FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Wednesday, May 22, 2013

“ከሁሉም በላይ የሚያስቆጨኝ ልጁን አቅፎ በአባትነት ፍቅር እንዳይደባብሰው እንኳ አለመፍቀዱ ነው” (የውብሸት ባለቤት ወይዘሮ ብርሃኔ ተስፋዬ)


ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በቅርቡ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ወደ ዝዋይ እንዲዘዋወር ተደርጓል፡፡ የቤቱ ምሰሶ የነበረው ጋዜጠኛው ማረሚያ ቤት በመወርወሩ ምክንያት ቤተሰቡ ችግር ላይ ይገኛል፡፡ ወደ ዝዋይ እንዲዘዋወር መደረጉ በራሱ ደግሞ የቤተሰቡን ችግር የበለጠ ያከፋዋል፡፡ ዳዊት ሰለሞን የውብሸትን ባለቤት ወይዘሮ ብርሃኔ ተስፋዬን በማግኘት በጉዳዩ ዙሪያ አነጋግሯል፡፡  
ላይፍ ፡- እስኪ ቃለ ምልልሳችንን ራስሽን በማስተዋወቅ ጀምሪ
ላይፍ ፡- ስሜ ብርሃኔ ተስፋዬ ይባላል፡፡ የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ባለቤት ነኝ፡፡
ላይፍ ፡- ከውብሸት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ስተገናኘችሁበት አጋጣሚ እናውራ፡፡ እንዴት ነበር የተገናኛችሁት ?
ብርሃኔ ፡- መገናኘት ( ትንሽ ዝምታ) የጀመርነው ከረዥም አመታት በፊት ነው፡፡ በአጭሩ አብረን ነው ያደግነው ማለት እችላለሁ፡፡ ከተጋባን ግን አምስት አመት ሆኖናል፡፡
ላይፍ ፡- ጋዜጠኛውን  ውብሸትን ይጽፋቸው በነበሩ ጽሁፎች እናውቀዋለን፡፡ ነገር ግን እንደ አባወራ ለቤቱና ለትዳሩ ምን አይነት ሰው ነበር ? 
ብርሃኔ ፡- ባል የሚለው ነገር ለእኔ ብዙም ግልጽ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቃሉ ይገልፀዋል ብዬ አላምንም፡፡ ለእኔ ውብሸት ባሌ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ነገሬ ነው ማለት እችላለሁ፡፡በዛ ላይ ደግሞ የልጄ ሁሉም ነገሩ ነው፡፡ እንደ እናትና አባት በመሆን ያሳድገው ነበር፡፡ ከአባት በላይ ነው፡፡ እኔ ለልጁ እናት ብሆንም እንደ ውብሸት ግን እሆንለታለሁ ብዬ አላምንም፡፡
ላይፍ ፡- ውብሸት ከታሰረ በኋላ ቤቱን የማስተዳደር ኃላፊነት ሙሉ ለሙሉ በአንቺ ላይ ወድቋል፡፡ እንዴት ነው ህጻን ልጅ ይዘሽ ህይወትን የተጋፈጥሽው ?
ብርሃኔ ፡- ውብሸት ከመታሰሩ በፊት ፍትህ ( የልጁ ስም ነው ) ትምህርት ቤት አልገባም ነበር፡፡ ትምህርት ቤት የገባው ከአባቱ መታሰር በኋላ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ የሶስተኛ አመት የኮሌጅ ተማሪ ነኝ፡፡ ትምህርቱን የጀመርኩት ውብሸት እያለ ነው፡፡ ፍትህ ትምህርት የጀመረው አምና ነው፡፡ ዘንድሮ መደበኛ ትምህርት ጀምሯል፡፡ የአባቱ አለመኖር ከፍተኛ ተጽእኖ በእኔ ላይ ፈጥሯል፡፡ የምንኖረው ቤት ተከራይተን ነው፡፡ በቀን ፕሮግራም የምማር በመሆኑ ስራ ወይም ሌላ ገቢ የለኝም፡፡ ሙሉ ለሙሉ ቤቱን ያስተዳድር የነበረው ውብሸት ነበር፡፡ ይህንን ማጣት የቤተሰቡን አባላት በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳል፡፡ ውብሸት በመታሰሩም እርሱን ለመጠየቅ ትራንስፖርት መጠቀም ግድ ይላል፡፡ በአጠቃላይ ለእኛ ነገሩ በጣም ፈታኝ ነው፡፡
ላይፍ ፡- ውብሸት በታሰረበት ወቅት ይሰራበት የነበረው ጋዜጣ ደሞዙን በፍጥነት ማቋረጡ ይነገራል፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው ? የጋዜጣው ባልደረቦች በዚህ በኩል ያደረጉት ነገርስ ምንድን ነው ?
