FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Sunday, July 14, 2013

የ600 ግለሰቦች የባንክ ሂሳብ በኮሚሸኑ ታግዷል

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መረጃ እየተሰባሰበባቸው በጊዜ ቀጠሮ ላይ የሚገኙ ባለሃብቶች በፀረ ሙስና ኮሚሽን የታገደባቸው የባንክ ሂሳብ እና ንብረት እንዲለቀቅላቸው ባለፈው ማክሰኞ ለችሎቱ አመለከቱ፡፡ ባለሀብቶቹ የባንክ ሂሳባቸው በመታገዱ በኩባንያዎቻቸው ተቀጥረው ለሚሠሩ ሠራተኞች ደሞዝ መክፈል እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን፤ እስካሁን የ600 ሰዎች የባንክ ሂሳብ መታገዱን ገልጿል፡፡ በእነ አቶ መላኩ ፈንታ መዝገብ ስር የተካተቱት የኬኬ ኃላፊቱ የተወሠነ የግል ኩባንያ ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ፣ የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት አቶ ስማቸው ከበደ፣ የአዲስ ልብ ሆስፒታል ባለቤት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ እንዲሁም በእነ አቶ ገ/ዋህድ መዝገብ ስር የተካተቱት የነፃ ትሬዲንግ እና ባሰፋ ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ነጋ ገ/እግዚብሔር እና የአልትሜት ፕላን እና የኢትባ ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ በእግዚአብሔር አለበል በጠበቆቻቸው በኩል የእግድ ይነሳልን ጥያቄያቸውን ለፍ/ቤቱ አቅርበዋል፡፡
የኬኬ ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ በጠበቃቸው በኩል ባቀረቡት አቤቱታ፤ ኩባንያቸው ከ600 በላይ ሠራተኞችን እንደሚያስተዳድርና ድርጅቱ የባንክ ሂሳም በመታገዱ ለሠራተኞች ከግንቦት ወር ጀምሮ ደሞዝ መክፈል እንዳልቻለ፣ ኩባንያው መደበኛ ስራውን መስራት ባለመቻሉም መንግሥት በሁለት ወር ውስጥ ከግብርና ከታክስ ያገኝ የነበረው ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማጣቱን በመጥቀስ፣ በሀገር ኢኮኖሚና በሦስተኛ ወገኖች ላይም ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የአዲስ ልብ ሆስፒታል ባለቤት ዶ/ር ፍቅሩ በጠበቃቸው በኩል ባቀረቡት አቤቱታም የሆስፒታሉ ሂሳብ በመታገዱ ለሠራተኞች ደሞዝ አለመከፈሉን፣ መገዛት ያለባቸው የህክምና ቁሳቁሶች አለመገዛታቸውን እንዲሁም ሆስፒታሉ የስራ ማስኬጃ ገንዘብ መቸገሩን ያመለከቱ ሲሆን ተጠርጣሪው ራሳቸው ስለ ጉዳዩ እንዲያስረዱ ችሎቱን ጠይቀው ሲፈቀድላቸውም፤ በራሳቸው ስም የተመዘገበ አንድም ገንዘብ አለመኖሩንና ሆስፒታሉ በውጭ ድርጅት የሚተዳደር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
30 ሺህ በሽተኞችን የሚያክመው የሆስፒታሉ ጀነሬተር ተበላሽቶ መግዣ ባለመኖሩ የህክምና አገልግሎቱ እየተስተጓጐለ መሆኑን ያከሉት ዶ/ር ፍቅሩ፤ “ድርጅቱ እንዲሰራ እኔ በባንክ የተያዘውን 10 ሚሊዮን ብር መተካት የሚችል ንብረት ማስያዝ እችላለሁ” ብለዋል፡፡ የነፃ ትሬዲንግ እና ባሰፋ ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ነጋ በጠበቃቸው በኩል ባቀረቡት ተመሳሳይ አቤቱታ፤ የሁለቱም ኩባንያዎች ሂሳብ መታገዱን በተለይም የትራንስፖርት ድርጅት የሆነው “ነፃ ትሬዲንግ” ከውጭ ያስመጣቸው 54 ተሽከርካሪዎች መታገዳቸው፣ በኩባንያውና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት እያስከተለ ነው ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ የባንክ ሂሳብ እግድ ይነሳልን አቤቱታቸውን በጠበቃቸው በኩል ለችሎቱ ያቀረቡት ኮንትራክተሩ አቶ በእግዚአብሔር አለበል፤ ድርጅታቸው ከ60 በላይ ጅምር ፕሮጀክቶች እንዳሉትና የባንክ ሂሳቡ በመታገዱ ከ700 በላይ ለሚደርሱ ሠራተኞች ደሞዝ መክፈል አለመቻሉን ገልፀዋል፡፡
