FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Tuesday, July 23, 2013

ከ “ድርጅታዊ ምዝበራ መጽሃፍ” ላይ የተወሰደ ማስታወሻ


በገለታው ዘለቀ
በቅርቡ ለንባብ የበቃው “ድርጅታዊ ምዝበራ” የተሰኘው  መጽሃፍ ደራሲ ዶክተር ኣክሎግ ቢራራ ጎንደር ተማሪ በነበሩበት ወቅት በኣንድ ነገር ተመስጠው ነበር። ይህ ምናባቸውን የገዛው ነገር በጎንደር ውስጥ እድሜው የትየለሌ የሆነ የኣንድ የዋርካ ዛፍ ተፈጥሮ ነበር። ይህን ዋርካ ባዩት ቁጥር ምናባቸው ተዛምዶን ይፈጥራል። ግዙፉ ዋርካ ዙሪያውን ያሉትን ቅርንጫፎችና ቅጠሎች ይዞ ዝንት ዓለም ይኖራል። ከምድሪቱ የሚያገኘውን ኣስፈላጊ ነገር እያመላለሰ ልጆቹን ያስተናግዳል። ቅጠሎቹም የራሳቸውን ድርሻ ይወጣሉ። ብዙ ቅርንጫፎችና ቅጠሎች እያሉ ግን ኣንድ ዋርካ ይባላሉ። ብዙ ሆነው እንደ ኣንድ ደሞ ኣንድ ሆነው እንደ ብዙ ናቸው። የበቀለባት ምድር ደግሞ እናት ትሆናለች። ዶክተር ኣክሎግ በዚህ ዋርካ ተፈጥሮ እየተደመሙ የኢትዮጵያን ብዙህ ተፈጥሮና ኣንድነት ያመሳስላሉ። ያን ዋርካ እያሰቡ ብዙሃዊትን ኢትዮጵያ በዚህ መጽሃፋቸው “ኢትዮጵያ ዋርካ ናት” ይሏታል። በዚህ በኢትዮጵያ ብዙህነትና ኣንድነት እምነታቸው ላይ የጸና ኣቋም እንዳላቸው  ከጽሁፋቸው በሚገባ የልባቸውን መረዳት ይቻላል። ይህ የጸና ኣቋማቸው ደሞ የጎሳ ተኮር ፌደራሊዝምን እና ኢፍትሃዊ እድገትን ኣምርረው እንዲታገሉት ያደረጋቸው ይመስላል። በዚህ መጽሃፋቸው የዚህችን ብዙህ ኣንዲት ኢትዮጵያን  ኣጠቃላይ ይዞታዋን ጥልቀት ባለው ሁኔታና በስፋት ይተነትናሉ፣ህመሟን ጉዳቷን ሁሉ ይመረምራሉ፤ መፍትሄውንም ይጠቁማሉ ኣማራጭ የፖሊሲ ኣቅጣጫዎችን በጠቆም ህክምናውንም ያሳያሉ።Review of Dr. Aklog Birara's new book in Amharic
“ድርጅታዊ ምዝበራ” ይዞት የተነሳው ጭብጥ ኣንድ ብቻ ኣይደለም። የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ(political economy) ጉዳይ እንደ ዋና ማጠንጠኛ ኣድርጎ የሰብኣዊ መብት ኣያያዟን፣ ታሪኳን፣ ኣጠቃላይ ማህበራዊ ጎኗን ሁሉ ይዳስሳል። ጸሃፊው ዶክተር ኣክሎግ የተለያዩ ጭብጦችን ይዘው  ሲጓዙ ኣምርረው የሚከራከሩላቸው ዋና ዋና ሁለት ጉዳዩች ግን ይታዩናል። እነዚህ የዚህ መጽሃፍ ምሰሶዎች  የሰብኣዊ ልማት(Human Development) ጉዳይና የፍትሃዊ እድገት ጉዳይ ናቸው። ፍትሃዊ እድገት ለዋናው እምነታቸው ለሰብኣዊ እድገት ዋና መንገድ(means) በመሆኑ እንደ ኣንድ ዋና ጭብጥ ኣጥብቀው ይዘውት ይታያል። በመጽሃፉ ውስጥ በሃይል የተተቹት የጎሳ ፌደራሊዝም ጉዳይ፣ የሙስና ጉዳይ የ ኣድሎና ሌሎች ጉዳዩች ሁሉ ለነዚህ መጽሃፉን ውስጥ ውስጡን ለሚከነክኑት  ሁለት የመጽሃፉ ወገኖች እንቅፋት ወይም ኣሜኬላ ተደርገው በመታየታቸው ነው።
