FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Tuesday, May 21, 2013

ከእነ መላኩ ፈንታ እስር በስተጀርባ


ሁለት የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከ12 ያላነሱ ነጋዴዎችና ባለ ሀብቶች በሙስና ተጠርጥረው ወደ ማረፊያ ቤት እንዲወርዱ መደረጋቸው አይዘነጋም፡፡
በሚኒስትር ደረጃ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የሆኑት አቶ መላኩ ፈንታና ምክትላቸው አቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የመደረጋቸው ዜና ይፋ ከሆነ በኋላ ከየአቅጣጫው የተለያዮ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው፡፡ከባለስልጣናቱ መታሰር በኋላ በፓርላማ በመገኘት የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽንን የአስር ወር ሪፓርት ያቀረቡት ኮሚሽነሩ አቶ አሊ ሱሌይማን ሰዎቹ መታሰር በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ትዕዛዝ ተፈጸመ ነው በማለት መናገራቸውን ኢቴቪ በዜና ዘገባው አስደምጧል፡፡
ለመሆኑ ጸረ ሙስና ኮሚሽን ለምን በአንድ መስሪያ ቤት ብቻ በማነጣጠር ሁለቱን ባለስልጣናት ዘብጥ እዲወርዱ አደረገ፣ሙስኛ በመስራትስ ከኢህአዴግ ሹመኞች ሊጠየቁ የሚገባቸው ሁለቱ ሰዎች ብቻ ናቸው(ምንም እንኳን ኮሚሽነሩ በፓርላማ ቀርበው ሌሎችም እንደሚጠየቁ የተናገሩ ቢሆንም)  ኮሚሽኑ ለምን ትልልቆቹን አሳዎች ሳያጠምድ ቀረ; የእነዚህን ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት ሁለት ጋዜጠኞችንና አንድ ወጣት ፖለቲከኛን አነጋግረናል፡፡
ወጣቱ ፖለቲከኛ ሀብታሙ አያሌው የአንድነት ለዴሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት አባል ሲሆን በወቅታዊው ጉዳይ በሰጠው አስተያየት‹‹ኢህአዴግ የፖለቲካ ፕሮግራሙም ሆነ አሁን እየወሰዳቸው የሚገኙ አንዳንድ ድርጊቶች  ሙስናን ቆርጦ ለመዋጋት ያለውን ተነሳሽነት ያሳዩለታል ብዬ አላምንም፡፡ሙስናን መዋጋት ባህሪውም አይደለም፡፡ከሙስና የጸዳ አካል በድርጅቱ ውስጥ ይገኛል ማለት በጣም ያስቸግራል፡፡የሰሞኑ ድርጊት በውስጥ ፖለቲካ እየተፈጠረ ያለውን ነገር ከማሳየት የዘለለ ትርጉም ይኖረዋል ብዬ አላምንም፡፡እንዳንድ ባለስልጣናት አገር ጥለው እንዲሄዱ ሌሎቹ ደግሞ እንዲታሰሩ አድርጓል ይህ የውስጥ ፖለቲካ ነጸብራቅ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ››
በሚኒስትር ደረጃ የሚገኙትን የአቶ መላኩ ፈንታ እስርን በመመልከት ጸረ ሙስና አቅሙን እያዳበረ መጥቷል በማለት መናገር እንችላለን የሚል ጥያቄ ከፍኖተ ነጻነት የቀረበለት ሀብታሙ‹‹ለእኔ አቶ መላኩ ከትልልቆቹ አሳዎች የሚመደቡ አይደሉም፡፡እንደሚታወቀው ሰውዬው በአብዛኛው የሚታወቁት ሞያዊ በሆነ ስራ እንጂ ወደ ፖለቲካው ገፍተው በመምጣታቸው አይደለም፡፡በቅርቡም እርሳቸው የሚመሩት ድርጅት በአፈጻጸም ረገድ ከመንግስት መስሪያ ቤቶች የተሻለ ነጥብ ማስመዝገቡ አይዘነጋም፡፡በእውነትም መስሪያ ቤቱ በለውጥ ጎዳና ላይ እንደነበር መናገር ይቻላል፡፡ይህ ማለት ግን በአቶ መላኩ የተሰራ ሙስና አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ነገር ግን በአፈጻጸም ረገድ የመጀመሪያውን ደረጃ ካገኘው ድርጅት የሙስናን ማጣራት ማድረግ ተገቢ ነው; ለሚለው ጥያቄ ኢህአዴግ ምላሽ ያለው አይመስለኝም››ብሏል፡፡
