FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Monday, March 10, 2014

የሴት ነገር ሰማያዊ በቢጫ (ከቹቹቤ)

ከቹቹቤ

Ethiopian women protested in Addis Ababa
በተለምዶ የሴት ነገር ስንል የማሳነስ የማቀጨጭ ነው። የሴት ነገር ግን ሁሌም ቢሆን ከዚህ በላይ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን። የሴትን ነገር የሚያሳንሱ ቢኖሩ ጉልበት አምላኪዎች ብቻ ናቸው። አርግዛ አምጣና ወልዳ የምታሳድግን ሴት እንደ ቅርንጫፍ ከጎድን አጥንት ተሰራች የሚለው አሳናሽ አገላለጽም የሃይማኖት ድጋፍ ይዞ ስለተነሳ ሴቶች ራሳቸው ያነሱ ሆነው እስከሚሰማቸው ድረስ ተጽዕኖ አሳዳሪ መሆኑ እውነት ነው። ዘፍጥረት ወንዴና ሴቴ ሆነው የተፈጠሩትን ሌሎች ፍጡራን (እንስሳውን እጽዋቱን) ሁሉ እግዜር እንዴት እንደፈጠራቸው መናገሩን አላውቅም።  የኔዋ እናት ግን በምንም መልኩ ከኔው አባት አንሳ የጎድን ፍልቃቂው ልትሆን አይቻላትም። እንዴት ተደርጎ! እኔም በማህጸን ውስጥ ሞተር ሲገጠምልኝ፣ እግርና እጅ ሲሰራልኝ አፍንጫ ጆሮና አይኔ ዲዛይን ሲደረግ ስለቆየሁ እርሷ የኔ ፈጣሪ ናት ብዬ ነው እምዬ ስላት ደስ የምሰኘው። እርግጥ ነው የተወሰነ ጥሬ ሃብት ከአባቴ ወስዳለች። በዚያው አይን የኔ የምትሆነው ሴቲቱ ከጎድኔ አንዱ ተቀንሶ እንደተሰራች መቀበል ያዳግተኛል። በእንስሳቱ አለም የሴቶች ሚና እጅግ በጣም ጉልህ መሆኑን ለተመለከተ የሰው ፍጡር ሲሆኑ ሊያሳንስበት የሚችልበት ምንም ምክንያት የለውም። በተለይ በማህበራዊ እንስሳትም ሆነ ነብሳት ውስጥ ሴቲቱ አልፋና ኦሜጋ ናት። ቢሆንም…..ቢሆንም አውቄ በድፍረት ሳላውቅ በስህተት ላልኩት ንስሃ ልግባና ሰማያዊ በቢጫ እንዴት ደስ እንዳሰኘኝ ልናገር።
የቪድዮ ሽራፊ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች መወያያ መድረክ ድህረ ገጽ ላይ ተመለከትኩ። ቢጫ ቲሸርት የለበሱ ቆነጃጅትም አየሁ። ሁሉም ያምራሉ በስፖርት የዳበረ የሰውነት ቅርጽም አላቸው። ወበታቸውን እያደነቅሁ አሯሯጣቸውን ለመመልከት የማጫወቻውን ቁልፍ ስጫነው የበለጠ ማረኩኝ። ማማር ብቻ ቢሆን ምን ነበረበት። የጥንካሬያቸው፣ የጀግንነታቸው የድፍረታቸው መጠን የበለጠውን ማረከኝ። ወጣትነትን በነጭ ሽብር፣ በቀይ ሽብር ስመለከት ቆይቼ ሰማያዊን በቀደም ሳደንቅ ነበር። ቢጫን የሰጠሁት ተስፋ ቆርጠው ጠጅ ቤት ለቀሩት ነበር። አሁን ቢጫ ንቁና የሚያማምሩ ወጣት ሴቶች ነፃነት ነፃነት እያሉ ሲዘምሩበት ሰማሁ ተመለከትኩም። የወያኔን እስር ቤት ያጨናነቁትን እገሌ ከእገሌ ሳይመርጡ ከጋዜጠኛው፣ ከፖለቲከኛው፣ በሃይማኖት ምክንያት ከታጎሩት ሳይቀር ስም እየጠሩ ይፈቱ እያሉ አደባባዩን ሲሰነጥቁ ተመለከትኩ። አይ ሴት! አልኩ ሴት እኮ ይሁን ብላ ከገባች የማትናወጥ ሃይል ናት እያልኩ ኮራሁ። በወጣቶች ተስፋ ማድረግ ለካንስ ህይወት ያለመልማል፣ በዚያ ላይ በወጣት ሴቶች! የነገውን ትውልድ አምጠው በሚወልዱት እናቶች መኩራት በእርግጥም ተስፋን ያለመልማል አልኩ።
ወደ ቪድዮው አናት ላይ የተጻፈውን ሳነብ ደግሞ የሰማያዊ ፓርቲ አክቲቪስቶች መሆናቸውን አነበብኩ፤ ሰማያዊ ነገር ለምልክትም ወጣቶቹ ላይ አላየሁም ነበር። ነገሩ ሲገባኝ የበለጠ ደስ አለኝ። ሌላውን ማንበብ ስጀምር ግን መታሰራቸውን ተረድቼ አዘንኩ።  አሁን ጥያቄያቸው በሙሉ ቀላል ሆኖ ሳለ በዲሞክራሲ በታነጸች አገር ዘለዓለማዊ ክብርና ሞገስ ለታጋዮቻችን የሚል እንደ ሃይለማርያም ያለ መሪ ባለበት ሃገር እነዚህ ወጣቶች መታሰራቸው ምን ይባላል? አልኩ። ሰውየው ለወያኔና ለተቀጥላዎቻቸው ሳይሆን ለታጋዮች በሙሉ ብለው አስረግጠው ከተናገሩ ወዲህ ያለው መዘባረቅ አይሆንምን? አሰኘኝ። ደግሞ ኑሮ ልክ አጣ አማረርን አሉ እንጂ በመንግስታችን ላይ ተማረርን አላሉም። ነፃነት የሚጠላ የትግሬ ነፃ አውጪ ነው አንዴ የሚገዛን? የሚል ቁጣን የሚያስነሳ ስህተት በመንግስት አካላት በመወሰዱ ሴቶቹ ሁሉ ተጋግዘው እንደ ላይቤርያ አምባገነኖችን ሊፈነግሉ ይችላሉና ማሰሩ ትግል ማክረሩን ላሳስባቸው ፈቀድኩ። ቢሰሙ ኖሮ ከሕዝብ ይስማሙ አልነበር አትድከም የሚል የኔው ሃሳብ አቋረጠኝና ምክሬን ተውኩት።
በዚህ ቪድዮ ላያ ያየሁት ትንሽ ቢሆንም የተሰማኝ ግን ትልቅ ስሜት ነበር። አዎ የሃገራችን ሴቶች ሊደመጡ ይገባል! ሊከበሩ ይገባል! ሊሳተፉ ይገባል! ለዚህም ሁኔታዎችን ማመቻቸትና መፍቀድ ይገባል! ስክነት ብልህነትና እውቀት እንጂ ሩጫ ግርግርና ጡንቻ ብቻውን አገር አይለውጥም! የሚል መፈክር እያሰማሁ ከሁዋላቸው የምከተልም መሰለኝ።
ለሴት እህቶቻችን፣ እናቶቻችን፣ ሚስቶቻችንና ጓደኞቻችን በሙሉ ክብር ይሁን!
ነገን አምጠው ለሚወልዱ ቁርጠኛ ወጣቶች ሁሉ ክብር ይሁን!
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11349/

No comments:

Post a Comment