FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Friday, July 12, 2013

በውኑ ድብኝት ይታጠባልን?


ከገለታው ዘለቀ
አንድ ጊዜ ታዋቂው የሰነ ጽሁፍ ሰው ጋሽ ስብሃት ገብረ እግዚኣብሄር አንዱን እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል::
 “ስራህ ምንድነው?”
“ኤዲተር ነኝ ጋሽ ስብሃት”
“አየ ጉድ! ድብኝት አጣቢ ነኝ አትለኝም”
አገላለጹ በተለይ የኤዲቲንግ ስራ ለሚሰሩ በደንብ ይገባቸዋል፣ ያስቃቸውማል:: ዛሬ ታዲያ ይህቺ አገላለጽ ለጸረ ሙስና ኮሚሽን ስራ ጥሩ ማሳያ ሆና አገኘኋትና ነው መግቢያ ያደረኳት። የጸረ- ሙስና ኮሚሽንም ድብኝት ኣጠባ ላይ መሆኑን ነው የምናየው።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትም ሳይቀሩ ተጠያቂ እየሆኑ ነው የሚል ዜና እየተሰማ ነው። መቼም ለየዋሆች ግራ ለተጋቡ ማለቴ ነው አይ ይሄ መንግስት ሳይቆርጥ ኣይቀርም ባለስልጣኑን ሁሉ ተጠያቂ እያደረገው ነው ሊሉ ይችላሉ። እውነቱ ግን ጸረ- ሙስና ኮሚሽን ከተቋቋመ  ከ2001 ወዲህ ሙስና በተቃራኒው ቀጥ ብሎ እያደገ ነው የመጣው። ይህ ተቋም በርግጥ በሃገሪቱ የተንሰራፋውን ከፍተኛ ሙስና ሊቀንሰው ያልቻለበት ኣንዱ ትልቁ ምክንያት የሙስናው ባህርይ የተለየ በመሆኑም ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ  ያለው የሙስና አይነት ከዚያም ከዚህም ትንሽ ትንሽ ቦጭቅ(competitive) አይነት ሳይሆን ጎልቶ የሚታየው የጠቅልል ሙስና(monopolistic corruption) አይነት  ነው። በብዙ አገራት የሚታየው የትንሽ ትንሽ ቦጭቅ (competitive-like) ሙስና በኢትዮጵያ ውስጥ ጎልቶ ኣይታይም። አንደሚታወቀው በተለይ በታችኛው ርከን ላይ ያሉትን ባለስልጣናት ኢህኣዴግ በከፍተኛ አውጫጭኝ ( “ግምገማ” ) ወጥሮ የያዛቸው ሲሆን ቢቻል ኣንድም ሳንቲም እንዳይነኩበት ይታገላል። እነዚህ ሰዎችም በአብዛኛው በፍርሃት የሚኖሩ እንዴውም ኢህኣዴግ አንድ ቀን ብሽ ሲለው በቀላሉ የሚወረውራቸው በመሆናቸው ለሙስና የሚደፍሩ አይደሉም።ለነሱ ስልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ናት። በመካከል ያሉትም ቢሆን እንዲሁ በግምገማ ተወጥረው የተያዙ ናቸው።
ኢህኣዴግ ይህን የሚያደርገው ለሃገር ሃብት አስቦ ሙስና እንዳይስፋፋ ተጨንቆ አይደለም። ይልቁን የሙስናው ባህሪ ሞኖፖሊስቲክ በመሆኑና ሁሉንም እኔ ላጋብሰው ከሚል ስሜት የመነጨ ነው።ይህ ኣይነቱ የሙስና አይነት ደግሞ  በአንድ ልፍስፍስና ነጻ ባልሆነ ተቋም ከቶውንም ሊጸዳ አይችልም። ምክንያቱም የሙስናው ባህርይ ራሱ ተቋማዊ ይዘት ስላለው የሚደፈር ኣይሆንም።
በመሰረቱ ይህ ተቋም ሲቋቋም ጀምሮም ሙስናን ለመቀነስ ሲሰራም አይታይም።ከፍ ሲል አንዳልነው እንዴውም የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ኣመታዊ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ይህ ተቋም ከተመሰረተ ጀምሮ ሙስና ማደጉን ነው የሚያሳየው። ይህ የሚያሳየው ደሞ በርግጥ እውነተኛ ስራው ላይ እንዳልሆነና ይልቁንም መንግስት ያበሸቀውን ሰው ሲስተማቲክ በሆነ መንገድ የሚቀጣበት ኣንድ ተጨማሪ ተቋም ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ያለው የጠቅል ሙስና በሌሎች ሃገሮች እንዳለ የሙስና አይነት ጉዳቱ አንድ ኣቅጣጫ ብቻ ኣይደለም ያለው። ይህ የሙስና አይነት ሲጠናከር አንድ ከፍተኛ የመጨቆኛ መሳሪያ ይሆናል። አብዛኛውን ማህበረሰብ በኢኮኖሚ ከመጉዳቱም በላይ ለውጥ እንዳይመጣ የህዝብን ድምጽ ለማፈን ትልቅ መሳሪያ ነው። ከሁሉ የከፋው ጉዳትም ይሄ ነው።
