FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Wednesday, July 3, 2013

አንድነት አባሎቼን በማሰር የማደርገውን የሕዝብ ንቅናቄ ማደናቀፍ አይቻልም አለ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
አንድነት ፓርቲ የሶስት ወራት የህዝባዊ ንቅናቄ የትግል ስልቱ  የመጀመሪያውን የአደባባይ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ሰኔ 30/10/2005 ዓ.ም በጎንደር ከተማ እንደሚያደርግ ማሳወቁ የሚታወስ ነው፡፡ ሁልጊዜም ህግ ጠብቆ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሰው ፓርቲያችን የአገሪቱ ህገ መንግስት በሚደነግገው መሰረት የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ ለሰሜን ጎንደር ዞን ማወቅ ለሚገባቸው የመንግስት አካልና ለከተማ መስተዳድሩ አሳውቆ ወደ ቅስቀሳ ከገባ ጥቂት ቀናት አልፈዋል፡፡
Imageምንም እንኳን ህግ አክብረን ሰላማዊ ትግላችንን ብንቀጥልም በሰሜን ጎንደር ዞን በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ አብርሃ ጅራ ከተማ የፓርቲያችን አባላት የሆኑት አቶ አለልኝ አባይ፣ አቶ እንግዳው ዋኘው፣ አቶ አብርሃም ልጃለምና አቶ አንጋው ተገኝ አንድነት ፓርቲ የሰጣቸውን ተልኮ ተቀብላችሁ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ለምን በተናችሁ ተብለው ከቅዳሜ ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ አቶ ማህሙድ ሸሪፍ፣ አቶ ጀማል ሰይድና አቶ አለሙ አባይነህ ፓርቲው የጀመረውን የሚሊዮኖች ድምፅ የሚያሰባስብ ፔቲሽን ለምን ታስፈርማላችሁ ተብለው ታስረዋል፡፡
ይህ ተግባር ህጉን ጠብቆ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ፓርቲያችን ላይ አሁንም በገዥው ፓርቲ ህግ ጥሶ ሰላማዊ ሰልፉን የማደናቀፍ ተግባር እየተፈፀመ ስለመሆኑ ግልጽ ማሳያ ነው፡፡ ይህና ሌሎች የገዢው ፓርቲ እኩይ ድርጊቶች አንድነትን በፍፁም ወደኋላ ሊመልሱት እንደማይችሉ ማሳወቅ እንወዳለን ፡፡ ይህን በድፍረት እንድንናገር ያስቻለን ከዓላማ ቁርጠኝነታችን በተጨማሪ ህግ አክባሪነታችን ነው፡፡ ስለዚህ በቅስቀሳ ቡድኑ ላይ ከሚካሄደው ዛቻና ማስፈራሪያ ውጭ በተለያዩ ወረዳዎች የፓርቲያቸውን ተልዕኮ ለማሳካት በፍፁም ሰላማዊነት እየሰሩ ያሉ አባላት ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ትግላችንን ሊቀለብሰው እንደማይችል ተገንዝቦ መንግስት ከህገ ወጥ ድርጊቱ እንዲቆጠብ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡
እነዚህ አባሎቻችንም በአስቸኳይ እንዲፈቱ እየጠየቅን ምንም አይነት ህገ ወጥ እርምጃ መብታችንን ከመጠየቅ እንደማይገድበን በድጋሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና የፀጥታ ሀይሎች በአንድነት አባላት ላይ እየወሰዱ የሚገኙትን እስርና ማስፈራሪያ ፊትለ ፊት በመቃወም ቁርጠኝነቱንና አጋርነቱን በማሳየቱ አንድነት ፓርቲ ለጎንደር ህዝብ የአክብሮት ምስጋናውን ያስተላልፋል፡፡
የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት!!!

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ሰኔ 24 ቀን 2005 ዓ.ም
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment