ነፃነት ዘለቀ (ከአዲስ አበባ)
ሙከራውን ማድረጉ ቢያንስ ኪሣራ የለውም፡፡ ውጤታማነቱን ግን እጠራጠራለሁ ብቻ ሣይሆን እንዲያውም መሣቂያ እንዳያደርጉን እሰጋለሁ፤ ክፉዎችና በሰው ስቃይ የሚደሰቱ ስለሆኑ በእሪታችን ቢሣለቁብን ማን ይከሳቸዋል? ከስም ባለፈ የሰላምን ምንነት ከማያውቅ ወያኔ በሰላማዊ መንገድ ችግርን ማስረዳትና መፍትሔ ለማግኘት መመኘት ከምኞትና ከህልም አያልፍም፡፡ እናም ወያኔን በእሪታ ለማስበርገግ የሚቻል አይመስለኝም፤ ተስፋ ለማስቆረጥ አይደለም – ተስፋ ብሎ ነገር ቀድሞውንም ከሀገራችን ከጠፋች ሰንብታለችና ማንም ማንንም ተስፋ ሊያስቆርጥ አይቻለውም፡፡ መቼም የጨነቀው እርጉዝ ያገባል ነውና ወደአእምሯችን የመጣልንን ዘዴ ሁሉ አሟጠን መጠቀሙን የመደገፍ የሞራል ግዴታ ስላለብን እንጂ በአራት ከተሞች አይደለም በአራት መቶ ከተሞች እሪታችንን ብናቀልጠው ወያኔ ንቅንቅ አይልም፤ በጩኸታችን ከማላገጥም በዘለለ አንጀቱ በሀዘኔታ አይላወስም፡፡ የጅቦች ስብስብ በጩኸት እሩምታ ሣይሆን በአልሞ ተኳሽ አናብስት ነው የማያዳግም እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ፡፡ ዓሣማው ወያኔ በሰላማዊ መንገድ ይወገዳል ወይም በምርጫ ሥልጣኑን ያስረክባል ብላችሁ ተጃጅላችሁ የምታጃጅሉ ወገኖች ካላችሁ – እንዳላችሁም ይታወቃል – ሕዝብን ከምታነሆልሉ ሌላ አማራጭ ብትፈልጉ ይሻላልና ጊዜና ምኞትን አታባክኑ፡፡ ሕዝቡ በዚህ ከዳሎል እሳተ ገሞራ ይበልጥ በሚያቃጥል የኑሮ ውድነት እየተቀቀለና እየተገነፈለ በግፍ አገዛዝ እየተሰቃዬ ባለበት ወቅት ወደ ተቃዋሚ ጽ/ቤቶች በብዛት የማይጎርፈው ለምን እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ የደነዘዘ የመሰለው የሚተማመንበት አታጋይ ድርጅት ያገኘ መስሎ ስላልታየው ሆን ብሎ አድፍጦ እንጂ አንድ ሁነኛ ድርጅት ቢያገኝ በደቂቃዎች ውስጥ ምን ሊሠራ እንደሚችል በበኩሌ ይገባኛል – ሚያዚያ 30/97ን እዚህ ላይ ማስታወስ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ እንደዚያች “ሙሽራው እየመጣ ነው፤ በተሎ ተዘጋጂ!” እየተባለ በተደጋጋሚ እንደተነገራትና የሚባለው ውሸት መሆኑን ስትረዳ “ካልታዘልኩ አላምንም” እንዳለችው ዕድለቢስ ሙሽሪት ሆኗልና እንዳንዳንድ የዋህ ታዛቢዎች ለነፃነት የመታገል ፍላጎቱ እንደተቀዛቀዘ የሚነገርለት ሕዝብ የሚያዋጣ መስሎ የሚታየው ታግሎ የሚያታግል ድርጅት ቢያገኝ ምን ተዓምር ሊሠራ እንደሚችል በቅርብ የምናየው ይመስለኛል፡፡ መነሻየ ወዳልሆነ ነገር ለምን ገባሁ?