ብርሃኔ ፡- ውብሸት ከታሰረ በኋላ ጋዜጣውም ብዙ መቀጠል አልቻለም፡፡ ቢሮ በመቀያየር ብዙ ወጪ በማውጣታቸውም ለእኛ የተለየ ነገር እንዳያደርጉ እንቅፋት ሳይፈጥርባቸው አልቀረም፡፡
ላይፍ ፡- ውብሸት ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በቅርቡ ወደ ዝዋይ እንዲዘዋወር ተደርጓል፡፡ የሚገኝበት ማረሚያ ቤት እየራቀ መምጣቱም ለተጨማሪ የትራንስፖርት ወጪ የሚዳርግ ይሆናል፡፡ እናስ ምንድን ነው ያቀድሽው ? 
ብርሃኔ ፡- ቂሊንጦ እያለ ለትራንስፖርት የሚከፈል በማጣቴ የተነሳ አይኑን ለማየት ልጁን በመያዝ የምሄደው በሳምንት አንድ ቀን ነበር፡፡ ወደ ዝዋይ እንደሄደም የሰማሁት ከሰዎች ነው፡፡
ላይፍ ፡- ወደ ዝዋይ እንደሚሄድ ቀደም ብላሽ አላወቅሽም ነበር ? ማረሚያ ቤቱስ ለታራሚዎቹ ቤተሰቦች መረጃ አይሰጥም ?
ብርሃኔ ፡- እሁድ እለት ሰዎች ደውለው ‹‹ውብሸት ዝዋይ ተወስጃለሁ›› ብሎሻል በማለት ነገሩኝ፡፡ በቃ ምንም አማራጭ ስላልነበረኝ ወደተባለው ቦታ ሄድኩኝ፡፡ የዝዋይ መንገድ በጣም አድካሚ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ 160 ኪሎ ሜትር ይርቃል፡፡ የቂሊንጦን ሶስት አራት እጥፍ ይሆናል፡፡ ወጪውም የዚያኑ ያህል ነው፡፡ ጠዋት 11፡00 ወጥቼ እቤቴ የገባሁት ምሽት ነው፡፡ በራሱ እዚያ ድረስ መሄድ ትልቅ መከራ ነው፡፡ ዝዋይ ድረስ የአራት አመት ህጻን ይዞ መመላለስ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆን ያልደረሰበት ያውቀዋል ለማለት እቸገራለሁ፡፡ የቂሊንጦ መንገድ በራሱ እንኳን ለህጻን ይቅርና ለትልቅ ሰው በጣም የሚያሰለች ነበር፡፡ ፍትህ አንደርስም ወይ እያለ እያለቀሰ ነበር የደረሰው፡፡
ላይፍ ፡- ፍትህ አባቱን ለመጠየቅ ወደ ማረሚያ ቤት እንደምትሄጂ ሲያውቅ ምን ይላል ?
ብርሃኔ ፡- አርብ ደርሶ ቅዳሜ ትምህርት እንደሚዘጋ ሲያውቅ ሁልጊዜም አባቢ ጋር ውሰጂኝ እያለ ያስጨንቀኛል፡፡ መንገዱ ሩቅ ነው ብለው ሊሰማኝ አይችልም፡፡ ያለኝ አማራጭ መውሰድ ብቻ ስለነበረ በመንገዱ ርቀት እየተማረረና እያለቀስም ቢሆን አድርሼው መጣሁ፡፡
ላይፍ ፡- ውብሸት በአሁኑ ሰአት የሚገኝበት የጤንነትና የስነ ልቦና ሁኔታ ምን ይመስላል ?
