FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Sunday, July 14, 2013

ዓባይን መገደብማ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሕልም ነው! (ሸንጎ)


የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)
ኅምሌ ፭ ቀን ፳፻፭
በስተሰሞኑ ዓባይን አስመልክቶ ህወሓት/ኢህአዴግ በተለመደ ፕሮፖጋንዳው የራሱን ‘አገር ወዳድ ሚና’ በማጉላት ተቃዋሚውን አኮስሶ ለማሳየት የሚያደርገው ጥረት እየተንፀባረቀ ነው። በዓባይ ግድብ ዙሪያም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች የህወሓት/ኢህአዴግ የመገናኛ ብዙሃን መሣሪያዎችና ተባባሪዎቻቸው የሚያናፍሱትን ፕሮፖጋንዳ ሕዝባችን ማዳመጥ ካቆመ ሰንብቷል። ይሁንና በዓባይና በግድቡ ጥያቄ ላይ ለወዳጅም ሆነ ለጠላት ሸንጎው አቋሙን ግልጽ ማድረጉ ደግሞ ተገቢ ነው። ስለዚህ በመጀመሪያ ሸንጎው በግድቡ መሠራት ላይ ያለውን አቋም (ህወሓት/ኢህአዴግም የዓባይ ግድብን ራዕይ ብቸኛ አፍላቂና ባለቤት ነኝ ባይነትና በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በተቃዋሚው ላይ የሚያካሂደው አሉታዊ ቅስቀሳ በተመለከተ እውነታውን ሲያመላክት) ቀጥሎም ሀገራችን ኢትዮጵያ ወንዙን የመጠቀም መብቷን በተመለከተ ግብፅ በሰነዘረችው ማስፈራሪያ ላይ ሸንጎ ያለውን አቋም ያቀርባል።
በግብፅና በአገራችን መካከል በዓባይ ዙሪያ ያለው ግጭት አዲስ አይደለም። ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ የሞከረችውን የጦር ወረራ በተባበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጋድሎ ከሽፏል። በ1876 (እ.ኤ.አ) የተደረገው የመጨረሻ ሙከራም በራስ አሉላ መሪነት ጉርዓ ላይ በተደረገው ጦርነት የግብፅ ጦር ምሱን አግኝቷል። ሆኖም ግን ግብፅ በጦር ግንባር ማሸነፍ ያልቻለችውን እስከ ዘመናችን ድረስ በእጅ አዙር የተለያዩ የውስጥ ተቃዋሚዎችን እያስታጠቀችና የገንዘብ ድጋፍ እየሰጠች እንደ ሻዕቢያና ህወሓት በመሳሰሉ ኃይሎች ኢትዮጵያን ሲታስወጋ ኖሯለች። ዛሬም ወደፊትም መሞከሯ የማይቀር ቢሆንም ሀገራችን ግን ለዘመናት ህልውናዋን አስከብራ ኖራለች።
ኢትዮጵያ ጥንታዊ አገር ናት። ዓባይም ዕድሜ ልኩን በገባር ወንዞቹ እየታገዘ የሀገሪቱ ለም መሬት እየጠራረገ ቁልቁል ሲፈስና ሱዳንንና ግብፅን ህይወት ሲዘራባቸው ኖሯል። በሱዳንና በግብፅ ዓባይ ወንዝ ላይ የተሠሩ ግድቦች ሱዳንንም ሆነ ግብፅን በእርሻ ልማት፣ በዓሣ እርባታ፣ በመጓጓዧ፣ በኃይል ማመንጫነት የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሲያደርግ ኢትዮጵያ ግን በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ድርቅ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝቧ በረሃብ ሲጎዳ እንኳን ወንዞቿን በመገደብ አገልግሎት ላይ ማዋል እንዳትችል በተለያየ አሻጥር ቀጥተኛና የድብቅ ማዕቀብ ሲደረግባት ኖራለች።
ዓባይንም ሆነ ገባር ወንዞቹን በየደረጃው የመገደብና ለኢኮኖሚ ልማት የማዋሉ ራዕይ የብዙ ትውልድ ራዕይ ሲሆን በተለይም ባለፉት ሃምሣ ዓመታት የኢትዮጵያዊ ሁሉ ህልም ነበር።