አሣዛኝ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አዲስ አበባና አካባቢዋ በጅብ መንጋ እየተወረረች ብዙ ዜጎች እየተበሉ ነው፡፡ በፉሪ ቆሼ ተራ በሚባለው አካባቢ፣ በአራት ኪሎ ግንፍሌ አካባቢ፣ ኮተቤ አዲሱ መንገድ አካባቢ ወዘተ. ሰዎች በጅብ መንጋ እየተጠቁ ሕይወታቸውን እያጡ ነው፡፡ ፍየልና በጎችማ በቀንም ሣይቀር እየተበሉ ነው፡፡ ጅብ ተፈጥሯዊ የሌሊት ይትበሃሉን ለውጦ ቀን ከሰው ጋር እየተጋፋ ያሻውን እያደረገ ነው፡፡ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ነን፡፡ “አንበሣን ፈርቼ ዛፍ ላይ ብወጣ ነብር ጠበቀኝ” እንደሚባለው የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማጥቃት ከወያኔ እስከ ዐረብ ጀማላ፣ ከ“ፌዴራል” ሠራዊት እስከ ጅብ አራዊት፣ ከተፈጥሮ ድርቅ እስከ ሰው ሠራሽ የቤተ ሙከራ ቫይረስ ሁሉም ይህን ዘመን ዳግም የማያገኘው ያህል በመቁጠር ይመስላል አናት በአናት ይረባረብበት ይዟል፡፡ የመጨረሻ ያድርግልን፡፡ ይሄ ሰሞነኛ የተፈጥሮ የጅብ መንጋ ደግሞ በሚገርም ሁኔታ ከወያኔ ጅቦች ላይ ተደምሮ ሕዝቡን መቆሚያ መቀመጫ እያሳጣ ይገኛል – ሕጻናትን ከጉያ እየነጠቀ መውሰድም ይዟል፡፡ ምን ዓይነት ፍርጃ ነው ጎበዝ!
እስኪ ይህችን ሴት እንዘንላት፡፡ በጀግንነቷና በአስተዋይነቷም እናክብራት፡፡ ነፍሷንም በነያዕቆብና በነአብርሃም ነፍሳት ጎን ለጎን እንዲያስቀምጥ ፈጣሪን እንለምንላት፡፡ የጀግንነት መገለጫ በግድ የመሣሪያ ተኩስና ግዳይ ማስቆጠር ብቻም አይደለም፡፡ እንዲህ ነው ታሪኩ፡፡
ድርጊቱ ከተፈጸመ አንድ ወር አልሞላውም፡፡ ሴትዮዋ ሥራ ለመግባት እንደወትሮዋ ማለዳ ላይ ትነሣና ትራንስፖርት ወደምታገኝበት ቦታ ጉዞዋን ትጀምራለች፡፡ ከቤቷ ወጥታ ጥቂት እንደተጓዘች ግን በጅቦች ትከበባለች፡፡ ይህች ቆራጥ ሴት የምታደርገውን ብታጣ ሞባይሏን ታወጣና ለባለቤቷ እንዲህ ትላለች፤ “ … አደራህን ከማንም ሰው ጋር እንዳትጣላ፡፡ ሰው ገደላት ብለህ ማንንም እንዳትጠረጥር፡፡ በጅቦች ተከብቤያለሁ፤ ሊበሉኝ ስለሆነ በጭራሽ አልተርፍምና እስከወዲያኛው ደህና ሁኑልኝ፤ ልጆቼንም ሣምልኝ፡፡…” ብላ ንግግሯን ከመጨረሷ የከበቧት ጅቦች ዘረጠጧት፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ቤተሰብና ጎረቤት ሲደርስ ከፀጉሯና ከጥፍሯ በስተቀር ሌላ የረባ የሰውነት ክፍል አላገኙም፡፡ በዚህ መልክ በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባና አካባቢዋ በጅብ መንጋ እየደረሰ ያለውን ያልተለመደ ወረራና ጥቃት ብናይ ምን መቅሰፍት ታዘዘብን የሚያስብል ትንግርት እንታዘባለን፡፡
ይህ ሁሉ ከወያኔ ጅቦች ያለፈ የእውነተኛ ጅቦች አስቀያሚ ድርጊት ምን ያመለክታል? ምልኪው ምንድን ነው?
