FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Monday, September 16, 2013

“የበሰበሱት” ህወሃት እና ሻዕቢያ

አንዱ ሌላውን የማጥፋት እሽቅድድም!


tplf-vs-eplf


አምባገነነኖች ከሚታወቁበት አንዱና ዋንኛ መለያቸው መካከል ሁለተኛ ሰው አለማዘጋጀታቸው ነው። አቶ መለስ በድንገት ሲስፈነጠሩ በውል የታየው አስከሬን ደብቆ ድብብቆሽም የዚሁ ውጤት ነው። ኢሳያስ ከስልጣን ቢወገዱ ማን ይተካቸዋል? የሚለው ችግርም ጎልቶ የሚታየው ከዚሁ የአምባገነኖች በሽታ አንጻር ነው።
ግጭትና ችግር ከመፈጠሩ በፊት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ደወል የሚያንጫርረው ዓለምአቀፉ የግጭት ቡድን (International Crisis Group) ፍርሃቻም ከዚሁ የመነጨ ይመስላል። በኤርትራ ህዝቡ በቃኝ ወደ ማለቱ ደረጃ መቃረቡን የሚጠቁመው የዘንድሮው ዓመት ሪፖርት ኤርትራ በቅርቡ መንግስት አልባ የመሆን እድሏ ሰፊ እንደሆነ ያወሳል። በቅርቡ “የሚከሽፉ መንግስታት” በሚል ስማቸው ከተዘረዘሩት ውስጥ አገሮች መካከል ኢትዮጵያም ተመልክታለች።
እኩል ወደ ስልጣን የመጡት ሻዕቢያና ወያኔ ደረጃቸው ቢለያይም ሊድኑ በማይችሉበት ደረጃ መበስበሳቸው በገሃድ የሚታይ እውነት እንደሆነ አብዛኞች ይስማማሉ። ከበሰበሱበት ባህርና ችግር ለመውጣት አግባብ ያለውን መንገድ ከመከተል ውጪ አንዱ ሌላውን ቀድሞ ለማጥፋት እሽቅድድም መርጠዋል። የዚሁ የእሽቅድድማቸው መድረሻ መሰረት ደግሞ አንዱ ለሌላው ተቃዋሚ ምርኩዝና አጋር የመሆንና አንዱ በሌላው መንኮታኮት የግል ትርፍን አስጠብቆ ለመዝናናት እንጂ ህዝብን ማዕከል ያደረገ አይደለም።
ኤርትራ “በነጻ” ምድሯ ላይ “አቅፋና ደግፋ” የያዘቻቸው የኢህአዴግ ተቃዋሚዎች የሚታይ ውጤት ባለማስመዝገባቸው ተግባር ለሚናፍቁ ወገኖች ጉዳዩ “ከበሰበሰ ባህር” አይነት ሆኖባቸው ዓመታት ተቆጥረዋል። ሰሞኑንን ከኢሳት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የግንቦት7 ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ይፋ ያደረጉት መረጃ አዲስ የውይይት አጀንዳ ዘርግቷል።
በኤርትራ መንግስት በኩል የሚደረገው ድጋፍ “ባለ አራትና አምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ ተቀምጦ የመታገል ያህል ነው” በማለትandargachew ያሞካሹት አቶ አንዳርጋቸው “ታይቶ የማይታወቅ፣ ከሚገባው በላይ የበዛ” ሲሉ የገለጹት የኤርትራ ድጋፍ አስቀድሞም ቢሆን ውጤት ማስመዝገብ ያልቻለው ኤርትራ በከተሙ ተቃዋሚዎች ችግር እንጂ በኤርትራ መንግስት እንዳልሆነ በቅርብ ሆነው ማየትና መረዳታቸውን በመግለጽ ምስክርነት ሰጥተዋል።
