከሰቱ የሚችሉ ብክለቶችን በዘዴ ያስወገደች አገር ሰርቢያ ናት። በሰርቢያ ሰላማዊ ትግል ሲያደርጉ የነበሩት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቁጥራቸው 16 ነበሩ። እነዚኽ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምርጫ ቀደም ብለው ህብረት በመፍጠር የሞልሶቪችን አምባገነን መንግስት ህገ-መንግስት እንዲያከብር ሲታገሉት ቆይተዋል። የሆነው ሆኖ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2000 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ የሰርቢያ 16 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህብረታቸውን ጠብቀው የሞልሶቪችን አምባገነን መንግስት ተፎካክረው በቀላሉ አሸነፉ። ሞልሶቪች ግን ድምጽ ሰርቆ ምርጫውን አሸንፌያለሁ አለ። በህብረት የቆሙት 16 ፓርቲዎች “የህዝብ ድምጽ ይከበር” የሚል ሰላማዊ ትግል ጥሪ አደረጉ። ህዝቡም “ድምጻችንን ካላከበርክ እኛም መንግስትህን አናከብርም” ብለው ሰላማዊ ትግሉን ተቀላቀሉ። ከዚያ መሸነፉን ከመቀበል በስተቀር የተሻለ አማራጭ እንደሌለው ሲገነዘብ ሞልሶቪች ሽንፈቱን ተቀብሎ ሰላማዊ የመንግስት ሽግግር ተደረገ። 16 ተቃዋሚ ፓርቲዎች የህብረት መንግስት መሰረቱ። ቀደም ብለው ባደረጉት ስምምነት መሰረት የሞሊሶቪችን አምባገነን መንግስት ካስወገዱ በኋላ ለተወሰኑ አመቶች በህብረት ገዙ። በህብረት ለመግዛት የተስማሙበት ዘመን (ሁለት ወይንም ሶስት አመቶች መሰለኝ) ሲያልቅ ነፃ ምርጫ ጠሩ። ለመጀመሪያ ጊዜ በሰርቢያ ታሪክ ነፃ ምርጫ የተደረገው በዚህን ጊዜ ነበር። አብላጫ የህዝብ ድምጽ ያገኘው ፓርቲ አገር አስተዳዳሪ (ገዢ ፓርቲ) ሲሆን ዝቅተኛ የህዝብ ድምጽ ያገኙት ፓርቲዎች ተቃዋሚ ፓርቲ በመሆን የፓርላማ ትግላቸውን ጀመሩ። በዚኽ አይነት ሰርቢያዎች የአገራቸውን የዴሞክራሲ ሽግግር አጭር እና ከውጣ ውረድ የጸዳ ማድረግ ችለዋል። ስልጣን ከለቀቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሶ በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት እስር ቤት ሳለ ሞተ ሞልሶቪች።
ኢትዮጵያችን ከግብጽም ከሰርቢያም መማር አለባት። ስለዚህ በኢትዮጵያ በዘልማድ ሰላሳ ሶስቱ ተብሎ የሚጠራው ቡድን፣ መድረክ እና አንድነት ከግብጽም ከሰርቢያም ከሌላም ይማራሉ ብለን እንገምታለን። የኢትዮጵያን ህዝብ የመንግስት ስልጣን ባለቤት ማድረግ ቀዳማይ ግባቸው ነው ብለን እናምናለን። ግባቸው ይኽ ከሆነ ደግሞ በመካከላቸው የሚኖረው ልዩነት ሁሉ-በጁ ሁሉ-በደጁ ከሆነው ከህውሃት መንግስት ጋር ካላቸው ልዩነት ጋር ሲነጻጻር እጅግ የደበዘዘ መሆን አለበት። በመድረክ እና በአንድነት ወይንም በ33 መካከል ያሉትን የመርህ ልዩነቶች እናውቃቸዋለን። ከህውሃት ጋር ካላቸው ልዩነት ጋር ሲነጻጸሩ ግን ጊዜ የሚሰጡ ናቸው። እስከዛሬ ድረስ ደክማችሁ የገነባችሁትን ህብረት እንደ ሰርቢያዎች ከብክለት ጠብቃችሁ ሰላማዊውን ትግል እንደምትመሩ ተስፋ እናደርጋለን። ከህውሃት መንግስት በኋላ የተወሰኑ አመቶች በህብረት ገዝታችሁ ነፃ ምርጫ መጥራት ትችላላችሁ ብለን እናምናለን። ከውስጣችሁ አብላጫ የህዝብ ድምጽ ያገኘው ፓርቲ ገዢ ፓርቲ ይሆናል። የቀራችሁት ተቃዋሚ በመሆን በፓርላማ ትግላችሁን መቀጠል ትችላላችሁ ሰርቢያዎች እንዳደረጉት። ይኽ የምር የህልውናችን ጉዳይ ነው።  ኢትዮጵያ እያስተዋለቻችሁ ነው። ዜጎችም ዝም ብለን ተመልካቾች አንሆንም።
ስለዚህ በላንበት መሄዳችንን አቁመን ከአምባገነን ገዢ ህውሃት ነፃ ለመውጣት እና የኢትዮጵያን ህዝብ የመንግስት ስልጣን ባለቤት የማድረግ ምኞታችንን ከፍጻሜ ለማድረስ ከፈለግን ሰላማዊ ትግላችንን ሊበክሉ የሚችሉ ተግባሮችን፣ አሰራሮችን እና ሁኔታዎችን ማወቅ እና ማስወገድ ይጠበቅብናል።
የሰላም ትግል አቀንቃኝ ሮበርት ሃርቬይ (Robert L. Harvey) “ስትራተጂያዊ ሰላማዊ ትግል” በሚል ርዕስ በአልበርት አነስታይን ተቋም ድረገጽ [www.aeinstein.org] ላይ ባተመው የጥናት ጽሑፉ ውስጥ የሰላማዊ ትግል በካዮች (Contaminants of Peaceful Struggle) በሚል ጽፏል። የሰላማዊ ትግልን መበከል ከመኪና ነዳጅ መበከል እና ከመኪናዋ እንጂን መቃጠል ጋር እንደሚከተለው ያመሳስለዋል። ለጥቆም በርካታ ምክሮችን ይለግሰናል። የሮበርት ሃርቬይ ፍሬ አሳብ እንደሚከተለው በአጭሩ ሊቀርብ ይችላል፥
“የመኪና ነጃ (ቤንዚን) ውስጥ ውሃ ከጨመርክ ነዳጁን እንደበከልከው ማወቅ አለብህ። በውሃ የበከልከውን ነዳጅ  ተጠቅመህ መኪናዋን ከቆመችበት ለማስነሳት ብትሞክር ጤናማ ያልሆነ ድምጽ ልትሰማ ትችላለህ። መኪናዋን ማስነሳትም አስቸጋሪ ሊሆንብህ ይችላል። ነዳጁ ውስጥ የከለስከው የውሃ መጠን ከፍ ካለ ደግሞ መኪናዋ ፍጹም ላትነሳ ትችላለች። አልፎም የመኪናዋ ኢንጂን (ሞተር) ሊቃጠል ይችላል። የተበከለ ሰላማዊ ትግልም እጣው እንደዚሁ እንደመኪናዋ ኢንጂን (ሞተር) መቃጠል ወይንም መሞት ነው” ይለናል። ይኼን ካለን በኋላ ሰላማዊ ትግልን ሊበክሉና ለአደጋ ሊያጋልጡት አልፎም ሊገሉት የሚችሉ ተግባሮችን፣ አሰራሮችን እና ሁኔታዎችን በሰፊው ያብራራል። ሙሉውን ጽሑፍ ከፍ ብዬ ከጠቀስኩት ከልበርት አነስታይን ሰላማዊ ትግል ምርምር ተቋም ድረገጽ ማግኘት ይቻላል።
ሮበርት ሃርቬይ በጽሑፉ ከጠቀሳቸው በካይ ተግባሮች፣ አሰራሮች እና ሁኔታዎች ውስጥ ጥቂቱን እና ከሌሎች ምንጮች የተወሰዱ ተዛማጅ በካይ ሁኔታዎችን እና መከላከያ ምክሮችን ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በማዛመድ በዚህ ጽሑፍ በአጭር በጭሩ ለውይይት ቀርበዋል፥
