የጎሠኛነት አጭር ትርጉም ዓለምን በራሱ ጠባብ ኢምንትነት የሚለካ ሰው ነው፤ ለኪው መለኪያው ነው፤ መለኪያውም ለኪው ነው፤ ጎሠኛነት የዘረኛነት የባሕርይ ልጅ ነው፤ ዘረኛነትም ሆነ ጎሠኛነት መሠረታቸው ድንቁርና ነው፤ የድንቁርናው ዓይነተኛ መገለጫ ‹‹ንጹሕ›› የሚለው ቃል ነው፤ ለዚህ ዋና ምስክር አድርጌ የማቀርበው አዶልፍ ሂትለርን ነው፤ ስለ‹‹አርያን ዘር›› ማንነትና ‹‹ንጹሕነት›› የሂትለር Mien Kampf የሚለውን መጽሐፍ ነው፤
የሰው ልጆች ባህል የሚባለው ሁሉ፣ ዛሬ የምናየው የሥነ ጥበብ፣ የሳይንስና የሳይንስ ጥበብ (ቴክኖሎጂ) ውጤት ሁሉ የአርያን ዘር የፈጠራ ውጤቶች ናቸው፤ … ‹ሰው› የሚባለውም እሱ ብቻ ነው።
የሂትለር ዘረኛነት የሰውን ልጅ ሁሉ ጉድጓድ ውስጥ ከተተው፤ አርያኑን ከንጹሕ የሰው ዘርነት ወደብቸኛ የሰው ዘርነት አሸጋገረው፤ ይህ ንጹሕ ድንቁርና ነው፤ የጎሠኞችም መነሻና መድረሻ፣ መንገዱም ይኸው ነው፤ በቅርቡ በፌስቡክ ላይ የታየው የቋንቋ ንጽሕና ክርክር የዚሁ የዘረኛነትና የጎሠኛነት ድንቁርና ቅጥያ ነው፤ ስለቋንቋዎች ባሕርይ ምንም ዓይነት እውቀት ሳይኖረው ቋንቋውን በማንገሥ እሱ ራሱ የነገሠ እየመሰለው ይደሰታል፤ ዓባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል እንደሚባለው፤ ሙት ቋንቋ ካልሆነ በቀር ቋንቋ እንደሰው ልጅ ይጋባል፤ ይዋለዳል፤ ይለወጣል፤ በ1944 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ አገር ለማየት ከአዲስ አበባ የወጣሁት በጣልያን ትሬንታ ኳትሮ (34) ከባድ የዕቃ መጫኛ መኪና ላይ ተጭኜ ነው፤ ደብረ ማርቆስ ስገባ የሚናገሩት አይገባኝም ነበር፤ እኔ ከለመድሁት የሸዋ አማርኛ ጋር በጣም የተራራቀ ነበር፤ ወሎም ሄጄ አንደዚያው ነበር፤ ዛሬ ከስድሳ ዓመታት በኋላ ሌላ ነው፤ ዘረኛነትም ሆነ ጎሠኛነት የእውቀት፣ የመሻሻልና የእድገት ጸር ነው፤ ቆሞ-ቀር ነው፤ የአእምሮው እይታ አጠገቡ ካለው ወንዝና ጉብታ አያልፍም፤ ራሱ በፈጠረው ግርዶሽ መተናፈሻውንና መንቀሳቀሻውን ያጠበበ ነው፤ ተንጋሎ የተፋ ለራሱ ከፋ!