ዶክተር ኣክሎግ በዚህ መጽሃፋቸው ውስጥ ሁለት ኣይነት የኣቀራረብ ቴክኒክ ያላቸው ሲሆን ኣንደኛው ኢትዮጵያን ከውጭ ሆነው ወደ ውስጥ የሚያዩበት መነጽር ነው። በዚህ ኣቀራረባቸው የኢትዮያን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ደረጃዎች(status) ከሌሎች ኣገሮች ጋር እያወዳደሩ ነው የሚያቀርቡት። በቅርብ ርቀት ለውድድር ካቀረቧቸው መካከል ጋና፣ ቦትስዋና፣ ታንዛኒያ ኬንያ እና ሌሎችም ሃገራት ናቸው። ከዚህ ወጣ ብለውም ከኣጠቃላዩ ኣለም ጋርም እያወዳደሯት ያላትን ኣጠቃላይ ቁመና በሚገባ ያሳያሉ።በተለይ ከጋና ጋር ጊዜ ወስደው ሰፋ ኣድርገው የሁለቱን ኣገሮች ልዩነት ያሳያሉ። ጋና ከሌሎች የኣፍረካ ሃገራትና  ከራሷ መጥፎ የፖለቲካ ተመክሮዎች ተምራ ሁሉን ኣቀፍ ኣሳታፊ የሆነ ስርዓት በመገንባት ላይ ያለች ኣገር መሆኗ ጥሩ ምሳሌ ኣድርጓታል። በኢኮኖሚው መስክ በ2003  ወደ ሃያ ፐርሰንት የሚሆን ዶመስቲክ ሴቪንግ ኣላት፣ በኣንጻሩ የኢትዮጵያ ዶመስቲክ ሴቪንግ 27 በመቶ ወደታች(negative) ነው።ጋና ከውጭ እዳ ነጻ ስትሆን ኢትዮጵያ ወደ 12 ቢሊየን የደረሰ እዳ ኣለባት። የጋና የመብራት ሃይል ፖሊሲ የዛሬ ስምንት ኣመት ሁሉም ጋናዊያን የመብራት ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ሲሆን ኢትዮጵያ ሃይል ወደ ውጭ ለመሸጥ ትቋምጣለች:: ጋና ዴሞክራቲክ ተቋሞችን እየገነባች ተከታታይ ፍትሃዊ ምርጫ ያደረገች ኣገር ስትሆን ኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህ ተቋማት እያደጉ ሲሄዱ ኣይታይም።
ዶክተር ኣክሎግ ቢራራ በኣለም ባንክ ውስጥ በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ከሰላሳ ኣመት በላይ መስራታቸው የኣለምን ፖሊቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ በጥልቀት እንዲያውቁ ስላገዛቸው ኢትዮጵያን በትኩስና ተኣማኒነት ባላቸው ብዙ ማስረጃዎች ለማሳየት ቀላል እንደሆነላቸው መረዳት ይቻላል። የዚህ መጽሃፍ ዋናው ኣንዱ ጥንካሬ በብዙ መረጃዎች የታጀበ መሆኑ ነው።
ከፍ ሲል እንዳልነው መጽሃፉ ሽንጡን ገትሮ የሚሟገትለት የዚህ የሰብኣዊ ልማትን ጉዳይ በቀጥታም በተዘዋዋሪም እያነሳ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ይጓዛል። በሰዎች ህይወት ላይ ለውጥ የማያሳይን እድገት ግንጥል ጌጥ ያደርገዋል። በራሳቸው በዶክተር ኣክሎግ ቢራራ ኣገላለጽ “ብልጭልጭ እድገት” ነው ማለት ነው።። ጸሃፊው ኣይቮሪኮስትን እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ። ኣይቮሪኮስት ውስጥ ከባድ ያልተመጣጠነ እድገት ተከስቶ ብዙ ህንጻዎችና ግንባታዎች ቢሰሩም ኣብዛኛውን ሜዳ ላይ የጣለ እድገት በመሆኑ ኋላ ላይ ለመፈራረስ በቅቷል።
