FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Sunday, November 25, 2012

ብዬ ሰሚ አገኛለሁ፣ ቅሬታ አቅርቤ ይፈታልኛል የሚል ዜጋ የለም!


የሕግ የበላይነት እንዲኖር፣ ሰብዓዊ መብት እንዲከበር፣ የፕሬስ ነፃነት እንዲረጋገጥ፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን የሚያደርጉ ሕገ መንግሥትና ሕጎች አሉን??????
ከድህነት የሚያላቅቅ፣ መካከለኛ ገቢ ወዳላት አገር የሚያሸጋግር፣ የቤት፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የትራንስፖርት፣ ወዘተ ችግሮችን የሚፈታ ዕቅድም አለን???????
እነዚህ አሉ ማለት ግን ዲሞክራሲ ተረጋገጠ፣ ልማት እውን ሆነ ማለት አይደለም፡፡ በመርህ ደረጃ ተግባር ላይ ካዋልናቸው ይጠቅማሉ፡፡ ካላከበርናቸው፣ ከረገጥናቸውና ከጣልናቸው ደግሞ ገጠመኝ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ምክንያት አለማደግና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አለመገንባት ብቻ ሳይሆን፣ ወደኋላ መንሸራተትም ሊያጋጥም ይችላል፡፡

ምርጫ! መርህ ወይስ ገጠመኝ? 

ፍርድ ቤቶች ራሳቸውን የቻሉ ነፃ የሕግ ተርጓሚ አካላት እንደሆኑ ሕገ መንግሥታችንም ሕጎቻችንም በግልጽ ያስቀምጣሉ፡፡ ስለሆነም በሕግ አንፃር ሲታይ ፍትሕ ማግኘት በመርህ ደረጃ ዘወትር በየትም ሥፍራ መረጋገጥ ያለበት እንጂ፣ ፍትሕ ዘወትር እየተረገጠ አልፎ አልፎ ሊገኝ የሚችል ገጠመኝ መሆን የለበትም፡፡

በተግባር ሲታይ ግን ፍትሕ ገጠመኝ እየሆነ ነው፡፡ የፍትሕ መጓደል በሚያሳስብ ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ በፍትሕ አካላት ውስጥ በአቅምና በአመለካከት ድክመት አለ፡፡ የሥነ ምግባር ጉድለት በትልቁ እየታየ ነው፡፡ በጠበቆች፣ በዳኞችና በዓቃቢያነ ሕግ በኩል አሳሳቢ የሥነ ምግባርና የአቅም ችግር እየተስተዋለ ነው፡፡ በአጠቃላይ የፍትሕ አካላት መጠናከር እያሳዩ ከመጓዝ ይልቅ እየተልፈሰፈሱና እየተንገዳገዱ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ፍትሕ ማግኘት መርህ መሆኑ ቀርቶ ገጠመኝ እየሆነ ነው፡፡ ጉቦ የአንቀጾች ሁሉ የበላይ አንቀጽ እየሆነ መጥቷል፡፡ 

መልካም አስተዳደር በሕግና በመርህ ደረጃ መከበር አለበት ተብሎ የታወጀ፣ የተነገረ፣ የተለፈፈለት ነው፡፡ በተግባር ደግሞ አቤት ብዬ ሰሚ አገኛለሁ፣ ቅሬታ አቅርቤ ይፈታልኛል የሚል ዜጋ የለም!!!! በዚህ ዙሪያም ጉቦና ጥቅማ ጥቅም የበላይነት እየያዙ ነው፡፡ የአቅም ማነስ ችግር ትልቅ እንቅፋት ነው፡፡ ስብሰባዎችና ሥልጠናዎች የችግር መፍቻ መድረኮች መሆናቸው ቀርቶ መደበቂያ እየሆኑ ነው፡፡ ‹‹በስብሰባና በሥልጠና ምክንያት ኃላፊ የለም›› የሚል ማስታወቂያ መለጠፍ ነው የቀረው፡፡ ኃላፊ ቢሮው ገብቶ አቤቱታ አንብቦ ችግር መፍታት መርህና ግዴታው መሆኑ ቀርቶ ገጠመኝ እየሆነ ነው፡፡

በዚህ ቀን የቢዝነስ ወይም የኢንቨስትመንት ላይሰንስ አውጥቼ፣ በዚህ ሳምንት መሬት አግኝቼ፣ በዚያኛው ሳምንት ግንባታ ጀምሬ፣ በዚህ ወር የባንክ ብድር አግኝቼ፣ በዚህ ዓመት ሥራ ጀምሬ ይህን ያህል አተርፋለሁ እያሉ ማሰብ መርህ የሚደግፈው ሒደት መሆን ሲገባው አጋጣሚ እየሆነ ነው፡፡