ብርሃኔ ፡- ቂሊንጦ እያለ የማረሚያ ቤቱን መጻኅፍት እየተጠቀመ ያነብ ነበር፡፡ ትምህርታቸውን በተለያዩ ምክንያቶች ያቋረጡ ታራሚዎችንም ያስተምር ነበር፡፡ ጊዜውን በስራ ያሳልፍ ስለነበር ጭንቀት አልነበረበትም፡፡ አሁን ግን ሁሉ ነገር ለእርሱ አዲስ ነው፡፡ ያለውን ሁኔታ እስኪላመድ ድረስም መቸገሩ አይቀርም፡፡ እንደነገርኩህ እኔ ተማሪ ነኝ፡፡ ልጁም የተሻለና ጥሩ ትምህርት ቤት መማር አለበት፡፡ እነዚህ ነገሮች ያስጨንቁታል፡፡
ላይፍ ፡- ፍትህን ውብሸት ጋር ስትወስጂው አባቴ ለምን እኛ ጋር አይመጣም በማለት አይጠይቅሽም ? 
ብርሃኔ ፡- ፍትህ ውብሸት እስር ቤት ስለመሆኑ አያውቅም፡፡ አባቴ ትምህርት ቤት ነው ብሎ ነው የሚያምነው፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሁለታችንም ታሰረ የሚለውን ነገር እንዳይሰማ ትልቅ ጥንቃቄ አድርገናል፡፡ ውብሸትም ትምህርቴን ስጨርስ እመጣለሁ ይለዋል፡፡ ህጻኑ የሚገኝበት የዕድሜ ክልልም ስለ እስር ቤት ለማወቅ የሚያስችለው አይደለም፡፡ አሁን የእኛ ስጋት የውብሸት ራቅ ያለ ቦታ መታሰር እንደነገርኩህ ከትራንስፖርት ችግር የተነሳ በየሳምንቱ በመሄድ ልጠይቀው አልችልም፡፡ በወር አንድ ጊዜም ማየት ከቻልኩ ትልቅ ነገር ነው፡፡ አራትና ሶስት ሳምንት ፍትህ አባቱን ማየት ካልቻለ ምን እንደምለው አላውቅም፡፡ ዝዋይ ወባ አለ፣ ልጁ በሚመላለስበት ወቅት ትንኝ ነክሳው በወባ ሊያዝ ይችላል የሚል ስጋትም ውብሸት እየተሰማው ይገኛል፡፡
ላይፍ ፡- ውብሸት የታሰረበት ማረሚያ ቤት እናንተ ከምትገኙበት አካባቢ ሩቅ መሆኑን በመጥቀስ በአቅራቢያው በሚገኝ ማረሚያ ቤት እንዲታሰር ጥያቄ አላቀረብሽም ?
ብርሃኔ ፡- በፍትህ ሚኒስትር በኩል ጥያቄዬን አቅርቢያለሁ፡፡ ሌላው ቢቀር የዚህ ህጻን አባቱን የማግኘት መብት ሊከበር ይገባዋል፡፡ ቤተሰቡ ካለበት ችግር አንጻር ውብሸት ቅርብ ቦታ እንዲሆንልን በቻልኩት መጠን እየተማጸንኩ እገኛለሁ፡፡
ላይፍ ፡- ውብሸት ፍትህን በማረሚያ ቤት ሲያገኘው አቅፎት እንዲስመውና የልጅነት ትንፋሹን እንዲያሸተው ይፈቀድለታል ?
ብርሃኔ ፡- በአጠያየቅ ደረጃ ከዝዋይ ይልቅ ቂሊንጦ የተሻለ ነበር፡፡ ቂሊንጦ እያለ ውብሸት ልጁን አቅፎ ወደ ውስጥ አስገብቶት እንዲያጫውተው ይፈቀድለታል፡፡በዝዋይ ግን እንዲህ አይነት ነገር አይፈቀድም፡፡ ባለፈው ይዤው ሄጄ ውብሸት ስፍሰፍ ብሎ ሊያቅፈው ሲል ፖሊሶቹ አይቻልም በማለት ከልክለውታል፡፡ ያለኝ አማራጭ ልጁን ማባባል በመሆኑ እንደምንም ብዬ ነገሩን እንዲረሳው አድርጌዋለሁ፡፡
ላይፍ ፡- ከአዲስ አበባ ዝዋይ ከደረስሽ በኋላ ከውበሸት ጋር ለመነጋገር የሚፈቀድልሽ ምን ያህል ደቂቃ ነው ?