የኢንተር ኮንቲነንታል ባለቤት በበኩላቸው በጠበቃቸው በኩል ባቀረቡት አቤቱታ፤ ምንም እንኳ ከታገዱት 7 የባንክ ሂሳቦች 3 ያህሉ ቢለቀቁም የተለያዩ ፕሮጀክቶች ስራ እየተደናቀፈ በመሆኑ ቀሪዎቹም እንዲለቀቁላቸው ጠይቀዋል፡፡ በሌላ በኩል ሁሉም አቤቱታ አቅራቢዎች ለየኩባንያዎቻቸው ወኪል አስተዳዳሪዎችን እንዲሾሙ ይፈቀድላቸው ዘንድም ጠይቀዋል፡፡ ባቀረቡት አቤቱታዎች ላይ የኮሚሽኑ አቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ፤ የኦዲት ማጣሪያ ሪፖርት ሳይቀርብና ሳይወሰን የባንክ ሂሳብ አሁን ይለቀቅ የምንልበት ሁኔታ ላይ አይደለንም፤ ስለዚህ እግዱ ባለበት ይፅናልን ያለ ሲሆን በሌላ በኩል የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የተላለፈ የእግድ ትእዛዝ የለም ብሏል፡፡ ለኩባንያዎቹም ወኪል ንብረት ጠባቂ ለማሾም ኮሚሽኑ በዝግጅት ላይ መሆኑን አቃቤ ሕግ ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ ዳኞችም አቃቤ ሕግ በሰጡት ምላሽ ላይ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ በተለይ የ3ኛ ወገን መብትን የሠራተኞች ደሞዝ ክፍያና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በተመለከተ ዳኞች ላቀረቡት ጥያቄ አቃቤ ሕግ በድጋሚ በሰጡት ምላሽ፤ የኦዲት ሪፖርቱ ቀጣዩን ሂደት ለመወሰን የግድ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ችሎቱ ጉዳዩን በይደር አቆይቶ በትናንትናው እለት በ20 ገፅ ፅሁፍ በሰጠው ብይን፤ የአምስቱ ኩባንያዎች አቤቱታ ጠቅለል ብሎ ሲታይ የስራ አመራር ቆሟል፣ ግብርና ታክስ መክፈል አልቻልንም እንዲሁም የሠራተኞች ደሞዝ መክፈል አልቻልንም የሚል መሆኑን አመልክቶ፤ ድርጅቶቹን ሊያስተዳድር የሚችል ገለልተኛ ወገን ይሾም፣ የሠራተኞች ጥቅምም ይከበር ብሏል፡፡
የሚሾሙት አስተዳዳሪዎች ከሁለቱም ወገን ገለልተኛ የሆኑ ሊሆን እንደሚገባና የኩባንያዎቹን የስራ ሂደት አንቀሳቅሰው ገቢ በማመንጨት የሠራተኞችን የመንግሥት ጥቅሞች ማስከበር የሚችሉ መሆን እንዳለባቸው ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን ገልጿል፡፡ የሚሾሙት አስተዳዳሪዎችን በተመለከተ ሁለቱ አካላት ቢቻል ተስማምተው ካልሆነም ሁለቱም የየራሳቸውን አማራጭ ከሐምሌ 12 ቀን 2005 ዓ.ም ይዘው እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ አዝዟል፡፡ በሌላ በኩል ችሎቱ በመደበኛ የክርክር ሂደቱ ከሰኞ እስከ ሃሙስ ባሉት ቀናት በእነ አቶ ገ/ዋህድ መዝገብ ስር የሚገኙ 11 ተጠርጣሪዎችን፣ በእነ አቶ መላኩ ፈንታ መዝገብ የሚገኙ 8 ተጠርጣሪዎችን፣ በእነ ጥጋቡ ግደይ መዝገብ የተካተቱ 4 ተጠርጣሪዎችን በእነ መሃመድ ኢሳ መዝገብ የተካተቱ 7 ተጠርጣሪዎችን እንዲሁም በእነ ተመስገን ስዩም ተጠርጣሪዎችንና በእነ መልካሙ እንድሪስ ከተጨማሪ ሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር የ6 ተጠርጣሪዎችን ተመልክቷል፡፡ የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን፤ የእነ አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስን መዝገብ በተመለከተ ባቀረበው የስራ መዘርዘር በተወሰኑ ተጠርጣሪዎች ላይ የሰነድ ማስረጃ ማሰባሰቡን፣በከፊል የሰው የምስክር ቃል መቀበሉን አመልክቷል፡፡ በተጨማሪም ከአራጣ ብድር ጋር በተያያዘ የኦዲት ሪፖርትና የባለሙያ አስተያየት መስማት፣ ከቀረጥ ነፃ የገቡ የ10 ሆቴሎች የግንባታ እቃዎች ከታለመላቸው አላማ ውጪ መዋላቸውን የሚያሳዩ ማስረጃዎች ማሰባሰቡን፣ በኮንትሮባንድ የገባ የህክምና እቃ በተመለከተ ማስረጃ ማሠባሰብ እና ሌሎች ስራዎችን መስራቱን አመልክቷል፡፡