መንግስት ራሱ የጦፈ ነጋዴ በሆነበት አገር፣ቡድኖች ያገኙትን ሃብት የባህላዊ ቡድናቸው ሃብት ነው ብለው በሚያስቡበት አገር ይህ ኣይነት የሙስና እድገት ከፍተኛ ችግር ነው። ዛሬ ኤፈርት ነው አንዱ የሃገሪቱን ሃብት ይዞ ያለው። ይህ ድርጅት በፊት በጦርነቱ ጊዜ በኢትዮጵያዊያን ስም የተገኘ፣ ከኢትዮጵያ ባንኮች የተዘረፈ ሆኖ ሳለ ንብረትነቱ የኣንድ ቡድን ብቻ ነው መባሉ ራሱ በራሱ ሙስና ነው። ዋናው ጥያቄ ኤፈርትን አንዳንድ ሰዎች እየበዘበዙት ነው ሳይሆን ራሱ ድርጅቱ በተፈጥሮው ሙሰኛ ነው። የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚመሩት፣ የኢትዮጵያዊያን ሃብት መሆኑን የካደ ድርጅት የሙሰኛች ሙሰኛ ነው።
ችግሩ እዚህ ድረስ ብቻ ሳይሆን ኤፈርትን ለዚህ ያበቃው ደሞ የታችኛው የፖለቲካው ቅርጽ(deep structure) ነው። ፖለቲካው ራሱ መገንጠል ዋስትና ነው ብሎ የሚያምን፣ ሁሉም ወደየጎጡ እንዲሮጥ የሚገፋ በመሆኑ የሙስናው ወለል ይህ የፖለቲካ ቅርጽ ነው። ይህ ደሞ በጸረ ሙስና ኮሚሽን የሚፈታ ሳይሆን በስርዓት ለውጥ ነው የሚፈታው።  የኢትዮጵያ የሙስና ጥያቄ ጉዳይ እከሌ ይህን ያህል ብር ወስዱዋል እከሊት ይህን ያህል በሚል ሳይሆን ራሱን የበሰበሰውን ለሞኖፖሊስቲክ ሙስና በር የከፈተውን ስርዓት መለወጥ ነው ፈውሱ።እነዚህ በከፍተኛ ሙስና የተመሰረቱና የሚኖሩ ድርጅቶች ደግሞ ከግለሰብ ብልጽግና ፍላጎት የዘለለ የቡድንተኛነት ስሜት ያላቸው በመሆኑ ሲበዛ ስግብግብ አድርጓቸዋል። የሃገሪቱ አጠቃላይ ሃብት GDP ሲታይ በየአመቱ እድገት የሚታይ ሲሆን ይህ እድገት ግን በሲቪል ሰርቫንቱ፣ በገበሬው ባጠቃላይ በአብዛኛው ህዝብ ላይ አለመታየቱ የሚያሳየው ነገር ሙስናው ጠቅልል መሆኑን ነው። እንደ UNDP የኢትዮጵያ GDP  በየአመቱ ያድጋል። በአንጻሩ የሙስና መለኪያዎች ደግሞ ሙስና በያመቱ እያደገ መሄዱን ያሳያሉ። የነፍስ ወከፍ ገቢም ሲባል መኖሪያ የሌለውን ጦሙን አዳሪውን ዜጋ  በሙስና ሰማይ የደረሱ ሰዎች ገቢ ጋር ይደመርና ለሁለቱም ተካፍሎ ለጭቁኑ ይህን ያህል ነው የነፍስ ወከፍ ገቢህ ተብሎ ይፈረድበትና ቁጭ ይላል።ያላየውን ያልበላውን ድሃ እንዲህ ይፈረድበታል።ይሄ የራሱ የቀመሩ ውሱንነት ሳይሆን ዋናው ችግር የስርዓቱ ሙሰኛ መሆን ነው። በሙሰኛ ስርዓት ውስጥ ከባድ የገቢ ልዩነት በመኖሩ ይህ የነፍስ ወከፍ ገቢ መለኪያ ከእውነቱና ከፍትህ ደጅ በጣም ይርቃል።
የተስፋፋው የሞኖፖል ሙስና የግሉን ሴክተር ኣክርካሬ አድቆ ይታያል። በሌላ በኩል ስለ ሙስና ስናወራ በገንዘብ ብቻ አይደለም የሚገለጸው። የመሬት ነጠቃው ራሱ አንዱ ከፍተኛ የሙስና ስራ ነው። ዜጎች በማያውቁት ውል መንግስት ብቻውን እየተዋዋለ ሰፋፊ እርሻዎችን እየሰጡ ነው። ባንድ በኩል ተርበናል እየተባለ ስንዴ ከውጭ እየለመንን በሌላ በኩል አገር ቤት እህል እየተመረተ ወደ ውጪ ይሄዳል። ይሄ ነው እንዴውም ከባዱ ሙስና።
ለመንግስት የምንለው ይህንን ነው። ኢትዮጵያዊያን ለውጥ እንፈልጋለን፣ ድብኝት ኣይታጠብም! ይህን የተበላሸ ሙሰኛ ፖሊሲ የሚያጥበው ደግሞ የህዝብ የተቃውሞ ጎርፍ ነው። ይህ ጎርፍ ሲመጣ በርግጥ ስርዓት ለውጦ በተሻለ ስርዓት ይተካል። በኢትዮያም ይህ ነገር በቅርቡ እውን መሆኑ አያጠያይቅም።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

No comments:

Post a Comment