(1) ኃይል እና ክፉ-ቃሎች በማንኛውም መልካቸው ቢሆን ሰላማዊ ትግልን ይበክላሉ። የኢትዮጵያ ሰላማዊ ትግል ሰራዊት የማሳመን እና የማግባባት ማለትም ሰላማዊ ሰልፍ፣ ህዝባዊ ስብሰባ፣ የህዝብ ፊርማ ማሰባሰብ፣ ወ.ዘ.ተ. ሰላማዊ ትግሎች ሲያደርግ ኃይል አይሻም። ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ትብብሮች የመንፈግ ትግል ሲያደርግም ሰላማዊ የሚሆነው። የህውሃት (የመንግስት) የፖለቲካ ድጋፍ ሰጪ ምሶሶዎችን ማለትም የሃይማኖት ተቋማት፣ የመምህራን እና ሰራተኛ ማህበሮችን፣ ወ.ዘ.ተ. ከህውሃት ካድሬዎች ቁጥጥር ነፃ ለማውጣት ወይንም በሌሎች ለመተካት የሚደረግ ትግልም ሰላማዊ ነው። የውጭ ለጋሽ አገሮችን ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ከውሃት ለመንጠቅ የሚደረጉም ዲፕሎማሲያዊ ትግሉችም ሰላማዊ ናቸው። እነዚህን ሁሉ ትግሎች ሲያደርግ የሰላማዊ ትግል ሰራዊት ኃይል አይጠቀመም። እንኳን ኃይል ክፉ ቃል አይጠቀመም። ይኽ ሁኔታ ሰለሰላማዊ ትግሉ የሚዘገቡ ዜናዎች እና የሚሰጡ መግለጫዎችን ይጨምራል። የሰላማዊ ትግል ዘገባዎች እና መግለጫዎች ከጀብዱኛ ፉከራ እና ቀረርቶ ነፃ ሊሆኑ ይገባል። ገና ምኑም ሳይያዝ ስለድል አድራጊነት መጻፍ የሚወዱ ሰዎች አሉ። ያን ማድረግ አስፈላጊም ጠቃሚም አይደለም። መንግስትን ወይንም የመንግስት ካድሬዎችን ለማበሳጨት ተብሎ የሚጻፍ ከሆነም ስህተት ነው። እንዲያውም ከተቻለ ካድሬዎችን ሳይቀር ሰላማዊ ትግል ይስባል (PULL ያደርጋል) እንጂ አይገፋም (PUSH አያደርግም)። የሰላም ትግል ሰራዊት ስለጀግንነቱ ማውሪያ ጊዜም የለውም።
(2) ሰላማዊ ትግላችን ወደ ኃይል ከተንሸራተተ ተበከለ ማለት ነው። ሰላማዊ ትግል አምባገነኖችን የሚገጥማቸው በደካማ ጎናቸው እንጂ በጠንካራ ጎናቸው አይደለም። ይኽን መሰረታዊ መርህ መዘንጋት እና በጀብዱኛነት የኃይሉን መንገድ መቀላቀል ሰላማዊ ትግላችንን ሊበክል እና ሊገድለው ይችላል። በሶሪያ እንደሆነው። የኃይሉን መንገድ ህውሃት የተካነበት እና እስከ ጥርሱ ድረስ የታጠቀበት መንገድ መሆኑን መርሳት የለብንም። በመንግስት ወይንም በመንግስት ደጋፊዎች አማካኝነት ለሚፈጸሙ የድንጋይ፣ የዱላ፣ የስድብ፣ የማዋከብ፣ የማንጓጠጥ፣ የጫጫታ ረብሻ፣ የትንኮሳ፣ የግድያ እና ሌሎች ጥቃቶች የሰላማዊ ትግል ሰራዊት እና ደጋፊዎቹ ምላሻቸው ሰላማዊ ነው። የኃይል ምላሽ ከሰጠን መንግስት እና የመንግስት ደጋፊዎች የሚመኙትን አገኙ ማለት ነው። በለመዱት ሃሰተኛነታቸው ጉዳዩን ጸጥታ የማስከበር ጉዳይ በማድረግ ሰላማዊ ትግሉ ቶሎ እንዳይነሳ አድርገው ሊመቱት ይችላሉ። ሰላማዊ ትግል ወደ ኃይል ከተንሸራተተ በሰላማዊ መንገድ ለነፃነት መታገል የጀመረው ህዝብ እምነት ይተናል። በትግሉ ከመቀጠል ፈንታ ስደተኛ መሆንን ይመርጣል። ከዚያ ትግሉ በታሪካችን የተለመደው በቡድኖች የሚመራ የርስ በርስ ጦርነት ይሆናል። አሸንፎ ስልጣን የሚጨብጠውም አዲስ አምባገነን ይሆናል። ኢትዮጵያ የሶሪያን ወይንም የቀድሞውን የርስ በርስ ጦርነት መንገድ አትወስድም።
