FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Monday, March 17, 2014

በአዲስ አበባ ውሃ እስከ 20ቀናት ይጠፋል

መፍትሔ ያጣው የውኃ ችግር ተባብሶ ቀጥሏል

waterline


* “የውኃ ምርት ችግር የለብንም የኤሌክትሪክና የማሰራጨት እንጂ” የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን
የፌዴራል መንግሥት መቀመጫና የአፍሪካ መዲና በሆነችው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ፣ ለሁለትና ሦስት ቀናት ይጠፋ የነበረው የውኃ ችግር እስከ 20 ቀናት እየጠፋ  መሆኑንና ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉን ነዋሪዎች እየገለጹ ነው፡፡
በተለይ ከሳሪስ እስከ ቃሊቲ፣ አየር ጤና፣ ወይራ ሠፈር፣ ለቡ፣ ጉለሌ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ፒያሳ፣ ሽሮ ሜዳ፣ መርካቶ፣ የካ በተለያዩ ወረዳዎች አራት ኪሎ (አልፎ አልፎ) በአጠቃላይ በከተማው ከአምስት እስከ 20 ቀናት ውኃ ጠፍቶ እንደሚሰቃዩ ገልጸዋል፡፡ ወ/ሮ ስንታየሁ አበበ የተባሉ የሳሪስ አቦ ማዞሪያ አካባቢ ነዋሪ እንደገለጹት፣ የውኃ ችግር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱ ያስገርማቸዋል፡፡ ቀን ቀን ይጠፋና እኩለ ሌሊት ይመጣላቸው በነበረው ውኃ ሲማረሩ፣ ይባስ ብሎ የመጥፋቱ ሁኔታ ወደ ሦስት፣ አራትና አምስት ቀናት አድጐ አሁን እስከ 20 ቀናት ውኃ እንደማያገኙ ጠቁመዋል፡፡ በመንገድ ግንባታ ምክንያት በሚል በተለይ ከ2001 ዓ.ም. እስከ 2004 ዓ.ም. መጀመርያ ወር ድረስ በፈረቃ በሁለትና ሦስት ቀናት ቆይታ ያገኙት የነበረው ውኃ፣ መንገዱ ከተጠናቀቀ በኋላ ብሶበት ወደ ወር ሊቃረብ መድረሱንና አሁን ባለው ሁኔታ በቅርቡ ወር ሙሉ ላያገኙ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
መንግሥት ከፍታ ባላቸው አካባቢዎች ውኃ ማዳረስ እንዳቃተው አምኖ ሲገልጽ የከረመ ቢሆንም አሁን ግን በለገዳዲ፣ ገፈርሳና አቃቂ ቃሊቲ የከርሰ ምድር ውኃ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎችም ውኃ እያጡ በመሆኑ ‹‹ምን ተፈጠረ?›› የሚል ጥያቄ እየተፈጠረባቸው መሆኑን ወ/ሮ ስንታየሁ ገልጸዋል፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ውኃና ኤሌክትሪክ  የሚጠፉበት ጊዜና ቀናት በመገናኛ ብዙኃን ይነገር እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮዋ፣ አሁን መንግሥት ሰልችቶት ይሁን አሳፍሮት ዝምታን መምረጡ እያሰጋቸው መሆኑን አክለዋል፡፡
ከመሀል አዲስ አበባ (ፒያሳ) ጀምሮ እስከ ዳር ከተማና አቀበት በሚባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሁሉ እንደ ወ/ሮ ስንታየሁ ‹‹የውኃ ያለህ›› እያሉ ሲሆን፣ የውኃና ፍሳሽ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች፣ በክፍለ ከተማና እስከ ማዘጋጃ ድረስ እየሄዱ አቤት ቢሉም ምላሽ ሊያገኙ እንዳልቻሉ እየገለጹ ነው፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ባቀረቡት የግማሽ በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ላይ፣ ውኃን በሚመለከት ያቀረቡትን ሪፖርት በተለይ በውኃ ችግር water lineውስጥ ያሉ ነዋሪዎች አምርረው እየተቃወሙ ነው፡፡ አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሽሮ ሜዳ ነዋሪ እንደገለጹት፣ ‹‹እኛስ መጣች መጣች ብለን ሌሊቱን ስንሯሯጥ መኖሩን ለምደነዋል፡፡ የኛ ዕጣ ፈንታ የደረሳቸው የመሀል ከተማ ነዋሪዎች ግን ያሳዝኑኛል፡፡ ይበልጥ ደግሞ ያዘንኩት የታደለ አገር በዘመናዊ መንገድ ማንኛውንም አቅርቦት እንደልቡ ሲቀርብለት፣ እኛ የውኃ ጥም ለማርካት ቦቴ መኪና እንደሚገዛልን እየተነገረን ነው፤›› በማለት የከንቲባውን ሪፖርት ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ተቃውመዋል፡፡
አስተዳደሩ ትኩረት በመስጠት ከተንቀሳቀሰባቸው ተግባራት አንዱ የውኃ ምርትን መጨመር መሆኑን የገለጹት ከንቲባ ድሪባ፣ በአቃቂ ቃሊቲ 19 ጥልቅ ጉድጓዶች መቆፈራቸውንና 80 ሺሕ ሜትር ኩብ ውኃ ማምረት መቻሉን፣ በለገዳዲም 11 ጥልቅ ጉድጓዶች እየተቆፈሩ መሆኑን፣ ለገዳዲን በማስፋትና የድሬ ግድብን በማሻሻል የውኃ ማምረት አቅምን ወደ 195 ሺሕ ሜትር ኩብ ለማሳደግ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ ወደ 260 ሺሕ ሜትር ኩብ የሚጠጋ ውኃ ማምረት የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መሆኑንና ሁሉም ሥራዎች ሲጠናቀቁ 610 ሺሕ ሜትር ኩብ የውኃ ምርት ከፍ እንደሚልም በሪፖርታቸው ከንቲባው አብራርተዋል፡፡
ነዋሪዎች ግን ሥራውና ዕቅዱ ወይም እንቅስቃሴው ከወረቀት ላይ እንደማያልፍ  በመግለጽ፣ የዕለት ጥማቸውን የሚያስታግሱበት መፍትሔ እንዲፈለግላቸው እየጠየቁ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ግን በነዋሪዎቹ አቤቱታና ሮሮ አይስማማም፡፡ ‹‹የውኃ ምርት እጥረት የለብንም፣ ችግራችን የሥርጭት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንገድ ግንባታዎችና በተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ መጥፋት ከፍተኛ ችግር እየፈጠረብን ነው፤›› ሲሉ የባለሥልጣኑ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ የሥራ ሒደት ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ከምሴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ለይቶ ማወቁንና ከፍተኛ ችግር አለባቸው የተባሉትን ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ጉለሌ፣ የካና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍላተ ከተማዎች ውስጥ ለሚገኙ ነዋሪዎች፣ ለተወሰኑት ጊዜያዊ የፕላስቲክ መስመር እየዘረጋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቀበት ለሆኑት ደግሞ በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ያሠራቸውን ታንከሮች እየተተከለ መሆኑን፣ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ደግሞ ጄኔሬተር እየተገዛና የፀሐይ ኃይል ለመጠቀም ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ (ሪፖርተር)
http://www.goolgule.com/no-water-in-addis-for-20-days/

No comments:

Post a Comment