ትናንት ማታ የሆነ ቦታ ከትላልቅ ሰዎች (elders) ጋር እጫወት ነበር፡፡ ከልምድና ከአያት ከቅድመ አያት ከሰሙት ተነስተው የተገነዘቡትን ሲነግሩኝ ፈራሁ፡፡ የፈራሁት እኔም ከአንዱ ቦታ ስመጣ ወይም ወደ አንዱ ቦታ ስሄድ ጅብ እንዳያነክተኝ በመስጋት አይደለም፡፡ እንዲያ ብቻ ቢሆን ዕዳው ገብስ በሆነ – ያንድ ሰው ጉዳይ ነውና፡፡ ምልኪው ጥሩ ስላልሆነ ነው ክፉኛ የደነገጥሁት፡፡ ባህላችን በምልኪ ያምናል፤ እኔም፡፡
የጅቦች ባልተለመደ ሁኔታ እንደዚህ በጠራራ ፀሐይ ሣይቀር ሰዎችን መተናኮልና መቆርጠም ምልኪው በግምባር ክፉ ዘመን የሚመጣ መሆኑን በግልጽ የሚያመለክት ነው ይላሉ አብረውኝ ያመሹ “የምልኪ ኤክስፐርቶች”፡፡ ድርቅ ሊሆን ይችላል፤ ጦርነት ሊሆን ይችላል፤ የተፈጥሮ መቅሰፍት ሊሆን ይችላል፡፡ ብቻ አደጋ አለ አሉኝ፡፡ ለነገሩ የወያኔን የመጨረሻ ሰዓታት እየጠበቀ ላለ እንደኔ ያለ ሞኝ ዜጋ የወደፊቱ ጊዜ ከእስካሁኑ አሳሳቢ እንደሚሆን ቢገምት አይፈረድበትም፡፡ ባህላዊ ሥነ ቃሉም እኮ “እንዲህ ጨሶ ጨሶ የነደደ እንደሆን፤ ያመዱ ማፍሰሻ ሥፍራው ወዴት ይሆን” ይላል፡፡ ስለሆነም የምልኪውን መፃኢ ውጤት ማለትም አደጋውን ፈጣሪ ቀለል እንዲያደርግልን መጸለይ እንጂ ወደፊት – በጣም በቅርቡ – መሬትን ከሰማይ የሚደባልቅ ከፍተኛ ሀገራዊ ቀውስና ሚሌኒየማዊ የሪከርድ ደረጃ ሊሰጠው የሚችል አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ከግምት ባለፈ እርግጠኛነት መተንበይ ይቻላል፡፡ አሁን እኮ ፊሽካው በኦፊሴል ባለመነፋቱ እንጂ ወያኔንና ጥምብ ሥርዓቱን የሚያስወግደው ሕዝባዊ ጦርነት ተጀምሯል፡፡ “እኔም በአንድ ቀን አልተቆመጥኩም” ብላለች አንዷ አክስቴ – ለልጇ፡፡ ጓዶች! ደርግ የወደቀው ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ነው እንዴ? ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ መሆኑ ቀረ እንዴ? የነበረ አለ፤ ያልነበረ እንደ አዲስ አይመጣም፡፡ ወያኔዎች ሲወድቁ የተፈጠሩባትን ዕለት እንደ ኢዮብ አምርረው እንደሚራገሙና – ሊያውም ለመራገምም ዕድል ካገኙ ነው – ከዚያም ባለፈ እንደጪስ በንነው እንደሚጠፉ ቅንጣት ልንጠራጠር አይገባም፡፡ እናያለን!! ምን ቀረው?
ልብ አድርጉ፡፡ በቦቅቧቃነቱ የሚታወቀው ጅብ ልብ አግኝቶ እንኳንስ የቆመ ሰው ሊጥል ሞቶ አሳቻ ቦታ ላይ የወደቀን የሰው ሬሣ ለመብላት ራሱ ስንትና ስንት የመጠጋትና የመፈርጠጥ maneuvering ካደረገ በኋላ ነው እንደምንም ደፍሮ የሚጠጋና የሚበላ የነበረ፡፡ ጥላውን እየፈራ እንትኑን የትም እየዘራ አይግባኙን የሚሸመጥጥ ጅብ በርግጥም አንዳች ምልኪያዊ ነገር የልብ ልብ ካልሰጠው በስተቀር እንዲህ ያለ ድፍረት ሊያገኝ አይችልም፡፡ ለማንኛውም እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ሀገራችንንና ሕዝቧን ይባርክ፤ ከጠላቶቿ ወጥመድም ይጠብቃት፡፡ ግን ግን አሁንም ፈራሁ …
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11577/
No comments:
Post a Comment