ይህ መረጃ ከተሰራጨ በኋላ ከኢህአዴግ ወገን ሁለት አንኳር ጉዳዮች ተሰምተዋል። በኤርትራ ላይ መከላከልን መሰረት ያደረገው ፖሊሲ “ተመጣጣኝ ርምጃ መውሰድ” በሚል በመቀየሩ ኢህአዴግ ባልተጠበቀ ወቅትና ጊዜ አስቀድሞ ጥቃት ለመሰንዘር እንደሚችል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለኤርትራ ያዘጋጀላትን አዲስ የአስተዳደር ቅርጽ ተግባራዊ የሚያደርጉ ድርጅቶችን ወደ ግንባር መግፋት የሚሉት የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ ሁለተኛው ግን ከወትሮው ለየት ያለ ሆኖ ተገኝቷል።
አዲስ ራዕይ የሚባለው የኢህአዴግ ልሳን ይፋ እንዳደረገው ወደ ጎረቤት አገራትም ሆነ ሌሎች አካባቢዎች የሚሰደዱ ዜጎች በተቃዋሚ ወገን ለውትድርና እየተመለመሉ እንደሆነና ይህ ሁኔታ በዝምታ ከታየ ስርዓቱ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል አመላክቷል። ከዚህም ጋር ተያያዥነት ባለው መልኩ ሌሎች ወገኖች ግብጽ እጇን የዘረጋችላቸው ክፍሎች ስለመኖራቸው መረጃዎች እንዳሉ ለማሳበቅ ሲሞክሩ ሰንብተዋል። ከዚህ አንጻር ቀደም ሲል ከነበሩት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በተለየ መልኩ ኢህአዴግ ስጋት ውስጥ ስለመሆኑ ይሰማል።
ከላይ የቀረቡት ሁለቱ አንኳር ጉዳዮች መላምት ሳይሆኑ በውል የተቀመጡ እውነታዎች ናቸው። ኢህአዴግ አደራጅቷቸው የስደት ፓርላማ የመሰረቱ የኤርትራ ተቃዋሚዎች ዝግጅታቸውን ተያይዘውታል። እነዚህ የብሔር ድርጅቶች የሚበዙበት ጥምረት ህወሃት እንደሚያስበው ወደ ስልጣን ከደረሱ ኤርትራን ቢያንስ በስምንት “ብሔር ተኮር” ክልል ይከፍሏታል። በአሜሪካ ኒው ጀርሲ ጠቅላይ ግዛት ሮዋን ዩኒቨርስቲ የማርኬቲንግ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር በርሀ ሃብተጊዮርጊስ በ9/8/2010 ለጀርመን ሬዲዮ እንደገለጹት “ኢትዮጵያ በራሷ ልክ የተሰፋ መንግሥት ነው ለማቋቋም የምትፈልገው፤ ይህ አይሳካም” በማለት ተናግረው ነበር። መምህሩ አያይዘው በቋንቋና በብሔር ኤርትራን የመተልተል እቅድ መያዙንም አጥብቀው ተናግረዋል። ህወሃት ይህንኑ አላማውን ለማሳካት ሲል ከሰላማዊ ድርድር ማፈግፈጉን አመልክተዋል።
ኤርትራ ጨለመች – “ከወያኔ ይልቅ ጨለማ !!”
