ህዳር ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በራያና አዘቦ ፣ በአላማጣ ከተማ ከኤልክትሪክ መስመር መቃጠል ጋር በተያያዘ በጥርጣሬ የተያዙ ከ20 በላይ ግለሰቦች ወደ ማይጨው ከተማ ተወስደው መታሰራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ቢናገሩም ፣ ዘመዶቻቸው እንዳይጠይቋቸው በመደረጉ ስለደህንነታቸው ሁኔታ ለማወቅ አልተቻለም።
ወጣቶች የታሰሩት ለኢንቨስተሮች ተብሎ የተዘረጋውን የኤልክትሪክ ምሰሶ አቃጥላችሁዋል በሚል ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጡት ታፍነው የተወሰዱት ወጣቶች በእስር ቤት ጉዳት ሳይደርስባቸው አልቀረም።
በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስት ባለስልጣናትን ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
በሌላ በኩል ደግሞ ስራ ለመቀጠር ወደ ጅጅጋ የሄዱ 9 ወጣቶች በፖሊስ ተዘርፈውና ተደብድበው ለልመና መዳረጋቸውን የአካባቢው ወኪላችን ገልጿል። ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ የተመረቁት 9ኙ ወጣቶች የተነሱት ሞጣ እየተባለች ከምትጠራ በምስራቅ ጎጃም ዞን በምትገኝ ከተማ ሲሆን፣ ወደ ጂጂጋ ያቀኑትም ለመምህርነት ስራ ተወዳድረው በማሸነፋቸው ነው። መምህራኑ ወደ ምድብ ቦታቸው እስከሚሄዱ ድረስ አልጋ ተከራይተው በመጠባባቅ ላይ ሳሉ፣ ሌሊት ፖሊሶች ወደ ክፍላቸው በመግባት ከ1600 እስከ 2000 ብር እንዲሁም የሞባይል ስልኮቻቸውን በድብደባ ቀምተዋቸዋል። ፖሊሶቹ ገንዘብ አልተወሰደብንም ብላችሁ ፈርሙ በማለት ካስፈረሙዋቸው በሁዋላ የመሳፈሪያ 50 ብር በመስጠት ሀረር ወስደው ጥለዋቸዋል። መምህራኑ ወደ አካባቢያቸው የሚመለሱበት የትራንስፖርት ገንዘብ ስላጠራቸው በአሁኑ ሰአት ሀረር ከተማ ውስጥ በልመና ላይ መሆናቸውን ወኪላችን ገልጿል።
ኢሳት በቅርቡ ክልሉን የጎበኘ አንድ ሰራተኛን አነጋግሮ፣ በክልሉ ውስጥ በሚኖሩ የሌላ አካባቢ ተወላጆች ላይ ልዩ ሚሊሺያዎች የሚፈጽሙትን በደል ማጋለጡ ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በከተማዋ የሚኖሩ የሶማሊ ተወላጅ ያልሆኑ ነዋሪዎች፣ ሶማልኛ ካልተናገራችሁ መታወቂያ አይታደስላችሁም በመባላቸው ችግር ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ነዋሪዎች እንደሚሉት የችግሩ ምንጭ ከዋናዋ ሶማሊያ የመጡ ግለሰቦች በስልጣን ላይ መውጣታቸው ነው። አብዛኛው የሶማሊተወላጅ እንደሌላው ተወላጅ ሁሉ በእኩል ስቃይ ይደርስባቸዋል።
No comments:
Post a Comment