(3) ሴቶችን በብዛት በሰላማዊ ትግል ሰራዊት ውስጥ አለማስገባት ሰላማዊ ትግሉን ሊበክል ይችላል። ጉልበተኛነት ተወግዶ ሁሉንም ነገር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈጸም ማድረግ ለአብዛኛዎቹ ሴቶች ተፈጥሮዋቸው ነው። የዚህ ህግ ተገዢዎች ናቸው። በተፈጥሮዋቸው ለጉልበተኛነት ተፃራሪዎች ናቸው። ይኽን ተፈጥሮዋዊ ባህሪያቸው በየቤታችን ሳይቀር የምናስተውለው ነው። ብርቱነትም (ጥንካሬም) ቢሆን ሰላማዊ ትግል የሚፈልገው ብርቱነት የመንፈስ እና የሞራል አቅም ነው። የሴቶች የመንፈስ እና የሞራል ጥንካሬ ሊተመን አይችልም። በሰላም ትግል ሂደት ውስጥ ረጋ ብሎ በማመዛዘን ደፋር እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ሴቶች ያን ማድረግ ይችላሉ። የሴቶች በሰላም ትግል ውስጥ መሳተፋቸው ለሰላማዊው የፖለቲካ ትግል ስብዕናን እና ግብረ ገባዊ ባህሪ ይሰጠዋል። ይህ ባህሪ ደግሞ ዲሞክራሲን ለመገንባት እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ሴቶች ዱላ ለማንሳት ስለማይጣደፉ ብቻ በነፃነት ትግል ላይ ያላቸውን ጀግንነት ከወንዶች ዝቅ አድርገው የሚያዩ ካሉ ተሳስተዋል። በተጨማሪ የኢትዮጵያ ህዝብ ግማሽ ያህሉ ሴቶች ናቸው። ስለዚህ ይህን ኃይል ወደጎን ከተውን ሰላማዊ ትግል አቅማችን ግማሽ ብቻ እንደሆነ እና ለድል አድራጊነት የሚበጅ ግማሽ ያህል ተጨማሪ ኃይል ትግሉን እንዳልተቀላቀለ ማወቅ አለብን።
(4) ሰማዕታትን እና በእስር ቤት የሚጉላሉ ጓደኞችን በሚመለከት የሚፈጸም ሰላማዊ ትግሉን ሊበክል ይችላል። ለምሳሌ በዚህ ወይንም በዚያ ቀን የሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ እነእከሌ የታሰሩበትን ቀን ማስታወሻ ነው ብሎ ማውራት በፖለቲካም ሆነ በሞራል ትክክል አይደለም። ሰላማዊ ትግልንም ይበክላል። ወዳጅ ያርቃል። ስለሆነም ሰላማዊ ትግሉን አብረው የጀመሩ የሰላም ትግል ሰራዊት ባልደረቦች በሙሉ አብረው ከመጨረሻው የነጻነት ቀን ላይደርሱ እንደሚችሉ በቅድሚያ በግልጽ መታወቅ አለበት። በርካታ የሰላም ትግል ሐዋሪያቶች እና ሰራዊቶች በተለያዩ ቀናት፣ ወራት እና አመተ ምህረት ሊታሰሩ እና መስዋዕት ሊሆኑ ይችላሉ። ቀሪው በትግል ላይ የሚገኘው የሰላም ትግል ሰራዊት በእስርም ሆነ በመስዋዕትነት የተለዩትን ጉዋደኞቹን እኩል ያከብራል። እኩል ያስታውሳል። እኩል ይዘክራል።
(5) በሰላማዊ ትግል ሚስጢር ማብዛት ሰላማዊ ትግልን ሊበክል ይችላል። ምስጢር መሆን የማይገባውን ሚስጢር ማድረግ በሰላም ትግል ሰራዊት ውስጥ ጥርጣሬ እና እርስ በርስ አለመተማመን ለፈጠር ይችላል። የሚስጥር ስራ በድርጅት ውስጥ መፍቀድ እና እንዲለመድ ማድረግ አንዳንድ አባሎች አደጋ ሊያመጡ የሚችሉ የሚስጢር ስራዎችን እንዲፈጽሙ ሊያበረታታቸው ይችላል። ሰላማዊ ትግል ግልጽነትን ይሻል። ህጋዊ መንገዶችን ይከተላል።
