ዳኛቸው ቢያድግልኝ
ሀዘኑ በተስፋ እንዲተካለት ከልብ የምመኝለት የወያኔ ቅጥረኞች ቁምስቅሉን ያሳዩትን ወጣት ቃለ ምልልስ ኢሳት ላይ እንድመለከት ስጋበዝ ስሜቴን ሰቅዞ የሚይዝ በእጅጉ የሚያስቆጣኝ ጉዳይ እንደነበር አልገመትኩም። ምክንያቱም መከራ ለምደናል፣ ሀዘን ከቤታችን ወጥቶ አያውቅም። ነውጠኞች፣ ባለጌዎች፣ ጎጠኞችና ክብረጠሎች ከእንስሳ ያነሰ ሆዳም ደመነብስ ይዘው ሀገር ማፍረሱን ከያዙ ስለቆዩ ምንም አዲስ ነገር የለም በማለቴ ነበር። ተሳስቻለሁ ተሥፋዬ ከሀዘን ይልቅ ብርታትን፣ ከውድቀትም በላይ መነሳትን ሲናገር ሞትን ፊት ለፊት እየተመለከተ መሆኑ በወጣቱ ትውልድ እጅግ እንድኮራ አድርጎኛል። በዚህ አጋጣሚ የሽንፈት ድባብ በማሸነፍ ተሥፋ እንዲተካልን የምንሻ ሁሉ የዚህን ወጣት ጤና በመታደግ የኛኑ የውስጣችንን የልብ ስብራት ልናክመው ይገባናል። በኢሳት ላይ እንደተጠቀሰው temetoesat@gmail.com ብትጽፉ ወይም በ +447424582713 ሥልክ ብትደውሉና መርዳት ብትችሉ በሰጣችሁት ልክ ከፈጣሪያችሁ ትቀበሉ ዘንድ እምነቴ ነው። ይህንን ቃለ ምልልስ ያልተመለከታችሁ ኢሳትን በዚህ አድራሻ ማግኘት ትችላላችሁ
ተሥፋዬ አርባ ጉጉ ላይ በተነሳው ግጭት አባቱን ያጣና በገዛ አገራቸው ስደተኛ መሆን ተገደው ናዝሬት ውስጥ በጠላ ንግድ በሚተዳደሩ እናት ያደገ ወጣት ነው። የስርዐት ክፋትን ከልጅነቱ እያየ አባትን ያህል ነገር በሞት ተለይተውበት ያደገ ወጣት መሆኑን ከውውይይቱ ለመረዳት ይቻላል። በዚህ አስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ ራሱን ማስተማር ችሎ ለሀገሩም ለቤተሰቡም አጋር ለመሆን የበቃ ወጣት ነው ። እንደወጣትነቱና እንደ ኢትዮጵያዊነቱ በነበረው የፖለቲካ አጋጣሚ ከቅንጅት ጎን ቆሞ ነበር። ይህ ግን በጠላትነት አስፈርጆት ቂመኞቹና ዘረኞቹ የትግራይ ተገንጣይ ወንበዴዎች ከመኖርያ ቤቱ ወስደው ለ23 ወራት ገረፉት፣ አሰቃዩት፣ በኤሌክትሪክ ጠበሱት ከሞቀ ውሀ ወደ ቀዝቃዛው እያመላለሱ አካሉን ሰባበሩት። ለኢትዮጵያዊው ወጣት ሀገሩን የገሀንም መናገሻ ከተማ አስመሰሉበት። ይህ ወጣት ዛሬ ሽንቱን አይቆጣጠርም፣ ለነገ ቤተሰብ መስርቶ ልጅ ወልዶ የመኖር ህልም የለውም። ስራው መመለስ አይችልም፣ የነበረው ንብረቱ በሙሉ ጠፍቷል ወይም ተዘርፏል። በቃ ያበቃለት ሰው ነው ብለው ሜዳ ጥለውታል። ቃል ቢተነፍስ እሱ ብቻ አይደለም ዘመዶቹ ሁሉ እንደሚያልቁ ተነግሮታል። ስለዚህ ቆሽሾ ሰው ተጠይፎት ዝንብ ወርሮት ሞቱን እንዲጠብቅ ተፈርዶበታል።
እንዲህ አይነት ግፍ የሚደርስባቸው ሰዎች ብዙ ናቸው ተሥፋዬን ልዩ የሚያደርገው ግን እንቅፋት የመታው እንኳን ያለመምሰሉ ነው። ኢትዮጵያዊነቱን ከስሜቱ ሊያወጡበት አልቻሉም፣ ዓላማውን አልገደሉበትም፣ ፊኛና ኩላሊቱን ቢቀጠቅጡም ወኔውን አላሸኑትም። እጅግ የሚያኮራ ወጣት ነው። እጅግ የሚያበረታታ ሀሳብ ያለውና ከደረሰበት ችግር በላይ ነፃነት ማጣቱ ያመመው ወጣት ነው። ማደርያ የለውም መሸሻም የለውም፣ እኛ ግን መሸሻም ማደርያም አጋርም ወገንም መሆናችንን ልናሳየውና ህልሙ እውን እንዲሆንለት በትግሉም ጠንክረን እሱን ብቻ ሳይሆን ወገኖቻችንን በጠቅላላው ከዚህ ሰቆቃ ነጻ ልናወጣ ይገባል። ተስፋዬ ተካልኝ እንደስሙ ሁሉ የዘረኛነትን ክፋት በኢትዮጵያዊነት ተስፋ ተተክቶ የነፃነት አየር ለመተንፈስ ይበቃ ዘንድ ምኞቴ ነው፡፡
biyadegelgne@hotmail.com
No comments:
Post a Comment