በዚህ መዝገብ ቀረኝ ብሎ ካመለከታቸው ተግባራት መካከልም የኦዲት ሪፖርት መቀበል፣ ቀሪ የሰነድና የሰው ማስረጃ ማሰባሰብ እንዲሁም የቀሪ ምስክሮችን ቃል መቀበል የሚሉት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ቀሩ የተባሉ ስራዎችን ለማከናወን የ14 ቀን ቀጠሮ ጠይቋል፡፡ የተጠርጣሪዎች ጠበቆች በበኩላቸው፤ ለምርመራ ቡድኑ ቀደም ሲል የተሰጠው የምርመራ ጊዜ መረጃ ለማሰባሰብ በቂ መሆኑን ገልፀው የተጠየቀው የ14 ቀን ቀጠሮ ተገቢ አይደለም፤ ቢፈቀድ እንኳ ደንበኞቻችን በዋስ ሆነው ጉዳያቸውን ይከታተሉ ብለዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የዋስትና መብቱን በመከልከል፤ የ14 ቀን ቀጠሮውን ወደ 10 ቀን አሳጥሮ መዝገቡን ለሐምሌ 11ቀን 2005 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡ በእነ አቶ ገ/ዋህድ መዝገብ ሁለት ተጨማሪ ተጠርጣሪዎች የተካተቱ ሲሆን እነሱም የአዳማ ገቢዎችና ጉምሩክ ቅ/ጽ/ቤት ሠራተኛ የሆነው አቶ ያለው ዋቆ እና የእንጀራ እናቱ ናቸው የተባሉት ወ/ሮ ሽቶ ነጋሽ ናቸው፡፡ ማክሰኞ እለት የተሰየመው ችሎት የእነ አቶ መላኩ ፋንታን ጉዳይ የተመለከተ ሲሆን በዚህ መዝገብ የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ያከናወናቸውንና የቀሩትን ስራዎች በመጥቀስ በተመሳሳይ የ14 ቀነ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡ ተከናወኑ ተብለው ከተጠቀሱት ስራዎች መካከል በህገወጥ መንገድ የተከለከለ ሲሚንቶ እንዲገባ በማድረግ የተከሰሱ ግለሰቦችን ክስ ማቋረጥንና ሰነዶች መሰብሰባቸውን፣ በተለያዩ የጉምሩክ ህጐች ጥሰት ሳቢያ የተመሰረቱ የጅምላ ክሶች ማቋረጥን በተመለከተ፣ ከገቢ በላይ ሃብት ማካበትን በተመለከተ ከተለያዩ ባንኮች እና ተቋማት ማስረጃዎች ማሰባሰቡን ፣ በከፊል የምስክሮች ቃል መቀበሉንና የኦዲት ሪፖርቶችን ከባለሙያዎች እየተቀበለና መዝገቡንም እያደራጀ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ቀሩ ካላቸው ተግባራት መካከልም በህገወጥ መንገድ የገባ ሲሚንቶን በተመለከተ የ6 ምስክሮች ቃል መቀበል፣ እንዲሁም በከፊል የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ማሰባሰብ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ እነዚህን ተግባራት ለማከናወን ቡድኑ የ14 ቀን ቀጠሮ የጠየቀ ቢሆንም ፍ/ቤቱ ሳይቀበለው የ10 ቀን ቀጠሮ ብቻ ፈቅዷል፡፡ በሌላ በኩል በዚህ መዝገብ ስር የአቶ መርክነህ አለማየሁ እህት ትዕግስት አለማየሁ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡ የተጠረጠሩበት ጉዳይም ምንጩ ያልታወቀ ሃብት ይዞ መገኘትና ከወንድማቸው የተቀበሉትን 1.2 ሚሊየን ብር አሽሽተዋል የሚል ነው፡፡ ረቡዕ ቀጥሎ በዋለው ችሎት፤ የእነ ጥጋቡ ግደይ እና የእነ መሐመድ ኢሣ መዝገብና የደረሰበትን የምርመራ ሂደት ችሎቱ የገመገመ ሲሆን መርማሪ ቡድኑ በእነ ጥጋቡ ግደይ መዝገብ ከአዲስ አበባ ወደ ሞጆ፣ አዳማ፣ ሚሌ እና አዋሽ የተላከው ቡድን የ31 ምስክሮች ቃል መቀበሉን፣ ተጠርጣሪዎቹ በልዩነት ያሳለፏቸውን እቃዎች ዲክላራሲዮን በከፊል መሰብሰቡን፣ አላግባብ የተቋረጡ የክስ ፋይሎችን በከፊል ማሰባሰቡን፣ ህገወጥ የታክስ ክለሳን በተመለከተ የኦዲት ሪፖርት ማሰባሰብ እና የመሳሰሉት፣ ህገወጥ የታክስ ክለሳን በተመለከተ የኦዲት ሪፖርት ማሰባሰብ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