መጽሃፍ ኢትዮጵያን በ1967 በኣሩሻ ታንዛኒያ የተፈረመውን   “የአንድን አገር ልማት የሚወስነው ሕዝቡ ነው። እድገቱ ስለ ህዝብ ኑሮ መሻሻል ነው። ስለገንዘብ (ኪራይ ሰብሳቢነት)( Political elite extraction of rent from society)) አይደለም።”የሚለውን ስምምነት ያስታውሳሉ። ኢትዮጵያ በዚህ የሰብኣዊ ልማት መለኪያ ከኣጠቃላይ በኣላም ላይ ካሉ 187 ኣገሮች 174ኛ መውጣቷ በርግጥ የሰብኣዊ ልማት ይዞታዋ ምን ያህል ኣስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ እንደዘቀጠ ያሳያል።
የኢትዮጵያ መንግስት ስለ ያልተመጣጠነ እድገት ሲያነሱበት ይህ የሃብት ልዩነት በኣዳጊ ኣገሮች የሚታይና የሚጠበቅ ኣድርጎ ያቀርበዋል። እንደሱ እምነት ኣገርን የሚያሳድጉት ጥቂት ግለሰቦችና ቤተሰቦች ናቸው። የዚህ ኣይነቱ ዝንባሌ በኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካና ማህበራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ኣንጻር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው። ከሁሉም በላይ ይህ ኣይነት የእድገት ኣቅጣጫ መገንጠል ዋስትና ነው በተባለበት ኣገር፣ የጎሳ ፌደራሊዝም በሰፈነበት ኣገር፣ ጎሳዎች የየራሳቸው የንግድ ድርጅት ባቋቋሙበት ኣገር ከፍተኛ እምቅ ችግር ሊሆን እነደሚችል ይታመናል። ህዝቦችም ይህ የተጠራቀመ ሃብት ወደኛ ኣንድ ቀን ይንቆረቆራል (wealth trickle down)ብለው በእምነት እንዲጠብቁ የሚያደርግ ከባቢና ዋስትና የላቸውም። ኢትዮጵያ በኣጠቃላይ ሁኔታ ለዚህ የሃብት ክፍፍል (wealth distribution) የማይመች ሁኔታ ላይ ስትሆን ራሱ ሳይንሱ ግን  ጨካኝ ኣይደለም። ኣሜሪካ ስትመሰረት ዶክተር ኣክሎግ እንደሚያስረዱን እነ ፎርድ፣ ቤተልሄም ብረታብረት እና ሌሎችም ሃብታም ድርጅቶች ቶሎ ቶሎ ኣዳዲስ ፈጠራዎችን በማምጣት፣ የስራ እድል በመክፈት ከፍተኛ የመካከለኛ መደብ የማስፋፋት ስራ ሰርተዋል::  ሩቅ ሳንሄድ እኛው ኣህጉር ውስጥ ጋና በ 2012 በ 14.6 በመቶ ኣድጋ የነበረ ሲሆን ይህ እድገቷም በብዙ መቶ ሺህ የሚሆኑ ህዝቦቿን ወደ መካከለኛ ገቢ ስቧቸዋል። በኣንጻሩ ኢትዮጵያ ላለፉት ስምንትና ዘጠኝ ኣመታት በተከታታይ በጥንድ ቁጥር እያደገች የመካከለኛ መደብ የማስፋፋት ስራ ኣይታይም። ኢህኣዴግ ከመጣ 20 ኣመታት በሗላ፣ ከስምንትና ዘጠኝ ኣመት ጥንድ ቁጥር እድገት በኋላ 90 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የቀን ገቢው ከ 2 ዶላር በታች ነው።