Written by አለማየሁ አንበሴ
ጠ/ሚ ኃ/ማርያም በአስረጂነት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ እንጠይቃለን ብለዋል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአማራ ተወላጆች ላይ በደረሰው መፈናቀል ተጐጂዎች ፍትህ እንዲያገኙ መኢአድና ሰማያዊ ፓርቲ ክስ ሊመሰርቱ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በአስረጂነት ፍ/ቤት እንደሚቀርቡ ተጠቁሟል፡፡ የመኢአድ ፕሬዚዳንት ኢ/ር ሃይሉ ሻውል እና አለማቀፍ የህግ ባለሙያው ዶ/ር ያዕቆብ ሃ/ማርያም ከትላንት በስቲያ በጋራ በሠጡት መግለጫ፤ መረጃዎች ከተሰባሰቡና ከተደራጁ በኋላ በፌደራሉ ፍ/ቤት ወይም በክልሉ ፍ/ቤት ሁለት ዓይነት ክሶች እንደሚመሰረቱ ተናግረዋል፡፡ ክሱ የሚመሠረተው በዋናነት የዜጐች ከቦታ ቦታ የመዘዋወርና የመኖር መብት የሚደነግገውን የህገመንግስቱን አንቀጽ መነሻ በማድረግ ሲሆን በወንጀል እና በፍትሃብሔር ተከፋፍሎ ይቀርባል ተብሏል፡፡
በወንጀል ክሱ ላይ በተለይ ከዘር ማጥፋት ጋር የተያያዙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደሚካተቱ የገለፁት ዶ/ር ያዕቆብ፤ ከተበዳዮች ከሚሰባሰቡት መረጃዎች በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ከዚህ ቀደም ፓርላማ ቀርበው በክልሉ ዜጐች መፈናቀላቸውንና ችግሩን የፈጠሩት ኪራይ ሰብሳቢዎች መሆኑን በይፋ በመግለፃቸው ሌላ ማስረጃ ሳያስፈልግ ራሳቸው ፍርድ ቤት ቀርበው አስረጂ ይሆናሉ ብለዋል - ዶ/ር ያዕቆብ ሃ/ማርያም፡፡ ወንጀሉ በሰው ዘር ላይ ከተፈፀሙ ከባድ ወንጀሎች ተርታ የሚመደብ መሆኑን ያመለከቱት የህግ ባለሙያው፤ በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ላይ ድርጊቱን የፈፀሙ እስከሞት ቅጣት ሊቀጡ የሚችሉበት ሁኔታ መቀመጡን ገልፀዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚቀርበው የፍትሃብሔር ክስም በዋናነት ለወደመው ንብረትና ለደረሰው ሰብአዊ ቀውስ ካሣ የሚያስገኝ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡
የክሱ አካሄድ በሃገሪቱ ያልተለመደ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ያዕቆብ፤ በአንድ ሰው ከሣሽነት ሌሎች ተመሳሳይ በደል የደረሰባቸው ወገኖች ፍትህ የሚያገኙበት አይነት ክስ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ክሱ ከሚመሠረትባቸው የመንግስት አካላት መካከል የፌዴራል ጉዳዮች ሃላፊዎች፣ የፖሊስ አባላት እንዲሁም የክልሉና የወረዳው ሃላፊዎች ዋናዎቹ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡ ክሱን መቼና እንዴት ይጀመር የሚለውን ገና ጉዳዩ እየመከርንበት ነው ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ፤ በመጀመሪያ የተበደሉ ሰዎችን ውክልና ማግኘት እንደሚጠበቅባቸውና ከዚያም መረጃዎችን አሰባስበው በሁለት የህግ ባለሙያዎች በመታገዝ ክሱን እንደሚመሰርቱ ተናግረዋል፡፡
ከክሱ ምን ትጠብቃላችሁ ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱም፤ ውጤቱ ምን ይሆናል የሚለው በሂደት የሚታይ ጉዳይ መሆኑን የተናገሩት ባለሙያው፤ ክሱ ተቀባይነት ካጣ ወደ አለማቀፍ ፍርድ ቤት እንደሚያመሩ ዓለምአቀፍ የህግ ባለሙያው ገልፀዋል፡፡ በአማራ ተወላጆች ላይ በደቡብ ክልል በቤንቺ ማጅ ጉራፋርዳ አካባቢ እየደረሰ ያለው መፈናቀልና የሰብአዊ መብት ጥሰት ዛሬም አለመቆሙን ያስታወሱት የመኢአድ ፕሬዚዳንት ኢ/ር ሃይሉ ሻውል በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ ዘረኝነት እየተስፋፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የዚህ ድርጊት ተባባሪ እንዳይሆንም ጥሪ አቅርበዋል - ኢንጂነሩ፡፡
No comments:
Post a Comment