FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Thursday, May 16, 2013

5 ሰዓታትን በቀድሞ ማዕከላዊ ፖሊስ (ፍሬው አበበ በአዜብ መስፍን ክስ ከተመረመረ በኋላ የፃፈው)


የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ
Frew-alyu
ሰኞ ዕለት ከሰዓት በኋላ የተንቀሳቃሽ ስልኬ አንጫረረ፡፡ ሳነሳው ለስላሳ የሴት ድምጽ ፍሬው መሆኔን ማረጋገጫ ጠይቃኝ ስታበቃ የቀድሞ ማዕከላዊ ስለምፈለግ ደረስ ብዬ መምጣት እችል እንደሆን በፍጹም ትህትና ጠየቀቺኝ፡፡ በዕለቱ እንደማይመቸኝ፤ ዕረቡ ጠዋት ግን መገኘት እንደምችል ለደዋዬ ነግሬ ሰልኩን ዘጋሁ፡፡ እንግዲህ በፕሬስ ክስ ጉዳይ ለፖሊስ ቃሌን ስሰጥ ይኸኛው ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ ከቀድሞዎቹ ሶስት ክሶች አንዱ የስም ማጥፋት ሲሆኑ ሌላኛው በተሰረዘ ፈቃድ ሰርታችሃል፣ ሌላው ደግሞ ያለፈቃድ ጋዜጣ ታትማላችሁ የሚል ነበር፡፡ በአጋጣሚ ሁለቱ የቀድሞ ክሶች ከፖሊስ ያላለፉ ሲሆን አንደኛው ማለትም የኒቲ የኒቨርሲቲ ያሳትመው የነበረው “ኤቢቢአይ ዊክሊ” የተባለው ጋዜጣ በተሰረዘ ፈቃድ ሰርታችሃል በሚል ክስ ከተመሰረተባቸው 14 ያህል ሰራተኞች አንዱ ሆኜ አንድ ዓመት ተኩል ጊዜያት ያህል ፍ/ቤት ከተመላለስኩ በኋላ እኔን ጨምሮ 13 ተከሳሾችን ፍ/ቤቱ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ ይሰናበቱ ሲል ውሳኔ በመስጠቱ ነጻ መሆን ችያለሁ፡፡ (እዚህ ምድብ ውስጥ የአዲስ ነገሩ አብርሃም በጊዜው ይገኝበት ነበር)
ዛሬ ረቡዕ በጠዋት ማልጄ በመነሳት ቁርስ ቀማምሼ ወደተጠራሁበት የቀድሞ ማዕከላዊ ፖሊስ 3፡15 ሰዓት ላይ ደረስኩ፡፡ ማልጄ መነሳቴ ወድጄ አልነበረም፤የሄድኩበትን የምርመራ ጣጣ ከምሳ በፊት ባጠናቅቅ በሚል ጉጉት ነበር ፤አልሆነም እንጂ፡፡ መርማሪዬ ትሁት ሴት ፖሊስ መሆኑዋ ጭንቀቴን ለጊዜውም ቢሆን እንድረሳ ረድቶኛል፡፡ ያው የተለመደውን አሰልቺ ቅጽ መሙላት ግን የግድ ነበር፡፡ ሙሉ ስም፣አድራሻ፣የእናት ሙሉ ስም፣የአባት ሙሉ ስም፣የትውልድ ቦታ፣ የትውልድ ቦታ አድራሻ፣ብሔር፣የባለቤቴ ስም፣አድራሻ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ስም፣የት/ቤቱ አድራሻ፣የተማርኩበት ጊዜ፤የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ስም፣አድራሻ፣ የተማርኩበት ጊዜ፣ የከፍተኛ ትምህርት የተማርኩበት ዩኒቨርሲቲ ስም፣አድራሻ፣የተማርኩበት ጊዜ፣የቀድሞ መ/ቤት ስም፣የነበረኝ ኃላፊነት፣የነበረኝ ደመወዝ መጠን፣ የአሁን መ/ቤት ስም፣ያለኝ ኃላፊነት፣ያለኝ የደመወዝ መጠን፣ የጋብቻ ሁኔታ፣የልጆች ብዛት፣ዕድሜያቸው፣አጠቃላይ ክሱ እና በክሱ ላይ ያለኝ ምላሽ፣ የተጠረጠርኩበትን መፈጸም አለመፈጸሜን (የእምነት ክህደት ቃል) ወዘተ….እጅግ አድካሚ ዶሴ ተሞላና ጨረስኩ ስል አሻራና ፎቶግራፍ መነሳት የግድ ነው ተባልኩ፡፡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሰጥቻለሁ ብልም ሰሚ አልነበረም፡፡ እዚያም የእያንዳንዱ ጣት አሻራ(የግራ የቀኝ) ፣ ፎቶ ፊትፊት በግራና ቀኝ መነሳት ግድ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ግን በፕሬስ ተፈጸመ ተብሎ በአንድ ሰው በቀረበ አቤቱታ መነሻነት ገና ለገና ተጠርጣሪ ነው የተባለው ፕሬስ ዋናአዘጋጅ የመጀመሪያዋ ቀላል ፈተና መሆኑ ነው፡፡