ብርሃኔ፡- የሚበዛውን ሰዓት በመንገድ የምጨርሰው በመሆኑ ውብሸትን እንደ ልብ ለማዋራት የሚያስችለኝን ጊዜ አላገኝም፡፡ 5፡30 ከደረስኩ ለ30 ደቂቃ ያህል አውርቼው ስድስት ሰዓት ሲሆን እንድወጣ እደርጋለሁ፡፡ ከሁሉም በላይ የሚያስቆጨኝ ልጁን አቅፎ በአባትነት ፍቅር እንዳይደባብሰው እንኳ አለመፍቀዱ ነው፡፡  ህጻኑ አባቱን ለመሳም እንደናፈቀ በመካከላቸው በቆመው አጥር ምክንያት ምኞቱን ሳይፈጽም መመለሱን ማየት ትልቅ ህመም ነው፡፡
ላይፍ ፡- ሁለቱ የስዊዲን ጋዜጠኞች በተለቀቁ ሰሞን ውብሸትም ሊወጣ እንደሚችል በስፋት ይነገር ነበር፡፡ ነገር ግን እስካሁን ብዙዎች ተስፋ ያደረጉት ነገር እውን መሆን አልቻለም፡፡ ባለቤትሽ ያልተፈታበትን ምክንያት ለማወቅ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሰዎች አነጋግረሻል ?
ብርሃኔ ፡- ሁሉም ሰው ገምቶት እንደነበረው የስዊዲን ጋዜጠኞች ሲወጡ ሰዎች እየደወሉ እንኳን ደስ ያለሽ ይሉኝ ነበር፡፡ እኔም ከተፈቱት ጋዜጠኞች ተለይቶ ማረሚያ ቤት እንዲቆይ ይደረጋል የሚል እምነት አልነበረኝም፡፡ የጋዜጠኞቹን መፈታት የሰማሁት በሸገር ራዲዮ ነበር፡፡ ከአሁን አሁን የውብሸትን ስም ይጠሩታል በማለት ስጠብቅ ነበር፡፡ በዜግነት ቦታ ተሰጥቶን ቅድሚያ አግኝተን የተሻለ ነገር ሊደረግልን ሲገባ እንዲህ መደረጉ አስገርሞኛል፡፡ የስዊዲን ጋዜጠኞች በመፈታታቸው አላዘንኩም፡፡ ምክንያቱም በእነርሱ መፈታት ደስተኛ የሆነና ከጭንቀት የዳነ ቤተሰብ አለ፡፡ ፍትህ ሚኒስትር ሄጄ ስጠይቅ አጥጋቢና ትክክለኛ ምላሽ አላገኝም፡፡ አንዳንዴ ነገሩ ሚኒስትሩ ጋር ቀርቧል፣ ተመልክተውታል ይሉኛል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ገና ሊቀርብ ነው ይሉኛል፡፡ አንድ አይነት ምላሽ ባለመኖሩም የሚባለውን ነገር ለማመን ተቸግሪያለሁ፡፡
ላይፍ ፡- አሁን ተስፋ የምታደርጊው ነገር ምንድን ነው ? ጉዳዩ ቶሎ አልቆ ውብሸትን እቤት አገኘዋለሁ ትያለሽ ?
ብርሃኔ ፡- ብዙ ነገሮች ጠብቀሃቸው ከቦታቸው ሳታገኛቸው ስትቀር ተስፋ ለማድረግ ትቸገራለህ፡፡ ስለዚህ እኔ ተስፋ የማደርገው ነገር የለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሞቱ የሆነ የተንዛዛ ነገር እንደተፈጠረ ሰምቺያለሁ፡፡ ነገር ግን አሁን ተተኪው ቦታውን በመያዛቸው ነገሮች እንደተረጋጉ ይሰማኛል፡፡ ስለዚህ የሚያደርጉትን በትእግስት መጠበቅ ነው፡፡
ላይፍ ፡- ልጃችሁን ፍትህ በማለት የሰየመው ማን ነው ? ትርጉሙስ ምን ይሆን ? 
