FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Monday, May 13, 2013

ኢትዮጵያን ተቃዋሚዎችም ሆኑ መንግስት በጋራ ሲዘምሩለት የነበረው ጉዳይ እነሆ ደረሰ!



እድገት እና ለውጥ የተፈጥሮ ሂደት ናቸው። የሚመጣውን ለውጥ ተመልክቶ ከወዲሁ በቂ መሰናዶ ማድረግ ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ጉዳይ ነው። በ1983 ዓም የመንግስት ለውጥ ሲደረግEthiopian Revolution 2013, blue party ኢትዮጵያ ውስጥ ”በመሳርያ ትግል ብቻ ለውጥ መምጣት የሚቆምበት ጊዜ መሆን አለበት” የሚሉ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ለሀገራችን በጎ የሚመኙ ብዙ ባእዳንም በቻሉት መንገድ ስለ ዲሞክራሲ በቅንነት ሰብከዋል። ኢትዮጵያ ከሶሻሊስቱ ጎራ ተነጥላ የግል ሀብት እና የምዕራቡን አስተሳሰብ እንድታሰርፅ የሚጣጣሩ የመኖራቸውን ያህል ‘ኢትዮጵያ ያለፈ ማንነቷን እና ያላትን የማደግ ዕድል ተጠቅማ ወደተሻለ ደረጃ መድረስ ይገባታል’ ያሉ ጥቂት አይደሉም። በለውጡ የመጀመርያ ሰባት አመታት ውስጥ ከለዘብተኛ እስከ ፍፁም ተቃዋሚ የሆኑ የህትመት ውጤቶች ብቅ ብለዋል። ከለዘብተኛ የ ታዋቂው ጋዜጠኛ የሩህ መፅሄት ከፍፁም ተቃዋሚ እነ ጦብያ መፅሄት እና ጋዜጣን መጥቀስ ይቻላል። እዚህ ላይ ባለቤት የሌለበት ቤት ያገኙ የመሰሉት የወሲብ መፅሄቶችን ሳንዘነጋ ነው። እርግጥ እነኝህ የወሲብ መፅሄቶች ከእድር እስከ መምህራን በተደረገ ርብርብ እና ጩሀት ”መብታቸው ነው” እያለ ሲፈቅድላቸው የነበረው አካልም ጉዳዩን እንደገና እንዲመለከት አስገድዶታል።
ከላይ በተጠቀሱት የህትመት ውጤቶችም ሆነ በሌሎች በተለይ እስከ 1997 ዓም ድረስ ጥቂቱን ከተሜ በሀገሩ ውስጥ ምን እየተደረገ እንዳለ እና የአለም አቀፍ ገፅታችንንም ጭምር ጥሩ መረጃ ሆነው ነበር። ይህ እንግዲህ እንዲህ እንዳሁኑ ኢንተርኔት ሳይኖር መረጃ ለማግኘት ወረቀት ማገላበጥ የግድ የሚልበት ጊዜ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። በእነኚህ ዘመናት ሁሉ የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎችም ሆነ መንግስትም በጋራ የዘመሩለት ጉዳይ አንድ እና አንድ ነበር።
የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎችም ሆነ መንግስትም በጋራ የዘመሩለት ጉዳይ እነሆ ደረሰ
የመንግስት የመዝሙር ስንኞች
የመንግስት ስንኞች በገዢው ፓርቲ ህወሓት ሆነ ይመሩት በነበሩት በ አቶ መለስ ብዙ ጊዜ ተዜሟል። ስንኞቹን በምክርቤት ስብስባ፣ በጋዜጣዊ መግለጫዎች፣ በመንግስት ልሳን በሆኑት ራድዮ እና ቲቪ፣ የመንግስት ደጋፊ እና አድናቂዎች፣ መንግስትን በሚደጉሙ ምዕራባውያን አፈቀላጤዎች፣ ማክያቶ እየጠጡ ”ይች ሀገር የሚሻላት” ብለው ንግግር በሚጀምሩ ከዩንቨርስቲ በወጡ ምሁራን፣ ውዘተ ተዘምሯል። የመዝሙሩ ስንኞች
• ሰላማዊ ትግል አስፈላጊ ነው፣
• የትጥቅ ትግል የነፍጠኛ አስተሳሰብ ነው፣
• ሰላማዊ ትግል የሚቃወም ሃሳቡን በሌሎች ላይ ለመጫን የሚሻ ውስጡ አማባገነን አምባገነን የሚሸት ነው፣
• ታሪካችን የጦርነት ታሪክ ነው መንግስት ለመቀየር ሁል ጊዜ ጫካ መግባት አለብን እንዴ?
• ለምን በሰላማዊ መንገድ በምርጫ መንግስት ለመቀየር፣ የተበደለውን ሕዝብ ድምፅ ለመሆን አንጥርም?
• ጦርነት ናፋቂዎች ለኑሯቸው ማደላደያ ነው እንጂ ሰላማዊ ትግል ነው የሀገራችን እጣ ፋንታ፣
• ”ኢህአዲግ በሰላማዊ ትግል ያምናል ማንም ሃሳቡን በተቃውሞ ሰልፍም ሆነ በፈለገው መንገድ ይችላል” (የጎዳ ላይ ነውጥ ናፋቂዎች፣የብርቱካናማው አብዮት ናፋቂዎች የሚሉትን አባባሎች አሁን እርሱልኝ)፣ ውዘተ ተዘምረዋል።