በበርካታ የኤርትራ ተወላጆች ዘንድ አንድ ትልቅ ስጋት አለ። በኤርትራ ቆላማ ክፍል የሚኖሩ ሙስሊሞች ቋንቋቸው አረቢኛ እንዲሆን ምኞት አላቸው። ቁጥራቸው ከክርስቲያኑ ስለሚበልጥ ይህንኑ የብሔር ጥያቄ ላይ የተንጠለጠለ በራስ ቋንቋ የመስራት መብት እንዲከበር ይፈልጋሉ። ከዚህም በላይ በደገኞች እጅ የተያዘውን የስልጣን ሞኖፖሊ አጥብቀው ይቃወሙታል።
ከሐምሌ 24 – ነሃሴ 3 ቀን 2010 ዓ ም ድረስ “ብሔራዊ ጉባኤ ለዴሞክራሲ ለውጥ” በሚል ርዕስ አዲስ አበባ ተደርጎ በነበረው ጉባኤ ጥምረት የፈጠሩት አስር ተቃዋሚዎች ከበርካታ ጭቅጭቅ በኋላ አቋም አድርገው የወሰዱት “የቋንቋና የብሔር መብት ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ነው” በሚል ነው። በወቅቱ የተያዘውን አቋምና የጉባኤው የመጨረሻ ውሳኔ ይፋ ሲሆን የተገለጸው ኢሳያስ ሲወገዱ ስልጣን ተረክቦ ኤርትራን የሚያስተዳድር የስደት ፓርላማ ለማቋቋም ነበር።
eritrea-opposition-conferenceከ330 በላይ ተወካዮች ከተገኙበት ስብሰባ ውስጥ 55 አባላት ያሉበት አደራጅ ኮሚሽን በማቋቋም የተጠናቀቀውን ጉባኤ አስመልክቶ ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ “ተቃዋሚዎች አቋማቸው ግልጽ አይደለም” በማለት ለመቃወም ጊዜ አልወሰዱም። ከእርሳቸው በተለየ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ትምባሆ ሞኖፖል ዋና ስራ አስኪያጅና የንግድ ምክር ቤት ጸሐፊ የነበሩት አቶ ረዘነ ሃብቱ በበኩላቸው ህግና ህገ መንግስት እንደማያውቅ የጠቀሱት ስርዓት አሁን ባሉት ተቃዋሚዎች ሊተካ እንደሚችል እምነታቸውን ያስቀምጣሉ።
በኮታ የሚሸጥ ቁራሽ ዳቦ ለመግዛት ሌሊት የሚሰለፉት የኤርትራ ተወላጆች፣ ኑሮ ቢግልባቸውም፣ የመኖር አቅም ቢያጡም፣ ውትድርናና የነጻ አገልግሎት ቢያንገሸግሻቸውም፣ በነጻነት የመደራጀትና በሰውነት ብቻ ሊያገኙት የሚገባቸው መብቶች ባይኖሩዋቸውም፣ ከሁሉም በላይ አሁን መብራት በሳምንት በፈረቃ አንድ ጊዜ ቢደርሳቸውና በሳምንት ስድስት ቀን በጨለማ ቢቀመጡም “ወያኔ” ያበጀው ስርዓት እንዲመሰረትላቸው አይመኙም።
አስገራሚው አቋማቸው ሁሌም የሚመዘነው ከ”ወያኔ” ጋር እንጂ ከጥቅል የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንዳልሆነ በይፋ ይናገራሉ። የህወሃት ሰዎችና ደጋፊዎችም ይህንን አቋም ይረዱታል። ኢሳያስን ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት በተፈለገው ፍጥነት ሊተገበር ያልቻለበት አንዱና ትልቁ ምክንያት ይህ በመሆኑ “ኢሳያስን ከአህጉርና ከዓለም ኣቀፍ ፖለቲካ በመነጠል አስልሎ ማጥፋት” የሚለውን ሁለተኛው ስልት ኢህአዴግ ዘግይቶም ቢሆን ለመጀመር መገደዱንና በስተመጨረሻ ውጤት እንዳገኘበት ይገልጻሉ።
በዚሁ የማስለል ስልት ወንበራቸው የተፈረካከሰው አቶ ኢሳያስ “የኤርትራ ወጣቶች እንዲሰደዱ የአሜሪካ የስለላ ድርጅት እየሰራ ነው” በማለት በጃንዋሪ 2013 የፈረንጆች አዲስ ዓመት ተናግረዋል። ችግር የሚቆላውን ህዝብ “የኤርትራ ህዝብ ችግር የለበትም ቀልማጣ ነው” ሲሉም አሙቀውታል። ኤርትራ በውጪ አገር መንግስታትና በኢትዮጵያ አማካይነት ጫና እንደተደረገባት መሆኑና መሸሸግ አልተቻላቸውም። ሰሞኑንን ለቅዱስ ዮሐንስ በቃለ ምልልስ መልክ ለህዝባቸው የደሰኮሩት ኢሳያስ የአገሪቱ ወጣቶች ለመኮብለላቸው ምክንያቱ ችግር ሳይሆን ኢትዮጵያንና አሜሪካንን ግንባር ቀደም ተጠቃሽ አድርገዋል። የኢሳያስ ደጋፊ ምሁራን ሳይቀሩ ህወሃት ኤርትራን ከዓለምአቀፍ መድረክ በመነጠል እንደጎዳቸው ማመናቸውን የሚገልጹ እንደሚሉት ህወሃት “የኤርትራን መንግስት በሚገባ አስልሎታል። አቅም አልባና የቀጣናው ተራና ውዳቂ፣ ህግና ወግ የማያውቅ ዱርዬ መንግስት ተደርጎ እንዲሳል አድርጎታል” ይላሉ። አያይዘውም “ህወሃት በግብሩ ከሻዕቢያ ባይሻልም በጉዳይ አስፈጻሚነትና አፍሪካ ህብረትን በወጉ መቆጣጠር በመቻሉ የውጭ ገጹን ማሳመር በመቻሉ ከሻዕቢያ የተሻልኩ ነኝ ብሎ ማሳመን ችሏል፡፡”
