የ ኢህአዲግ ኢ-ሳይንሳዊ የ ልማት ፖሊሲ
- የ አቡነ ጴጥሮስን እና የ አፄ ምኒልክን ሃውልት ማፍረስ የ ኢህአዲግ የ አዲስ አበባ 125ኛ አመት በዓል ስጦታ!
ልማት (development) የ አለም አጨቃጫቂው ፖለቲካዊ ቃና የተላበሰ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል። የ አለማችን ፖለቲካዊም ሆኑ ማህበራዊ ኩነቶች የተቀየሩት በ ልማት ዙርያ ከተነሱ የ ፍልስፍና አስተሳሰቦች መሆናቸውን ምንጊዜም መዘንጋት የለብንም። ከኢንዱስትሪው አብዮት በሁዋላ የተነሱት የ ካፒታሊስቱ እና የ ሶሽያልስቱ ጎራዎች የ ሀገሮችን ጆግራፊ የቀየሩት፣አዳዲስ ሃያላን መንግስታትን ያወጡት ከ ልማት ጋር በሚነሱ ፍልስፍናዎች ተሞክሮዎች እና የ ልማቱ ፍልስፍና የሚወልደው የ ፖለቲካ ስርዓት ሳብያ ነበር።የ ካፒታሊስቱ አለም የ ግል ሃብትን መሰረት ያደረገ የ ኢኮኖሚ መንገድን ሲያበረታታ ከ ጎን ዲሞክራስያዊ አሰራሮችን ይሆናል ባለው መልኩ እያደራጀ ነበር። አሁን በምንኖርበት አለም የ ምዕራቡ አለም አንድ አይነት የ ካፒታሊስት ፖለቲካ የሚከተል ከመሰለን ተሳስተናል። የ ግራ ዘመሙ፣የሶሻል ዲሞክራቱ፣ሙሉ ሊበራሉ ወዘተ መጥቀስ ይቻላል። በ ልማት ስም ህዝቦች ነፃነታቸውን አጥተዋል ፣ ለ እጅ አዙር ቅኝ ግዛት ተዳርገዋል፣የረቀቀ ደባ ተሰርቶባቸዋል። በ አለም ባንክ እና በ ታዳጊው ዓለም በ 1980ዎቹ እና 1990ዎቹ ተነስቶ የነበረው ውዝግብ ተጠቃሽ ነው። የ አለም ባንክ የ ታዳጊውን አለም የልማት መርሃግብር ከመቅረፅ ጀምሮ እስከ ማከናወን ድረስ በኃላፊነት ካልሰራሁ ያለባቸው፣ ይህንኑ ተከትሎ ብዙ የማህበራዊ እና የ ኢኮኖሚ ቀውሶች መከተላቸው ይታወሳል። በተለይ ከ ልማት ድርጅቶች የ መዋቅር ለውጥ (Structural Adjustment Policy) ጋር በተያያዘ ብዙ ሰራተኞች ከስራ እየተፈናቀሉ ለ ከፍተኛ ችግር ተዳርገው የነበረ መሆኑ አይዘነጋም።በተቃራኒው ግን በ አደጉት ሀገሮች መንግሥታት ለ ዜጎቻቸው የ ሥራ ዋስትና ለመስጠት ብዙ ሲጥሩ ይስተዋል ነበር። ሥራ ያላገኙቱ የ ማህበራዊ ዋስትና ስለተዘጋጀላቸው በ እዚሁ እንዲረዱ ይደረግ ነበር። አሁንም እየተሰራበት ነው። የ ፕሬዝዳንት ኦባማ ካፒታሊዝምም በ ምርጫ ውድድሩ አሸናፊ የሆነው የ እሳቸው የ ልማት እቅድ በ መካከለኛ እና በ ዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኘውን ሕብረተሰብ የሚደግፍ ለምሳሌ የ ጤና ዋስትና እና የ ታክስ ማሻሻያዎችን የያዘ ስለነበር ነው። ልማት ከ እቅዱ ጀምሮ እንዲህ ያነጋግራል፣ያፋትጋል። ምክንያቱም ልማት ልማት በ መሆኑ ብቻ ሊደገፍ አይችልም። ይዞ የሚመጣው ቀውስ አብሮ ተመዝኖ ብቻ ይፀድቃል።ለምሳሌ ልማቱ የ ሕዝቡን ማህበራዊ፣ሃይማኖታዊ እና ቁሳዊ መብቱን እና መገለጫዎቹን ከ ጎዳ ልማት ሳይሆን ለጊዜው የተሻለ ቃል ባላገኝለትም ጥፋት የሚለው ስም ግን ይስማማዋል።
ሁለቱ ሳይንሳዊ የልማት መሰረታዊ መርሆዎች ልማት ከ ስር ወደ ላይ መከናወን አለበት (development from bottom to top) ከስር የ ልማቱን ችግር የሚያውቀው ሕዝብ የ ልማቱ ሃሳብ አመንጪ መሆን አለበት። ኤክስፐርቶች ቢሮ ቁጭ ብለው የሚቀርፁት ልማት እታች ካለው ማህበረሰብ ጥያቄ ጋር የማይገናኝ የሚሆንበት ብዙ አጋጣሚ አለ። በመሆኑም ልማት ሲታቀድ ቢቻል ከ ህዝቡ ጋር የተለያዩ መድረክ አዘጋጅቶ ከ እቅዱ ጀምሮ እንዲያውቀው ማወያየት እና እቅዱ መስተካከል ካለበት እየተስተካከለ እንዲሄድ የ ልማት ሳይንሱ ያዛል። ”የ ልማት ሂደት ከ ስር ወደላይ የሚመጣ ግብአት አለው።ከ ታች ከ ህዝቡ የሚገኘው ግብአት እና መረጃ ለ ልማት ስትራቴጂው አስፈላጊ ነው።” (Develop process which has bottom up input – The information and input from the people on the ground are important to the development of the strategy) ‘Economic Theory and Sustainable Development, by Vincent Martinet,April 2012.
ልማት ሕዝቡን ማሳተፍ አለበት (Participatory development ) ልማት የምሰራው ሕዝብ ነው ። የ ሕዝብ አዎንታ የሌለበት ልማት ዛሬ ቢሰራ ነገ እንክብካቤ በማጣት ወይም ሆን ተብሎ በ ህዝቡ እንዲፈርስ ይደረጋል።ታንዛንያ ውስጥ አንድ ግብረ-ሰናይ ድርጅት የሰራው ሥራ ብዙ ጊዜ በ ልማት ባለሙያዎች ይነገራል። ድርጅቱ በ አንድ ገጠራማ የ ታንዛንያ መንደር የ ውሃ ጉድጉአድ ለመቆፈር ያቅድ እና ከ ነዋሪዎቹ የ 10 ደቂቃ እርቀት ላይ ውሃውን ለማውጣት በ አካባቢው ያለውን ትልቅ ዛፍ ይቆርጣል፣ ቀጥሎም ውሃው ይቆፈር እና ይወጣል። ከ እዚህ በፊት የመንደሩ ነዋሪ ውሃ የሚያገኘው ከ አንድ ሰዓት በላይ ተጉዞ ነበር እና በ ሪፖርቱ ላይ ትልቅ ስኬት መስራቱን ለዋናው ቢሮ ይነግራል። ውሃው ከተመረቀ ቀጥሎ ባሉት ቀናት ግን አሁንም የመንደሩ ሰዎች በቅርባቸው ያለውን ውሃ ትተው ድሮ ይጠጡት የነበረውን ቆሻሻ ውሃ ከ አንድ ሰዓት በላይ ሄደው መቅዳታቸውን ቀጠሉ። ጉዳዩ ሲጠና ለካ ድርጅቱ የቆረጠው ዛፍ ከ አያቶቻቸው ጀምሮ ያመልኩበት የነበረ እና አሱ ተቆርጦ የምንጠጣው ውሃ ‘ቅስፈት’ አለው ስለሚሉ ነብር። ለምን መጀመርያ አልተናገራችሁም ሲባሉ መልሳቸው ”ማን አማከረን? ባለሙያዎቹ ቀን ሲሰሩ ውለው ማታ ወደ ከተማ ሄደው ነው የሚያድሩት።” ብለው መለሱ። ልማት የ ህብረተሰቡን መልካም እሴቶች፣ሃይማኖት፣ታሪክ እና ባህል ካላከበረ ልማት ሊባል አይችልም። የኢህአዲግ ኢ-ሳይንሳዊ የልማት ፖሊሲ ከላይ ለማውሳት አንደሞከርኩት የ አለማችን ታሪክ በ ልማት እና እድገት ዙርያ (እዚህ ላይ ልማት የሚለው ፅንሰ ሃሳብ እንደየዘመኑ የተለያየ ስም የነበረው መሆኑን ሳንዘነጋ) ፖለቲካዊ ፍልስፍናዎችን እየፈጠረ ይኑር እንጂ በተለይ አሁን ባለንበት ዘመን የ ልማት ስራዎች አተገባበር በተለይ የ ፕሮጀክት አቀራረፅ እና ማሟላት የሚገባቸው ነጥቦች ላይ ብዙም ክርክር የለም።ምክንያቱም ሳይንሳዊ መልክ በመያዙ እና አንዱ ካንዱ ተሞክሮ እያገኘ በመሆኑ ነው።በተለይ ልማት ከ ታች ወደ ላይ እና ህዝብን ያሳተፈ የሚሉት መሰረታዊ እና ቁልፍ ተግባራት ምሁራን የሚስማሙበት ፅንሰ ሃሳብ ነው። የ ኢህአዲግ ኢ-ሳይንሳዊ የ ልማት ፖሊሲን ከ አንድ የ ልማት ፕሮጀክት አተገባበር ጋር እንዴት አንደሚጣረስ እንመልከት። ኢህአዲግ ”ልማቱን እኔ አውቅልሃለሁ ” የሚል መንገድ ከመቀጠሉ እና የሚሰራው ሥራ ሁሉ በ ቢሮው ካድሬዎች እና ”እበላ ባይ ምሁራን ” በሚቀርፃቸው ፕሮጀክቶች ሀገሪቱን ወደ አደገኛ መንገድ እየመራት ይገኛል።”