76 በመቶ የሚሆነው ኣምራቹ ክፍል ወጣቱ ከሃገር ብን ብሎ መጥፋትን ይመኛል።ሰማኒያ በመቶ የሚሆነው የማምረት ኣቅም ያለው ወጣት ስራ ኣጥቶ በየሱቁ ስር ይቆማል።ጉልበት በጣም ይባክናል። ቢያንስ 15 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የለጋሾችን የምግብ ርዳታ ተስፋ ኣድርገው ይኖራሉ። በ2011 ኢትዮጵያ በጤና ጥበቃ ኣገልግሎት ከኣለም 109ኛ ስትሆን በንጹህ ውሃ ኣቅርቦት የመጨረሻ ናት።  ምግብ በማጣት እድገታቸው የተሰናከለ (malnourished children) ህጻናት ቁጥር ሰላሳ አምስት ከመቶ ደርሷል። 80 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የሚኖረው በቀን ከ $1.25  በታች ነው። 0.22 ሃኪም ለኣንድ ሺህ ኢትዮጵያዊ ነው።ኢንተርኔት ሃያ ኣራት በመቶ ብቻ ነው። የሲቪል ሰራተኛው ሪል ኢንካም እየቀነሰ ነው የመጣው:: የዋጋ ግሽበት በ 2011 ሃምሳ በመቶ ነበር:: እነዚህ እውነቶች የሚያጋልጡት በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የሃብት መንቆርቆር (wealth trickle down) ጉዳይ “ላም ኣለኝ በሰማይ ወተቷንም ኣላይ” መሆኑን ነው። ያ የጥንድ ቁጥር እድገት ምናልባትም የኤፈርት እድገት  ይሆናል።
ዶክተር ኣክሎግ ቢራራ የጎሳ ፌደራሊዝምን ተከትሎ ስለመጣው ኢፍትሃው እድገት ሲገልጹ።
ከፖለቲካ ውጭ ለመበልጸግ ሳይሆን ኑሮን ለማሸነፍ የራስ ዳሸንን ተራራ የመውጣት ያህል ነው። ይላሉ::
ቦትስዋና በ1966 ነጻነቷን ስታገኝ በእጇ ያገኘቻቸው የተማሩ ሰዎች 22 ብቻ ነበሩ። ዛሬ ከኣፍሪካ ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ያላት ብዙ ምሁራንን ያፈራች ኣገር ናት።ለዚህ ፈጣን እድገቷ ትልቁን ሚና የተጫወተው የተረጋጋ ፖለቲካና ፍትህ በመኖሩ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ  ህግ ኣውጪውና ህግ ኣስፈጻሚው ነጻ ስላልሆነ Check and balance ኣይኖርም:: በህግ  የበላይነት ጥራት መለኪያ ኣሜሪካ  91.8% ያስመዘገበች ሲሆን ኢትዮጵያ 16.4% ኣስመዝግባለች::  በኢትዮጵያ ውስጥ በርግጥም ይህ የጎሳ ፖለቲካ ከመጣ ወዲህ የኢትዮጵያዊያን ዋና የልብ ጥያቄ የኢኮኖሚ እድገት ጉዳይ ሳይሆን የፍትህ ጥያቄ ሆኖ ይታያል። ዋናው ጥያቄ ቢያንስ ቤታችን ያፈራውን፣ ያለችንን