ተከሳሾቹ ለአንድ ፖሊስ ኃላፊ መሞት ተጠያቂዎች ናቸው
* ውሳኔው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን አስደንግጧል
በሕዝብ ከተመረጡ በኋላ በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣናቸው የተወገዱትን የቀድሞ የግብጽ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲን በመደገፍ በፖሊስ ጣቢያ ላይ አደጋ አድርሰው የነበሩ 529 ተጠርጣሪዎች ትላንት ሰኞ ዕለት የሞት ቅጣት ተበየነባቸው፡፡ የብይኑ ፍጥነትና የተፈረደባቸው ተከሳሾች ብዛት አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን አስደንግጧል፡፡ አሶሺየትድ ፕሬስ እንደዘገበው ከሆነ ውሳኔው ለይግባኝ የሚቀርብ ሲሆን በሙስሊም ወንድማማች ላይ ሆን ተብሎ የተነጣጠረ ጥቃት እንደሆነ ዘግቧል፡፡
በዓለማችን በቅርብ ጊዜያት ከተካሄዱ የሞት ፍርድ ብያኔዎች በብዛትም ሆነ በፍጥነት ለየት ያለ እንደሆነ የተጠቀሰለት ይህ የፍርድ ሂደት በግብጽ የሕግ የበላይነት እየከሰመ የሄደ መሆኑን የሚያመላክት ነው ሲሉ በርካታ የሕግ ምሁራን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ተከሳሾቹ በሙሉ የሙስሊም ወንድማማች አባላትና የቀድሞው ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ ደጋፊ መሆናቸው ብያኔው እውነተኛ የፍርድ ሂደት የተከተለ ሳይሆን ወደፊት ሊነሳ ለሚችል ተቃውሞ ማስተማሪያ እንዲሆን ታቅዶ የተከናወነ ነው ሲል የፍትሕ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ አሶሺየትድ ፕሬስ በተጨማሪ ዘግቧል፡፡
ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስ ባለፈው ነሐሴ ወር ሚኒያ በተባለች የግብጽ ከተማ በሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ ላይ በተሰነዘረ ጥቃት በተከናወነ የነፍስ ግድያ፣ የግድያ ሙከራ፣ መንግሥትን ለመገልበጥ ሕገወጥ ቡድንን መቀላቀል እና የመንግሥትን የጦር መሣሪያ መስረቅ በሚሉ ወንጀሎች ናቸው፡፡ በወቅቱ በፖሊስ ጣቢያው ላይ በደረሰ ጥቃት የሚኒያ ከተማ ምክትል የፖሊስ ኃላፊ ሞሐመድ አል-አታር መገደላቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህ ጥቃት በኋላ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዘው ወታደራዊው አገዛዝ በሙስሊም ወንድማማች ደጋፊና አባላት ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆነና አሰቃቂ ጥቃት በማድረስ በዚያን ወቅት ብቻ ከ600 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል፡፡
ከ545 ተከሳሾች ውስጥ 528ቱ ጥፋተኞች ሆነው በመገኘታቸው የሞት ፍርድ እንደተበየነባቸው የመንግሥት ሚዲያ ሲያስታውቅ አንዳንድ ባለሥልጣናት ቁጥሩ 529 እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 150 በሌሉበት ፍርዱ የተበየነባቸው ሲሆን የተቀሩት ግን በነጻ ተለቅቀዋል፡፡ በግድያው የተሳተፉት ብቻ ፍርድ ሊበየንባቸው ይገባል በማለት የሚከራከሩ ወገኖች እንደሚሉት በማስረጃነት የቀረቡት 20 የሚሆኑ የቪዲዮ ምስሎች እንደሚያሳዩት የተወሰኑ ሰዎች የፖሊስ አዛዡን በብረት በትር ሲደበድቡ እና አንድ ሐኪም ደግሞ በእሣት ማጥፊያ የኦክስጂን ሲሊንደር (ካንስተር) የፖሊሱ ጭንቅላት ሲፈረክስ ታይቷል ይላሉ፡፡
