FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Monday, May 13, 2013

! ….. ኢህኣዴግና ሙስና ………! በአብረሃ ደስታ


abcኢህኣዴግ የተገነባው በሙስና ነው። የፓርቲው ሰዎች የተሰባሰቡበት ነጥብ የፖለቲካ ዓላማ ሳይሆን እህል- ዉሃ ነው። ወደ ፓርቲው በመቀላቀላቸው እህል-ዉሃውን ካገኙት (የፓርቲው አባላት ያልሆኑ ካላገኙት) የሚያገኙትን ነገር በሙስና መሆኑ ነው። አዎ! “ሙስና” ሰዎች ወደ ፓርቲው የሚገቡበት መንገድ ያመቻቻል። በመጨረሻ ደግሞ ለፓርቲው ህልውና አደጋ ይሆናል። ኢህኣዴግ በሙስና (በጥቅም በመደለል) ብዙ … አባላት አፍርቷል። እነዚህ አባላት ለፓርቲው አደጋ እየፈጠሩ ነው። በዚህ መሰረት ገዢው ፓርቲ መስቀለኛ መንገድ ቆሟል። ፓርቲው በስልጣን መቆየት ይፈልጋል። በስልጣን ለመቆየት ግን ልማት ማምጣት ያስፈልጋል። ልማት ለማምጣት ሙስና ማስወገድ ወይ መቀነስ ግድ ይላል። ሙስና ከተቀነሰ አባላት ይቀነሳሉ (በሙስና የሚበላ ነገር ካላሳየሃቸው አባላት እንዲሆኑና ሁነው እንዲቆዩ በምን ታጠምዳቸዋለህ???)። አባላት ከተቀነሱ ፓርቲው ይዳከማል። በሙስና የተገነባ ድርጅት ረዥም ዕድሜ ሊኖረው አይችልም። ለዚህ ነው ኢህኣዴጎች በሙስና ጉዳይ አይተው እንዳላዩ የሚሆኑት። ስለዚህ ኢህኣዴግ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው። በኢህኣዴግ ብዙ የሙስና ተግባራት እንደሚከናወኑ ይታወቃል። እህል-ዉሃ ያሰባሰባቸው ግብዝ አባላት ገዢው ድርጅት ብዙ ዕድሜ ሊኖረው እንደማይችል ሲረዱ የመንግስት ሃብት ዘርፈው ለማምለጥ ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም። (በደርግ ግዜም ተመሳሳይ ነገር ተፈፅሞ ነበር)። በሌላ በኩል ደግሞ እርስበርሳቸው መግባባት ሲያቅታቸው አንዱ ሌላውን ለማሸነፍ (ወይ ለማባረር) አሸናፊውን ለተሸናፊው ማሳሰር ይችላል። (ድሮ በአብዮቱ ግዜ ‘ምስጢር እንዳያወጡ’ በሚል ሰበብ ይገደሉ ነበር)። ለማሳሰር ምክንያት ስለሚያስፈልግ በኢህኣዴጋዊ ስልት “ሙስና” ጥሩ መሳርያ ነች። ምክንያቱም በኢህኣዴግ መንግስት ሙስና ያልነካው ባለስልጣን አለ ለማለት ይከብዳል። የሆነ ሁኖ ኢህኣዴጎች (በሙስና ምክንያት ይሁን በሌላ) ጓዶቻቸውን ማሳሰር ጀምረዋል። ግን እነ መላኩ ፋንታ በሙስና ከታሰሩ እነ አስመላሽ ወልደስላሴስ በምንድነው የሚታሙ? ብቻ እርስበርሳቸው መወነጃጀል ከጀመሩ በፓርቲው ውስጥ ያለ ችግር ሊፈነዳ ተቃርቧል ማለት ነው። በሙስና ሰበብ ማሳሰር ከጀመሩ ሁሉም ሙስና የሰሩ ባለስልጣናት መታሰር አለባቸው ማለት ነው። ሁሉንም ከታሰሩ፤ አሳሪዎቹም ጭምር ይታሰራሉ (ምክንያቱም ኣሳሪዎቹም ከሙስና የፀዱ አይደሉም)። ሁሉም አባላት ከታሰሩ ኢህኣዴግ ታሰረ ማለት ነው። ኢህኣዴግ ከታሰረ እኛ ነፃ ወጣን ማለት ነው። ያኔ ከኢህኣዴጎች በምን እንደምንሻል እናሳያለን። ስለዚ በሙስና ምክንያት ማሰር መጀመራቸው መልካም ነው። ችግሩ ግን የሙስና ወንጀል አሳሪዎቹ ጋር ሲደርስ ያስቁሙታል። ሙሰኞቹ ይታሰራሉ፤ ሙስኞቹ ያስራሉ። ሙስኞቹ ሄደው ሙሰኞቹ ይመጣሉ። ለውጥ የለውም። ከ“ባለ ራእዩ መሪ” ሞት በኋላ በትግራይ ክልል ሙስና “ሕጋዊ ስራ” የሆነ ይመስላል፣ የተለመደ ተግባር ነው። ሙሰኞቹ የመንግስት ሃብት መዝብረው ሲያበቁ ሌላ ተጨማሪ ውድመትም ያደርሳሉ። መቀለ ውስጥ ነው። ከሦስት ዓመታት በፊት በአንድ የዓይን ሕክምና ክሊኒክ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ይደርሳል። በዛ ግዜ መንስኤው አልታወቀም። በኋላ ሲጣራ ግን እሳቱ የለኮሱት የክሊንኩ ሰራተኞች ሁነው ተገኙ። ለምን ቢባል፣ ሰዎቹ የክሊኒኩ ገንዘብ ዘርፈውታል። የኦዲቲንግ ግዜ ስለደረሰ የዘረፉትን ገንዘብ እንዳይታወቅ (ገንዘብ የተቀመጠበት ክፍል ማውደም) በእሳት ማጋየት ብቸኛው አማራጭ ሁኖ አገኙት። በቅርቡም በሑመራ ከተማ በተመሳሳይ ምክንያትና አደጋ አንድ ሆስፒታል ወድሟል። በዚሁ ወር ውስጥም በነበለት ከተማ አንድ ትምህርትቤት በእሳት ቃጠሎ መውደሙ ይታወቃል። ማን እንዳቃጠለው፣ በምን ምክንያት እንደተቃጠለ እስካሁን አይታወቅም። ምናልባት በሙስና ይሆን እንዴ? ግን መላው አካላቱ ሙስና የሆነ ድርጅት እንዴት ሙስና ሊዋጋ ይችላል? ለኢህኣዴግ ‘ሙስናን መዋጋት’ ማለት ኢህኣዴግ ራሱን መዋጋት ማለት ነው። ይሄ ደግሞ ራስ ማጥፋት ነው። እስቲ ኢህኣዴግ ራሱ በራሱ ሲያጠፋ እንይ!?

No comments:

Post a Comment