‹‹ሰው ያስባል እግዚአብሔር ይፈጽማል›› ተብሎ የሚገባበት እንጂ፣ ሰው ያመለክታል አስተዳደሩ ወይም ኃላፊው ይፈጽማል የሚባልበት ማስተማመኛ የለም፡፡ አዲስ ለመጀመርና የተቋረጠ ካለ ለመቀጠል ዕድሉ ገጠመኝ ነው፡፡

ይህም በእጅጉ እየጎዳን ነው፡፡ ጥርጣሬ እየበዛ በውጭ ኢንቨስተሮች ላይ ፍርኃት እያስከተለ ነው፡፡ ችግር አይኖርም፣ ሕግ አለ፣ መመርያ አለ፣ ተብሎ በእምነት የሚገባበት መሆኑ ቀርቶ፣ የደም ግፊትና የስኳር ኪኒኖችን በመያዝ የሚገባበት ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡

የበደለ፣ የአገር ሀብት ያባከነ፣ ሕገ የረገጠ ግለሰብ ማጥፋቱ እየታወቀ ይቀጣል ወይስ አይቀጣም ለሚለው ጥያቄ ወሳኙ ማስረጃ መሆኑ እየቀረ ነው፡፡ ገጠመኝ ሆኗል፡፡ ይታሰራል የተባለው ሊሾም፣ ተጠያቂ ይሆናል የተባለው ጠያቂ የሚሆንበት ሁኔታ አለና፡፡ ገጠመኝ!

የባንክ ብድር አግኝቶ መሥራት ይቻላል? አዎ! ነገር ግን ዛሬ ተችሎ ነገ ሊቆም ይችላል፡፡ ኤልሲ በመክፈት ከውጭ ዕቃ እያመጡ መነገድ ይቻላል? አዎን! ግን ኤልሲ ሊከለከል ይችላል፡፡ መርህ መሆኑ ቀርቶ ይህም ገጠመኝ እየሆነ ነው፡፡

መንግሥት በሚያወጣቸው ጨረታዎች ሕግ ተከትሎና አክብሮ ተጫርቶ ማሸነፍ ይቻላል? አዎን! ግን በመርህ ደረጃ ይህ ሀቅ ቢሆንም በተግባር ግን ጨረታው ቀርቶ በቀጥታ ለግለሰብ ወይም ለድርጅት ተሰጥቷል ሊባልም ይችላል፡፡ በቴክኒክ ብቃትና በሚጠየቀው ገንዘብ የማይጠቅመው አሸንፎ፣ የሚጠቅም ነገር ያቀረበው ሊሸነፍ ይችላል፡፡ በብዛት የጨረታ አካሄድ መርህ መሆኑ ቀርቶ ገጠመኝ እየሆነ ነው፡፡

ብዙ ብዙ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እያልን ያለነው በአጭሩ ሲቀመጥ ግን ሕገ መንግሥት ይከበር፡፡ ሕገ መንግሥትን ማክበርና ሁሌም ሁሉንም በሕጋዊ መንገድ ማስተናገድ ይቅደም፡፡ ይህንን በመርህ ደረጃ አምነን የምንፈጽመው እንጂ፣ ለእከሌ ሌላ ለእከሊት ሌላ እያደረግን በዘፈቀደ በጥቅም የምንሠራው መሆን የለበትም ነው፡፡

ሕጎች፣ አዋጆች፣ ደንቦች፣ መመርያዎችና አሠራሮች ለሁሉም እኩል የሚያገለግሉ እንጂ ገመጠኞች አይደሉም፡፡ ላይ ያለው ባለሥልጣንም፣ ታች ያለው ባለሥልጣንም፣ እዚህና እዚያ ያሉ ሠራተኞችም ሁሌም ሕገ መንግሥትን፣ ሕግን፣ አዋጅን፣ ደንብን፣ መመርያን ተንተርሰው ይሠራሉ እንጂ፣ ‹‹እንደ ሰውና እንደ ገንዘቡ እናስተናግዳለን›› የሚል አጉል ድርጊት መፈጸም የለባቸውም፡፡ ሁሉም በሕግ ፊት እኩል ሆኖ ይስተናገድ፡፡ ሁሉም ኃላፊ፣ ሁሉም ሹም ሕግን መሠረት አድርጎ ይሥራ ያገልግል ነው ቁምነገሩ፡፡

በሚገባ እናስብበት፤ መርህ በገጠመኝ እየተተካ ነው፡፡ ቀስ በቀስ ሰላማችን፣ ሉዓላዊነታችን፣ አንድነታችንና ህልውናችን በመርህ ደረጃ ዋስትና ያላቸው መሆናቸው ቀርቶ ገጠመኝ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ህልውና ገጠመኝ ሲሆን ደግሞ የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው፡፡
ስለዚህ መርሆች ገጠመኞች እንዳይሆኑ ጠንቀቅ!    

No comments:

Post a Comment