ባለፉት ዓመታት ውስጥ ያልተመለሰው ጥያቄ ዓባይ እንዴትና መቼ ይገደብ የሚለው ነበር እንጂ ይገደብ/አይገደብ የሚለው አከራካሪ ሆኖ አያውቅም። ህወሓት/ኢህአዴግም “የህዳሴ ግድብ” ሲል፣ ሕዝቡ ያነሳው ጥያቄ ዓባይ ይገደብ/አይገደብ ሳይሆን፣ በእውነት ታስቦበት ነው? ወይስ ሌላው የህወሓት/ኢህአዴግ “ላሞኛችሁ ተከተሉኝ” ዓይነት ጨዋታ ነው? የሚል ጥያቄ ነበር ያስነሳው። ህወሓት/ኢህአዴግ ለከሰረ ፖለቲካው ነፍስ መዝሪያ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ አንጀት ውስጥ ለዘመናት የኖረውን የዓባይን ጉዳይ በማላወስ የፖለቲካ ዕድሜውን ለማራዘም ሌላ መሣሪያ ሊያደርገው ነው ወይ? ነበር ጥያቄው። ይህን ጥያቄ ለመመለስ ደግሞ ህወሓት/ኢህአዴግ የሀገርና የሕዝብን ጥቅም በማስጠበቅ የሚታማ ባለመሆኑ ያከናወናቸውን ኩነታዎች መመርመር ይበቃል። ከብዙዎቹ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ፦
  • ዛሬ ሊወጋን በሚያስፈራራን የግብፅ መንግሥት እየተረዳ ኢትዮጵያን በማዳከምና በመበታተን የትግራይ ሪፑብሊክን ለመመሥረት እታገላለሁ ያለው ህወሓት እንጂ የተቃዋሚው ኃይል አልነበረም።
  • ኤርትራንም ከኢትዮጵያ በማስገንጠል ቁልፍ ሚና ከመጫወት አልፎ ኢትዮጵያ በአሰብ በኩል የባህር በር እንኳን እንዳይኖራት ያስደረገው ህወሓት/ኢህአዴግ እንጂ የተቃዋሚ ኃይሉ አይደለም።
  • ኤርትራን ካስገነጠለ በኋላም ሻዕብያን ለማጠናከር የተቀናጀ የኤኮኖሚና ወታደራዊ ውል ያደረገ፤ ከዚያም አልፎ የ2000 ዓ. ም ከሻዕብያ ጋር በነበረው ጦርነት ፍጻሜ ላይ ኤርትራን ለይቶ የሚጠቅም ውል በአልጀርስ የተፈራረመው ህወሓት/ኢህአዴግ አንጂ ተዋዋሚው አይደለም።
  • የ1600 ኪሎሜትር ርዝመትና ከ30 እስከ 60 ኪሎሜትር ስፋት ያለውን መሬት፤ ለማመን በሚያዳግት መልክ ለሱዳን አሳልፎ የሰጠው ህወሓት/ኢህአዴግ አንጂ ተቃዋሚው አይደለም።
  • በልማት ስም ኢትዮጵያውያንን ከሚኖሩበት ቀዬ እያፈናቀለ መሬታችንን በገፍ ለባዕዳን እየሰጠ ያለው ህወሓት/ኢህአዴግ እንጂ ተቃዋሚው አይደለም።
ስለዚህም ነው ሸንጎው ህወሓት/ኢሕአዴግ በህዳሴ ስም ዓባይን እገድባለሁ ሲል ጥርጣሬ ውስጥ የሚያስገባው፣ አገዛዙ ለሀገር ጥቅም የቆመ ባለመሆኑ።
በተለያዩ ዘርፎች እንደታየው የህወሓት/ኢህአዴግ የገንዘብ ዘረፋ፣ ለግድቡ ተብሎ የሚሰበሰበውን ገንዘብ ለድርጅቱ ሥልጣን ላይ መቆያ በማዋል የግድቡን ጉዳይ አኮላሽቶ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንዳያሳዝን ህወሓት/ኢሕአዴግ የግድቡን አጀንዳ ያነሳበትን እውነተኛ ምክንያት ለሕዝብ ማጋለጥ አስፈላጊ ሆኗል። ይኸውም በዐረብ አገራት ተፈጥሮ በነበረው የሕዝብ መነሳሳት አምባገነናት ሲወድቁ የተመለከተውና የተደናገጠው የአምባገነን ቡድን በድንገትና በጥድፊያ ይፋ ያደረገው የግድብ ፕሮጀክት፣ አወጣጠኑ ግልጽነት የሌለው ከመሆን አልፎ ግንባታውም ተጠያቂነት በሌላቸውና በሙስና በተጨማለቁ የአገዛዙ ባለሥልጣናት የተያዘ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዕለት ጉርሱ እየተሞለቀቀ የሚሰበሰበው ገንዘብ ለህወሓት/ኢህአዴግ ባለሥልጣናትና ለዘመድ አዝማዶቻቸው የአንድ ጀንበር የሚሊዮን ባለሀብቶች መሆንና ለውጭ ባንክ መደለብ ምክንያት መሆኑ ሊታበል በማይችል መልክ እውነታው እየታየ ነው።
ህወሓት/ኢህአዴግ የግድቡን ሥራ እጀምረዋለሁ ባለበት ወቅት በተለያዩ ዘርፎች ዕውቀቱ ያላቸው ባለሞያዎች እንዲያጠኑት፣ ጉዳዩም ለሕዝብ ይፋ እንዲሆንና የመላ አገሪቱ ሕዝብ ሊሳተፍበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን በማመን የሲቪክና የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲመክሩበት እንዲደረግ የማሳሰቢያ ሃሳብ በተቃዋሚው ተደጋግሞ ቀርቦ ነበር።