ቀሩ ተብለው በቡድኑ ከቀረቡት መካከልም ወደ አዳማ፣ ሚሌ፣ ሞጆ አዋሽ የተላከውን ቡድን ስራ ማጠቃለል፣ የኦዲት ስራ አጠናቆ የባለሙያ ቃል መቀበል፣ የኤሌክትሮኒክስ ትንተናና የባለሙያ ቃል መቀበል የሚሉት ይገኙበታል፡፡ የተጠርጣሪ ጠበቆችም በበኩላቸው፤ ይቀረናል የተባለው ስራ ካለፈው ቀጠሮ ከቀረበው ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ስለዚህ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ሊፈቀድ አይገባም፣ ደንበኞቻችንም በዋስ ሆነው ጉዳያቸውን ይከታተሉ የሚል መከራከሪያ ያቀረቡ ሲሆን ችሎቱም ተጠርጣሪዎች የጠየቁትን የዋስትና መብት ውድቅ በማድረግ የ14 ቀኑን ጥያቄ ወደ 10 ቀን በማሳጠር፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ መዝገቡን ለሐምሌ 12 ተቀጥሯል፡፡ በተመሳሳይ በእነ መሐመድ ኢሣ መዝገብ በቀረቡ 7 ተጠርጣሪዎች ላይ የምርመራ ቡድኑ ያከናወናቸውን ተግባራትና ቀሩኝ ያላቸውን በዝርዝር ያስመዘገበ ሲሆን በአብዛኛው ከሌሎች መዝገቦች ጋር ተመሳሳይ የሆነ ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡ የእነዚህንም የ14 ቀኑን ቀጠሮ ወደ 10 ቀን በማሳጠር ለሃምሌ 12 መዝገቡን ቀጥሯል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሐሙስ እለት ውሎው በእነ ተመስገን ስዩም መዝገብ የሚገኙ የ7 ተጠርጣሪዎችን እና በእነ መልካሙ እንድሪስ ስር የሚገኙ የ4 ተጠርጣሪዎችንና ከዚሁ መዝገብ ጋር ተጣምሮ ጉዳያቸው እንዲታይ የተጠየቀባቸውንና አዲስ ተጠርጣሪ የሆኑትን በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ መስሪያ ቤት የአዳማ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ፈታሽ እና የዋጋ ትመና ክፍል ኃላፊ አቶ ነገደ ከበደ እና አቶ ፈቃዱ ሰቦቃን ጉዳይ ተመልክቷል፡፡
የምርመራ ቡድኑ በእነዚህ ሁለት መዝገቦች የሠራቸውን ተግባራት ለፍርድ ቤቱ በዝርዝር ያቀረበ ሲሆን ቀሩኝ ብሎ ከዘረዘራቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከልም ቀሪ የምስክሮች ቃል መቀበል፣ የኤሌክትሮኒክስ ትንተና መቀበል፣ ቀሪ የሰነድ ማስረጃ ማሰባሰብ፣ በመሸሽ ላይ ያሉ ንብረቶችን ተከታትሎ መያዝ የሚሉት ይገኙበታል፡፡የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው፤ መርመሪ ቡድን ከዚህ በፊት ቀይሮ ከጠየቀባቸው የምርመራ ጉዳዮች የተለየ ምንም አዲስ ነገር አላስመዘገበም፤ ስለዚህ ምርመራው ያለቀ በመሆኑ የክስ መመስረቻ ቀጠሮ ብቻ ይሰጠው እንዲሁም የተለያዩ ምክንያቶችን በመዘርዘር ደንበኞቻችን ጉዳያቸውን በዋስ ሆነው ይከታተሉ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትእዛዝም ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ተገንዝቦ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ከተጠየቀው የ14 ቀን ቀጠሮ ውስጥ 10 ብቻ በመፍቀድ ለሐምሌ 15 ቀጠሮ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ በሰጠው ማሳሰቢያም በመርማሪ ቡድኑ የሚቀርቡ ሪፖርቶች ድግግሞሽ የሚመስሉ በመሆናቸው ይህንን ለጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ማቅረብ ተገቢ አይደለም ብሏል። አክሎም የኦዲት ስራው በየጊዜው የደረሰበት ሁኔታ በግልፅና በተብራራ መልኩ እንዲቀርብ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment