FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Thursday, March 20, 2014

በጋዜጠኞች ላይ ያለ ማስረጃ የሚሰነዘሩ ውንጀላዎች ባስቸኳይ እንዲቆሙ እንጠይቃለን!

ከኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ) የተሰጠ መግለጫ

ማህበራችን ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዶ የምዝገባ ሰርተፊኬት ለማግኘት የጀመረው እንቅስቀሴ በቅርቡ ከመንግስት አወንታዊ ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋ በማድረግ የተቋቋመለትን አላማ ለማሳካት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅና የመናገር ነፃነትን ከማበረታታት ባለፈም ከአህጉራችን አፍሪቃ ጋዜጠኞች ጋር በመተባበር የመላው አፍሪቃ ጋዜጠኞችን መብትና ጥቅም የሚያስጠብቅና የመናገር ነፃነትን የሚያበረታታ አህጉራዊ ተቋም ለመመስረት ተነሳሽነትን ወስዶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በቅርቡም የምስራቅ አፍሪቃ ጋዜጠኞችን በማስተባበር አህጉር አቀፍ እንቅስቃሴያችንን ለማስጀመር ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተግባር ጋዜጠኛውን ሳይወክሉ የጋዜጠኛውን ስም የያዙት የኢጋማ፣ የኢነጋማና የኢብጋህ አመራሮች ነን የሚሉት ግለሰቦች በመቀናጀት በየሚዲያው እየቀረቡ ጋዜጠኞችንና የሚዲያ ተቋማትን ለማሸማቀቅ ያለመ ውንጀላና አሉባልታ የመንዛት ዘመቻ ጀምረዋል፡፡ ግለሰቦቹ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ቀርበው በጋዜጠኞች ላይ ከሽብር ፈጠራ እስከ ሀገር ማተራመስ የደረሰ የውንጀላ መዓት ቢደረድሩም አንዳችም ማስረጃ አላቀረቡም፡፡
ለምሳሌ የካቲት 22 ቀን 2006 ዓ.ም በታተመው አዲስ አድማስ ጋዜጣ (ቅጽ13 ቁጥር 737) ላይ ስማቸውን ደብቀው ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ጋዜጠኞች ሀገር ለማተራመስና ሽብር ለመፍጠር እየተዘጋጁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ “ምን ማስረጃ አላችሁ” ለሚለው የጋዜጠኛዋ ጥያቄ የመለሱት “እኛ እና እነሱ እንተዋወቃለን፡፡” የሚል አስገራሚ መልስ ነው፡፡ ይህ መሰረተ ቢስ ውንጀላ ጋዜጠኞችን ለማሸማቀቅ የተወረወረ በመሆኑ የኢጋማ፣ የኢነጋማና የኢብጋህ አመራሮች ነን የሚሉት ግለሰቦች ጋዜጠኞችን እና የሚዲያ ተቋማትን ያለ ማስረጃ መወንጀላዎች ባስቸኳይ እንዲያቆሙ ይጠይቀል፡፡
በመቀጠልም በሪፖርተር ጋዜጣ (የዕሁድ እትም ቅፅ 19 ቁጥር 1446) የካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም “ኢጋማ በምስረታ ላይ ያለውን የጋዜጠኞች መድረክ አስጠነቀቀ” የሚል ዜና ተመልክተናል፡፡ ሆኖም በጋዜጠኞች ስም ተሰባስበው ጋዜጠኛውን የሚጠቅም አንዳች እንቅስቃሴ ሳያደርጉ ከመተኛታቸው ብዛት አልጋቸው ለረገበ ማህበራት ማስጠንቀቂያ ምላሽ በመስጠት ጊዜ በመሆኑም ምለሻችን በዝምታ መስራት ነው፡፡
የግለሰቦቹ የውንጀላ ንግግር የሚያስረዳው ከህግ፣ ከሞራል እና ከሙያዊ ስነምግባርም በላይ ራሳቸውን ለመሾም የሚፍጨረጨሩ መሆኑን ነው፡፡ ግለሰቦቹ በተለያዩ ጊዜያት መንግስት የፕሬስ ተቋማት ላይና ጋዜጠኞች ላይ የወሰዳቸውን ኢ-ህገመንግስታዊ እርምጃዎች እንደ ጋዜጠኛ ማህበር መሪ ከመኮነን ይልቅ የመንግስትን እርምጃ ሲያወድሱ ተስተውለዋል፡፡ በተጨማሪም በእስር ላይ ሆነው ህክምና በመከልከላቸው ለከፋ ስቃይ ስለተዳረጉ ጋዜጠኞችም ትንፍሽ ሲሉ አልታየም፡፡
እነዚህ የጋዜጠኛ ማህበራት መሪዎች ነን ያሉት ግለሰቦች እንደማህበር መሪ ሳይሆን እንደ ስለላ ተቋም ጋዜጠኞች እና አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ሃገር ለማተራመስና የሽብር ጥቃት ለመፈፀም እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ መረጃ እንዳላቸው በይፋ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም
1ኛ. የሶስቱ ማህበራት መሪዎች አለን የሚሉትን መረጃ ለመንግስት በአፋጣኝ ሳይሰጡ መቆየታቸው በሀገራችን ህግ መሰረት ሊጠየቁው እንደሚገባ እንዲሁም
2ኛ. የሶስቱ ማህበራት መሪዎች በጋዜጠኞች እየተቀነባበረ ነው ካሉት የሽብርና ሀገር የማተራመስ እንቅስቃሴ ጀርባ እንዳሉ የጠቀሷቸውን ኤምባሲዎች በግልፅ ጠቅሰው ለመንግስት እና ለህዝብ እንዲያስታውቁ እንጠይቃለን፡፡
የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ)
መጋቢት 10 ቀን 2006 ዓ.ም
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11487/

No comments:

Post a Comment