FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Friday, March 14, 2014

የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ተጨማሪ አራት ቀን እስር ቤት እንዲቆዩ ተደረገ

Semayawi Party- Ethiopia

Blue Party’s executives and female members
ባለፈው ሰኞ ፖሊስ መረጃ ለማሰባሰብ በሚል ፍርድ ቤት የ14 ቀን ጊዜ ጠይቆ 5 ቀናት እንደተፈቀደለት ይታወቃል፡፡ ዛሬ መጋቢት 5 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የካ ምድብ ችሎት ቢቀርቡም ፖሊስ አሁንም ‹‹ምርምራውን አልጨረስኩም፣ ተጨማሪ የምይዛቸው ሰዎች አሉ፣ የተያዙትም ቢለቀቁ ሌላ ወንጀል ይሰራሉ›› በሚል ሰባት ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጡት ጠይቋል፡፡
በአንጻሩ የታሳሪዎቹ ጠበቃ ሆነው የቀረቡት የጋዜጠኛ ርዕት አለሙ አባት አቶ አለሙ ጌደቦ በበኩላቸው ፖሊስ ተሰጥቶት የነበሩት ሰባት ቀናት መረጃ ለማሰባሰብም ሆነ ሌሎች የምይዛቸው ተጨማሪ ሰዎች አሉ ያላቸውን ቢኖሩ ኖሮ ለመያዝ በቂ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ታሳሪዎቹ በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚሰሩና ቋሚ አድራሻ ያላቸው በመሆኑ በዋስ ተለቀው ጉዳያቸውን መከታተል ስለሚችሉ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ተከራክረዋል፡፡Semayawi party activist court show up
በሌላ በኩል ታሳሪዎቹ በምርመራ ወቅት በፖሊስና ‹በደህንነቶች› እየተፈጸመብን ነው ያሉትን በደል ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡ ‹‹የታሰርነው በያዝነው አስተሳሰባችን ምክንያት ነው›› ያለው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ መታወቂያ ለማሳየት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሲቪል የለበሱ ግለሰቦች ‹‹ሰማያዊ ከሚባል አሸባሪ ወጥታችሁ ከእኛ ጋር ካልሰራችሁ መቼ እንደምንገላችሁ አታውቁም፡፡›› በሚል እንዳስፈራሩዋቸው ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ወንድ ፖሊሶች ሌሊት ሴቶች እስር ቤት ውስጥ በመግባት እንደሚያስፈራሩዋቸውም ተገልጻል፡፡ ሴቶቹ ታሳሪዎች ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ ወንድ ፖሊሶች ከታሰሩበት እያስወጡ እንደሚያስፈራሩዋቸውም የየራሳቸውን አጋጣሚዎች ለፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡ ወጣት አቤል ‹‹ከእኛ ጋር ከሰራህ የተሻለ እንከፍልሃለን›› ብለውኝ አልፈልግም በማለቴ እንገልሃለን ብለውኛል በማለት ገልጹዋል፡፡
በተቃራኒው ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ሌሎች ታሳሪዎች ላይ ቅስቀሳ እያደረጉ መሆኑን፣ በጋራ እንደሚዘምሩ፣ ቃል ለመስጠት ፈቃደኛ እንደማይሆኑ በመግለጽ ተጨማሪ 7 ቀን እንዲሰጠው በድጋሜ ጠይቋል፡፡ ዛሬ ጠዋት ወደ ችሎት ሲመጡ የታላቁን ሩጫ ቲሸርት ካለበስን አንሄድም ማለታቸውንም ታሳሪዎቹ በቀጣይነትም ወንጀል ሊሰሩ ይችላሉ ለሚለው መከራከሪያው እንደ ማስረጃ አቅርቧል፡፡ ዳኛው ፖሊስ በታሳሪዎቹ ላይ እንዳደረሰው የተገለጸውንና ታሳሪዎቹ ሌሎች ታሳሪዎችን በመቀስቀስና በመረበሽ ያቀረበውን ክስ ላይ ምክር አዘል መልዕክት ካስተላለፈ በኋላ ተጨማሪ 4 ቀን የምርመራ ጊዜ ሰጥቷል፡፡
ችሎቱ መደበኛ ስራውን ይጀምራል ከተባለበት አንድ ሰዓት ዘግይቶ ሊጀምር ችሏል፡፡ በክርክሩ ወቅት መረዳት እንደተቻለውም ጠዋት ታሳሪዎቹ ወደ ፍርድ ቤት በሚመጡበት ጊዜ በሩጫው ዕለት ለብሰውት የነበረውን የታላቁን ሩጫ ቲሸርት መልበሳቸውን ፖሊስ በመቃወሙ በነበረው አለመግባባት መዘግየቱ እንደተከሰተ ታውቋል፡፡
ፖሊስ ሰኞ ዕለት ያስመዘገበው የክስ ጭብጥ እንደሚያመለክተው ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ያዋለው ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል፣ የጣይቱ ልጆች ነን፣ የምኒልክ ልጆች ነን፣ ዳቦ ራበን፣ ብለዋል በሚል ነው፡፡ በዛሬው የክርክር ሂደት እንደተስተዋለው ግን ፖሊስ የመጀመሪያዋን ጭብጥ ብቻ መዝዞ ተከራክሯል፡፡ መርማሪ ፖሊሱ በወቅቱ አሉኝ ያላቸውን የክርክር ነጥቦች በሚያስረዳበት ወቅት አለመረጋጋት ጎልቶ ይታይበት እንደነበር ተስተውሏል፡፡
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11410/

No comments:

Post a Comment