ፖሊስ ቃል ከመስጠቴ በፊት ሁለት ጥያቄዎች እንዲመለሱልኝ ለመርማሪዬ ጥያቄ አቀረብኩኝ፡፡ አንዱ የተከሰስኩበት ጉዳይ እና ከሳሼ ማን እንደሆነ ነበር፡፡ የተከሰስኩበት ጉዳይ በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ከቤተመንግስት አለመውጣታቸውን ጠቅሰህ ጽፈሃል፣በዚህ ስም አጥፍተሃል የሚል ይዘት ያለው መሆኑ ተነገረኝ፡፡ ዜናው የተሰራው በአበሻ አቆጣጠር መስከረም 30 ቀን 2005 ዓ.ም ሲሆን በጠቅላው ወደስምንት ወር ገደማ ሆኖታል፡፡
Frew-alyu
የዜናው ይዘትም በአጭሩ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ከቤተመንግስት አለመውጣታቸውን በአንድ በኩል በሌላ በኩል በወቅቱ ከተሾሙ 19 ቀናት የሞላቸው ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መኖሪያ ቤታቸው ከሚገኝበት ሳር ቤት አካባቢ በየዕለቱ ትራፊክ እያዘጉ በመውጣትና በመግባት ላይ መሆናቸው፣ የአካባቢውን ህብረተሰብ የመንቀሳቀስ ነጻነት ላይ ችግር መፍጠሩን፣ለደህንነታቸውም ቢሆን አስጊ መሆኑን፣ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ቤተመንግስቱን እንዲለቁ በተደጋጋሚ ተጠይቀው ባልታወቀ ምክንያት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን የሚያትት ነበር፡፡ ዜናውን ስንሰራው በትልቁ ታሳቢ ያደረግነውና እንደጋዜጠኛ ሙያዊ ነጻነታችን ተወጥተኛል ብለን የምናስበው የጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስራቸውን ማከናወን በምንም መልኩ ተቀባይነት ያልነበረውና ደህንነታቸውንም በእጅጉ ለአደጋ ያጋለጠ የመሆኑ ጉዳይ ነበር፡፡ የዚህ ዜና መውጣት በአገር ውስጥና በውጪ መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ በመቆየቱ ወ/ሮ አዜብ በክብር ወደተዘጋጀላቸው ቦታ እንዲዛወሩ፣አቶ ኃ/ማርያምም ወደቤተመንግስት እንዲገቡ በማድረግ ረገድ ሁለቱንም ወገኖችን የጠቀመ ውጤት አስገኝቷል ብለን እናምናለን፡፡ በዚህ ዜና መሸለም እንጂ መጉላላትና ክስ ይቀርብብናል ብለን አስበንም አናውቅም፡፡
ሌላው መርማሪዬን የጠየኳት ጉዳይ ከሳሼ ማን ነው የሚል ነበር፡፡ ይህን ጥያቄ በቀጥታ ለመመለስ አልፈለገችም፡፡ምናልባትም አለቆችዋ እንዳትነግር አስጠንቅቀዋት ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ ግን እንደተከሳሽ ቃሌን ለመስጠት ቢያንስ ከሳሼ ማን እንደሆነ የማወቅ መብቴ ሳይከበርልኝ ቀርቷል፡፡ በድፍኑ “ከሳሽ ፖሊስም ሊሆን ይችላል” ተብዬአለሁ፡፡ በስም ማጥፋት ክስ ጉዳይ ግለሰብ ከሆነ ራሱ በሚያቀርበው አቤቱታ፣የመንግስት ሹመኛ ከሆነ በዓቃቤ ሕግ በኩል ክስ ሊቀርብ እንደሚችል ያለውን ድንጋጌ አንስቶ መከራከር እዚህ ቦታ ላይ ዋጋ አልነበረውም፡፡ ያም ሆነ ይህ ከሳሼን የማወቅ መብቴ ተከልክዬ እነሆ ቃሌን ለመስጠት በቃሁ፡፡
 በዚህ ሁኔታ ጠዋት 3፡15 ገደማ የቀድሞ ማዕካዊ የገባሁ የአምስት ሺ ብር ዋስ እስካቀርብ ድረስ የቁም አስረኛ ሆኜ ከቀኑ 8፡30 ሰዓት ገደማ ግቢውን ለቅቄ ወጥቻለሁ፡፡
ፍሬው አበበ
የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ

No comments:

Post a Comment