ሃብት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንካፈል የሚል ይመስላል። ይህ እውነት ነው። ዋናው የመንግስት መኖር ኣስፈላጊነት ለፍትህ መስፈንና የእድገት ኣቅጣጫዎችን ለመቀየስ ነው። መቼም መንግስት ኣያርስም ኣይቆፍርም። የመንግስት ኣስፈላጊነት ዋናው እና ትልቁ ጉዳይ ይሄ ነው። ድሆችን እየነጠቁ ሃብታም የሚሆኑበት ኣገር መንግስት ኣለ ማለት ያስቸግራል። ኣሁን ያለው ኢፍትሃዊ እድገት መንግስት ባይኖረንም ሊከሰት ይችላል። ጉልበተኞች ድሃውን እየነጠቁ ሃብታም በመሆን እንዲህ ኣይነት ልዩነት ይመጣል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ኣዲስ የሚነሱ ሃብታሞች ከታች ህዝቡ ደግፏቸው፣ ከመካከለኛ ገቢ ወደ ከፍተኛ የሚያድጉ ሳይሆን ኣንድ ሃብታም የሚወለደው ብዙ ድሆችን በመጨመር ነው። የብዙ ድሆችን ቤት እየዘጉ በፍጥነት ሃብታም መሆን ህገ ኣራዊት ነው። ትልቁ የማስተዳደር ጥበብ የሚፈተነው ፍትሃዊ እድገት በማምጣት ነው።በኢትዩጵያ ውስጥ በተለይ በነዚህ ኣርባ ኣመታት መንግስት የሚባለው ትልቅ የህብረተሰብ ተቋም በፓርቲ ተውጦ ነው የሚታየው። ፓርቲው መንግስትን መዋጡን የሚያሳየው ኣንደኛ የተቋማት ነጻ ኣለመሆን ብቻ ሳይሆን የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ሁሉ በራሱ በፓርቲው የውስጥ ኣሰራር መቅረጹ ነው። የግምገማው ስልት፣ ከዘበኛ ጀምሮ የኣባልነት ፎርም ማስሞላት፣ ኣዲስ የሚቀጠሩ የመንግስት ሰራተኞች ኣባል ካልሆኑ ያላመቀጠራቸው ጉዳይ፣ ስኮላርሺፕ ኣንዱ መለኪያ በኣባልነት የመሆኑ ጉዳይ የሚይሳየው መንግስትን እያጠፉ ኣገሪቱን በፓርቲ መዋጣቸውን ነው የሚያሳየው። እንዲህ ሁሉም የመንግስት ሰራተኛ የኣንድ ፓርቲ ኣባል እንዲሆን ከተገደደ እንዴት ሆኖ ነው በምርጫ ሌላ መንግስት የሚመሰረተው?::  ስልጣን የያዘ ፓርቲ ልማትን ማፋጠን(accelerate ማድረግ) ስራው የነበረ ቢሆንም መንግስትን ማጥፋቱ ለሃገሪቱ ሁለንተናዊ ችግር ከፍተኛ ኣስተዋጾ ኣድርጓል።
ዶክተር ኣክሎግ የሰባዊ መብት ጥያቄም ኣንዱ የተመጣጠነ እድገት የማምጫ መሳሪያ ኣድርገው ያዩታል። ኣጽንዖት ሰጥተው ሲገልጹትም
ለኣገር መክሸፍ ዋናው ምክንያት የሰባዊ መብቶች መታፈን ነው። ጎሳ ተኮር ፌደራሊዝም ብሄራዊ ማንነትን ኣብሮ ማደግን ቀብሮታል
