FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Friday, March 14, 2014

ችግር ነው አስቀድሞ ማሰብ (ፐ/ር መስፋን ወ/ማርያም )

ወያኔ/ኢሕአዴግ ጥሩምባ ነፍቶ የብሔሮች፣ የብሔረሰቦችና የሕዝቦች ነጻነት ብሎ ከአወጀና ሁሉንም ለሃያ ሁለት ዓመታት በተስፋ ከአስፈነደቀ በኋላ ችግር ተፈጠረበት፤ ችግሩ ምንድን ነው? ችግሩ የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች የሚባለው ነው፤ ችግሩ አፍ ከሚችለው በላይ ለመጉረስ ከራስ ጋር መተናነቅ ሆነ፤ ችግሩ የማሰብ ድርቀት ነው፤ ችግሩ ከአሜሪካና ከአውሮፓ መንግሥታት ጀምሮ እስከቀበሌ መዋቅር ያሉትን ሁሉ በአንድ ዘዴ እያባበሉና እያታለሉ ማደናበር ነው፤ ችግሩ በሃያ ሁለት ዓመታት ውስጥ ዘዴው ሻግቶ ዓላማው ደብዛው መጥፋቱ ነው፤ ግሩ የዘዴው መሻገትና የዓላማው መክሸፍ መጋለጡ ነው፤ ችግሩ ወያኔ የተቀመጠበት የሥልጣን ወንበር መቆርቆር መጀመሩ ነው።