eritreans in line
በኤርትራ የዳቦና ወተት ወረፋ (ፎቶ: ኒው ዮርክ ታይምስ)
በዚሁ መነሻና በውስጥ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ቀውስ እየወላለቁ አሉት ኢሳያስ ከስጋትና ከፍርሃቻ እንደሆነ በሚያስታውቅ ጎልዳፋ ፍልስፍና “ኤርትራ በኢትዮጵያ ቅኝ ግዢ ስር ነበረች ተብሎ በተደጋጋሚ ሲወራ ለወያኔዎች ኩራት ሆኗቸዋል” ሲሉ ለተደገሰላቸው ድግስ የኤርትራ ተወላጆችን እልህ ውስጥ የሚከትት ንግግር አሰምተዋል። በርካቶች ኢትዮጵያን ዝቅ አድርገው የተመለከቱ መስሏቸው ቢናደዱም አቶ ኢሳያስ ግን በሳቸው ዘመን ኤርትራ በህወሃት ቅኝ ግዢ እንዳትያዝ ማስጠንቀቂያ ማስተላለፋቸው እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ለጎልጉል ተናግረዋል። ጳጉሜን 2፤ 2005ዓም (በሴፕቴምበር 7፤ 2013) አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ኤርትራ ለኢትዮጵያዊያን ነጻ መውጣት ሊታመን የማይችል ድጋፍ እየሰጠች ነው ባሉበት ማግስት ኢሳያስ “ለመሆኑ ኢትዮጵያ የተፈጠረችው መቼ ነው?” በማለት እንደ አንድ ታሪክ አልባ አገር አበሻቅጠው ማቅረባቸው ቀደም ሲል የነበረውን ቅሬታና ጥርጣሬ እንዲያገረሽ አድርጎታል የሚሉ ወገኖችም አልታጡም።
ህወሃት ልክ እንደነ ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ደኢህዴን እና መሰል ድቃይ ድርጅቶች ኤርትራን እንዲመሩ ያደራጃቸውን ክፍሎች አስተምሮና አንቅቶ ከመዘጋጀቱ ጋር ተዳምሮ ኢሳያስን ጤና የነሳቸው ጉዳይ ዓለምአቀፉ የግጭት ቡድን (International Crisis Group) በዝርዝር ያስቀመጣቸው መሰረታዊ ጉዳዮች የኤርትራን መንግሥት በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ስለከተቱት ነው። በጦር አመራሮችና በፖለቲካ ክንፎች ውስጥ የተከሰተ አለመተማን፣ ተሞክሮ ከሸፈ የተባለው መፈንቅለ መንግሥት፣ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት አሊ አብዶን ጨምሮ የቅርብ ታማኞች መክዳት፣ የወጣቶች አገር ጥሎ መኮብለል፣ እስር፣ የኑሮ ውድነት፣ የምንዛሬ ችግር መባባስ ህወሃት ለሚወስድባቸው ማንኛውም ርምጃ መቋቋም የሚችሉበት ትከሻ ስለሌላቸው እንደሆነ ከግምት በላይ አስተያየት የሚሰጥበት እውነት ነው። በስንቅና ትጥቅም ደረጃ አይመታጠኑም የሚሉ ባለሙያዎችም ካላይ በቀረበው ሃሳብ ይስማማሉ።
ምንም ሆነ ምን ህወሃት ኢሳያስን አስወግዶ አሻንጉሊት መንግስት ከሚያስቀምጥላቸው ይልቅ የኤርትራ ተወላጆች ከኢሳያስ ጋር በመሆን መሰቃየትን እንደሚመርጡ ቀደም ሲል ታጋይ የነበረችና አሁን በስደት ላይ የምትገኝ የኤርትራ ተወላጅ ትናገራለች። ባልደረባዋም ሃሳቧን ይጋራታል። “በየትኛውም መመዘኛ ህወሃት (ወያኔ) ኤርትራ ላይ አሻንጉሊት መንግስት አስቀምጦ አይገዛንም። ኢሳያስ ይሻለናል። በብሄር ሊበጣጥሱንና እኛ በማያቋርጥ ችግር ውስጥ ስንኖር እነሱ ሊስቁብን ነው” በማለት አንገቱን እያወዛወዘ አስተያየቱን ሰጥቷል። ሁለቱም ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀዋል።
ሻዕቢያ ኢትዮጵያ ጠንካራ ሉአላዊ አገር እንድትሆን ይፈልጋል?