በኢትዮጵያ ውስጥ ያላግባብ የታሰሩ ጋዜጠኞች ጉዳይ፣ ግፍ እየተፈጸመባቸው ስላሉት ወገኖች ጉዳይ ኣጠቃላይ ስላለው የሰባዊ መብት ኣያያዝ በሰፊው መጽሃፉ ይዘረዝራል።በኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጽዳት ኣለማቀፍ ወንጀል በሚገባ ለታሪክ ኣስቀምጠውታል። ስደትን በተመለከተ ስምንት በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ በተለይ ወጣቱ ተሰዶ ይኖራል። ከ 1941-1974 ድረስ በኣጠቃላይ ለትምህርትና ለተለያዩ ጉዳዩች የተሰደዱ 20  ሺህ ሲሆኑ በኣሁኑ ሰኣት የታወቁት ብቻ ስድስት ሚሊየን ደርሰዋል።ለዚህ ስደት ከሚያበቃቸው ጉዳዩች መካከል ሙሰኛ የሆነው የጎሳ ፖለቲካ የኢኮኖሚ እድላቸውን ስለዘጋው፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በፖለቲካ ኣመለካከትና በጎሳ ተጽእኖ ነው።
ዶክተር ኣክሎግ ከፍ ሲል እንዳልነው የኢትዮጵያን ኣቋቋም የሚመዝኑት ከላይ ሆነው፣ ከውጭ ወደ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ውስጥ ለውስጥ በየ ሴክተሩ እየዞሩ ጓዳ ጎድጓዳዋን በባትሪ ያሳያሉ። ውስጥ ውስጡን ያለውን የሙስና ጉድ በሃቀኝነት ኣጋልጠዋል። የመጽሃፋቸውን ርእስ ለምን “ድርጅታዊ ምዝበራ” እንዳሉት የሚገባን ኋላ ላይ ለሙስና የሰጡትን ሰፊ ትርጉም ስንረዳ ነው። በዚህ መጽሃፍ ሙስና የታየበት መነጽር ከቁሳቁስና ከገንዘብ ዝርፊያ በላይ ኣድልዎ የሞላበትን ፖሊሲና የጎሳ ፖለቲካን ሁሉ ይጠቀልላል። ለዶክተር ኣክሎግ 99.6 በመቶ ፓርላማውን መቆጣጠር ራሱ ሙስና ነው። በሃገሪቱ የሚታየውን ኢፍትሃዊ እድገት፣ የመብት ረገጣ የተንሻፈፈ ፖለቲካ ሁሉ የሞሰሰ ስርዓት ውጤት ኣድርገው ነው የሚያዩዋቸው። ከዚህ ኣንጻር ኣጠቃላይ የመጽሃፉ ርእስ የተነሱትን ጭብጦች ጠርንፎ የያዘ መሆኑን መረዳት ይቻላል።
ሙስና የመጀመሪያው ቤቱ ኣእምሮ ውስጥ ነው። በተለያዩ ምክንያቶች የሞሰሰ ኣይምሮ የሚያወጣው ፖሊሲና የሚያቆመው ፖለቲካ ለሙስና ትልቅ በርን እየከፈተ ኣገር ያጠፋል።ይሁን እንጂ እንዲህ ለድሆች የተሰጠን ርዳታ ሳይቀር በቢሊዩን የሚቆጠር ዘረፋ እየተካሄደ፣ ለጋሾች የሚሰጡት ገንዘብ ለሰባዊ መብት መጣሻ መሳሪያ እየሆነ ሳለ ለጋሹ ኣለም ስለምን ችላ ኣለ? የሚለው ጥያቄ የብዙ ኢትዮጵያዊያን ጥያቄ ነው።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ እርዳታ ተቀባይ ከሆኑት መካከል ከኣለም ሶስተኛ ደረጃ ያላት ሲሆን ይህም ያለ እነዚህ ለጋሾች ድጋፍ መንግስት ሊቆም እንደማይችል ከፍተኛ የሆነ የሰባዊ ልማት እንደሚያስፈልግ ያሳያል። ታዲያ በርግጥ እነዚህ ለጋሽ ኣገራት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሆነውን ሙሉ በሙሉ ኣያውቁም ማለት ሳይሆን እኛ ባየነውና በገባን ልክ ኣያውቁም። የዚህ መንግስት ኣንዱ “ጥንካሬ” በከፍተኛ ሁኔታ ማስመሰል መቻሉ ነው። እነዚህ ብልጭልጭ እድገቶች ሁሉ ማሳያዎችና ለጋሾችን ማደናገሪያዎች ናቸው። የሰባዊ ልማቱን በመረጃ ማጭበርበርም ስለሚኖር ይሄን ያህል ትኩረት የሰጡት ኣይመስልም።ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ ኣንዴ በእርዳታ መልክ የሰጡትን ገንዘብ የት ኣደረሳችሁት ብለው ለመጠየቅ የሚያፍሩና  የሞራል ጉዳይም የሚያነሱ ይመስላል። ደፍረው ገንዘቡ የዋለበትን ለመጠየቅ፣ ኦዲት ለማድረግ ኣይደፍሩም። እውነቱ ግን ለድሆች የተለገሰ ገንዘብ ለመጨቆኛ ሲሆን ከዚህ የበለጠ ግፍ ስለሌለ ኣይን ኣውጥተው ጥልቅ ኦዲት ሊያደርጉ ይገባል። ኣንዱ ይሄ ነው:: ሌላው ደግሞ በኣፍሪካ ቀንድ ኣካባቢ የኢትዮጵያ መንግስት በጦር ሃይል የበላይነት ለማሳየት ባደረገው ጥረት በዚያ ቀጣና መረጋጋትን ሊያመጣ ይችላል ከሚል እምነት የጣሉ ሲሆን ይህ እምነታቸው በውስጥ ያለውን የዴሞክራሲና የሰባዊ መብት ይዞታ ጉዳይ በደንብ እንዳያዩ ኣድርጓቸዋል። ነገር ግን ህዝቡን እያሰቃየ ለራሱ ህዝብ ኣሸባሪ የሆነ መንግስት ኣንድ ቀን ድርምስ ቢል የዚያ ቀጣና መረጋጋት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገባል። ዛሬ ኢትዮጵያ በጎሳ የተከፋፈለች ስለሆነችና የመገንጠል ጥያቄ ይዘው ነፍጥ ያነሱ ወገኖች ባሉባት ሃገር የሚመጣው ኣለመረጋጋት እጅግ የከፋ ይሆናል።
ሌላው ደራሲው ዶክተር ኣክሎግ የሚሞግቱለትና ጥብቅና የቆሙለት  ጉዳይ የመሬት ነጠቃውን ጉዳይ ነው። ከ90 ሚሊዮን ህዝብ 88 በመቶ የሚሆነው ህዝብ እርሻን ተመክቶ በሚኖርባት ኣገር ባለፉት ኣንድ ኣስርት ኣመታት ኢትዮጵያ ፈረንሳይን የሚያህል የእርሻ መሬት ከሳውዲና ከሌሎች ኣገሮች ለመጡ ኢንቨስተሮች ኣስረክባለች። በዚህ ንጥቂያ የተፈናቀለው ህዝብ ኣንድ ሚሊዮን ኣምስት መቶ ሺህ የደረሰ ሲሆን ይህም ኦሞ ሸለቆን ሳይጨምር ነው።በየኣመቱ በሚሊየን የሚቆጠር ህዝብ እየተራበባት የስንዴ እርዳታ ከውጭ እየለመነች በሌላ በኩል እዚያው ኣገር ውስጥ እየተመረተ ከፍተኛ መጠን ያለው ሩዝና ስንዴ እየተጫነ ይወጣል። ገና ለሳውዲዎች በጋምቤላ ብቻ 290,000 ሺህ ሄክታር እንደሚሰጥ መንግስት ተስማምቷል።  በነገራችን ላይ ሳውዲ ከዚህ በፊት የከርሰ ምድር ውሃዋን እየተጠቀመች ስንዴ ማምረት ጀምራ ለተወሰነ ኣመታት ኣለምን ኣስደንቃ ነበር። ይሁን እንጂ በኣሁኑ ሰኣት የከርሰ ምድር ውሃዋ በማለቁ ነው ከጅሎች ኣገር ሞፈር ልትቆርጥ የወጣችው።
ስለ መሬትና ውሃ ሙስና ሲነሳ ብዙ ሰው እንደሚለው ግልጽ መሆን ያለበት ነገር ኣለ ። በእርዳታ የምትኖር ኢትዮጵያ ሳውዲን ከመሬቴ ድርሽ እንዳትይ እንድትል ኣይደለም የሚጠበቀው። ነገር ግን ግልጽ በሆነ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ኢትዮጵያዊያንና ሳውዲዎች ኣብረው ሊጠቀሙ ይገባል። ፖሊሲው ርህራሄን፣ መከባበርን፣ሶሊዳሪቲን እና የሃላፊነት ስሜትን ያገናዘበ መሆን ኣለበት። ዛሬ ኢትዮጵያ ከዚህ ፈረንሳይን ከሚያህል ከሰጠችው መሬት ምን እንደምትጠቀም ኣይታወቅም። ሙስና ስላለ ዜጎች ስለዚህ ግዙፍ መሬት ውል ኣያውቁም። የስራ እድል እንዳይባል የስራ እድል የሚፈጥረው በሄክታር 0.005% ብቻ መሆኑን መጽሃፉ ያሳየናል ።
