ብሩክ ሲሳይ
ለረጅም አመታት በተለያዩ የአለም ክፍሎች እየተዘዋወርክ በመሮጥ የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ ማድረግህን አንዘነጋውም። በነዚያ ወርቃማ የሩጫ ዘመኖችህ ባገኘሃቸው ድሎች አንተም ተደስተህ እኛንም ብዙ ጊዜ ያስደሰትከን መሆኑን አንረሳውም። ሀገራችንን የምትወክለውን ሰንደቅ አላማ ይዘህ በመሮጥህ ብቻ ሀገርህን እና ህዝብህን ትወዳለህ ማለት አይቻልም። አዎ ሀገርህን መውደድ መገለጫው ብዙ ነው፤ ሀገሩን የሚወድ ሰው የሀገሩን ባህል፣ ቋንቋ፣ ወግና ልማድ፣ አለባበስ ይወዳል፣ ሀገሩን የሚወድ ሰው የሀገሩን ህዝብ ይወዳል፣ ሀገሩን የሚወድ ሰው የሀገሩ ማህበረሰብ የተገነባበትን ሞራላዊ እና ስነምግባራዊ እሴቶች ያንፀባርቃል።
በውጭ የሚኖሩ ዲያስፖራ ወገኖቻችን ልጆቻቸው የሀገራቸውን ቋንቋ እና ባህል እንዲያውቁ ጥረት ያደርጋሉ ልጆቻቸውም በሀገራቸው ቋንቋ ሲናገሩና ባህላቸውን ሲያንፀባርቁ እናያለን ነገር ግን አትሌት ኃይሌ በኢትዮጵያ እምብርት የሚኖሩት ያንተ ልጆች የራሳቸውን ቋንቋ መናገር ሲሳናቸው እና ባህላቸውን ረስተው የምዕራባውያንን የህይወት ዘይቤ ሲያንፀባርቁ በቴሌቪዥን መስኮት ሳይ ያፈርኩትም የፈረድኩትም በአንተ ነው። አዎ ልጆቹማ ምን ያድርጉ የሰጧቸውን ነው የሚቀበሉት፣ ያሳዩቸውን ነው የምያደርጉት እንዲያውም በግጥምም እኮ እንዲህ ይባላል።
ከማንም ከምንም ከሁሉም በላጩ፥
ለልጆች ሥርዐት ቤተሰብ ነው ምንጩ
ለልጆች ሥርዐት ቤተሰብ ነው ምንጩ
ባህልንና ቋንቋን መውደድ አንዱ የሀገር ፍቅር ማሳያ እና መግለጫ ነው። አትሌት ኃይሌ ለሀገርህ ያለህን አመለካከት ምን አይነት እንደሆነ በትንሹም ቢሆን ይች ታሳያለች።
አንድ ጓደኛየ ከጥቂት አመታት በፊት አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ እኮ ባህርዳር ላይ ትምህርት ቤት አለው ብሎ ሲያጫውተኝ፤ ትምህርት ቤቱ በበጎ አድራጎት መልክ ለወላጅ አልባና ድሀ ቤተሰብ ላላቸው ህፃናት ማስተማሪያ የሚውል መስሎኝ ደስ ብሎኝ ነገሩን ጠበቅ አድርጌ ጓደኛየን ስጠይቀው የከበርቴ ልጆችን ታሳቢ አድርጎ ለቢዝነስ የተሰራ ትምህርት ቤት እንደሆነ በመንገር ግምቴን ናደው። ለነገሩ ስህተቱ የኔ ግምት ነው፣ አትሌት ኃይሌ እስኪ ላንዳፍታ አስበው እኛን የማያውቁን እንደ የሜዳ ቴኒስ ኮከቡ ሮጄር ፌደር አይነት የሩቅ ሀገር ባዕዳን ሰዎች ሰብአዊነት ተሰምቷቸው ለአሳዛኝ ህፃናት ወገኖቻችን የሚያገለግል ት/ት ቤት ያሰራሉ፣ ህፃናቱን በሀገራቸው እየተማሩ እንዲያድጉ ከፍተኛ እርዳታ ያደርጋሉ። የኛው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ደግሞ የእነዚህ ህፃናት ቤተሰቦችን መሬታቸውን እንዲያጡ ከመንግስት ጋር እየተሞዳሞድክ በኢንቨስትመንት ስም ብዙ ሺህ ሄክታር መሬት እየተቀበለክ ከትራክ ሩጫ ወደ ቢዝነስ የሩጫ ውድድር መግባትህን ሳይ በመጀመሪያ አዝናለሁ ቀጥየ ደግሞ ይሄ ሰው ግን ኢትዮጵያዊ ነውን? ብዬ እጠይቃለሁ፤ ምክንያቱም የቤተሰቦቻችን እና የማህበረሰባችን በአጠቃላይ ያደግንባቸው የሀገራችን ስነምግባራዊ እና ሞራላዊ እሴቶች እንዲህ አይነት ፍፁም ስግብግብ ባህርይ ያለው ግለሰብ እንዲፈጠር ምቹ አይደለም ብዬ ስለማስብ ነው።
አትሌት ኃይሌ እስኪ ከጓደኛህ ከኬንያዊዩ ፖልቴርጋት ሰብአዊነት ምን እንደሆነ ተማር፤ የሚገርመው ደግሞ ይህን ስግብግብ ባህርይህን ለሰው መርዳት ጥሩ አይደለም፣ እርዳታ ሰነፍ ነው የሚያደርገው፣ እኔ በጥረት ነው እዚህ የደረስኩት እያልክ በአስመሳይ ቃላት ስትሸፍንና ምክንያታዊ ለመሆን ስትጥር ሳይ ታበሽቀኛለህ። ያንተን ጥንካሬ አደንቃለሁ ነገር ግን ወላጅ የሌለውን ህፃን ማስተማርና ማሳደግ፤ የሚበላው ያጣን ህፃን ምግብ ማብላት፣ ደብተር እና እስክርቢቶ ገዝቶ ትምህርት ቤት መላክ እንዴት ነው ህፃናቱን ሰነፍ የሚያደርጋቸው?? አትሌት ኃይሌ እርዳታ ለማድረግ እኮ ከአንተ ኪስ አይጠበቅም በውነቱ አንተ ሰብአዊ ልቦና እና ጊዜህን ለመልካም ነገር ብታውለው ስምህ ብቻ ይበቃ ነበር፤ በስምህ ብቻ አለምአቀፍ እርዳታወችን ታሰባስብበት ነበር ልክ እንደ ጓደኞችህ፤ እሺ ይሄንም ተወው ቢያንስ እስኪ አንተ መስጠት እንደማትወደው ሁሉ ደሀን እያፈናቀልክ መሬት በርካሽ ዋጋ አሊያም በነፃ መቀበሉን ከመንግስት አቁም። ባለፈው ሰሞን መንግስት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ መሬት ይዘዋል ወይም ደግሞ መሬት ዘርፈዋል ካላቸው ከፍተኛ ከበርቴዎች ውስጥ አንተ መኖርህን ስሰማ በጣም ነው ያፈርኩት
በባለፈው ሰሞን መምህራን ኑሮው ከብዶናል ወርሀዊ ምንዳ ይጨመረን ብለው ቢጠይቁ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስተር ይህን የጠየቁትን መምህራኖች ብቃት የሌላቸው ናቸው ብለው አሳፋሪና የማይገናኝ መልስ ያውም በፓርላማ ሲሰጡ፣ ብዙዎቻችን ሰውየው እየሳቱ ነው አሊያም ደግሞ አሞቸዋል ብለን ነበር ነገር ግን በጣም ያዘንኩት አንተ እነኚህን መምህራን ሰነፍ ስለሆኑ ነው ደመወዝ ይጨመረን ያሉት ብለህ የሟቹን ጠቅላይ ሚኒስተር አሳፋሪ እና በሬ ወለደ ንግግር ስትደግመው አፈርኩብህ። ማን ያውቃል ከዚች ንግግር በኋላ ሟቹ ጠቅላይ ሚ/ር ሃሳባቸውን ስለደገፍክ ብዙ ሄክታር የደሀውን ህዝብ መሬት በዳረጎት መልክ አሰጥተውህ ሊሆን ይችላል።
አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ባገኘሀው ዝና እንዲሁም ባካበትከው ሀብት ምክንያት በዙሪያህ ብዙ ሰወች ይከተሉህ ወይም ይከቡህ ይሆናል፣ ጌታየ አቤት ወዴት የሚሉ ብዙ ሰዎች በዙሪያህ ሊኖሩ ይችላሉ፣ ከአፍህ የሚወጣውን ንግግርክን እየጠበቁ ባያስቅም እንኳ የሚፈነድቁልህ ብዙ ይኖራሉ፣ ኃይሌ አንተ እኮ ምርጥ እና ለየት ያልክ ሰው ነህ እያሉ የሚክቡህ ብዙ ሺህ ሰወች በዙሪያህ ሊኖሩ ይችላሉ፤ በመሆኑም አንተ የምታስበው ሁሉ ትክክል እንደሆነና እና ካንተ በላይ አዋቂ ኢትዮጵያዊ የሌለ እየመሰለህ ራስክን ክበህ እና ቆልለህ በየቦታው እና ሜዲያው እየተገኘህ የምታደርጋቸውን አሳፋሪ ንግግሮችን መስማትና ማድመጥ ሰልችቶናል እባክህ ዝም በልልን። በነዚህ አሳፋሪ ንግግሮችህ እንዲሁም የግል እና የንግድ ህይወትህ ግን ምን ያክል ህዝብ እንደሚጠላህ የምታውቅ አይመስለኝም፤ ለዚያም ነው መሰለኝ ደግሞ ፖለቲከኛ እሆናለሁ እያልክ የምትቀባጥረው። ቆይ ግን ኢህአዴግን የሚቃወም ፖለቲከኛ ነው መሆን የምትፈልገው ወይስ የኢህአዴግ ካድሬ? ነው ወይስ የአዲስ አበባ የኢህአዴግ ደጋፊ ነጋዴወች ማህበር ማለቴ አንተን ጨምሮ እነ አብነት ገ/መስቀል ያሉበት አጎብዳጅ የዘራፊ ነጋዴዎች ስብስብ እጩ አድርጎህ ይሆን?
ምናልባት የአሁኑ ዘመን የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የቢዝነስ ሰራውን ስለተቆጣጠሩት እና የቢዝነስ ውድድሩን በያዙት ስልጣን ተጠቅመው በቀላሉ እያሸነፉህ ተቸግረህ ይሆን ወደ ፖለቲካው ለመምጣት ያሰብከው? ምናልባት ሳትሮጥ እና ከላይ ከታች ሳትል በቀላሉ እንደ ሴቷ ጠቅላይ ሚኒስተራችን ቢሊየነር ለመሆን አቅደህ ይሆን ፖለቲካ ያማረህ? ብቻ ዕቅድክን አንተው ታውቀዋለህ ነገርግን አትሌት ኃይሌ እኛ እኮ ነጋዴ እና ስግብግብ ፖለቲከኛ አላጣንም ይሄው 23 ዓመት ይዘውን የለ እንዴ፤ ዝም ብለህ የለመድከው ንግድህ አይሻልህም ወይ ለነገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ንግድ ሳይሆን ማጭበርበር እና ዝርፊያ ነው ያለው።
ለማኛውም ወግና መንገድ አይከለከልም ይባል የለ ፖለቲከኛ የመሆን ፍላጎት አለኝ ብለህ የማውራት መብት አለህ ነገርግን ህዝብ የሚወድህና ለአገር የምትጠቅም ፖለቲከኛ ለመሆን በቅድሚያ ኢትዮጵያዊ የማያስመስሉህ ስነምግባሮችህን ቀይራቸው፣ በመቀጠል አስፈላጊውን እውቀት ከታሪክ ጀምሮ በመመርመር ተረዳ። ከዚያም ለዝርፊያ ብለህ ከተጠጋህበት ከኢህአዴግ ጉያ ወጥተህ ህዝብን ወግነህ ለህዝብ በመቆም የሚደርስብህን ችግር ልክ እንደነ አንዱአለም አራጌ እና እስክንድር ነጋ ስትጋፈጥና ለኢህአዴግ በማጎብደድ ያበላሸሀውን ስብዕናህን ስትፍቅ እኛም አትሌት ኃይሌ የትራኩ ንጉስ ሆይ ምንሊክ ቤተመንግስት ውስጥም ንገስ እንላለን።
No comments:
Post a Comment