(6) ዘመቻ መቼ ማቆም እንደሚገባ በቅድሚያ ማወቅ ያስፈልጋል። ማፈግፈግ ሲያስፈልግም መቼ ማፈግፈግ እንደሚያስፈልግ ማወቅ ያስፈልጋል። ይኽ መርህ መሆን አለበት። ማፈግፈግ አስፈላጊ ሲሆን አለማፈግፈግ ጀግንነት ሳይሆን ጀብዱ ወይንም ሌላ ምክንያት ሊኖር ይችላል። ዘመቻዎች ፕላን ሲደረጉ የዘመቻዎቹ አድማስ፣  እስከከየት ድረስ መሄድ እንዳለባቸው እና በሂደት ላይ የተገኙትን ውጤቶች እንደ ድል መቆጠር እንዳለባቸው እና የተጀመሩት ዘመቻዎች መቼ መቆም እንዳለባቸው በግልጽ መታወቅ አለበት። ዘመቻዎቹ ከመጀመራቸው ቀደም ብሎ ለህዝብ እና ለመንግስት እስከ ዝርዝር መርሃ-ግብራቸው ማሳወቅ ሰላም ትግልን ከብክለት ያድናል። በዘመቻው የተወሰኑ ግቦች ተፈጻሚ ከሆኑ በኋላ ተጨማሪ ግቦችን ተፈጻሚ ለማድረግ ሲባል የተጀመረው ዘመቻ ቀደም ብሎ ከታቀደለት አድማስ እና ጊዜ ገደብ አልፎ እንዲሄድ ማድረግ አንዳንዴ ብልህ እርምጃ ላይሆን ይችላል። ሰላማዊ ትግሉንም ሊበክለው እና አልፎም ሊገድለው ይችላል። ይኽን ጉዳይ አስመልክቶ ሮበረት ሃርቬይ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1989 ዓመተ ምህረት በታይናሜን አደባባይ የተፈጸመውን በማስታወስ እንደሚከተለው ይተነትናል፥ “በአደባባይ የወጡት ቻይናውያን ተማሪዎች የጀመሩት ዘመቻ ከመንግስት በኩል ያስገኘላቸውን መለስተኛ እሺታ እንደ ድል በመቁጠር የመንግስት ጦር ኃይል በታንክ እና በእግረኛ ወታደር ጥቃት መፈጸም ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ዘመቻውን አቁመው መበተን ነበረባቸው። ያን ሁሉ ታንክ እና ጦር ኃይል ገጥመው ከማለቅ ቀደም ባሉት ሳምንቶች ያገኙትን ድሎች ይዘው ማፈግፈግ ነበረባቸው” ይለናል። ማፈግፈግ ፍራቻ አይደለም። ጀግኖች ያፈገፍጋሉ። አላንዳች ጥቅም ሰራዊትህን ማስጨረስ የለብህም። አልፎም ሰላማዊ ትግሉን አታስገድልም። ይኸው ከ1989 ወዲህ እስከ አሁን ድረስ ለ23 አመቶች በቻይና ያን አይነት ሰላማዊ ትግል ገና አልተጀመረም። ለምሳሌ የአንድነት ፓርቲ የጀመረውን የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት ዘመቻ አስመልክቶ ግቦቹን፣ አገር አቀፍነቱን፣ ከተሞቹን፣ የከተሞች ዘመቻዎችን ቅደም ተከተል፣ የዘመቻው እድሜው ሶስት ወሮች እንደሆነ በቅድሚያ ማስታወቁ ትክክል ነው። ለጊዜውም ቢሆን በመቀሌ እና በባሌ ሮቢ ያደረገው ማፈግፈግም ስህተት አይደለም።
(7) የሰላማዊ ትግል መሪዎች አንድ እርምጃ ለመውሰድ ሲያስቡ በቅድሚያ እርምጃው የሚያስገኘው ጥቅም እና እርምጃው የሚያስከፍለውን ዋጋ መገምገም እና ማነጻጸር አለባቸው። ዋጋው በድርጅቱ የሚመራውን ሰላማዊ ትግል ቀጣይነት የሚፈታተን ከሆነ እርምጃው ውድቅ መደረግ አለበት። ስለዚህ ሁልጊዜ የሰላማዊ ትግል መሪዎች ምንም አይነት እርምጃ ከመውሰዳቸው ወይንም መግለጫ ከማውጣታቸው በፊት ዋጋ እና ጥቅም (Cost/Benefit) ትንታኔ ማድረግ አለባቸው።