ከዚህ የመሬት ነጠቃ ኣንዱ የመንግስት ስሌት  የታወቀ ነው። እነዚህ መሬት ነጣቂዎች ኣንዱ ያሳሰባቸው ጉዳይ የኣለም ህዝብ ብዛት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሄዱ ይህም በኣላም የምግብ ዋስትና ላይ ጥላ  ይፈጥራል በሚል ስጋት ነው። በዚህ መጽሃፍ ላይ እንደተጠቀሰው የኣለም ህዝብ ብዛት ከኣርባ ኣመት በኋላ ዘጠኝ ቢሊዮን ስለሚሆን ቶሎ ቶሎ የድሆችን መሬት እየነጠቁ ነው። እነዚህ ኢንቨስተሮች መሬት የሚወስዱት ለኣሁኑ ሳይሆን ለሚመጣው ትውልድ ይዞ ለማቆየት ብለው ነው ማለት ነው። ይህ ሞቲቭ መሬታቸውን ላጡ ህዝቦች በብዙ መንገድ እንዲሰጉ ያደርጋቸዋል። ኣንደኛው እቅዳቸው የረጅም ጊዜ በመሆኑ የያዙትን መሬት እንደያዙ ለመቆየት ከሚያስችላቸው ዘዴ መካከል ኣንዱ ይህንን መሬት የሸለማቸውን መንግስት በስልጣን ላይ እንዲቆይላቸው መታገል ነው። እነዚህ ሃብታሞች በሃብታቸው የሃገሪቱን ፖለቲካ በማወሳሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ይታመናል። ቢያስተውሉት ግን ለጋራ ጥቅም በሚደረግ የእርሻ ኢንቨስትመንት ውስጥ ቢገቡና በሩቁ ቢያስቡ የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ያለ ስጋት ይሰራሉ።ለውጥን ያልተረዳ እቅስቃሴ ጦሱ ለልጅ ልጆችም ይተርፋል።
በሌላ በኩል ያሉንን እሴቶች መንከባከብ እንዳለብን መጽሃፉ ይመክራል። ማህበራዊ ካፒታልን(Social capital) ወደ ምርት መለወጥ ጠቃሚ ነውም ይላል። በኣጠቃላይ ነጻነት የህግ የበላይነት መኖር እንዳለበት ያሰምራል። ከሁሉ በላይ ኣጠቃላይ ሲስተሙን ያረከሰውን የጎሳ ፖለቲካ ማስወገድ ለፍትዊ እድገት መሰረት መሆኑን ኣጥብቆ ይመክራል። የውጭ መንግስታትም የሚሰጡትን እርዳታ እንዲቆጣጠሩ ይመክራል። የተለያዩ የፖሊሲ ኣቅጣጫዎችንም ይዘረዝራል።ሌላው የዚህ መጽሃፍ ትልቅ ጥራት(quality) በሁሉም ደረጃ ላሉ ሰዎች መጣኝ መሆኑ ነው። በኣጠቃላይ መጽሃፉ ትኩስ መረጃዎችን ይዞ ኢትዮጵያ ኣሁን ያለችበትን ሁኔታ ቁልጭ ኣድርጎ የሚያሳይ ሲሆን ለወደፊቱ ደግሞ ቅርስና ታሪከ ሆኖ የሚያገለግል ነው።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
geletawzeleke@gmail.com

No comments:

Post a Comment