FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Friday, March 7, 2014

ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ይሻላል! (ግንቦት7)

Ginbot 7 weekly editorial

የባህርዳር እና አካባቢው ሕዝብ ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ሺህ ጊዜ እንደሚሻል አካሉን ብቻ ሳይሆን ህሊናውንም ለትግራዩ ነፃ አውጪ ህወሓት ባርነት ላስገዛው “የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)” እያለ እራሱን ለሚጠራው ድርጅት መሪዎች ተናገረ።
ባርነት ክፉ ነው። በባርነት ላይ የጭንቅላት ባዶነት ሲታከልበት ደግሞ አለምነው መኮንንን የመሰሉ የብአዴን መሪዎችን ይፈጥራል። የብአዴን መሪዎች ለጌታቸው ህወሓት ያላቸውን ታማኝነት ለማሳየት ራሳቸውን ማዋረዳቸው ሳያንስ እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ በጅምላ መስደባቸው ብአዴን እንደ ድርጅት የሚገኝበት የተዋረደ ደረጃ ያሳያል።
ህሊና ያለው ባርያ ዛሬ ነፃ ባይሆንም ወደፊት ነፃ የመውጣት ህልም አለው። ዛሬ በጉልበተኛ የባርያ አሳዳሪ ነፃነቱን ቢያጣም የህሊና ነፃነቱን ያላስደፈረ ባርያ ለነፃነት መታገሉ የማይቀር ነው። እንደ ብአዴን መሪዎች በታማኝ ባርያነቱ እየፈነጠዘ ያለ ባርያ ግን ነፃ ሰው የመሆን ህልሙንም ጭምር አጥቷል። እንዲህ ዓይነቱ ባርያ በአካልም፤ በመንፈስም ባሪያ ነው። ነፃ ሰው የመሆን እድል የለውም።
የአማራ ሕዝብ ብአዴንን የመሰለ አሳፋሪ ድርጅት በታሪኩ ገጥሞት አያውቅም። በፋሽስት ጣልያን ወረራ ጊዜ ለጠላት ያደሩ ባንዶች እንኳን ከዛሬዎቹ ብአዴኖች የተሻለ ክብር ነበራቸው። እነሱም ከዛሬዎቹም በተሻለ በጌቶቻቸው ጣሊያኖች ይሰሙ ነበር። በገዢዎቹ ለመወደድ የራሱን ሕዝብ የሚዘልፍ፣ የሚሰድብና የሚያዋርድ እንደ ብአዴን ያለ አዋራጅ ድርጅት በአማራ ምድር አልታየም።
ለዚህም ነው የባህርዳር እና አካባቢው ሕዝብ የብአዴንና የወያኔን አፈናዎችን በጣጥሶ የካቲት 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ቁጣውን በባዶ እግሩ አደባባይ በመውጣት የገለፀው። እግር ባዶ መሆኑ ጭንቅላት ባዶ የመሆኑ ያህል የሚያሳፍር አይደለም። ድህነት ወንጀል አይደለም። ነፃ አዕምሮና የሕዝብ ይሁንታ ያገኘ አስተዳደር ካለ ድህነትን ማሸነፍ ይቻላል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁመው የየካቲት 16 ቀን 2006 ዓ.ምን ሕዝባዊ ተቃውሞ ላደራጁና በተቃውሞውም ለተካፈሉ ሁሉ ያለውን አክብሮት ይገልፃል። ሕዝብ ብሶቱን የሚገልጽበት ሕዝባዊ ተቃውሞ ማደራጀትና መምራት መቻል ትልቅ ነገር ነው። ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ወደ ሕዝባዊ እምቢተኝነት የማደግ እድል አላቸው። ስለሆነም ግንቦት 7 ለባህርዳሩ ሕዝባዊ ተቃውሞ አደራጆችና ተሳታፉዎች “እንኳን ደስ ያላችሁ” በማለት የትግል አጋርነቱን መግለጽ ይሻል።
ግንቦት 7፣ ብአዴንን ከአባላቱ ለይቶ ማየት ይሻል። ከዚህም በተጨማሪ የብአዴንን ከፍተኛ አመራር ከሌላው ለይቶ ይመለከታል። ብአዴን ነፍሳቸውን ሳይቀር ለወያኔ በሸጡ ሰዎች የሚመራ፤ ነፃ የመውጣት ተስፋ የሌለው ራሱ ባርያ የሆነ ድርጅት ነው። አባላቱ ግን ከዚህ የተለዩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግንቦት 7 ያውቃል።
ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከዚህም በፊትም ደጋግሞ እንደገለጸው፤ በተለያዩ ጊዜያት ራሳቸውን ከወያኔ ባርነት ነፃ ለማውጣት በወሰዱት እርምጃ መስዋእትነት የከፈሉ የብአዴን አባላት መኖራቸውን ያውቃል። ግንቦት 7 ለእነዚህ ቆራጦች ትልቅ አክብሮት አለው። ዛሬም ህሊናቸውን ሙሉ በሙሉ ያልሸጡ የብአዴን አባላት አሉ ብሎ ያምናል። እነዚህ ወገኖቻችን ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት የግል፣ የወገንና የአገር ግዴታ አለባቸው ብሎ ያምናል።
ስለሆነም ዛሬም ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመን ጥሪዓችንን እናድሳለን።
የብአዴን አባላት ሆይ!!! የገዛ ራሳችሁን፣ የአማራን ሕዝብ እና ኢትዮጵያን እያዋረደ ካለው ብአዴን ተላቀቁ፤ አሊያም እውስጡ ሆናችሁ ድርጅቱን ግደሉት። የብአዴን መኖር ለወያኔ ካልሆነ በስተቀር ለማንም አይበጅም። ነፃነት ካለ ድህነትን በሥራ ማሸነፍ ይቻላል። ሰው ባርያ ሆኖ በሀብት ቢንበሸበሽ ምን ይፈይድለታል?
የብአዴን አባላት ሆይ!!! ወደ ህሊችሁ ተመለሱ። ራሳችሁንም የበደላችሁትን ሕዝብ የመካስ እድል አላችሁ ተጠቀሙበት። ይህንን ባታደርጉ ግን ለገዛ ራሳችሁ ፀፀት፤ ለልጆቻችሁ ሀፍረትን የምታወርሱ መሆኑን አትዘንጉ። ወያኔ መሸነፉ በጭራሽ የማይቀር መሆኑን እያወቃቸው በድህረ ጣልያን ወረራ ባንዶች ያገኙትን ምህረት እናገኛለን ብላችሁ አታስቡ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11307/

No comments:

Post a Comment