ዘረኛነትና ጎሠኛነት ከስጋትና ከፍርሃት የመነጨ ነው፤ አልጋው ፍርሃት፣ ትራሱ ስጋት ስለሆነ ጭንቀቱ እያባነነው እንቅልፍ አይወስደውም፤ ሲያቃዠው ያድራል፤ ለየት ያለና ትንሽም ሻል ያለ ነገር ሲያይ ሆን ብሎ እሱን ለማኮሰስ ወይም ለማሳነስ የመጣበት እየመሰለው ይደነግጣል፤ ስለዚህም ከሱ የተሻለውን በማጥፋት እሱ ወደትልቅነት የሚሸጋገር ይመስለዋል፤ ስለዚህም ዘረኛነትና ጎሠኛነት የሽብርተኛነት ምንጭ አንዱና ዋናው ምክንያት ከሱ የተለየውን ለማጥፋት ያለው ዝንባሌ ነው፤ ዘረኛነትና ጎሠኛነት ልብን በጥላቻ ያቆሽሻል፤ አእምሮን በክፋት እየመረዘ ያደነዝዛል፤ ሰውነትን ወደርኩስ መንፈስነት ይለውጣል፤ በባነነና በቃዠ ቁጥር የሚታየው ማታለል፣ ማጥፋት፣ ማፍረስ፣ ማዋረድ፣ ማጎሳቆልና ማደህየት ብቻ ነው፤ ለዘረኛና ለጎሠኛ እድገት ማለት የሌሎች መቀጨጭና መሞት ነው፤ ማደህየት፣ ማሰቃየት፣ ማቀጨጭና መግደል፣ ንብረትንም ማውደም የሽብርተኛነት መገለጫው ነው፤ የሽብርተኛነት ማለትም የዘረኛና የጎሠኛ የደነዘዘ አንጎል ጥፋትን እንደልማት፣ መቀጨጭን እንደእድገት ይመለከታል።
የዘረኛና የጎሠኛ ሽብርተኛነት የሚፈጥረው የደነዘዘ አንጎል ራስንም አይምርም፤ ለራሱ ልጆችና ቤተ-ዘመዶች አያስብም፤ በዙሪያው ያለውን ከሱ የተለየ ዓለም በሙሉ ወደአንጠርጦስ ሲከታቸው የሱም ወገኖች አብረው አንጦርጦስ ቢወርዱ ግድ የለውም! አይጸጽተውም! የተረፉት በሙታኑ መቃብር ላይ አሸብርቀው ሕያዋን መስለው ይታያሉ፤ እነሱ ባያዩትም የቆሙበት መቃብር ጠርንፎ ይዟቸዋል፤ ሕያዋኑና ሙታኑ ተቆራኝተዋል፤ ሙታኑ በተፈጥሮ ሕግ ይበሰብሳሉ፤ ሕያዋን የሚመስሉት በገዛ ሥራቸው ይበሰብሳሉ።
ዘረኛም ሆነ ጎሠኛ ሂሳቡ ምንጊዜም ጅምላ ነው፤ የዘረኛነትም ሆነ የጎሠኛነት የደነዘዘ አንጎል የሚያየው ጅምላ ነው፤ የጥፋቱ ሁሉ መሠረት የሚሆነውም ጅምላውን ደፍጥጦ አንድ አድርጎ ማየቱ ነው፤ ስለዚህም ጥፋቱ ጅምላ ነው፤ የሽብርተኛነት ሂሳብም ጅምላ ነው፤ ዘረኛም ሆነ ጎሠኛ ወይም ሽብርተኛ ራሱንም የሚያየው የጅምላ አካል አድርጎ እንጂ ራሱን የቻለ ነጻ ሰው አድርጎ አይደለም፤ ብቻውን አይደለም፤ ራሱን የሚያየው በጅምላ ከሌሎች መሰሎቹ ከሚላቸው ጋር ነው፤ ከአሱና ከመሰሎቹ የተለዩ ግለሰቦችንም ሲያይ በነጠላ ሳይሆን በጅምላ ነው፤ ለዚህ ምክንያት አለው፤ ራሱን በጅምላ የሚያየው ምሽጉ ውስጥ ሆኖ ከፍርሃት ነጻ ለመሆን ነው፤ ከእሱ የተለዩትንም በጅምላ የሚያየው ሁሉም ኢላማ ስለሆኑ ነው፤ ይህንን ሁነት በትክክል ለመገንዘብ አንድ ሀ ና ለ የሚባሉ ጎሣዎች አሉ እንበል፤ እነዚህ ጎሣዎች ውስጥ ሁ፣ ሂ፣ ሃ፣ ሄ፣ ህ፣ ሆ የሚባሉ አባሎች አሉ፤ ደግሞም ሉ፣ ሊ፣ ላ፣ ሌ፣ ል፣ ሎ የሚባሉ አባሎች አሉ፤ በትክክል ማሰብ የሚችል ሰው ሁሉ በአንዴ እንደሚገነዘበው ሉ የአንዳቸውንም የሌሎቹን የለ ጎሣ አባሎች ተግባር ሊፈጽም አይችልም፤ ሌሎቹም ሉ ን ሊሆኑ አይችሉም፤ የዘረኛና የጎሠኛ መሠረታዊ ድንቁርና እነዚህን ልዩነቶች ማየት ሳይችል በ‹ሀ› በ‹ለ› መሀከል ያለው ልዩነት በጣም ጎልቶ ይታየዋል፤ የድንቁርናውም፣ የጥላቸው፣ የፍርሃቱም፣ የክፋቱም፣ የተንኮሉም፣ የሽብርተኛነቱም መነሻ ይኸው ራሱን ማሰብ እንደሚችል ሰው ያለዘር ወይም ያለጎሣ ምርኩዝ መቆም የማይችል ዝልፍልፍ ደካማ መሆኑ ነው።
በድንቁርናው ከዝልፍልፍነትና ከደካማነት ያወጣኛል ብሎ የመረጠው መንገድ የጎሣ ምሽጉ ውስጥ ገብቶ በ‹ሀ›ና በ‹ለ› መሀከል ያለውን ልዩነት መስበክ ነው፤ በ‹ሀ› ውስጥ ያለ ጎሠኛ በ‹ሁ›ና በ‹ሂ› መሀከል ያለው ልዩነት፣ በ‹ለ› ውስጥ ላለ ጎሠኛም በ‹ሉ›ና በ‹ሊ› መሀከል ያለው ልየነት አይታየውም፤ ስለዚህም ድንቁርናው ከጥላቻውና ከክፋቱ ጋር እየተጋገዘ ወደቀላሉ የጅምላ ውሳኔ ይመራዋል፤ የሽብርተኛነትም ዋናው የድንቁርና ዘዴ ጥፋት በጅምላ ነው።
በዘረኞችና በጎሠኞች አመለካከት አንድም አህጉር ውስጥ የተለያዩ ሰዎች አይኖሩም ነበር፤ የትም ቦታ ቢሆን ሰዎች እንደሰዎች እየተገናኙ እየተፋቀሩ አይጋቡምና አይዋለዱም ነበር፤ በደቡብ አፍሪካ የነጮች ዘረኛ አገዛዝ ‹የክልሶች ክልል› አይፈጠርም ነበር፤ የሰው ልጅ ሰው ሲሆን የሚያደርገው ያስደንቃል፤ በአንድ የአውሮፓ አገር አንድ ወያኔን እንደክፉ በሽታ የሚጠላ ሰው አውቃለሁ፤ ሚስቱ ወያኔ ነች! በአፍሪካ አዳራሽ ይሠራ የነበረ አንድ ግብጻዊ አውቃለሁ፤ ሚስቱ የአሜሪካን ይሁዲ ነበረች! እስክንድር ነጋ ሚስቱ ትግሬ ነች፤ ርእዮት ዓለሙ ጓደኛዋ ትግሬ ነው፤ የሰው ልጅ ሰውነቱን የሚያሳየው ለራሱ አስቦ፣ ከጅምላው ወጣ ብሎ ለብቻው ሲቆም ነው፤ ስለዚህም ለሽብርተኛነት ተፈላጊ የሆነው ነገር ሁሉ ድንቁርናም ሆነ ጥላቻና ክፋት ከጅምላ አመለካከት ጋር ርእዮትና እስክንድር የለባቸውም ብሎ በእርግጠኛነት ለመናገር ይቻላል፤ ስለከሳሾቹ ሳይታለም የተፈታ ነው፤ እነሱው ይናገሩታል፤ ደፍረው የማይናገሩት አሸባሪነታቸውን ብቻ ነው።
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11605/
No comments:
Post a Comment