ግርማ ሞገስ (girmamoges1@gmail.com)
ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2005 ዓ.ም.
ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2005 ዓ.ም.
የሚሊዮኖች-ድምጽ-ለነጻነት የሚለው ስትራተጂካዊ ዘመቻ ግቡ ምን እንደሆነ እና እድሜው ሶስት ወሮች እንደሚሆን አንድነት ፓርቲ ግልጽ አድርጓል። ከመግለጫው እንደተረዳሁት አንድነት ፓርቲ ጊዜ ወስዶ ብዙ አውጥቶ እና አውርዶ ያሰላው ለነፃነት እና ለዴሞክራሲ የሚደረግ ዘመቻ ነው። አንድ ነገር ግልጽ መሆን የጀመረ ይመስለኛል። ከንዋዮች መንግስት ፍንቀላ ጀምሮ ኢትዮጵያችን ለ50 አመቶች ያህል ብዙ ህይወት እየከፈለች በፖለቲካ ስርዓት ለውጥ ትግል ጎዳና ስትወድቅ እና ስትነሳ ከርማ ዛሬ ትክክለኛውን ወደ ዴሞክራሲ የሚያደርሳትን ጎዳና ያገኘችው መሰለኝ። ወደፊትም መውደቅ መነሳት ሊኖር ይችላል። መንገዱም አልጋ ባልጋ አይሆንም። ይሁን እንጂ የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት ዘመቻ ኢትዮጵያ ትክክለኛውን ጎዳና ማግኘቷን አብስሯል። የዚህ ዘመቻ ስሌት የፖለቲካ ትግል ባህላችንን እድገት ያመለክታል። የስልጣኔም ምልክት ነው። የሚሊዮኖች-ድምጽ-ለነፃነት ዘመቻ በርቀት ብርሃን አሳይቷል። በዚህ ጉዳይ ላይ ሶስት ተከታታይ ክፍሎች ያሉት ጽሑፍ በማቅረብ የተሰማኝን ለአንባቢ አጋራለሁ። ክፍል ሁለት በሽብር ህግ እና በሽብርተኛነት በታሰሩት የሰላማዊ ትግል ሐዋርያት ዙሪያ ያተኩራል። ክፍል ሶስት ደግሞ ዛሬ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት ዘመቻ እና ወደፊት የሚካሄዱ ተመሳሳይ ዘመቻዎችን ከብክለት እና ከውድቀት ለመጠበቅ ይረዳሉ የምላቸውን ምክሮች አንድ ሁለት እያልኩ ለአንባቢ አቀርባለሁ። ክፍል አንድ ግን የፖለቲካ ትግል ባህል ሽግግር በማድረግ ላይ መሆናችንን እንደሚከተለው ያቀርባል።
የትናንቱ እንደሚከተለው ነበር። የገደልን እኛ (The People)። የሞትን እኛ (The People)። የትግሉ እና የድሉ ባለቤት ግን እርስ በርስ ካጫራሱን ቡድኖች ውስጥ በጦርነቱ የቀናው ቡድን ሲሆን የመሰረተው መንግስት ደግሞ የጋራ አገራችንን የግል የጓሮ እርሻው ያደረገ እና ከቀድሞው የከፋ ሽብርተኛ አምባገነን ነው የሚል ነበር የትናንት የፖለቲካ ትግላችን ታሪክ። የትናንቱ የፖለቲካ ለውጥ ትግል ጎዳና በጦርነት የተሞላ ነበር። ብዙ ትምህርት ቤቶች ፈርሰዋል። መንገዶች ወድመዋል። የጦር ካምፖች እና የጦር መኪናዎች ጋይተዋል። ያ ሁሉ የኛ ንብረት ነበር። በህዝባችንም መካከል መቃቃር እና ክፍፍል እያደገ እንዲሄድ በማድረጉ የተወሰኑት ጥለውን እንዲሄዱ እና ከቀረነው ውስጥም ወደ ውጭ የሚመለከቱ እንዲፈጠሩ አድርጎ አንድነታችንን ክፉኛ አዳክሟል የትናንቱ የፖለቲካ መንገዳችን። አዲሱን አምባገነን መንግስት አብዣኛው የአገሪቱ ዜጎች ህጋዊ አድርገው ስለማይቆጥሩት እሱ ስልጣን የጨበጠበትን የመጨራረስ አዙሪት ጉዞ እንድንደግም የሚሰብኩን አዳዲስ ቡድኖች ተፈጥረዋል። የፖለቲካ ትግል ባህላችንም ቢሆን በመገዳደል ደም የተጨማለቀ በመሆኑ የመንግስት ስልጣን የጨበጡት ግለሰቦች ስብዕናቸው የተሟጠጠ ነው። ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ደግሞ በስልጣን ላይ የሚገኙት መሪዎች ፖለቲካ ባህል ከደም መጽዳት እና ስብዕናቸው የተሟላ መሆን ወሳኝ ነው። ባጭሩ ከሶስት ሺ አመቶች በላይ አብሮን የቆየው የፖለቲካ ትግል ባህላችን ከዴሞክራሲ ጋር ጸበኛ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲኽ ግን ህዝባችን የትናንቱን ደም አፋሳሽ የፖለቲካ ትግል ባህል አዙሪት ሰብሮ በመውጣት አዲስ የፖለቲካ ትግል ባህል ጀምሯል። ይኽ አዲስ ክስተት በትልቁ እውቅና እና ድጋፍ ሊለገሰው የሚገባ የፖለቲካ ትግል ባህል እድገት ምልክት ነው። ስልጣኔም ነው። የሙስሊሙ ማህበረሰብ ከአንድ አመት በላይ በበርካታ የኢትዮጵያ ከተሞች ያካሄዳቸው እና ዛሬም የሚያካሂዳቸው በድስፕሊን የታነጹ እንከን የለሽ ሰላማዊ የመብት ትግሎች የፖለቲካ ትግል ባህላችን ማደጉን ያመለክታሉ። መንግስት ለህዝብ ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጥ ጫና ለማድረግ ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 25 ቀን በአዲስ አበባ የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ አጀማመር እና አፈጻጸም የፖለቲካ ትግል ባህላችን ሰላማዊነትን እንደመረጠ ይጠቁማል። በተለይ ‘የሚሊዮኖች ድምጽች ለነፃነት‘ በሚል ቀዳሚ መርህ አንድነት ፓርቲ የኢትዮጵያን ሽብር ህግ እዲሰረዝ እና የህጉ ሰለባ የሆኑት የሰላማዊ ትግል ባህል ሐዋሪያት እንዲፈቱ በመንግስት ላይ ጫና ለማድረግ ሐምሌ 7 ቀን በጎንደር እና በደሴ ከተሞች ያካሄዳቸው ሰላማዊ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች የፖለቲካ ትግል ባህላችን መብሰሉን እና መሰልጠኑን ያመለክታል።
በተጨማሪ ሐሙስ ሐምሌ 12 ደግሞ አንድነት ፓርቲ ከሐምሌ 21 እስከ መስከረም 5 ቀን 2006 ዓመተ ምህረት የሚዘልቁ አዲስ የሚሊዮኖች-ድምጽ-ለነፃነት ዘመቻ ስምሪቶች ይፋ አድርጓል። እነሱም፥ በወላይታ ሶዶ፣ በመቀሌ፣ በድሬ ደዋ፣ በአዋሳ፣ በአምቦ፣ በደብረ ማርቆስ እና በአዲስ አበባ ያቀዳቸው ህዝባዊ ስብሰባዎች እና በባህር ዳር፣ በጅንካ፣ በአርባ ምንጭ፣ በአዳማ፣ በባሌ፣ በወሊሶ፣ በፍቼ፣ በአምቦ፣ በጋምቤላ፣ በአሶሳ እና በአዲስ አበባ ያቀዳቸው ሰላማዊ ሰልፎች ናቸው። እያንዳንዱ ዘመቻ ስኬታማ እንዲሆን እራሳችንን የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሰራዊት አባል አድርገን የምንቆጥር በሙሉ የተቻለንን ያህል ተሳትፎ ማድረግ አለብን።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የአደባባይ ተቃውሞ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ በተካሄዱት ሰላማዊ ትግሎች እርስ በርስ አልተላለቅንም እኛ (The People)። ትምህርት ቤት፣ መንገድ፣ ፋብሪካ አልፈረሰም። ስራ አልተቋረጠም። የአንድነት ፓርቲ መሪዎች ሳይቀሩ በአደባባይ ከህዝብ ጎን ቆመው ሲታገሉ፣ ከህዝብ ጋር ሲታሰሩ እና ሲፈቱ አስተውለናል። አንድነት ፓርቲ አንድ የፓርላማ አባል (ግርማ ሰይፉ) ብቻ ቢኖረውም ካለምንም ስስት እሱንም በደሴው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ አሰማርቶት ነበር። እንግዲህ በአለማችን ታዋቂዎቹ የሰላም ትግል መሪዎች እነ ጋንዲ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ እና ሌሎችም ሌላ ምን አደረጉ? ያደረጉት ይኽንኑ ነበር። ከህዝባቸው ጋር እየታሰሩ እና እየተፍቱ መታገል። የሰላማዊ ትግል መሪዎች ከትግሉ ሂደት ውጭ አይሆኑም። ግባቸው እራሳቸውን መረማመጃ አድርገው ህዝቡን የአገሩ እና የስልጣን ባለቤት ማድረግ ነው። ይኽ የሰላማዊ ትግል ባህል ህዝብን ከማቀራረብ አልፎ የትግል እና የድል ፍሬ ባለቤት ያደርገዋል። ህዝብ መሪዎቹን በቀርብ እንዲያውቃቸው ያደርጋል። እንደ ትጥቅ ትግል የእውቀታቸው እና የአዕምሮዋቸው ጤንነት ደረጃ የማይታወቁ ካለ ህዝብ ተሳትፎ ብድግ ብለው አገር የሚያፈርሱ እንደ መለስ ዜናዊ አይነት መሃይም እና ንክ (እብድ) የትጥቅ ትግል መሪዎች ገዢዎቹ አይሆኑም። አዎ! መሐይም። አዎ! ጥራዝ ነጠቅ ነበር። የአልቤንያ እና የሲቪየት ህብረት አምባገነኖች የጻፉትን የፖለቲካ መመሪያ ቃል በቃል ገልብጦ ኢትዮጵያ ላይ በመድፋት የኢትዮጵያ ህዝብ በሽብር አስፈራርቶ አመራሩን እንዲቀበል ማድረግ አዋቂ መሪ አያደርግም። በአውሮፓ ከተሞች ስለ አየር ጸባይ በእንግሊዘኛ ቋንቋ መናገርም ብቻውን አዋቂ መሪ አያደርግህም። ተሳዳቢነት እና አጭበርባሪነትም አዋቂ አያደርግህም። የአዋቂ መሪ መስፈርቱ ሌላ ነው። የራስን አገር ህዝብ ታሪክ ሳትንቅ በጥልቀት አጥንተህ እና አውቀህ፣ ኢትዮጵያዊ የሆነ የአመራር አሳብ አመንጭተህ፣ ከተቃዋሚዎችህ ጋር አብረህ መስራት ችለህ፣ ቀደም ባለው ታሪካችን የተፈጸሙ ስህተቶችን አርመህ፣ ህዝብን አግባብተህ እና አቀራርበህ ፊቱን ወደ ዴሞክራሲ እና እድገት እንዲመልስ ማድረግ ከቻልክ ብቻ ነው ምናልባት አዋቂ መሪ የምትባለው። መለስ ዜናዊ ግን ችግራችንን አባብሶ ሄደ። የሆነው ሆኖ በጎንደር እና በደሴ እንዳስተዋልነው የአንድነት ፓርቲ መሪዎች እንደ ጋንዲ በህዝባቸው መካከል ሆነው መብት እንዲከበር ታግለዋል። ይኽ ሁኔታ ህዝባዊ ስብዕናቸው እንዲያድግ እንጂ እንዲሟጠጥ አያደርግም። የፖለቲካ ባህላቸውም ከገዳይነት ደም የጸዳ እንዲሆን ያደርጋል። በዚህ አይነት የትግልም ሆነ የድል ባለቤት የሚሆነው እራሱ ህዝቡ ነው። ማለትም በምርጫ የመንግስት ስልጣን ባለቤት የሚሆነው እራሱ ህዝቡ ነው። ስለዚህ ሰላማዊ ትግል እና ዲሞክራሲ የማይነጣጠል ዝምድና አላቸው።
ወሳኙ የውስጥ ትግላችን ነው። ዜናዎች እንደሚያመለክቱት የአውሮፓ ህብረት፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂውማን ራይትስ ዋች፣ ድንበር የለሽ ጋዜጠኞች ሳይቀሩ በኢትዮጵያ ውስጥ መብት ለማስከበር እየተካሄደ ባለው በሳል እና እንከን አልባ ሰላማዊ ትግል ተደንቀዋል። ድጋፋቸውን ለግሰዋል። እየተጠናከረ በሄደ ቁጥር ትግሉ የሚያገኘው ድጋፍ እንደሚጨምር አትጠራጠሩ። እንግሊዝ እና አሜሪካም ለምነውን የሚደጉን ቀን ቅርብ ነው። ወሳኙ የውስጥ ትግላችን መጠናከር እንደሆነ ለአንዲት ደቂቃ እንኳን እንዳንዘነጋ።
ስለዚኽ በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ የምንኖር የሰላም ትግል ሰራዊት እና የዴሞክራሲ አርበኞች ኢትዮጵያውያን በመካሄድ ላይ ያለውን አገር አቀፍ የሚሊዮኖች-ድምጽ-ለነፃነት ዘመቻ በሙሉ ልብ መደገፍ እና መሳተፍ አለብን። እያንዳንዱን ዘመቻ ለማደራጀት (ለማዘጋጀት እና ለማኪያሄድ) ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው። የገንዘብ እርዳታ በማድረግ የዚህ ታላቅ የፖለቲካ ባህል ለውጥ ታሪክ አካል እንሁን! ነፃነት ገፋፊው የሽብር ህግ እንዲሰረዝ እና የህጉ ሰለባ የሆኑት የሰላማዊ ትግል ሐዋሪያት እንዲፈቱ በመንግስት ላይ ጫና ለማድረግ በተጀመረው ዘመቻ ካለ ምንም ስስት እንሳተፍ። በአሳብ ወይንም በገንዘብ! በተለይ በውጭ ያለን ዜጎች ዘመቻውን በገንዘብ በመርዳት ኢትዮጵያ በመስራት ላይ ባለቸው ታሪክ ላይ ማህተማችንን እናስቀምጥ!
በክፍል ሁለት እንገናኝ።
No comments:
Post a Comment