ህዳር ፲፭ (አስራ አምት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ከፒያሳ ተነስቶ፤ በመርካቶ በኩል አቋርጦ አብነት በታች የሚገኘው የኮካ ኮላ ፋብሪካ ጋር ይደርሳል ተብሎ የታሰበው የመጀመሪያው የባቡር ሃዲድ ዝርጋታ፣ በአጼ ኃይለ-ስላሴ ዘመነ መንግስት የተተከለውን የብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ለዘመናት ከነበረበት ስፍራ በቅርቡ እንደሚነሳ የአዲስ አበባ መስተዳድር አስታውቋል።
ምንም እንኳን አሁን በይፋ ባይገለጽም የደብረ-ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት የሚገኘው የአጼ ምኒልክ ሃውልትም ከዚሁ የባቡር ሃዲድ መስመር ስራ ጋር በተያያዘ ካለበት ቦታ ሳይነሳ እንደማይቀር ውስጥ አዋቂዎች እየተናገሩ ናቸው።
በ1928 ዓ.ም የፋሺሽት ኢጣሊያ ጦር አገራችንን በዕብሪት በወረረበት ወቅት በዱር በገደሉ የሚዋደቁት አርበኞችን በማበረታታትና በመደገፍ የሚታወቁት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ በኢጣሊያ ጦር ላይ የሚነዙትን የማጥላላት ስብከት በማቆም ለወራሪው ጦር እንዲያድሩ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ባለመሆን “ፋሺሽቶች ያገራችንን አርበኞች ሽፍታ ቢሉ እውነት እንዳይመስላችሁ፣ ሽፍታ ማለት ያለ አገሩ መጥቶ የሰው አገር የሚወር ይህ በመካከላችሁ የቆመው አረመኔው የፋሺሽት ጦር ነው። እንኳን የኢትዮጵያ ሕዝብ ምድሪቱ ለኢጣሊያ እንዳትገዛ አውግዣለሁ!” በማለት ሰኔ 21 ቀን 1931 ዓ.ም በግፍ በመትረየስ የጥይት እሩምታ ተድብድበው የተገደሉት፣ ይኸው አሁን እንዲነሳ ከተወሰነበት ሃውልታቸው ቆሞ ከሚገኝበት ስፍራ ላይ ነው።
ጉዳዩን በማስመለክት በሚጽፋቸው ጽሁፎችና በሚሰጣቸው አስተያየቶች ብስለት ከፍተኛ እውቅና ያተረፈው ዲያቆን ዳንኤል በብሎጉ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ ” ይህን ታሪክና ቅርስ እያጠፉና እያበላሹ የሚመጣ ለውጥ አንገት ቆርጦ ፀጉርን እንደማስተካከል ነው የሚቆጠረው፡፡ እናም የሚመለከታቸው ሁሉ ወደ ርምጃ ከመግባታቸው በፊት ሦስት ጊዜ ሊያስቡ ይገባል፡፡ መቼም የመጀመርያውን ባቡር ያስገቡትን የዐፄ ምኒሊክን ሐውልት አፍርሶ ባቡር እናስገባ ማለት የታሪክ ምጸት ነው፡፡ ለነጻነት የተሠውትን የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ነቅሎ በባቡር ላይ በነጻነት ለመሄድ መከጀል ግፍ መሥራት ነው የሚሆነው፡፡” በማለት ድርጊቱን ነቅፎአል።
ዲያቆን ዳንኤል ለኢሳት እንደገለጸው በተለያዩ አገሮች ሀውልቶች አደጋ ላይ እንዳያወድቁ እንደሚነሱ ገልጾ፣ በሀውልቱ ዙሪያ በቂ መረጃ ባለመሰጠቱ ጥርጣሬ እንዲያደርግበት እንዳደረገው ገልጿል ( 01፡19- 3፡10)
የባቡር ግንባታው ከተጠናቀቀ በሁዋላ ሀውልቱን ሌላ ቦታ ላይ ለማቆም መንግስት ቢፈልግ፣ ችግር ያመጣል ወይ በማለት ለቀረበለት ጥያቄ ዲያቆን ዳንኤል፣ ሀውልቱ የተተከለበት ቦታ አቡኑ የተሰውበት ቦታ በመሆኑ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ወስዶ መትከሉ ታሪካዊ ፋይዳውን እንደሚያደበዝዘው ተናግሯል ( 4፡00-05፡07 )
መንግስት ለኢትዮጵያ ቅርሶችና ታሪክ ተገቢውን ክብር አይሰጥም እየተባለ ይተቻል፣ ሀውልቱን ለማንሳት የተፈለገው ከዚህ አንጻር ይሆን ተብሎ ለተጠየቀው ዲያቆን ዳንኤል ሲመልስ ” አይመስለኝም፣ በባለስልጣናት መካከል በተፈጠረ አለመናበብ የተፈጠረ ችግር ይመስለኛል” በማለት መልሶአል ( 06፡07- 07፡41 )
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን “ቅዱስ” የተሰኙት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ ከተወለዱበት ፍቼ ከተማ ላይ በስማቸው ቤተክርስቲያን እንደተተከላቸው ይታወሳል በማለት ቅዱስ ሀብት በላቸው ከአውስትራሊያ ዘግቧል።
No comments:
Post a Comment