ህወሓት/ኢህአዴግ ግን ለፖለቲካ ህልውናው አድርጎ የያዘው በመሆኑ የተቃዋሚው ኃይል ግድቡ እንዳይሠራ ይፈልጋል በማለት በስፋት ሊቀሰቅስበት እየሞከረ ነው። የህወሓት/ኢህአዴግ እውነተኛ ዓላማ ከግንቦት 2000 ዓ. ም በኋላ የደረሰበትን የፖለቲካ ክስረት ለመቋቋምና የዐረብ ሕዝብ መነሳሳት ዓይነት ወላፈን እንዳይደርስበት ያቀደው መሣሪያ እንደሆነ ከሚያመላክቱት አካሄዶቹ አንዱም ይኼው ነው።
ለአገራችን የኃይል ማመንጫ የሚውል ከፍተኛ ግድብ መሥራትን ከመደገፍ ወደኋላ ብለን እንደማናውቅ ሁሉ ወደፊትም በትክክል በሥራ ላይ የሚውልበትን ሁኔታ ለመፍጠር የበለጠ እንታገላለን።
በቅርቡ በግብፅ መንግሥትና በተወሰኑ ተቃዋሚዎቹ የግድቡን ጉዳይ አስመልክቶ በሀገራችንና በሕዝቧ ላይ የሰነዘሩትን ዛቻና ማስፈራሪያዎች ሸንጎው በጥብቅ ያወግዛል። ዓባይን የመገደብ ፕሮጀክት አገዛዙ በምንም ምክንያት ይሁን የጀመረው፣ እንዲሁም የፈለገው ዓይነት መንግሥት በግብፅ ቢኖር፣ ግድቡን የመሥራት መብት የላትም ብሎ በኃይልም ሆነ በተጽዕኖ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የሚነሳን ኃይል ሸንጎው አጥብቆ ይኮንናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ተፈጥሯዊ መብቱን ለማስከበር በሚያደርገው ትግል ከጎኑ ሆኖ ይታገላል። ኢትዮጵያውያን የግድቡ ሥራ የማይበጀን መስሎ ከታየን በራሳችን ፍላጎት የመተው መብት እንዳለን ሁሉ ይጠቅመናል ካልን ደግሞ የላይና የታች ተፋሰስ አገሮችን የሚመለከቱ ዓለም ዓቀፍ ሕጎችን አክብረን ግድባችንን የመሥራት መብታችን ደግሞ የተጠበቀ መሆን አለበት።
ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ግድቡን እንዳትገነባ እንቅፋት የሆኑባት ምክንያቶች በቂ የገንዘብና የቴክኒክ አቅም አለመኖር ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ሁኔታውም ግብፅን የሚደግፍ መሆኑም ጭመር ነበር። በእንግሊዝና በግብፅ መካከል የተፈረመው የ1902 ዓ. ም ስምምነትና በግብፅና በሱዳን የተፈረሙት የ1959 ዓ. ም እና የ1992 ዓ. ም ስምምነቶች ኢትዮጵያን ያላሳተፉና የራሳቸውን ሙሉ ጥቅም ብቻ ያካተቱ በመሆናቸው ስምምነቶቹ በኢትዮጵያም ሆነ በተቀሩት የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም። በምትኩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰባት የዓባይ ተፋሰስ አገሮች በቅርቡ ያደረጉት የዓባይ ስምምነት (ትሪቲ) አግባብ ያለውና የሚደገፍ ነው።
በመጨረሻም ሸንጎው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት መቆም እንዳለበትና ወደ ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ ውይይት ማምራት ለአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጅማሮ መሠረት መጣል ብቻ ሳይሆን በዓባይ ግድብ ዙሪያ ግልጽነትና ብሄራዊ ትብብር እንዲኖር፣ የሚያስፈልገውን የገንዘብና የሰው ኃይል አሟልቶ ግድቡን ከአገዛዙ የፖለቲካ መሣሪያነት ወደ ተግባራዊ ፍጻሜ እንዲደርስ ያደርጋል ብሎ ያምናል።
ዓባይን መገደብ በማንም ሊነጠቅ የማይችል ተፈጥሯዊ መብታችን ነው!
ኢትዮጵያ በነፃነት ለዘለዓለም ትኑር!

No comments:

Post a Comment