Prof. Mesfin Woldemariam
Prof. Mesfin Woldemariam
የግለሰብ ነጻነት ታፍኖ የጎሣ ነጻነት መታወጁ ፋይዳ እንዳላመጣ ታየ፤ የግለሰብን ነጻነት ለመደፍጠጥ ሲባል የጎሣዎች ነጻነትም አብሮ ተደፍጥጦ ነበር፤ ይህንን አስቀድሞ ለማየት ለምን ሳይቻል ቀረ? የሚል ጠያቂ ከመጣ መልሱ ቀላል ነው፤ በሚልዮኖች ብር እየወጣ መንገድ ሲሠራና አስፋልት ሲለብስ ቆይቶ ከጥቂት ወራት በኋላ የባቡር ሀዲድ ለመዘርጋት ተብሎ የተሠራውን አስፋልት የለበሰ መንገድ ማፍረስ እንዳስፈለገ አይተናል፤ የባቡሩ ጉዳይ ለምን አስቀድሞ አልታየም? የጎሣን ነጻነት ለማጉላት ሲባል የግለሰብን ነጻነት መደፍጠጡ ዞሮ ዞሮ የጎሣውንም ነጻነት አንደሚደፈጥጠው ያልታየበት የተለየ ምክንያት የለውም፤ አሰቀድሞ አለማየት የባሕርይ ነው፤ በተጠቀሱት ምሳሌዎች ሁለቱም ዋጋ ያስከፍላሉ፤ ልዩነቱ የአንዱ ዋጋ የሚከፈለው በፖሊቲካ ኪሳራ ሲሆን፣ ሌላው የሚከፈለው በኢኮኖሚ (በሀብት) ኪሳራ ነው፤ ሆኖም የፖሊቲካውም ሆነ የሀብቱ ኪሳራ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በሙሉ ያለምንም የጎሣ ልዩነት ሲጫንበትና ችጋር ሲያንዣብበት በሥልጣኑ ወንበር ላይና በዙሪያው የሚንሳፈፉት ፈጣሪዎቹ ናቸውና የችግሩ ሸክም ሲያልፍም አይነካቸው! እንኳን ለፖሊቲካና ለሀብት ኪሳራ ለሕይወት ኪሳራም ቢሆን የማይጠየቅ መሆኑን በምክር ቤት በሚባለው ውስጥ በድፍረት የተነገረበት አገዛዝ ነው።
የትግራይ ሕዝብ የአገዛዙ ጉልበትና የጥቅም ተካፋይ ነው እየተባለ እስቲያምመው ድረስ በሐሜት ተለበለበ፤ የሚናገርለት ቡድንና የሚናገርበት መድረክ ሳያገኝ ሃያ ሁለት ዓመታት ያህል ኢትዮጵያዊ ትእግስቱን አሳየ፤ ዛሬ አረና የሚባለው የትግራይ የፖሊቲካ ቡድን ወያኔ ለብቻው በትግራይ ሲቆጣጠረው የቆየውን የፖሊቲካ መድረክ ለመጋራት ፊት ለፊት በሰላማዊ የፖሊቲካ ትግል እየተጋፈጠው ነው፤ ይህ አዲስ ሁኔታ በትግራይ ብቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያ የፈጠረውንና ሊፈጥር የሚችለውን የፖሊቲካ እንቅስቃሴ እንኳን ሌሎች በሩቅ የሚከታተሉ ወያኔዎችም ገና አልገባቸውም፤ በፖሊቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው አገዛዙ ችግርን አስቀድሞ የማየት ብቃት እንዳላሳየ ከላይ በተጠቀሱት ምሳሌዎች አረጋግጠናል፤ ስለዚህም አገዛዙ በትግራይ የገጠመውን ሰላማዊ ፉክክር ለመቋቋም አዲስ ዘዴ አላገኘም፤ እስካሁን በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች እንደተደረገው ሁሉ በትግራይም ተቀናቃኞቹን በእስርና በዱላ ለማገድ እየሞከረ ነው፤ ሌላ ዘዴ ገና አላገኘም፤ የሚፈልግም አይመስልም፤ በዱላ መጠቀም ሲለመድ አንጎል ይደነድናል፤ ወገንን ጠላት ያደርጋል፤ ወገን ጠላት ከሆነ ማን ወዳጅ ሊሆን ነው? ትልቁ አደጋ ይህ ነው።
መሠረታዊ ችግርም አለበት፤ በእውነተኛ የጎሣ ፖሊቲካ ውስጥ የማይታዩ ነገሮች እየተከሰቱ ነው፤ በአንድ ጎሣ ውስጥ ከባድ የሆነ የአስተሳሰብ ልዩነት፣ የሥልጣን ክፍፍልም ሆነ የሀብት ልዩነት ጎልቶ ሲወጣ የጎሣው ሥርዓት መክሸፉንና መምከኑን ያመለክታል፤ መስታወት ሆኖ የመሠልጠንና የመለወጥ ልዩነት የሚታየው በዚህ ጊዜ ነው፤ መሠልጠን የማይለውጣቸውን ሰዎች መማር ይለውጣቸዋል፤ ከማትጊያ ጋር በሚሰጥ የቡድን መመሪያ የሚሠሩትን ሰዎች በግል ማንበብና ማሰብ ይለውጣቸዋል፤ ይህንን የማይቀርና ሊታገድ የማይችል የለውጥ አቅጣጫ ማየት የማይችሉ ለዛሬ እንጂ ለነገ የሚኖሩ አይደሉም፤ በትግራይ በመታየት ላይ ያለው የነጻ ሰዎችን፣ የነጻ ግለሰቦችን አስተሳሰብ የሚገልጽ አንቅስቃሴ ለትግራይ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው፤ የመንጋ አስተሳሰብን ለመረዳት ፌስቡክን ማጥናት ነው፤ የወያኔ የካድሬ ሠራዊት በሻገተው አስተሳሰቡ (መለስ ዜናዊ በጸያፍ ቃላት ገልጾታል፤) እያየው በዚያው በለመደውና ባስለመዱት የዱላና የጉልበት ዘዴ ሊያመክነው እየጣረ ነው፤ ወጣቶቹ ግን እየተደረገ ያለውን በአለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ከተጫነባቸው የተስፋ ክምር ጋር እያስተያዩ ማን እንደጠገበና ማን እንደተራበ ያያሉ፤ ያመዛዝናሉ፤ አቅዋማቸውንም ያስተካክላሉ፤ የትግራይ ወጣቶች የፖሊቲካ ንቃትና ነጻ አስተሳሰብ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ወጣቶች ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተጽእኖ የወያኔ ካድሬዎች አስበው ሊደርሱበት አይችሉም፤ የተለመደው አስቀድሞ አለማየት አወዳደቅን የሚጎዳ፣ የሚያስከፋና የሚያሳፍር ያደርገዋል!
የጭቆና ሠራዊት እንዲሆን የሚሠለጥነው የካድሬ ሠራዊት ጸረ-ማሰብ ነው፤ አስቦ ሳይሆን ለትእዛዝና ለሆዱ የሚገዛ ነው፤ ከላይ እስከታች በአንድ አስተሳሰብ ብቻ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ የአገር ጉዳዮችን ለሕዝባዊ ሙግት አይከፍትም፤ ስለዚህም ሀሳቡ አይናፈስም፤ ስለዚህም አስተሳሰቡ የጊዜ መጫወቻ ይሆናል፤ ይሻግታል፤ ጸረ-ማሰብ ሆኖ ከመሻገት መዳን አይቻልም፤ መለስ ዜናዊ ይህንን በደንብ ያውቅ ነበር! ዛሬ እነኮኸንና እነሺን (ኮኸን በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ውስጥ የአፍሪካ ክፍል ኃላፊ የነበረ ሲሆን ሺን ደግሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ነበር፤) በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ የሚናገሩት በኤርትራና በሶማልያ ላይ የተነደፈው መመሪያ አልሠራምና እንደገና መፈተሽ አለበት እያሉ ነው፤ እነዚህ ሰዎች የሚናገሩት የማንን መሠረታዊ ጥቅም ለማራመድ ነው? በጊዜው ጥያቄውን ለመመርመርና በትክክል ለመመለስ ካልተቻለ በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የአፍሪካ ቀንድ ሁኔታ ሲለዋወጥ የኢትዮጵያ አገዛዝ ይጨማደድና ብዙ ባዶ ቀፎዎችን ይዞ ይቀራል።
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11397/

No comments:

Post a Comment