ሁለት ቀናት ብቻ በፈጀው በዚህ የፍርድ አሠጣጥ ሥርዓት ላይ የተከሳሽ ጠበቆች በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የማስረጃ ሰነዶችን ለመመልከትም ሆነ በቂ ጊዜ አግኝተው የደንበኞቻቸውን ጉዳይ ለፍርድቤቱ ለማስረዳት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ከፍተኛ ባለስልጣን ለአሶሺየትድ ፕሬስ እንደገለጹት ከዚህ ዓይነቱ የሞት ብያኔ በኋላ ማንም በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደማይሳተፍ ጠቁመዋል፡፡ የፍርዱን አካሄድ ሲገልጹም “ሁኔታው እጅግ ለየት ያለ ነው፤ እያንዳንዱን ተከሳሽ እየጠራን ክሱን እንዲከራከር፣ ጠበቃ እንዲያቆም፣ ወዘተ ለማድረግ በቂ ጊዜ የለንም” ብለዋል፡፡ በፍርዱ ሂደት ላይ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው በጠየቁ ጠበቆች ላይ ችሎቱ የመሩት ዳኛ ሰዒድ ዩሱፍ ጠበቆቹን በቁጣ መዝለፋቸው አብሮ ተዘግቧል፡፡
የሞት ፍርዱ በግብጽ ሙፍቲ (የአገሪቱ ከፍተኛ እስላማዊ ባለሥልጣን) መጽደቅ ያለበት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የተከሳሽ ጠበቆች ይግባኝ በማለት ፍርዱን ለማስቀየር እየሠሩ መሆናቸው ተገልጾዋል፡፡
ሌሎች ወደ 700 የሚጠጉ የሙስሊም ወንድማማች ተከሳሾች ዛሬ ማክሰኞ ለፍርድ ይቀርባሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የወንድማማቹ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ሞሐመድ ባዴይ እና ሌሎች ከፍተኛ ኃላፊዎች ይገኙበታል፡፡ በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን የተወገዱት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ሙርሲም በቅርቡ ለፍርድ የሚቀርቡ ሲሆን ዛሬ የሚቀርቡትን ጨምሮ ሙርሲም ሞት ሊፈረድባቸው ይችላል የሚል አስተያየት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን ዓለምአቀፍ ተጽዕኖን በመፍራት ሙርሲ ላይ ሞት የመፈረዱ ጉዳይ አጠራጣሪ እንደሆነ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ አመልክተዋል፡፡
የሰኞ ዕለቱን ብያኔ ተቃውሞ የቀረበበበትን ያህል የፍርዱን ትክክለኛነት የደገፉ ግብጻውያንም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አሚን ፍቱሕ የተባሉ የካይሮ ነዋሪ ለአሶሺየትድ ፕሬስ እንደተናገሩት “ቁርዓን እንደሚለው ገዳዮች ሞት ይገባቸዋል፤ እነዚህ ሰዎች ግድያ ስለፈጸሙ በአጸፋው መገደል ይገባቸዋል” ብለዋል፡፡
ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሂውማን ራይትስ ዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሰኞው ዕለት ፈጣን የሁለት ቀን ብያኔና በቀጣይ የሚደረጉት የፍርድ ሂደቶች እጅግ ያሳሰቧቸው መሆኑ ገልጸዋል፡፡ አምነስቲ ብያኔውን “በቅርብ ዓመታት በዓለማችን ከተካሄዱ የሞት ብያኔዎች በዓይነቱ ብቸኛው” በማለት ሲገልጸው ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ደግሞ “ኅሊናን የሚያስደነግጥና የፍትሕ ውርጃ የታየበት” ነው ብሎታል፡፡ (ፎቶ: AP እና BBC)
http://www.goolgule.com/egyptian-court-issues-death-sentence-verdict-for-529-people/
No comments:
Post a Comment