“ለኢትዮጵያዊያን አገራቸው ክብራቸው ናት። ማንም በታሪካቸውና በማንነታቸው እንዲሳለቅ አይወዱም። መለስ የሚባሉት ክፉ መሪ ህዝብ እንደረገማቸው ያለፉት ኢትዮጵያንና ታሪኳን ከፍ ዝቅ በማድረግ በማራከሳቸው ነው። ታሪካችንን ወደ 100 ዓመት በማኮሰስ፣ ሰንደቃችንን ከተራ “የመገነዣቸው እራፊ” ጋር በማመሳሰላቸው ሲተፉና ሲወገዙ ኖረው መሞታቸውን በማውሳት  ኢሳያስ ደፍረውና ታብየው “ለመሆኑ ኢትዮጵያ ማን ናት?” ለማለት የተነሱበትን ምክንያት በማስቀደም አስተያየታቸውን ይጀምራሉ።
“በስብሶ ሊወድቅ የደረሰ ስርዓት የሚመራ፣ በልመናና ከስደት በሚገኝ ቀረጥ የምትተዳደር፣ ዳቦ በራሽንና በወረፋ የሚሸጥበት አገር እየመሩ፣ በ20ኛው ክፍለዘመን በኩራዝ የምትበራ አገር ይዘው  ራሱን ችሎ የሚኖርን ህዝብ መተንኮስ አግባብ አይደለም” በሚል ኢሳያስን የተቃወሙ ጥቂት አይደሉም። የኢሳያስ ንግግር በስደት “መብታቸው ተከብሮ” አዲስ አበባና የተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚኖሩ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የራሳቸውን አገር ሰዎች ጭምር የሚያስደስት እንዳልሆነ፣ ይልቁኑም የሚያሸማቅቅ እንደሆነ ነው የሚሰማው። የዚያኑ ያህል “ጨንቋቸው ነው። ምን ይበሉ? አዲስና ለህዝብ ጥቅም ያለው ወሬ ሲጠፋ ከታሪክና ከምኞት ጋር መጣላት የጊዜው አማራጫቸው ነው” በማለት ያጣጣሏቸውና ምላሽም እንደማያስፈልጋቸው የገለጹ ጥቂት አይደሉም።
አቶ ኢሳያስ ሲፈልጋቸው “ኢትዮጵያ በቅኝ ስትገዛን ኖራለች፤ ነጻነት እንፈልጋለን” በሚል በሺህ የሚቆጠሩ ንጹሃን ህይወትን የገበሩት ሳያንስ ዛሬ፣ “ለመሆኑ ኢትዮጵያ መቼ ነው የተፈጠረችው” ሲሉ ጠይቀው “ኢትዮጵያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ድል የተቀዳጁ ለጥቅማቸው ማስጠበቂያ ሲሉ የፈጠሯት አገር መሆኗን ነው እኔ የማውቀው” ማለታቸው ኢሳያስ መቼም ቢሆን ኢትዮጵያ ላይ ያላቸው አመለካከት የጸዳ እንዳልሆነ የሚያረጋግጥ ይሆናል። ከዚህ አንጻር ብቻ ሳይሆን በበርካታ ጉዳዮች ችግር ቢኖርብንም “ኢሳያስን ጠንቀቅ” የሚሉ ወገኖች ለክብር ቅድሚያ እንዲሰጥ ይመክራሉ።
-   ማታ ነው ድሌ” ማን?
