FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Monday, March 3, 2014

የዋሽንግተንና የአዲስ አበባ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየተተቸ ነዉ

በሙስና በእምነት ማጉደል በማታለልና በአመለካከት የሚለዩን ዝም በማሰኘት ሐይልን የያዛችሁ በተሳሳተ የታሪክ ገጽታ ላይ ነው ያላችሁትቡጢያቹን የምትፈቱ ከሆነ እጅ እንዘረጋላችሗለን” ያሉት ኦባማ አንባገነናዊ ቡጢያቸዉን ካልፈቱአንባገነናዉያን ጋር  እጃቸዉን ዘርግተዉ ሲጨባበጡ መታየታቸዉ ትዝብት ላይ እየጣላቸዉ ነዉ!

ዋሽንግተን ዲሲ፤ የካቲት 24/2006 (ቢቢኤን የዩናይትድ እስቴትስ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉን ገደብየለሽ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማመላከት ያደረጋቸዉን ጥናቶች ዋቢ በማድረግበየካቲት 20/2006 ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።መሰረቱን አርሊንግተን ቨርጂኒያ ያደረገዉ ፖለቲኮ የሚባለዉ ጋዜጣ/መጽሔት የኦባማ አስተዳደር የኢትዮጵያ መንግስትን ከመሰሉ ለነጻነት ምቹ ካልሆኑ አገራት ጋር ያለዉ ምጸታዊ የዲፕሎማሲ ቁርኝትንም ይተቻል።
ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ጀምሮ የዩናይትድ እስቴትስ መንግስታት ዜጎቻቸዉን ከሚጨቁኑ አገራት ጋር ግንኙነት ለመመስረት እምብዛም እንደማይጥሩ ፖለቲኮ እየገለጸ፤ለሚዛናዊነቱ ተስፋ የተጣለበት የኦባማ ካቢኔ ከሌሎቹ የዩናይትድ እስቴትስ ፕሬዝዳንቶች  በባሰ መልኩ ለዜጎቻቸዉ ደህነነት ምቹ ካልሆኑ 25 አገራት ጋር ግንኙነት አለዉ ሲል የኦባማን የብሐራዊ ደህነነትና ጥበቃ አማካሪ የሆኑትን ሱዛን ራይስ ንግግርን በዋቢነት ያቀርባል። ራይስ “ግልፅ እንሁን አንዳንዴ እኛ አጥብቀን የምንይዛቸዉን ዉድ የሆኑ መብቶችን ከማያከብሩ መንግስታት ጋር የስራ ግንኙነት አለን” በማለት በባለፈዉ የነሐሴ ወር መናገራቸዉን ፖለቲኮ ይገልጻል።
ፖለቲኮ ለነጻነት የማይመቹ ብሎ ከጠራቸዉ 25 አገራት ዉስጥ ኢትዮጵያን በቁጥር 11 ላይ ያስቀመጠ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስቴር ሐይለማሪያም ደሳለኝ ይመሯታል የምትባለዋ ኢትዮጵያ የጸረ-ሽብር ህጓን ፖለቲከኞችን፣አክቲቪስቶችን፣መንግስትን ተጠያቂ የሚያደርጉ አካላትን ለማሰር እንደ ማህተም ትጠቀምበታለች ሲል ተጠያቂ ያደርጋል።ፖለቲኮ አክሎም የመለስ ዜናዊ አስተዳደር በ1999 ሶማሊያን በመዉረር እራሱን ለዩናይትድ እስቴትስ ግልጋሎት ማቅረቡን ያስረዳል። ይህንንኑ አጋጣሚ በመጠቀም በአሜሪካ የሰለጠኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከብሔር ብሔረሰቦች የተነሱ አማጺያንን ለማስቆም የጦርነት ወንጀል መፈጸማቸዉ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ክስ ቢቀርብበትም  ዋሽንግተን አዲስ አበባን በዲፕሎማሲ “እቅፍ-እቅፍቅፍ” እያደረገች መቀጠሏን ገልጿል።
ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብትን ይጥሳሉ ከሚባሉት ጭቋኝ አገራት ጎራ ብትመደብም ፤እንደ አዉሮፒኣይኑ ቀመር በ2008 ብቻ ከዩናይትድ እስቴትስ 969 ሚሊዮን ዶላር በእርዳታ ተቀብላለች!
በኢትዮጵያ ዉስጥ ቀጣይ የሆነ የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ግድያ፣እስር፣የሐይማኖትነጻነትን መነፈግ፣የፕሬስ ነጻነት መመንመን፣የመማርና ማስተማር ሒደት ነጻነት በመንግስት መዳፍ ዉስጥ መግባት፣የመደራጀት-የመሰባሰብ-ሐሳብን በነጻ የመግለጽ ሁለንተናዊ መብት፣ የፍርድ ቤት አሰራር መበላሽትና በስልጣን መባለግን በመተንተን የዩናይትድ እስቴትስ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በየካቲት 20/2006 አመታዊ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል። የኦባማ አስተዳደር አካል የሆነዉ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አሳቃቂ የሆነ የመብት ረገጣ ኢትዮጵያ ዉስጥ መኖሩን እያወጀ የኦባማዉ ቤተ-መንግስት ኢትዮጵያን ከመሰሉ በአንባገነናዉያን ከሚመሩ አገራት ጋር “መለስ-ቀለስ” ማለቱ እያስተቸዉ ነው። የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱን የሚመሩት ጃን ኬሪ አገራቸዉ ከስህተት የጠራች አለመሆኗን ያስረዳሉ።
“ዛሬ ስለ ሌሎች አገራት ያለዉ ሪፖርት ይፋ ለማድረግ ብንመጣም፤ እዚሁ አገራችን ላይ እራሳችንን በከፍተኛ መልኩ ተጠያቂ እናደርጋለን! እንከን የለሽ አለመሆናችንን እናዉቃለን” ጃን ኬሪ።
ጃን ኬሪ መስሪያቤታቸዉ ይፋ ያደረገዉ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ዋሽንግተን ዲሲ ባሉ የመስሪያ ቤቱ አባላት ጥናት ብቻ የተዘጋጀ  ሳይሆን በእያንዱ አገራት ያሉ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶች ተሳታፊ መሆናቸውን ሲያስረዱ “በመላዉ አለም ያሉ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶች በጥናት እንደዚሁም እነዚህን ጽሁፎችን በመጻፍ አክቲቪስቶችን በመቅረብ መንግስታትን በማናገር የኤንጂኦና የሚዲያ ሪፖርቶችን በመተንተን አያሌ ሰአታትን አባክነዋል”ሲሉም ገልጸዋል።
ኬሪ ለነጻነትና ለመብት በሚደረግ ጥረት ዉስጥ ግለሰባዊ ሚና የጎላ መሆኑን መሆኑንም ይገልፃሉ።ከተለያዩ አገራት የለዉጥ ተምሳሊት የሚሏቸዉን ግለሰቦችን ስም በማንሳት የኢትዮጲያዉን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሚናን አድንቀዋል  “እስክንድር ነጋ ሐሳብን በነጻ ስለመግለጽ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚጽፍ ነው” ብለዋል።
በሚያዚያ 4/2004 የፔን አሜሪካን ሽልማትን ያገኘዉ እስክንድር ነጋ አለም አቀፋዊ ትኩረትን ያገኘ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ነዉ። የኢትዮጵያ መንግስት በሽብር ፈጠራ ወንጅሎት ከመስከረም 3/2003 ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛል።
የዩናይትድ እስቴስ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ነጻነትን ከሚነጥቁ ጥቂቶች ጋር ሳይሆን ነጻነትን ከተነፈጉ ብዙሗን አጋር በመሆን አብሮ እንደሚቆም ኬሪ ቃላቸዉን እያደሱ ይናገራሉ “ዛሬ ቃላችንን በድጋሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን! ክብርን ከሚነፍጉ ጥቂቶች ጋር ሳይሆን ክብርን ከሚሹ ብዙሗን ጋር አብረን ለመቆም ዝግጁ መሆናችንንም ለመግለጽ እንወዳለን!”በማለት ቢያስረዱም መንግስታቸዉ ከጨቋኝ አንባገነናዊያን ጋር በሚያደርገዉ ዲፕሎማሲያዊ ቅርርብ ተጠያቂ እየሆነ ነው።
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ብዙ ቃልኪዳን የገቡት በራክ ኦባማ ቃሊኪዳናቸዉ አለተፈጸመም። በተመሳሳይ መልኩ ያሁኑ የዉጭ ጉዳይ መስራያ ቤት ሐላፊ ጃን ኬሪም ሆኑ የቀድሞዋ ሒላሪ ክሊንተን ከአንባገነናዊያን ጋር ያለዉን ግንኙነት ሲያደረጁ እንጂ ሲያመነምኑ አልተስተዋለም በማለት  በርካታ ምሁራን፣ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ ተንታኞች ወቀሳ ያቀርቡባቸዋል።
በጥር 12/2001 ቃለመሃላ የፈጸሙት ፕሬዝዳንት ኦባማ ሰላምና ክብርን ለሚሹ የአለማችን ዜጎች የርሳቸዉ መመረጥ ብስራት እንደሆነ አመላክተዉ ነበር። ከትላላቅ የአለማችን መዲናዎች ጀምሮ ወላጅ አባታቸዉ እስከመጡበት የኬኒያ መንደር የተስፋ ቃል ነበራቸዉ! እንዲም በማለት  ስሜትን በሚነካ መልኩ ተናግረዉ ነበር…
“ከትላልቆቹ መዲናዎች እስከ አባቴ የተወለደባት መንደር ዛሬ ለሚመለከቱን ህዝቦችና መንግስታት፤ አሁን አሜሪካ የእያንዳንዱ አገር የእያንዳንዱ ግለሰብ ወዳጅ ናት! ሰላምና ክብርን ለሚፈልጉ ሴቶችና ህጻናት ዳግም ለመምራት ዝግጁ ነን” ፕሬዝዳንት በራክ ኦባማ።
ኦባማ ምንጫቸዉ ለሆነችዋ አፍሪካ ፕሬዝዳንታዊ ሐይላቸዉን በመጠቅም ያበረከቱት አስተዋፅኦ አናሳ ነዉ።ፕሬዝዳንቱ ቃለመሃላቸዉን ሲፈጽሙ ስልጣንን በማጭበርበር-በሙስናና የሐሳብ ልዩነትን በማፈን በሚቆናጠጡ አንባገነናዉያን ላይ ጣታቸዉን ቢቀስሩም ከነዚህ ምቹ ያልሆኑ አሳፍሪ መንግስታት ጋር እርሳቸዉም ይሁን ካቢኔአቸዉ ዲፕሎማሲያዊ ገደብን አለማበጀቱ አጠያያቂ እየሆነ ነዉ።
በአሜሪካዋ መዲና በዋሽንግተን ዲሲ ጥር 12/ 2001 ቀዝቃዉ አየር በጭብጨባ እየሞቀ ብዙዎች እያለቀሱ ኦባማ ለአንባገነናዊያን መልእክት አስተላልፈዋል።
“በሙስና በእምነት ማጉደል በማታለልና በአመለካከት የሚለዩን ዝም በማሰኘት ሐይልን የያዛችሁ በተሳሳተ የታሪክ ገጽታ ላይ ነው ያላችሁት! ቡጢያቹን የምትፈቱ ከሆነ እጅ እንዘረጋላችሗለን” ያሉት ኦባማ አንባገነናዊ ቡጢያቸዉን ካልፈቱ አንባገነናዉያን ጋር  እጃቸዉን ዘርግተዉ ሲጨባበጡ መታየታቸዉ ትዝብት ላይ እየጣላቸዉ ነዉ።
ብዙ የተገቡ ቃልኪዳስኖች ተግባራዊ ሳይሆኑ በየካቲት 20/2006 ከዩናይትድ እስቴትስ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአመቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲታወጅ “ከነጻነት ፈላጊዎች ጋር እንቆማለን!” የሚል ቃልኪዳን ተገብቷል።የዩናይትድ እስቴትስ መንግስት ባወጣዉ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት የኢትዮጵያን መንግስት “ጨቋኝ-አፋኝ-አሳሪ-ገዳይ-ኢዲሞክራሲያዊ” መሆኑን ይፋ አድርጓል። ፖለቲኮ ጋዜጣ/መጽሔት ይህ ሪፖርት በወጣበት ማግስት የኦባማ አስተዳደር ኢትዮጵያን ከመሰሉ ለዜጎቻቸዉ ምቹ ካልሆኑ አገራት ጋር ይወዳጃል ሲል ይተቻል።
የዲሞክራሲ ተምሳሊት ነን የሚሉ የምእራቡ አገራት ለአንባገነናዊያን ዲፖሎማሲያዊ ከለላ መስጠታቸው የጥቅም ትስስር ወይስ ምጸታዊ የሆነ የዲፕሎማሲ ጨወታ? የሚለዉ ጥያቄ ቢነሳም …ትችቱእንደቀጠለ ነዉ።
ሳዲቅ አህመድ
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11303/

No comments:

Post a Comment