(8) የሰላም ትግል አመራር በወጣቶች ብቻ ከተሞላ ሰላማዊ ትግል ሊበከል ይችላል። እርግጥ ወጣት ከግል ጥቅም ነፃ በመሆኑ ህይወቱን ሙሉ በሙሉ ለትግል ይሰጣል። ወጣት የድፍረት፣ የአቅም፣ የተነሳሽነት እና የተስፋ ምንጭ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ወጣት ወጣት ነው። ተመክሮ ያንሰዋል። ዳኝነቱ አርቆ ያላስተዋለ እና ብስለት የጎደለው ሊሆን ይችላል። ከአዕምሮ ይልቅ ወደ ስሜት ሊያዘነብል እና ጀብዱኛነትን ጀግንነት አድርጎ ሊወስድ ይችላል። እራሱን ከሁሉ የተሻለ አድርጎ ሊገምት ይችላል። እነዚኽ ሁሉ የወጣትነት ባህሪዎች ሰላማዊ ትግልን ሊበክሉ ይችላሉ። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ከምርጫ 97 በኋላ ፓርላማ እንግባ አንግባ በሚለው ውይይት ላይ ‘አትግቡ’ የሚለው አቋም በአብዛኛው በወጣቱ የተደገፈ ነበር። ፓርላማ አለመግባት ስህተት ነበር። ፓርላማ የገቡት በማርላማ ውስጥ ህግ በማስቀረጽ እና በማጸደቅ ለኢትዮጵያ ብዙ ሊያደርጉ ይችሉ ነበር ከሚል እምነት ሳይሆን እዚያው በትግሉ ሂደት ውስጥ እንዲቆዩ እና ትግሉ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ይጠቅም ነበር ከሚል ጽኑ እምነት የተነሳ ነው። ከትግሉ ሂደት ውጭ ሆነህ ድል አድራጊ ልትሆን አትችልም። ይኸው ግንቦት 25 ቀን የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ከስምንት አመቶች በኋላ የተደረገበት ዋንኛው ምክንያትም ተቃዋሚው ከሂደቱ በመውጣቱ ትግሉን ማስቀጠል በለመቻሉ ነው። በቅርብ ዶክተር ያዕቆብ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ጥያቄ ተጠይቆ ሲመልስ ዛሬ ላይ ሆኖ ወደኋላ ሲመለከት ፓርላማ አለመግባት ስህተት ነበር ማለቱን አንብቤያለሁ። ትክክለኛ ግምገማ ነው። ያም ሆነ ይኽ በተለይ አገራዊ ሰላማዊ ትግልን አስመልክቶ ወጣቱ በእድሜና በተመክሮ ከበሰሉ እና የኢትዮጵያን ውስብስብ ታሪክ ከሚያውቁ የሰላም ትግል መሪዎች ጋር ተቀይጦ መስራት አለበት። በዚኽ በወጣቶች ጉዳይ ላይ ሮበርት ሃርቬይ (Robert L. Harvey) “ስትራተጂያዊ ሰላማዊ ትግል” በሚል ርዕስ በአልበርት አነስታይን ተቋም [www.aeinstein.org] ድረገጽ ላይ ባተመው የጥናት ጽሑፉ ውስጥ በርካታ ገጾች ሰጥቶ ጽፏል። እንድታነቡት ጋብዣችኋለሁ።
(9) የሲቪክ ድርጅቶች አመራሮች በአምባገነኖች ቁጥጥር ስር ከሆኑ የሰላም ትግል በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተበክሏል ማለት ይቻላል። ለምሳሌ የመምህራን፣ የሰራተኛ፣ የወጣቶች ማህበራት አመራሮች በገዢው ቡድን ቁጥጥር ስር ከሆኑ እነዚህ ተቋሞች የመጨቆኛ አጋዥ ምሶሶዎች ሆነዋል ማለት ነው። ነፃ ማውጣት አሊያም ሌላ ትዩዩ (Parallel) ድርጅቶች መመስረት ያስፈልጋል። እነዚህ ተቋሞች የነፃነት ትግልን ኃላፊነት ለእያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ለማከፋፈል ይጠቅማሉ።