ዋናው ነገር ይልማ” የማይባልበት ዘመን ላይ መሆናችንን ማወቅ አለብን። የ ልማት ፕሮጀክቱ ልከለስ፣ሊስተካከል ወይንም የ ህዝብን ይሁንታ ማግኘት መቻል አለበት። ኢህአዲግ የልማት አጠገባበሮችን በ ሳይንሳዊ መንገድ መስራት ቀርቶ የሚከተሉትን የ አንድ ፕሮጀክት መገምገምያ ሰነድ ያላሟላ አሰራር ይታይበታል። -ልማቱ ህዝብን ያከበረ ልማት ነው? -ዘለቀታነት አለው ? -የሀገሪቱን ጥቅም ለ ጉዳት ይሰጣል? -ሕዝብ ተወያይቶበታል? -የ ሕዝቡን ባህል፣ታሪክ እና የ ሀገሪቱን አሻራ ያፈርሳል? እና ሌሎችም ጥያቄዎች የ ኢህአዲግ የ ልማት ፕሮግራም ለመመለስ ሞራላዊ ብቃት የለውም። ለ እዚህም ማስረጃ የሚሆነው ለ ልማት ሥራ እያለ በ ዋልድባ ገዳም ይዞታ ላይ ፣በ አፋር ሕዝብ ይዞታ ላይ፣በ ጋምቤላ ገበሬዎች፣በ አዲስ አበባ በ ሺህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ከመኖርያቸው በ ህገወጥ ስም ማፈናቀል ወዘት የተፈፀሙት ግፎች የ ልማትን መሰረታዊ ሳይንስ የጣሰ ድርጊት ብቻ ሳይሆን የ ልማቱን ግብ እና ፍላጎት በደንብ ለመጠየቅ የሚያስገድድ ወቅት ላይ መሆናችንን የሚያመለክት ነው። አንድ የ ልማት ፕሮጀችት ትክክለኛ ነው ተብሎ የሚረጋገጠው ውጭያዊም ሆነ ውስጣዊ አካባቢያዊ ሁኔታዎችን ያስማማ ሲሆን ብቻ ነው።ከ እዚህ ውጭ ፕሮጀክት ሌላ ተልኮ ከሌለው በስተቀር ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ ሊቀየር አይችልም። የ ጉልበት ፕሮጀክት የሚሰራው በ ጦር ሜዳ ብቻ ነው። የ ልማት ፕሮጀችት የ ሁሉንም ይሁንታ እስኪያገኝ ይቆያል።
የአቡነ ጴጥሮስን እና የአፄ ምኒልክን ሃውልት ማፍረስ የኢህአዲግ የአዲስ አበባ 125ኛ አመት በዓል ስጦታ ኢህአዲግ ባለፈው ዓመት በዋልድባ ፣በ አፋር፣በጋምቤላ ወዘተ ዘረጋሁት ባለው ፕሮጀክት ከ ሕዝብ ጋር ሲጋጭ ከርሞ ዘንድሮ ደግሞ የተለመደ ኢ-ሳይንሳዊ ፕሮጀክቱን ይዞ ብቅ አለ። የ አቡነ ጴጥሮስ እና የ አፄ ምኒልክን ሃውልት አፍርሼ ባቡር እንዲሄድ አደርጋለሁ። የ እዚህ አይነት ውሳኔ በሰለጠነው አለም በተለይ የነበረ የ ታሪክ ቅርስን ማበላሸት፣ቦታውን መቀየር፣ወዘተ ከፍተኛ በ ሕዝብ ላይ የተሰሩ ውነጀሎች ውስጥ ስለሚካተት ፓርላማው ድረስ ቀርቦ ከፍተኛ ውሳኔ የሚሰጥበት ብሎም ለከባድ ቅጣት የሚዳርግ ድርጊት ነው። አቡነ ጴጥሮስ ተደብድበው በሞቱበት ቦታ ላይ ሃውልት መሰራቱ ታሪካዊ ክስትቱ ከ ቦታው ጋር ስለሚዛመድ እንጂ ወደፊት ኢትዮጵያ ባቡር እንደሚኖራት አፄ ሀይለስላሴም አጥተውት አልነበረም። የ ግራዚያን ሃውልት እና መናፈሻ ሲሰራለት ኢትዮጵያውያን በ እየ አደባባዩ ሲቃወሙ ቃል ያልተነፈሰው ኢህአዲግ ዛሬ ጣልያንን ሊያስደስት የ አቡነ ጴጥሮስን እና የ አፄ ምኒልክን ሃውልት ላፈርስ ነው ብሎ መናገር ደረጃ መድረሱ አስገራሚም አስደናቂም ነው።
የአቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ደራሲና ገጣሚ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን እና ”ጴጥሮስ በዚያች ሰዓት” ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን አምቦ ተወልደው ጀነራል ውንጌት ትምህርት ቤት የመጀመርያ እና የ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው በሀገር ውስጥ የ ቀድሞው ”ኮሜርስ ” የ አሁኑ የ አዲስ አበባ ንግድስር ኮሌጅ በ ንግድ ሥራ ተመርቀዋል። በውጭ ሀገር ከ ለንደኑ ”ሮያል ኮርት ትያትር” እና ፓሪስ ከሚገኘው ”ኮመዴ ፍራንሴ ” ከተሰኙት ዩንቨስቲዎች በ ትያትር ሙያ እውቀት የቀሰሙ ስሜ ጥር ገጣሚና ደራሲ ነበሩ። ። ደራሲና ገጣሚ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ”ጴጥሮስ በዚያች ሰዓት” ለሚለው ድርሰታቸው ምክንያት የነበረው ምን እንደነበር ነፍሱን ይማረው እና ጋዜጠኛ ታምራት ታደሰ አንድ ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር :- ” ፒያሳ ከ ራድዮ ጣብያው ወደመርካቶ መውረጃ ሳይታጠፍ ቁምጣውን እንዳደረገ ታዳጊው ወጣት በንዴት አንድን ሰው ተመለከተ ሰውየው ሰክሮ በተኮላተፈ አንደበት ‘አንተ ሃውልት ምን ተገትረህ ታየኛለህ እኔ ሰማይ ምድሩ ዞሮብኛል አንተ ታየኛለህ? እንዳውም ሽንተን የምሸናው አንተ ስር ነው ።’ ብሎ ሽንቱን ለመሽናት ሲመቻች ታዳጊው ወጣት ከመንገዱ ጌታ አደረገ እና ድንገት ደርሶ በ ጡጫ የመታው እና ይወድቃል ከላይ ቆሞ አንተ ውሻ ! ዛሬ በነፃነት እንደፈለክ የምታወራው እሱ ባፈሰሰው ደም ነው።” እልህ ቁጣ በተቀላቀለበት ስሜት በ እንባ እየታጠበ መናገሩን ቀጠለ- ወጣቱ። ሰው ተሰበሰበ ምክንያቱን ጠየቀው ገላጋይም በዛ። ወጣቱ ተናገረ ”እኔ በሕይወት እያለሁ በ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ስር ሽንቱን አይሸናም።” ያንጊዜ እንባ እየተናነቀው የተናገረው ወጣት ታላቁ ደራሲና ገጣሚ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ነበር ።የዝያን ጊዜው ወጣት አደገ እና ለ ኢትዮጵያ ደረሰላት እና ”ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት” የሚል ተውነት ደረሰ እና በ ሀገራችን የ ትያትር መድረኮች ብዙዎቻችንን ሲያስለቅሰን ኖረ። ተውኔቱ በጣልያን ጊዜ የነበሩ የ አርበኞች ተጋድሎ እና የ አቡነ ጴጥሮስን ሰማዕትነት፣ፅናት እና ተጋድሎ ልክ በቦታው የነበሩ ያህል ያሳያል። ሎሬት ፀጋዬ ሀውልቱ ስር ሽንቱን የሸናውን ሰው የተቃወሙት ኢትዮጵያዊነት ውስጣቸው ስለተንተከተከ ነው።ዛሬ ሐውልቱን ለማፍረስ ኢህአዴግ ቀናት ሳይሆን ሰዓታት እየቆጠረ መሆኑን እየነገረን ነው። አዲስ ነገር እያመጣ የ ሕዝቡን አይምሮ ወደ አዲስ ነገር እየቀየረ ያለ እና ሕዝቡን በ ልማት ስም እየከፋፈለ፣ከመከፋፈሉም የተጠቀመ የመሰለው ኢህአዲግ ከመቸውም ጊዜ በላይ በ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ላይ ማንነቱን የነገረን ለመሆኑ ግን ጥሩ ማሳያ ነው።
No comments:
Post a Comment