ህዳር ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የሙስሊም ኢትዮጵያውያንን ሰላማዊ ተቃውሞ በመምራታቸው በሽብርተኝነት ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት የድምጻችን ይሰማ የአመራር አባላት ዛሬ ልደታ በሚገኘው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቢቀርቡም ለህዳር 27 ቀን 2005 ዓም የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ወደ እስር ቤት ተመልሰዋል።
የኮሚቴ አባላት ጠበቃ የሆኑት አቶ ተማም አባቡልጋ ለኢሳት እንደገለጡት የዛሬው ችሎት አቃቢ ህግ በጠበቆች በኩል ለቀረበው መቃወሚያ መልስ ለመስጠት ተብሎ የተቀጠረ ነበር። አቃቢ ህግ መልሱን በንግግር ለፍርድ ቤት ማቅረቡን የገለጡት አቶ ተማም ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን መከራከሪያ ሰምቶ ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ቃላቸውን ይስጡ አይስጡ በሚለው ላይ ውሳኔ ለማስተላለፍ የፊታችን ሀሙስ መቀጠራቸውን ተናግረዋል።
አቶ ተማም እንዳሉት ፍርድ ቤቱ በመጪው ሀሙስ ክሱ እንዲቀጥል፣ እንዲሻሻል፣ ወይም ውድቅ እንዲሆን ብይን ይሰጣል።
ጠበቆች ባለፈው ሳምንት ባቀረቡት መቃወሚያ በአቃቢ ህግ የቀረበው ክስ ህገመንግስቱን የጣሰና በርካታ የህግ እጸጾች ያሉበት ነው በማለት መገልጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለኮሚቴ አባላቱ ድጋፋቸውን ለመስጠት ወደ ልደታ ያቀኑ ሙስሊሞች በፖሊሶች መባረራቸውን አንዳንዶችም በፖሊስ መኪኖች ተጭነው መወሰዳቸው ታውቋል።
ጉዳዩን በማስመልከት በአካባቢው የነበሩ የተለያዩ የእስልምና እምነት ተከታዮችን አነጋግረን እንደተረዳነው ፖሊሶች እናቶችን ብቻ በመለየት እየደበደቡ ወደ እስር ቤት ውሰደዋቸዋል
ሌላ ሙስሊም በበኩሉ ” ወንዶችን ቢደበድቡ የተለመደ ነው፣ እናቶችንና እህቶቻችንን መደብደባቸው ግን ሊወጥልን አልቻለም” ብሎአል
የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ እንደቀጠለ ባለበት በዚህ ጊዜ መንግስት፣ ኮሚቴ አመራሩን የሚያወግዙ ሰልፎችን በተለያዩ ከተሞች እያዘጋጀ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።
በኦሮሚያ ክልል አዳማን ጨምሮ በተለያዩ ዋና ዋነ ከተሞች ለማዘጋጀት የኮሚቴ አባላት መዋቀራቸውን ለማወቅ ተችሎአል።
No comments:
Post a Comment