(10) አግላይነት ሰላማዊ ትግልን ሊበክል ይችላል። በሰላም ትግል ኃይሎች ወይንም ድርጅቶች የሚሰጡ መግለጫዎች ሌላውን የሰላም ትግል ኃይል ወይንም ድርጅት የሚያገሉ ከሆኑ የተገለለ የመሰለው ወገን ወደ ጸበኛነት ሊሄድ እንደሚችል ቀደም ብሎ መገመት እና መግለጫዎች ሌሎችን እንዳያገሉ ተደርገው መጻፍ አለባቸው። ለምሳሌ የአንድ ተቃዋሚ ድርጅት አባል ሲታሰር የሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶች ጉዳይ መሆን ይገባዋል። መንግስት ሁሉንም በወዳጅ አይን እንደማያያቸው እና ቢቻል ሁሉም ቢጠፉለት እንደሚፈልግ መዘንጋት የለብንም። ጥቃቱ ተራ ጠብቆ የሁሉንም በር እንደሚያንኳኳ ማወቅ ያስፈልጋል። አንዱ ላይ ጥቃት ሲደርስ ጥቃቱን የሁሉም ጥቃት አድርጎ መመከት ያስፈልጋል።
(11) ፖሊሶች ከከተማው ህዝብ ጋር ተቀላቅለው ስለሚኖሩ ጥሩዎቹን ልናርቃቸው አይገባም። ለምሳሌ ጎረቤቴ ፖሊስ ቢሆን እና እኔ ፍጹም የሰላም ትግል አማኝ መሆኔን እንዲያውቅ እና እንዲያምንበት አደረኩት እንበል። ከዚያ አለቃው ከፖሊስ ጣቢያ እከሌ (እኔን) ሽብርተኛ ነው እና ይዘህ አምጣ የሚል ትዕዛዝ ቢሰጠው ለአለቃው ሽብርተኛ አለመሆኔን ሊናገር ይችላል። ውይይታቸው እዚያ ላይ ላያቆምም ይችላል።
(12) መለዮ ለባሾች ለሰላማዊ ትግል ድጋፋቸውን የሚለግሱት ህገ-መንግስቱን በማክበር ብቻ እንደሆነ በተደጋጋሚ በአደባባይ መገለጽ ያስፈልጋል። መፈንቅለ መንግስት ወይንም ሌላ የኃይል መንገድ ሰላማዊ ትግልን ይበክላል። ስለሆነም ሰራዊቱ፣ ፖሊስ፣ ደህንነት ለህገ-መንግስቱ ተገዢ የመሆን ህገ-መንግስታዊ ግዴታ እንዳለባቸው የሰላማዊ ትግል ሰራዊት በአደባባይ መስበክ እና ማስተማር አለበት። ህዝብም ይህን ሃቅ እንዲያውቅ ማድረግ ያስፈልጋል። በሰላማዊ ሰልፎች ላይ ነጭ አበባ ለፖሊሶች መስጠት ግን የሰላምነት እና የወዳጅነት ምልክት ነው።
(13) ሰላማዊ ትግል በሚያራምዱ ተቃዋሚ ድርጅቶች መካከል የሚፈጠር የአሳብ ፉክክር አለጊዜው ወደ የፖለቲካ ባላንጦች ፉክክር ካደገ ሰላማዊ ትግሉን ሊበክል ይችላል። በባላንጣነት ፉክክር የተጠመዱ በሙሉ ይሰምጣሉ። በህዝብ ዘንድ የፖለቲካ ካፒታላቸውን ያጣሉ። ተፎካካሪነት ባላጣነት መሆን የለበትም። መርህ የለሽ ፉክክር ግን ወደ ባላንጣነት ሊያመራ ይችላል። በተፎካካሪ ሰላማዊ ትግል ድርጅቶች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን በፍጥነት ለመፍታት የሚያስችል የጋራ መወያያ እና መደራደሪያ መድረክ ሊኖር ይገባል። በሆነ ባልሆነው መጋጨትን ማስወገድ ያስፈልጋል። ትልቁን ህዝብን የመንግስት ስልጣን ባለቤት የማድረግ ጉዳይ (ግብ) አለመርሳት ያስፈልጋል። ጥቃቅን ነገሮችን ቸል ማለት ይመረጣል። በማኪያሄድ ላይ ያለነው ሰላማዊ ትግል መሆኑን እና በሰላማዊ ትግል ደግሞ ስልጣን የሚመነጨው ከምርጫ ሳጥን እንጂ በመጠፋፋት እንዳልሆነ ማስታውስ ተገቢ ነው።
(14) በሰላማዊ ትግል ድርጅቶች መንደር መንግስት ሰርጎ ከገባ ሰላማዊ ትግልን ሊበክል ስለሚችል መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ተጨባጭ መረጃ ካለ በስውር የመንግስት አገልጋይ የሆኑ አስመሳይ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ማጋለጥ ተገቢ ነው። በስህተት ሰም እንዳናጠፋም መጠንቀቅ የግድ ነው። ከመጠን ያለፈ ተጠራጣሪዎችም መሆን እና ከሌሎች ጋር በህብረት ከመስራት  መራቅም ሰላማዊ ትግሉን ይበክላል።
