FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Tuesday, March 11, 2014

“በዴሞክራሲ” ስም የሚደረግ የመሬት ነጠቃና የዘር ማጥፋት ወንጀል በኢትዮጵያ

“በዚሁ ከቀጠለ አገሪቷ ወደ እርስበርስ ግጭት ማምራቷ አይቀሬ ነው”

panelist
ስብሰባውን የጠራው ድርጅት በመወከል ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት ማርየስ ቮንዳርፈር እንደተናገሩት Fronline Club የተባለ ድርጅት በኦስሎ የተቋቋመው በያዝነው ዓመት ሲሆን አላማውም በዓለምአቀፍ ታዋቂ የፊልም እና የፎቶግራፍ ባለሙያዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ እና ምሁራንን በመጋበዝ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይቶች እና ዶክመንተሪ ፊልሞችን ማቅረብ መሆኑን ገልጸዋል።  የዓመቱ  ስራውንም የጀመረው በዚሁ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እንደሆነ ተመልክቷል።
ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ ጠንካራ ነቀፋና ተቃውሞ ያልተለየው መሆኑ ይታወቃል። የዚህም ውይይት ዋና አላማ በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዙሪያ የሚደርሰውን ችግር ትኩረት ለመስጠትና ተጽዕኖ ለማድረግ የሚያስችሉ አካላትን ጠርቶ ማወያየት ነው። በመሆኑም በውይይቱ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍንና የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የምዕራባውያን መንግስታት በተለይም የኖርዌይ መንግስት ሚና ምን መሆን እንዳለበት በስፋት ትኩረት ተሰቶበታል። በውይይቱ ላይ አራት የተለያዩ አካላት ንግግር አድርገዋል።Abdulahi
የውይይቱ የመጀመሪያ ተናጋሪም አቶ አብዱላሂ ሁሴን ሲሆኑ እርሳቸውም የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ልዩ አማካሪና የኦጋዴን ቲቪ ቻናል ሃላፊ ሆነው ሰርተዋል። ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሲሰሩ በነበሩበት ወቅት ያሰባሰቡትን መረጃ በቪድዮ የተደገፈ ዶክመንተሪ በዚህ ስብሰባ አቅርበዋል። የቀረበው ቪድዮ በክልሉ ፕሬዝዳንት እና በክልሉ ባለስልጣናት፣ ፖሊሶችና የጸጥታ አካላት መካከል የተደረጉ ምስጢራዊ ስብሰባዎችን አካቷል። በክልሉ እየተደረገ ያለውን ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ማሰርን፣ ማሰቃየትን፣ ግድያን እና በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እና ስቃይ ራሳቸው የጸጥታ ኃይሎች የሰጡትን ምስክርነት ዶክመንተሪው አካቷል። በመንግሥት ወታደሮችና ፖሊሶች አማካኝነት በክልሉ እየደረሰ ያለውን አሰቃቂ ወንጀሎች ዶክመንተሪው በማስረጃነት የሚያሳይ በመሆኑ በቀጣይነት ሄግ ለሚገኘው አለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት እንደሚያቀርቡ አቶ አብዱላሂ አመልክተዋል።
በሶማሌ ክልል በሚሰሩበት ወቅት በተለያዩ ቦታዎች በህዝቡ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ችግር የተመለከቱ መሆኑን ከመጥቀሳቸው በተጨማሪ በአሰቃቂ ሁኔታ የሚካሄደው የዘር ማጥፋት ወንጀል ትኩረት እንዳልተሰጠው ተናግረዋል። ዓለምአቀፉ ማህበረሰብም ሆነ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን በመንግስት ባለስልጣናት እና የጸጥታ ኃይሎች እየደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በተመለከተ በቂ መረጃ እንደሌላቸው አቶ አብዱላሂ አመልክተዋል። ይህ የሆነበትን ምክንያት ለማስረዳት ተናጋሪው ሁለት ነጥቦች አንስተዋል። በመጀመሪያ ደረጃ ኢህአዴግ ጋዜጠኞችንና ዓለምአቀፍ ገለልተኛ ድርጅቶች ወደ ክልሉ እንዳይንቀሳቀሱ በመከልከሉ ሲሆን ይህም ድርጊት በተጨባጭ በክልሉ እየደረሰ ያለው እውነታ እንዳይሰማ፣ እንዳይታይ አድርጎታል። በሁለተኛ ደረጃ ኢህአዴግ ምዕራባዊያንን በውሸት የማሳመኑን ስልት የተካነበት በመሆኑ እስካሁን በክልሉ የሚደርሰውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በመሸፈኑ ተገቢውን ትኩረት እንዳያገኝ አድርጎታል ብለዋል። የሳቸውም አላማ ይህንን የሰበሰቡትን የቪዲዮ መረጃ ለዓለምአቀፉ ህብረተሰብ በማቅረብና በክልሉ የሚደርሰውን የዝር ማጥፋት ወንጀል በማስቆም ለዚህ ተጠያቂ የሚባሉ ባለስልጣናትና የጸጥታ ኃይሎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።
በመቀጠል ንግግራቸውን ያደረጉት እውቁ የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዳይሬክተር የሆኑት የተከበሩ አቶ ኦባንግ ሜቶ ሲሆኑ የኖርዌይ ህዝብና መንግስት ለኢትዮጵያውያን ብሎም ለአጠቃላይ ሰብዓዊነት እያደረጉ ያለውን አስተዋጽዖ በማድነቅ ንግግራቸውን ጀምረዋል። በግጭትና በተለያዩ የፖለቲካ ቀውሶች ምክንያት በዓለማችን ተጠቂ ህዝቦች ካንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመሰደዱ ሁኔታ የተለመደ መሆኑን በማመልከት ብዙ ስደተኞች ወደ ኖርዌይ የሚመጡበት ምክንያት አገሪቷ ሃብታም እና የበለጸገች ስለሆነች ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ እና ለሰብዓዊነት ክብር ቅድሚያ በመስጠቷ መሆኑን አቶ ኦባንግ አመልክተዋል።
Panelist2በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የመሬት ነጠቃ ሁኔታ በመጥቀስ የኖርዌይ መንግስትና እርዳታ ሰጪዎች ሊወስዱ የሚገባቸውን እርምጃ በንግግራቸው ጠቁመዋል። በመቀጠልም ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት የሚያሳይ ምስል በማቅረብ ምን ያህል አገሪቱ በተፈጥሮ የታደለች መሆኑንና ያገሪቱ ዋና ችግር የመልካም አስተዳደር እጦት እንደሆን አስረድተዋል። በስልጣን ያለው አገዛዝ በህዝቡ ላይ የሚያደርሰው ጭቆና አላንስ ብሎ የአገሪቱን መሬት ለህንድ፣ ለቻይና እና ለሳውዲ ኢንቨስተሮች በርካሽ እየሸጠ ይገኛል። በዚህም ምክንያት ከሚሸጠው መሬት የሚፈናቀሉ ዜጎች በአስከፊ የድህነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ በመጥቀስ የሚያፈናቀሉት ዜጎች ህይወት በመሬቱ ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ ኢህአዴግ በኢንቨስትመንት ስም የሚደርገው ድርጊት የዜጎችን ኑሮ አናግቷል። ምዕራባዊያን አገሮችም በተለይም የኖርዌይ መንግስት ይህንን አስከፊ የህዝቡን ስቃይ እና ችግር እያዩ እንዳላዩ በመሆን ለአምባገነናዊ መንግስት የሚያደርጉትን ድጋፍ እና ድጎማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ይገኛሉ። ይህም የምዕራባዊ መንግስታት ዕርዳታ ህዝቡ እራሱን በራሱ ከአምባገነናዊ አገዛዝ ነጻ እንዳያወጣና ለማውጣት የሚያደርገውን ጥረት ላይ ትልቅ እንቅፋት እንደሆኑበት አቶ ኦባንግ ተናግረዋል።
