ክንፉ አሰፋ
በብሄራዊ ትያትር አካባቢ አንዲት አነስተኛ ምግብ ቤት ነበረች። «ገሊላ ምግብ ቤት» ትባል ነበር። በአዲስ አበባ «ቁምራ» ከመግባቱ በፊት በአካባቢው ያሉ የመንግስት ሰራተኞች በምሳ ሰዓት ይህችን ምግብ ቤት ያጨናንቋት ነበር። ቁምራን የማታውቁ ካላችሁ፤ ለጽድቅ የሚደረግ መንፈሳዊ ጾም እንዳይመስላችሁ። እድገትና ትራንስፎርሜሽኑ ያመጣው አዲስ ክስተት ነው – ቁርስ ምሳና ራት በአንድ ጊዜ የመመገብ ዘዴ። «ኑሮ በዘዴ፣ ጾም በኩዳዴ» ይባል ነበር። ይህ አባባል አሁን መኖ በዘዴ በሚል ተቀይሯል። መቼም ሁሉም ነገር በነበር እየቀረ ነው።
ጋዜጠኛ አቤል አለማየሁ በቅርቡ ባሳተመው “የአዲስ አበባ ጉዶች” የሚል መጽሃፉ ላይ ስለዚህች ታሪካዊ ምግብ ቤትም ትንሽ ብሏል። የምግብ ቤትዋ ባለቤት “ገሊላ ምግብ ቤት” የሚለው ጽሁፍ በከፊል አጥፍተውታል። አሁን ምግብ ቤት የሚለው ተነስቶ “ገሊላ” የሚለው ብቻ ነው የቀረው። ጉዳዩ በህግ እንዳያስጠይቃቸውም ይመስላል ጽሁፉ ላይ ነጭ ቀለም ነው የደፉበት። የምግብ ቤቷ ትራንስፎርሜሽን መሆኑ ነው። የዚህ ትራንስፎርሜሽን ትርጉም የገባቸውም ሆነ ያልገባቸው ተስተናጋጆች ወደ ገሊላ (ምግብ ቤት) ጎራ ማለታቸው አልቀረም። የዚህች ቤት አዲሶቹ ደንበኞች በአነስተኛና ጥቃቅን የተደራጁ ወጣቶች ናቸው። እዚያ ሲገቡ ሰልፍ ይጠብቃቸዋል። ይህች ስፍራ ስፋትዋ ለምግብ ቤት በቂ ነበር። ለቀን አልጋ አገልግሎት ግን ትንሽ ስለጠበበች ነው ሰልፍ ሊከሰት ያቻለው። ተራ የደረሳቸው በመጀመርያ ሜኑ ይቀርብላቸዋል። የቀድሞው የምግብ ሜኑ በወይዛዝርት ፎቶ ተቀይሯል።….
ይህ ዘርፍ አሁን ከኮብልስቶንም የበለጠ አዋጭ እየሆነ በመምጣቱ፤ ምግብ ቤቶች የአገልግሎት አይነታቸውንና የሜኑ ደብተራቸውን እየቀየሩት መሆናቸው እውነት ነው።
የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ወሬ መሰማት ከተጀመረ ትንሽ ዘገየ። ይህ አዋጅ ከተሰማ በኋላ የእርሻ፣ የኢንዱስትሪና የሃይል አቅርቦቶች በሙሉ በአስር እጥፍ ነው ያደጉት። እድገታቸው ታዲያ ወደላይ ሳይሆን እንደባህር ዛፍ ወደታች ነው። በእርግጥ የለውጥ ምልክቶች በሀገሪቱ እየታዩ ነው ከተባለ የዝሙት ኢንደስትሪው በደንብ ለመጠቀስ ይችላል። ይህ ዘርፍ በተለይ ከአረብ ሃገር የበርካታ ቱሪስቶች መስህብ ሆኗል። በዚያን ሰሞን አንድ በአዲስ አበባ የሚታተም ጋዜጣ ድንግልና በአስር ሺህ ብር እንደሚሸጥ አስነብቦን ነበር። አንዲት ደናግል ለዚህ ጸያፍ ነገር ስትዳረግ ድህነትን ብቻ አይደለም የምትሰናበተው። የማንነትዋ መግለጫ የሆነው የሞራል ጉዳይም አብሮ ይሄዳል።
የአገልግሎት ክፍያው የሚከናወነው በዶላር መሆኑ ደግሞ በዚህ ዘርፍ ላይ የግሽበት ችግር አይደርስበትም። ኢንደስትሪው ለሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ምንጭም ስለሆነ ይመስላል ከመንግስት በኩል እየተበረታታ የመጣው። የውጭ ምንዛሪ በማስገኘቱም «ልማታዊ» ተግባር ተብሏል። መንግስት ከዚህ ሴክተር ምን ያህል እንደሚጠቀም በውል ባይታወቅም አገልግሎት ሰጭዎቹ (ደላሎቹ) ግን ሃብታም እንደሆኑ ይነገራል።
ወደ ጎተራ አካባቢ በተሰራው የኮንዶሚንየም መንደር ደግሞ ሌላ ታሪክ አለ። ይህ ኮንዶ «ፌስቡክ» የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ለምን ፌስቡክ እንደተባለ ለማወቅ ብዙም ግዜ አይፈጅም። የቆነጃጅት ኮረዳዎች ሁሉ መሰብሰቢያ ነው። ትምህርት አቋርጠው ወይንም ከቤተሰብ ተኮራርፈው የተሰወሩ የቤት ልጆችን ለማግኘት ወላጆች ወደ ፖሊስ ጣብያ መሄድ አቁመዋል። ወደ ጎተራው «ፌስቡክ» ብቅ ካሉ የጠፉትን ሁሉ እዚያ ያገኙዋቸዋል። ባለሃብቶች እና ባለግዜዎች ወጣት ሴቶችን እየወሰዱ እዚያ እንደ እቃ ያስቀምጧቸዋል። ይህን የሚያጫውቱኝ ወዳጆቼ እየሳቁ ነበር የነገሩኝ። ነገሩ ያሳዝናል እንጂ አያስቅም!
በዚህ ልማታዊ «ቢዝነስ» ውስጥ ጨቅላዋ ማሪቱም ገብታበታለች። የማሪቱን ነገር ማንሳቱ ብቻ ሁኔታውን በደንብ ይገልጸዋል።
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11275/
No comments:
Post a Comment