(15) ከሰላም ትግል ድርጅቶች አመራር ውስጥ ህሊና ደካማዎቹ ግለሰቦች በመንግስት እየተመለመሉ ሰላማዊ ትግሉን ሊበክሉ ይችላሉ። እነዚኽን ህሊና ደካማ ሰዎች መንግስት በጥቅማ ጥቅም በመደለል እና በማግባባት ህሊናቸውን  በመግዛት ወሬ እንዲያቀብሉት (informants) ያደርጋል። በዚህም ጉዳይ ላይ ቀደም ብሎ ሊታሰብበት እና አደጋ መከላከያ ወይንም መቀነሻ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል። እነዚህ ወደ መንግስት ወሬ አቀባይነት የተለወጡት የሰላም ትግል ድርጅት አመራር አባላት  ለውይይት በሚነሱ ጉዳዮች ላይ ሆን ብለው ስምምነት እንዳይኖር ያደርጋሉ። ዞር ብለው ደግሞ ለሰላማዊ ትግል ሰራዊት እና ለታጋዩ ህዝብ ስምምነት ጠፋ ይሉታል። ህዝብ ስምምነት ጠፋ ብሎ እንዲያምን እና በትግሉ እምነት እንዲያጣ ለማድረግ። የተለያዩ የሃሰት ዜናዎች እየፈጠሩ በማሰራጨት ህዝቡ ከፍራቻ ወጥቶ እንዳይታገል ለማድረግ ይጥራሉ።
(16) የመንግስት መልክተኛ ቆስቋሾች (agent provocateurs) ሰላማዊ ትግልን ለመበከል እና ለማስመታት በመንግስት ወይንም በፖለቲካ ባላንጣዎቻችን የተተከሉ አሊያም ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚኽ ሰዎች ሆን ብለው የኃይል እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋሉ ወይንም እራሳቸው ድንጋይ ይወረውራሉ። ወይንም ፈንጂ ያፈነዱ እና ህግ አክባሪው ሰላማዊ ትግል ሰራዊት (ሰልፈኛ) እንዲመታ ያደርጋሉ። ብጥብጥ ያነሳሳሉ። ጀብዱኛነትን ጀግንነት አስመስለው ያራምዳሉ።
(17) ከውጭም ሆነ ከውስጥ የሚነሱ ጸብ ጫሪዎች (provocateurs) እንዲሁም በትግል ስም የህዝብ እና የመንግስት ንብረት አውዳሚ ተግባሮች ሰላማዊ ትግል ይበክላሉ። ሰላማዊ ትግል (የተቃውሞ ሰልፍ፣ ህዝባዊ ትብብር፣ ስራ ማቆም፣ ወይንም ሌላ) ሲካሄድ በሰላማዊ ትግል ድስፕሊን የታነጸ የሰላም ትግል ሰራዊት በጸታ ተቆጣጣሪነት ተግባር መሰማራት አለበት። ይኽ በድስፕሊን የታነጸ የሰላም ትግል ሰራዊት ከውጭም ሆነ ከውስጥ የሚነሱ ጸብ ጫሪ ተግባሮችን ይከታተላል። በፍጥነት ያጋልጣል። ሰላማዊውን ተሳታፊ ያረጋጋል። ሰላማዊ ትግል በማኪያሄድ ላይ ካለው ህዝብ ተቀላቅሎ በፖሊሶች፣ በመንግስት ንብረት፣ በህዝብ ንብረት ላይ አደጋ ለመፍጠር የሚሞክር ወዲያውኑ መጋለጥ እና ለፖሊሶች መሰጠት ያስፈልጋል።
ግርማ ሞገስ
ግርማ ሞገስ
በመስቀል አደባባይ እጅ ለእጅ ተያይዘን “በመጨረሻ ነፃ ወጣን!” “በዴሞክራሲ አደባባይ!” ብለን በደስታ የምንዘምርበትን ቀን ህውሃት እራሱ እያቀረበው ነው።
መልካም ውይይት! (girmamoges1@gmail.com)

No comments:

Post a Comment