“ሻዕቢያና ኢህአዴግ ተመሳሳይ ፖሊሲ መከተል ጀምረዋል” የሚሉ የጎልጉል የዘወትር አስተያየት ሰጪ “ኢህአዴግ ሶማሊያ ላይ የሚከተለውን ፖሊሲ ሻዕቢያም እየተገበረው ነው” ይላሉ። አያይዘውም “ኢህአዴግ በሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር መስራትና፣ ኢትዮጵያ የምታስቀምጠውን አጀንዳ የሚሸራርፍ መንግስት በማዕከላዊ መንግስትነት እንዲቀመጥ እንደማትፈልግ ሁሉ፣ አሁን አሁን ኤርትራም የጀመረችው የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች በዚሁ መልኩ የማደራጀት ስራ ነው” በማለት ይዘረዝራሉ።
በሶማሊያ ከኢህአዴግ ሃሳብ ውጪ ለመንቀሳቀስ የሚያስብ ማዕከላዊ መንግስት ብቅ ቢል ወዲያው መብራቱን ያጠፉበታል። በደቡብ ሱዳን ያለው እውነታ ተመሳሳይ ነው። ደቡብ ሱዳን እየተመራች ያለችው በኢህአዴግ፣ በተለይም በህዋሀት ሰዎች መሆኑንን የሚያመለክቱት አስተያየት ሰጪ፣ “ያለ ምንም ማመንታት ኤርትራ ከውስጥ ያለባት ችግሯ፣ በዓለምአቀፍ ደረጃ የደረሰባት ኪሳራና በመንግሥቱ ውስጥ ከተፈጠረው መፈረካከስ ጋር ተዳምሮ የጎረቤቶቿ እድል ይገጥማታል። ኢሳያስ ያበቃላቸዋል። ኢህአዴግ የሰራው መንግስት ይቋቋማል” ብለዋል።
ኢህአዴግ በአገር ውስጥ ያለበት ቀውስ ቀኑን ጠብቆ የሚፈነዳ እንደሆነ ያመለከቱት አስተያየት ሰጪ “የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በስተቀር ኢሳያስ አሁን ባሉበት ደረጃ ለኢህአዴግ ስጋት አይሆኑም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ኢህአዴግ በግፍ፣ በኑሮ ውድነት፣ ፍትሃዊ ባልሆነ የሃብት ክፍፍል፣ በሙስና፣ ወዘተ የፈጠረው ምሬት ከመጠን ያለፈ ቢሆንም እንደ ሻዕቢያ በቀላሉ የሚናድበት ደረጃ ያለ እንደማይመስላቸው የገለጹት አስተያየት ሰጪ “ኢህአዴግን ከምንም በላይ የሚያሰጋውና የሚያስጨንቀው የከረረ ሰላማዊ ትግል ነው። በትክክለኛ መርህ ላይ የተመሠረተ እውነተኛ ሰላማዊ ትግልና ሕዝባዊ እምቢተኝነት ስለማይገባውና በጉዳዩ ላይ በቂ ተሞክሮ ስለሌለው የሚያሸብረውና አስገድዶ ወደ ድርድር የሚያመጣው እሱ ብቻ እንደሆነ አምናለሁ” ሲሉ አስተያየታቸውን አጠቃለዋል። በሌላ ወገን ደግሞ የተቃዋሚዎች አቅም ከቀድሞው በተለየ የተጠናከረና የፕሮፓጋንዳውን ዘመቻ በማሳደጋቸው ምን አልባት መከላከያ ሰራዊቱ አካባቢ የመከፋፈል ችግር ሊፈጠር ይችላል የሚል ግምት ያላቸውም ብቅ እያሉ ነው።

No comments:

Post a Comment