የተቃዋሚ አካላት የመዝሙር ስንኞች
• ህገመንግስቱን አክብረን በሰላማዊ መንገድ ትግላችንን እናፋፍማለን፣
• ብቸኛ መንገድ የምንለው የሰላማዊ የትግል መስመር ነው፣
• የሰላማዊ ትግል ስንል ሕዝብ ይወስናል ማለታችን ነው።መንግስት ካልሰማው ግን ይህ የተራበ ሕዝብ መንግስትን ሊበላ ይችላል፣
• እኛ በትጥቅ ትግል ዘላቂ ሰላም፣ዲሞክራሲ እና እውነተኛ የህዝቡን ችግር የሚፈታ መንግስት ይመጣል ብለን አናስብም፣
• ለሰላማዊ ትግል ሁሉም ሕዝብ እኩል ድምፁን ማሰማት አለበት፣ ወዘተ
ሜዳውም ይሄው ፈረሱም ይሄው -የሰማያዊ ፓርቲ የሰላማዊ የትግል መድረክ ያማይደገፍበት ምን ምክንያት አለ?
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በመርህ ደረጃም ቢሆን መንግስትእና ተቃዋሚዎች(በሀገር ውስጥ ተመዝግበው ከሚንቀሳቀሱት) በጋራ የዘመሩለት ጉዳይ ቢኖር የሰላማዊ ትግልን ወርቃማ መንገድነት ነው። መንግስትም ጥይት አታጩሁብኝ እንጂ ችግር የለም ብሏል( ስለተግባራዊነቱ እንዳትጠይቁኝ)። ሰላማዊ ትግል ሲባል በሰላማዊ መንገድ ካለምንም ሁከት ተቃውሞን በተለያየ መንገድ መግለፅ ነው። ይሄውም በሰላማዊ ሰልፍ፣በረሃብ አድማ፣ ተቃውሞን በሚያሳዩ ልዩ ልዩ መንገዶች ለምሳሌ ጥቁር በመልበስ፣ መሬት በመቀመጥ፣ ከቤት ባለመውጣት፣ ወዘተ ይገለፃል።
የሰማያዊ ፓርቲ የሰላማዊ የትግል መስመር ተከትሎ የተቃውሞ ጥሪ አስተላልፏል።በጥሪው መሰረት የአፍሪካ ህብረት ምስረታን 50ኛ አመት በአልምክንያት በማደረግ ለሚመጡት አለም አቀፍ ማህበረሰብም ሆነ የሰላማዊ ትግልን አስፈላጊነት ከ 20 አመት በላይ ለሰበከን መንግስት የህዝቡን ድምፅ ለማሰማት
1ኛ/ ከግንቦት 15 እስከ 17/ 2005 ዓም ህዝቡ ጥቁር በመልበስ እና
2ኛ/ ግንቦት 17/2005 ዓም ህዝቡ ሰላማዊ የተቃውሞ ድምፁን በአፍሪካ ህብረት ፊት ለፊት እንዲያሰማ ጥሪ አቅርቧል።
የሰላማዊ ትግል አንዱ ተመራጭነት ንብረት ሳይወድም፣ የሰው ሕይወት ሳይቀጠፍ በሰላም እና በሰለጠነ መንገድ ተደማምጦ ሃሳብን መግለፅ ሃሳብን ያዳመጠው መንግስት ደግሞ ችግሩን ከስሩ አይቶ እራሱን እንዲያርም እና ሃገሩን የእውነት ሀገር ማድረግ ይጠበቅበታል። ሃያ አንድ አመት የተዘመረለት የሰላማዊ ትግል አፍጥጦ መጣ። የዘመሩቱ የዘመሩትን ያህል ናቸው? የሚባልበት ጊዜ ነው። ሰማያዊ ፓርቲ እርግጥ ነው ከተመሰረተ ገና 17 ወራትን ነው ያስቆጠረው። ላለፉት 21 አመታት አልዘመረም። ነገር ግን የሰላማዊ ትግልን አስፈላጊነት የነገሩን ከረም ያሉት ተቃዋሚዎችም ሆኑ ”የሰላማዊ ትግል ነው የኢትዮጵያ ዕጣ” ያለን መንግስት ”ሜዳውም ይሄው ፈረሱም ይሄው” ማለት የሚቻልበት ጊዜ ይመስላል። ይህ ማለት ሌሎች ተቃዋሚዎችም ከዝምታ ይልቅ አብረው ለዘመሩለት ሰላማዊ ትግል ለመቆም፣ መንግስትም በአንዳቸው ላይ ላይተኩስ፣ ላያስር እና ላያንገላታ ማለት ነው።
በውጭ የሚገኘው ማህበረሰብም ከማህበራዊ ድህረ ገፆች ጀምሮ እርቀት ሳይገድበው የጥያቄው አካልነቱን ልዩ ልዩ ስልቶች እየቀየሰ መደገፍ አለበት።ምናልባት መንግስት ላለፉት 21 አመታት የዘመረውን መዝሙር ከረሳው ”ሰላማዊ ትግል” ወደ ፋይል ክፍል የሚገባበት አጋጣሚ እንዳይሆን መስጋት ካለበት አሁንም በመጀመርያ መንግስት መሆን አለበት። ”የሰላማዊ ትግል ለኢትዮጵያ አይበጅም ወያኔ የሚገባው በለመደው ንግግር ብቻ ነው” የሚሉቱን ለጊዜው አቆይተን የሰላማዊ ትግል የዘመርንሎቱ ሁሉ አሁን የሰማያዊ ፓርቲን ጥሪ የምንገፋበት ምን አይነት ሞራል ይኖረን ይሆን?
አበቃሁ
ጌታቸው
ኦስሎ

No comments:

Post a Comment