የፍትህና የልዕልና ጋዜጦች ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ኃይለመስቀል በሸዋምየለህ ‹‹ክርክሩ ሰዎቹ ሙስናውን ሰርተዋል ወይም አልሰሩም አይደለም፡፡ትልቁ ነገር መሆን ያለበት ሌሎቹስ ንጹህ ናቸውን የሚለው ነው፡፡ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው ምላሽ ምን እየተካሄደ ነው የሚለውን  ለማወቅ ይረዳናል፡፡ባህርዳር ላይ ተካሂዶ በነበረው ዘጠነኛው የኢህአዴግ ጉባዔ አቶ መላኩ ፈንታ ሁለት መቶ የሚደርሱ ትግርኛ ተናጋሪ የሆኑ የኢኮኖሚ ልሂቃን ግብር በመሰብሰቡ ረገድ አላሰራ እንዳሏቸው ተናግረው ነበር፡፡በዚህ ሁኔታም መላኩ በአመትና በመንፈቅ ይገኛል በማለት ይተብቀው የነበረ ግብር ወርዶበታል፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ህወሃት በሚታይና በማይታይ እጁ የራሱን ደጋፊዎች የኢኮኖሚ አቅም እያጎለበተ ነው ማለት ነው፡፡መላኩ በጉባዔው የብአዴን አለቆቹን እነ በረከትን ሳያስፈቅድ ሪፖርቱን ያቀርባል የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ ያነሳው ነጥብ ለህወሃት ከፍተኛ ቀውስ ሊፈጥር የሚችል በመሆኑ ለእስሩ የወዲያውኑ ምክንያት እንደሆነ ይሰማኛል››ብሏል፡፡
ለኃይለ መስቀል ገብረዋህድ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበው ያደረጉት ንግግር አስቂኝ ነገር ሆኖበታል ምክንያቱን ሲያብራራም‹‹አስቂኙ ነገር የገብረዋህድ ወይም የባለቤቱ መታሰር አይደለም፡፡ወዴት እየሄድን ነው በማለት መናገራቸው አስቂኝ ነው፡፡››አቶ መላኩ ሁለት መቶ የሚደርሱት ነጋዴዎች ባደረሱባቸው ጫና ለእስር ተዳርገዋል የሚለው መከራከሪያ ለምን ከመታሰራቸው ቀደም ብሎ ህዝብ እንዲያውቀው አልተደረገም የሚል ጥያቄ የቀረበለት ኃይለ መስቀል‹‹አቶ መላኩ በጉባዔው እንዲህ አይነት ሪፖርት ስለ ማቅረባቸው መረጃ አለ፡፡ይህንን ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት አንድ የተማመኑበት ሃይል እንዳነበር ይሰማኛል በስተመጨረሻ ግን ይህ ሃይል ሳይከዳቸው አልቀረም፡፡መላኩ የሚተማመንበት አንድ ነገር ሳይኖር በአደባባይ ይቅርና ኮሪደር ላይ እንኳን ሊናገረው አይደፍርም፡፡ስለዚህ በእርግጠኝነት የብአዴን ዋነኛ ሰዎች መላኩን መስዋዕት እንዳደረጉት መመልከት
እንችላለን›› ብሏል፡፡
በቅርቡ የኢህአዴግ ፍጻሜ የተሰኘን መጽሀፍ በማሳተም ለንባብ አብቅቷል ጋዜጠኛ ሰለሞን ስዮም፡፡ሰለሞን ኢህአዴግ በሙስና የተፈጠረ ሙስና እንደ ጋንግሪን ሊቆርጠው የደረሰ ድርጅት መሆኑን በማውሳት‹‹የሰዎቹ እስራት ምክንያት ይህ ነው በማለት መናገር ባይቻልም የህወሃት መነሻ በራሱ ከዝርፊያ ጋር የተቆራኘ መሆኑን አክሱም ውስጥ የሚገኝን ባንክ ገጠመኝ ማስታወስ ብቻ ይበቃል፡፡በ1978 ደግሞ ማሊሌት ሲመሰረት መለስ ዜናዊና አረጋዊ በርሄ ይከራከሩ ነበር፡፡ በወቅቱ መለስ እየጎመራ የመጣ ወጣት ነበር፡፡ መለስ አረጋዊን በክርክር መርታት እንደማይችል ሲረዳ ‹‹አረጋዊ ጋንግሪን ነው ቶሎ ቆርጠን ካላወጣነው ድርጅቱን ይበክላል›› በማለት እንዲባረር አደረገው፡፡ ህወሃት አረጋዊን በማባረር ጋንግሪኑን ቆርጦ አውጥቶ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሙስናውን የተወሰኑ ባለስልጣናትን በማሰር ብቻ ያጠፋዋል የሚልእምነት የለኝም፡፡ምክንያቱም ሙስናው እስከ አናቱ ድረስ ውጦታል፡፡ሌላው በከፍተኛ ደረጃ ሙስና ያልሰራ የትኛው ባለስልጣን ነው ብለህ ብትፈልግ ነጻ ሰው ማግኘት ስለመቻልህ እጠራጠራለሁ ከተማው የሚያወራውም ይህንኑ ነው፡፡ መለስ የ1993 ክፍፍል ይፋ ከመሆኑ በፊት ባቀረበው የቦናፓርቲዝም ጽሁፉ ሙስና በቤተሰባዊነት ውስጥ ያለውን ትስስር ጠቅሶ ነበር፡፡በዚህ መነሻነትም በኋላ ላይ ስዬና ወንድሞቹ በሙስና ለመጠየቅ በቅተዋል፡፡እንዳለመታደል ሆኖ ግን መለስ በቦናፓርቲዝም ሌሎቹን ለማጥቂያነት ተጠቀመበት እንጂ የራሱን ቤተሰብ ሊመለከትበት አልፈቀደም፡፡አሁን እያንዳንዱን ሰው ከሴት የኢህአዴግ አመራሮች መካከል ዋነኛዋ ሙሰኛ ማንናት በማለት ብትጠይቅ ብዞዎቹ የሚጠቅሱልህ የመለስን የቀድሞ ባለቤት ናት፡፡
ሰለሞን መረሳት የሌለበት በማለት የሚጠቁመው ነጥብ‹‹ኢህአዴግ አባላቱን የሚያበዛበትን መንገድ እንድንመረምር ነው፡፡‹‹በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በድርጅቱ ርዕዮተ አለም አምነው የተመዘገቡ አይደሉም፡፡ምክንያቱም ድርጅቱ ወጥ የሆነ የፖለቲካ ፍልስፍና የለውም፡፡የሚበዙትን ሰዎች ወደ ኢህአዴግነት እያመጣቸው የሚገኘው ነገር ጥቅም ብቻ ነው፡፡ይህ ደግሞ ሙስና ነው፡፡››በማለት አስተያየቱን ቋጭቷል፡፡

No comments:

Post a Comment