ይህ ሁኔታም በዚሁ ከቀጠለም አገሪቷ ወደ እርስ በርስ ግጭት የማምራት ሁኔታ አይቀሬ መሆኑን በማመልከት ምዕራባዊ አገሮች በተለይ የኖርዌይ መንግስት ይህ ከመሆኑ በፊት የህዝቡ ስቃይ እና እንግልት የሚቆምበትን መንገድ በማፈላለግ እና በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብ ትልቅ ሚና መጫወት እንዳልባቸው አቶ ኦባንግ አሳስበዋል።
በሶስተኛ ደረጃ ንግግራቸውን ያደረጉት ዮሃን ሂላን የተባሉ የማህበራዊ ምሁር ሲሆኑ በሰሜን እና በምስራቅ አፍሪቃ በልማት ዘረፍ የማማከር እና የምርምር ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ ከመድረኩ ተጠቅሷል። ባሁን ወቅትም በርገን በሚገኘው በክርስትያን ኤይድ ኢንስቲትዩት ውስጥ እየሰሩ ሲሆን ይህም ኢንስቲትዩት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር እንደሚሰራ ታውቋል። እኝህ ምሁር ከኢህአዴግ ጋር ያላቸውን ቀረቤታ እና ለአምባገነናዊው መንግስት ያላቸውን አወንታዊ አስተያየት በሚያመለክት መልኩ ንግግር አድርገዋል። በስልጣን ላይ ያለው “መንግሥት” ከጎረቤት አገሮች አንጻር የተሻለ መረጋጋትና የኢኮኖሚ ዕድገት የሚታይበትን መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን እኝህ ምሁር ባቀረቡት አስተያየት ላይ ከመድረኩም ሆነ ከተሳታፊዎች ትችት ተሰንዝሮባቸዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች እንደተገለጸው እንደ ዮሃን ሂላን የመሰሉ ምሁር ነን ባይ ግለሰቦች የኢትዮጵያ ህዝብ በምን ሁኔታ እንዳለ የማያውቁና በተጨባጭ እውነታውን የማያሳይና የተሳሳቱ መረጃዎችን በመጠቀም የምርምር ውጤቶችን የሚያቀርቡ ምሁራን እንዳሉ የተጠቆመ ሲሆን በዚህም የተሳሳተ የምርምር ድምዳሜ ምክንያት ምዕራባውያን መንግስታት የተወላገደ የፖሊሲ አቅጣጫ እንዲከተሉ አድርጓል።
በመጨረሻም በኖርዌይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ጥገኝነት ጠያቂወች ዙሪያ የሚያጠነጥን ዶክመንተሪ ቪድዮ ያቀረቡት አርቲስትና የሰብአዊ መብት ተማጋች የሆኑት ሶልቬይ ስይቨርሰን ናቸው። ይህንን ዓይነቱን ጥናት ለማድረግ ያነሳሳቸው ዋናው ምክንያት የኖርዌይ መንግስት እና የኢትዮጵያ “መንግስት” ስደተኞችን ለመመለስ ያደረጉትን ስምምነት አሳስቧቸው መሆኑን ተናግረዋል። በኖርዌይ የሚገኙ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኙ በመጥቀስ የኖርዌይ መንግስትም ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የጉዳዩን ውስብስብነት እንዳልተመለከተው ጠቁመዋል። ያቀረቡትን ዶክመንተሪ ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚያቀርቡና የተሻለ የጥገኝነት ፖሊሲ እንዲቀረጽ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በመጨረሻም በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ አጭር ውይይት የተደረገ ሲሆን የተለያዩ አካላት ጥያቄና አሰተያየቶች ሰንዝረዋል። የስብሰባው አዘጋጆችም በጉዳዩ ዙሪያ ተከታታይ ውይይት እንደሚደረግ በመጠቆም የዕለቱን መረሃ ግብር አጠቃለዋል።
ከስብሰባው ጋር በተያያዘ የተቀናበረ ቪዲዮ ለመመልከት እዚህ ላይ ይጫኑ
http://www.goolgule.com/in-the-name-of-democracy-land-grab-and-genocide-in-ethiopia/

No comments:

Post a Comment