ህዳር ፲፯ (አስራ አምት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ መንግስት ሁለት ኢትዮጵያዊ የአሜሪካ ዜጎችን ለ 48 ሰአታት ማሰሩ ተሰማ። በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ከመንግስት ሰዎች ጋር ተሞግቶ እንዳስፈታቸውና ከቦሌ በቀጥታ ወደ አሜሪካ እንደላካቸው ተገልጿል።
የአኟዋክ ብሄር ተወላጅ የሆኑትን አሜርካዊያንን ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ይዞ ያሰረው የኢትዮጵያ መንግስት ግለሰቦቹ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ለመመስረት ወደ ጋምቤላ መጓዛቸውን ቢገልጹም የለም የፖለቲካ አጀንዳ አላችሁ፤ ታጣቂዎችን ትደግፋላችሁ በማለት መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ለድርጅት ምስረታ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው የነበሩት ሁለቱ የአኙዋክ ተወላጆች አሜሪካዊያን ለዚህ ፕሮጀክት ወደ ጋምቤላ በተጓዙበት ጊዜ ስራቸው ላይ የክልሉ ሀላፊዎች ችግር በመፍጠራቸው ርዕሰ መስተዳድሩ ጋር ቀርበው በክልሉ ስላለው የአሰራር ብሉሹነትና ሙስና መናገራቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ምንጮቻችን እንደገለጹት ምናልባትም በቦሌ እንዲያዙ ምክንያት የሆነው የክልሉ መስተዳድር ለፌደራል ባለስልጣናት ግለሰቦቹ አስተዳደራቸውን መተቸታቸውን በመናገራቸው ሊሆን ይችላል ብለዋል።
አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው ሁለቱ የአኝዋክ ተወላጆች ል 48 ሰአታት ከታሰሩ በሆላ የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጎቼ ይፈቱ ብሎ በመጠየቁ መፈታታቸውንና ከዛው ከአውሮፕላን ማረፊያ ወደ አሜሪካ መላካቸውን ለማወቅ ተችሏል።
No comments:
Post a Comment