FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Thursday, July 25, 2013

በኦሮሚያ 10 ተጠርጣሪ ሙሰኞች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ተመዝብሯል
owwce


  • ተጠርጣሪዎቹ ሽፈራው ጃርሶ የሚመሩት ቦርድ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ናቸው
ከሙስና ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ አሥር የኦሮሚያ ክልል ውኃ ሥራዎችና ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ባለፈው ሰኞ በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡
ኮሚሽኑ በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው ከእነዚህ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተጨማሪ፣  ሌሎች 15 የሥራ ኃላፊዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የፍርድ ቤት ማዘዣ አውጥቶ ፍለጋ መጀመሩን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ግዥና የመንግሥትን የፋይናንስ ሕግ ባልተከተለ መንገድ ኪራይ ፈጽመዋል በሚል ጥርጣሬ መሆኑን፣ የክልሉ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ ኮሚሽኑ ለአንድ ዓመት ባካሄደው ጥናታዊ ምርመራ በዚህ የሙስና ወንጀል መንግሥትን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እንዳሳጣው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የኮሚሽኑ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በቁጥጥር ሥር የዋሉት የክልሉ ውኃ ሥራዎችና ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢፋ በዳዳ፣ ምክትላቸው አቶ ጎዳና ዳባ፣ የፋይናንስ ቡድን መሪ አቶ ተሾመ አዱኛ፣ አቶ ተክሉ ተፈራ፣ የማኔጅመንት ኮሚቴ አባላት ወ/ሮ መስከረም ኤጀርሳ እና አቶ ግርማ ቂጣታ፣ የመጋዘን ኃላፊዋ ወ/ሮ ራሔል አሰፋና የክፍያ ሰነድ አዘጋጅዋ ወ/ሪት ሳምራዊት ግርማ፣ የጨረታ ኮሚቴ አባላት አቶ ዘለቀ ጎንፋና አቶ ዱላ ማሞ ናቸው፡፡
የኦሮሚያ ክልል ውኃ ሥራዎችና ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ከተመሠረተ ሁለት አሥርት ዓመታትን ያስቆጠረ የክልሉ ግዙፍ የልማት ድርጅት ነው፡፡
ኢንተርፕራይዙ በኦሮሚያ ክልልና በሌሎች ክልሎች የሚካሄዱ የመስኖ ግድቦችና የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መንገዶችንና ስታዲየሞችን ከመገንባቱም በላይ፣ በፌዴራል መንግሥት የሚመራውን ለደዴሳ ስኳር ፋብሪካ አገልግሎት የሚውል ግድብ በደዴሳ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡
ኢንተርፕራይዙ ሁለት ቢሊዮን ብር የተመዘገበና 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ባለቤት ነው፡፡ ኢንተርፕራይዙ የሚተዳደረው በሥራ አመራር ቦርድ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የሥራ አመራር ቦርዱን በመምራት ላይ የሚገኙት ቀደም ሲል የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር በኋላም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፋሰስ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት አቶ ሽፈራው ጃርሶ ናቸው፡፡
በጉዳዩ ላይ የክልሉን የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ታከለ እንኮሳ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ (ሪፖርተር)

No comments:

Post a Comment