ብርሃኔ ፡- ፍትህ በማለት የሰየመው ውብሸት ነው፡፡ ፍትህ ምኞት ነው፡፡ የልጁ አንድ አመት በተከበረበት ወቅት ውብሸት ‹‹አንተና የአንተ ትውልድ አባላት ፍትህ በሰፈነባት አገር እንደትኖሩ መልካም ምኞታችን ነው ›› በማለት ተናግሮ ነበር፡፡ መቼም ጥሩ ነገር የማይመኝ የለም፡፡ ከዚህ አንጻር ውብሸት ዜጎቿ የማያለቅሱባት፣ መልካም ነገሮች የሚገኙባት አገር እንደትኖረን በመመኘት ልጁን ፍትህ በማለት ሰይሞታል፡፡
ላይፍ ፡- ይህንን መልካም ነገር ለአገሩ የተመኘ ጋዜጠኛ ታስሮ ነገር ግን ፍትህ ልጅ ሆኖ ስታገኚው ምንድን ነው የሚሰማሽ ?
ብርሃኔ ፡- ወብሸት ምኞቱን የገለፀው ለልጁ ትውልድ በሙሉ ነው፡፡ ፍትህ ልጅ ሆኖ አጠገቤ መገኘቱ ለእኔ በራሱ ትልቅ ፍትህን እንደማግኘት ነው፡፡ እስኪ አስበው ውብሸት ታስሮ ብቻዬን ብሆን ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር? ፍትህ አጠገቤ በመሆኑ ግን እፅናናለሁ፡፡
ላይፍ ፡- ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ በቅርቡ የዩኔስኮን አለም አቀፍ ሽልማት አግኝታለች፡፡ ውብሸት በርዕዮት መሸለም የተሰማው ምንድን ነው ?
ብርሃኔ ፡ - እጅግ በጣም ተደስቷል፡፡ የተሰማውን ደስታም ለርዕዮት ለመግለጽ ሰዎችን ልኳል፡፡ እውነቱን ለመናገር ሽልማቱ ‹‹ለካ አለም አልረሳንም›› የሚል ስሜት እንዲፈጠርበት አድርጎታል፡፡ ሽልማቱ የታሳሪዎቹን ሞራል በመገንባቱ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበርክት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ላይፍ ፡- የውብሸት ባለቤትና የልጁ እናት በመሆንሽ ምንድን ነው የሚሰማሽ ?
ብርሃኔ ፡- ይህንን የምለው ሁልጊዜም ነው፡፡ የውብሸት ባለቤት በመሆኔ እድለኛ ነኝ፡፡ ውብሸት እኔን ወደ ሙሉነት የቀየረኝ ሰው ነው፡፡ እርሱ ለእኔ አባቴና እናቴ ነው፡፡ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ስመጣ እርሱ ቀድሞኝ እቤት ከደረሰ ልጁን ይዞ እኔን ለመቀበል ወደ ውጪ ይወጣ ነበር፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁልጊዜም በእርሱ ደስተኛ እንድሆን አድርገውኛል፡፡
ላይፍ ፡- ውብሸት ከመታሰሩ በፊት ይጽፋቸው በነበሩ ጽሁፎች የተነሳ ሊታሰር ይችላል የሚል ስጋት ነበረሽ?
ብርሃኔ ፡- እኔ ብዙም ጠልቄ አላውቅም፡፡ ነገር ግን ጋዜጠኝነት በራሱ የሆነ አደጋ እንዳለው ይታወቀኝ ነበር፡፡ ይህም ቢሆን ግን አንድ ቀን እንኳን ስራውን እንዲያቆም ተጭኜው ወይም ተናግሬው አላውቅም፡፡ ምክንያቱም የሚሰራው የሚወደውን ነገር እንደሆነ አውቃለሁ፡፡
ላይፍ ፡-  ነገ ፍትህ አድጎ የአባቱን መንገድ በመከተል ጋዜጠኛ ቢወጣው ምክርሽ ምንድን ነው የሚሆነው ?
ብርሃኔ ፡- የተሻለ ነገር እንዲሰራ በመምከር እንዲበረታታ ከጎኑ እቆማለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment