FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Thursday, November 22, 2012

የሕዝብ ራእይ ለምን በአምባገነን ስም ይጠራል?


THURSDAY, NOVEMBER 22, 2012


የኢትዮጵያ ሲቪክ ንቅናቄ
Ethiopian Civic Movement

አቶ ሃይለማርያም „የታላቁን መሪ ራእይ“ እንደሚተገብሩ ቃል ገብተዋል፤ ለውጥ እንደሚያደርጉ ግን አልገለፁም፡፡ ኢህአዴግ በአቶ መለስ ፍላጎት ብቻ ይመራ፣ የኢትዮጵያ ህዝብም በሰውየው ፍላጎት ይገዛ ነበር፡፡ ከዛ ፍላጎት ማፈንገጥ ለግምገማ ያጋልጥና በጠላትነት ያስፈርጅ ነበር፡፡ ያገዛዙ ጠባይ በድርጅቱ አባላትም አለመተማመንን አስርፆና አስፍኖ፣ አባላቱ በግልፅ ሃሳባቸውን እንዳይገልፁ አፍኖ ስለቆየ ኢህአዴግ ከአቶ መለስ ሞት በሁዋላም እስካሁን የሚመራው በሟቹ መንፈስ ነው፡፡አባላቱ ከአፋኙ ባህል ገና አልተላቀቁም፡፡ ስለዚህ የአቶ ሃይለማርያም ንግግር የተጀመረውን መቀጠል ከሚለው ሃሳብ አለመውጣቱ ለጊዜው አያስገርምም፡፡

አቶ ሃይለማርያም የኢህአዴግ ባለስልጣን ሆነው፣ በተለይም በመለስ ዜናዊ ተመርተው ለዚሁ ስልጣን የበቁ እንደመሆናቸው፣ ባጫር ጊዜ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋትና አንዳንድ የፖለቲካ ለውጦችን በማድረግ አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገር ይችላሉ ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡ በተለይም ቁልፍ የሆኑ ተቋሞች እንደ ዴህንነትና የጦር ሓይሉ በወንጀል የሚጠየቁና በሙስና የተጨማለቁ የህወሓት ሰዎች ቁጥጥር ውስጥ እስከሆኑ ድረስ ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አገርን በማስቀደም ላይ የታነፀ ፍላጎትና ራእይ ካላቸው ግን ታሪክን መስራት ባጭር ጊዜ ባይሆንም ይችላሉ፡፡ በጎርባቾቭ የለውጥ ፍላጎት እንደ ህወሓት/ኢህአዴግ ስታሊናዊ አሰራርና አደረጃጀት የነበረውና ብቻውን ከ70 ዓመት በላይ የገዛው የሶቬት ኮምዩኒስት ፓርቲ ሊፈርስ እንደቻለ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡

ስለሆነም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለወደፊቱ የኢትዮጵያ ህዝብን ለመምራት ያበቃቸው ታሪካዊ አጋጣሚ የአንድ ግለ-ሰብን ራእይ በመከተል ብቻ ሊወጡት አይችሉም፡፡ የህዝብ ጥቅምንና ድምፅን የሚያስከብርና የድርጅታቸውን አባላት በነፃነት የሚያሳትፍ የራሳቸው ሕሊና ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህ መሠረት እሰካሁን የነበሩትን የመንግስት፣ ማለትም የአቶ መለስ አቋሞች፣ ድርጊቶችና እቅዶች በመመርመር የሚተዉ፣ ተስተካክለው የሚቀጥሉና የሚጨመሩ ጉዳዮች መለያየት ያስፈልጋል፡፡

የቆየው የመንግስት ወሳኝ ሃሳብና አሰራር

ከአቶ መለስ ህልፈተ ህይወት በሁዋላም በሃሳባቸው ለመቀጠል መፈለግ ማለት ሌሎች ሃሳቦች እንዳይፈልቁና በቆየው ሃሳብ ውስጥ የነበሩ ስህተቶች እንዳይታረሙ መግታት ነው፡፡ የነበረውን አሰራር መቀጠል ማለት ደግሞ ሁሉም ሰው እንደ ሃይማኖት በአንድ ሃሳብ መመራቱን ለማረጋገጥ ቁጥጥር፣ ግምገማና መሸማቀቅ ያስከትላል፤ ያስቀጥላል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብና አሰራር ላይ የተመሰረተ ስርዓት ነፃነትን በማሳጣት የመተራረም ዕድልን ስለሚዘጋ ለልማት እንደሚጠቅም ዋስትና የለውም፡፡

የቆየው ሃሳብ መለያው የሚወርደውም የሚቀየረውም ከላይ ከመሆኑ ሌላ አንድ ወጥነት አልነበረውም፡፡ አቶ መለስ የቆሙለት የተለመደ፣ አንድ ወጥ የሆነ ማህበራዊ ስርዓት፣ እንደ ካፒታሊዝም ወይም ሶሻሊዝም አልነበራቸውም፤ ከሁለቱ ስርዓቶች ተቀይጦ ሲቀርብም ቅንነት የጎደለውና የሚቀያየር ነበር፡፡ ሰውየው አንዴ ነጭ ካፒታሊዝም ያሉትን ሌላ ጊዜ ሶሻሊዝምን ያስመስሉት ነበር፡፡ ስታሊናዊ የቁጥጥርና የአፈና መዋቅር ተዘርግቶና ካድሬዎች ተሰማርተው ህዝብ በግምገማ እየተዋከበ የአንድ ሰው ፍላጎት ብቻ እንዲሰርፅበትና (indoctrinated እንዲሆንና) ሌላ ሃሳብ እንዳያፈልቅ ሲገደድ ቆይቷል፡፡ ይህ አሰራራቸው ከስታሊናዊ የጭቆና ስልት እንዳልተላቀቁ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

ሆኖም ሟቹ፣ ከስታሊናዊነት አስከፊውን ያፈና ገፅታ እንደመረጡ ሁሉ ከካፒታሊዝምም አስከፊውን የሙስና ገፅታ አስፍነው ጥቂት ደጋፊዎቻቸው በአጭር ጊዜ ብዙ ሃብት እንዲያካብቱና ብዙ ህዝብ በድህነት እንዲራቆት አድርገዋል፡፡ ስርዓቱ አምባገነኑን ለሚደግፉት ሙስና፣ መብታቸው እንዲከበር ለሚፈልጉት አፈና ሆኖ ቆይቷል፡፡ በተለይ ጉልበትን በመጠቀምና ምርጫን በማጭበርበር ከ99% ያለፈው የፖለቲካው ሙስና ካለ አግባብ ስልጣንንና ሃብትን መቆጣጠር አስችሏል፡፡ ሌብነትንና ጉቦን ለሚያካትተው ሙስና መሰረቱ የፖለቲካ ሙስና እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

አቶ መለስ ከሳቸው የተለየ ሃሳብ እንዳይፈልቅ አጥብቀው ይቆጣጠሩ ነበር፡፡ እሳቸው ራሳቸው ግን ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮም የተወሰኑ ሰዎችን ለማጥቃት በፈለጉ ቁጥር የማደናገር መፈክራቸውን (በማኦ ዜዱንግ፣ በኢንቨር ሆጃ፣ በቦናፓርቲዝም፣ በነጭ ካፒታሊዝም፣ በኒዮ ሊበራሊዝም፣ በልማታዊ መንግስት ወዘተ) ስለሚቀያይሩ ተከታዮቻቸው በአንድ ሃሳብ እንዳይፀኑ የሚያደርግ ስሜት ፈጥረዋል፡፡ ስለዚህ የተከታዮቻቸው እጣ ፈንታ መፈክር ሲቀየር እየተከታተሉ ማስተጋባት ነበር፡፡

ስርዓቱ በፖለቲካ የማይደግፉትን በብዙ ዘርፍ እንዲሰቃዩ የማድረግ ጠባይ ስለነበረው አቶ መለስ መንግስታዊ ስልጣን እንደያዙ የማይፈልጓቸውን ዜጎች ከስራ አስወጥተዋል፡፡ ዜጎችን ከስራ ሲያባርሩ ግን ስታሊናዊ የመመንጠር እርምጃ እንደሚወስዱ (purge እንዳደርጉ) አልገለፁም፡፡ ስለዚህ ቢሮክራሲውን እንደሚቀንሱና አላስፈላጊ የሚሏቸውን ሰራተኞች እንደሚያባርሩ የገልፁት በኒዮ ሊበራል መርህ መሰረት ነበር፡፡ ያ መርህ ከዓለም የገንዘብ ድርጅትንና ከዓለም ባንክ የመጣ የመዋቅር ማስተካከያ መርሃ ግብር (Structural Adjustment Programme) ይባል ነበር፡፡ በወቅቱ አቶ መለስ ኒዮ ሊበራል የኢኮኖሚ መርህን ከስታሊናዊነት ጋር ቀላቅለው ከመተግበር አልቦዘኑም፡፡

የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ በኒዮ ሊበራል መርሃ ግብራቸው በድሆች አገሮች ላይ ብዙ ቀውስ ካስከተሉ በሁዋላ አለም አቀፍ ተቃውሞ ሲበዛባቸው መርሃ ግብሩን ቀየሩት፡፡ የድርጅቶቹ ባለስልጣኖች ከነበሩት እንደነ ጆሰፍ ስቲግሊትዝ (Josef Stiglitz)፣ ኒዮ ሊበራል የኢኮኖሚ መርህን ተቃውሞው መፃፍ ጀመሩ፡፡ በ1998 በፈረንሳይ የተቋቋመውና ከ50 በላይ አገሮች ዜግነት ያላቸው አባሎች ያሉበት በገንዘብ ንግድ ላይ ግብር ለመጣልና የተሰበሰበውን ግብር ለዜጎች ጥቅም ለማዋል የቆመ ማህበር ማለት Attac (L’Association pour la taxation des transactions financières et pour l’action citoyenne) የሚባል ማህበር አለ፡፡ ማህበሩ የግሎባላይዘሽን ሂደት በኒዮ ሊበራሊዝም የነፃ ገበያ መርህ ድሃ አገሮችና ህዝቦች እንዳይጎዳ ይከራከራል፤ አቶ መለስም ኒዮ ሊበራል መርህ ይከተሉ እንዳልነበሩ መስለው ለካድሬዎቻቸው ከኒዮ ሊበራል ጋር የሚያያይዙትን ሙስና „ኪራይ ሰብሳቢነት“ እንዲባል ከትእዛዝ ጋር የተያያዘ ስብከት ሲያሰራጩ ቆይተዋል፡፡ በተግባር ባጭር ጊዜ በሙስና የተዘፈቁት ግን የአብዮታዊ ዴሞክረሲ ባለስልጣኖች ናቸው፡፡

አገዛዙ ያንድ ፓርቲ ስርዓት አራማጅ በመሆኑ ምክንያት እንዳይወገዝ ለመከላከል ሰውየው ኢሕአዴግን አውራ ፓርቲ ብለውታል፡፡ ይህ አውራ ፓርቲ ተግባሩ (ያንድ ፓርቲ ስርዓትነቱ) እንደ ቻይና ሆኖ፣ አጠራሩ አውራ ፓርቲ በመባል የካፒታሊስት ስዊድንና ጃፓን ዓይነት ፓርቲ እንዲመስል ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ስርዓቱ የቻይና እንዳይመሰል ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲኖሩና ምርጫ እንዲደረግ ለይሰሙላ ቢፈቀድም፣ ያንድ ፓርቲ አገዛዙ እንዲቀጥል ደግሞ የህዝቡ የመምረጥና የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የመመረጥ መብቶች ተረግጧል፡፡

ብዙ ጊዜ እንደ አውራ ፓርቲ የሚጠቀሱት ፓርቲዎች ለረዥም ጊዜ ስልጣን ላይ የቆዩት የስዊድን ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲና የጃፓን ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ናቸው፡፡ የስዊድን ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ በመቶ ዓመት ውስጥ ከ1911 እስከ 2010 ድረስ ከ50% በላይ የህዝብ ድምፅ ያገኘው በ1940 ዓ/ም 53.8% እና በ1968 ዓ/ም 50.1% ሁለት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ የጃፓን ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲም ከ1955 እስከ 2009 ድረስ (ከ1993/94 በስተቀር) ስልጣን ላይ ቢቆይም፣ ፓርቲው ከ50% በላይ ድምፅ ያገኘበት ጊዜ በ1958፣ በ1960 እና በ1963 ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህ ሁለቱም ፓርቲዎች ለብዙ ጊዜ ስልጣን ላይ የቆዩት፣ አንደኛ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንጂ በጉልበትና በማጭበርበር አልነበረም፤ ሁለተኛ ሁለቱም ፓርቲዎች አብዛኛውን ጊዜ ተቃዋሚዎቻቸውን አግልለው ህዝቡን ለመግዛት የሚያስችላቸው በቂ የህዝብ ድምፅ ማግኘት ስላልቻሉ ስልጣናቸውን ከሌሎች ጋር እንዲጋሩ ይገደዱ ነበር፡፡ እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ትልቁ ቁምነገር ጃፓንና ስዊድን ነፃ የሆኑ ዴሞክረሲያዊ ተቋማት ያሏዋቸው ዴሞክራሲያዊ ስርኣት የገነቡ አገሮች መሆናቸው ነው፡፡ በዚህ መሰረት ኢህአዴግ አምባገነናዊ ፓርቲ እንጂ በአውራ ፓርቲነት ከሚታወቁት ድርጅቶች የሚያገናኝ ዴሞክራሲያዊ ይዘት የለውም፡፡

አብዮታዊ ዴሞክረሲ ባንድነት ጥያቄ

በኢትዮጵያ አውራ ፓርቲው ልማታዊ መንግስት እንደሚመሰርት ተገልፀዋል፡፡ አቶ መለስ ዴሞክራሲና የምጣኔ ሃብት እድገት እንደማይገናኙ ቢገልፁም፣ ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ የህልውና ጥያቄ እንደሆነ ይገልፁ ነበር፡፡ በአገዛዙ ዴሞክራሲ ሲባል ግን በስታሊናዊ ማእከላዊነትና በግለ-ሰብ አምባገነንነት ላይ የተመሰረተው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባለው ብሄር/ብሄረሰቦችን ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመች የተደረገ፣ በመገንጠል አገርን የመበታተን አደጋን የሚጋብዝ አካሄድ ነው፡፡

ይኸው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ደግሞ በተገላቢጦሽ ኢትዮጵያን ከመበታተን እንዳዳነ ይነገርለታል፡፡ ለመሆኑ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ባይኖር ኖሮ ከኢትዮጵያ ማን ይገነጠል ነበር? ሻዕብያ በከፍተኛ ያቶ መለስ ትብብር ኤርትራን ገንጥሏል፤ ኢትዮጵያ የባህር በር አጥታ ለፀታ አደጋና ለምጣኔ ሃብታዊ ኪሳራ ተጋልጣለች፡፡ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ድርጅቶች መገንጠል የሚያስችላቸው ወታደራዊ አቅም ስላልነበራቸውና እስካሁንም ስለሌላቸው አንዱን የኢትዮጵያ አካል መገንጠል አልቻሉም፡፡ አንድን ብሄር ከኢትዮጵያ ለመገንጠል አቅም የነበረውና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ምክንያት የመገንጠልን ዓላማ እንደተወ የሚገልፅ ራሱን ችሎ የቆመ ድርጅት ህወሓት ብቻ ነው፡፡ እውነት ግን የህወሓት አመራር መገንጠልን ያልመረጠው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ምክንያት ነው ወይስ በስልጣንና በኢትዮጵያ ደረጃ ከስልጣን የሚገኝ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥቅም እንዳይቀርበትና የትግራይ ህዝብ የመገንጠል ፍላጎት እንደሌለው ስለሚያውቅ? ዓላማቸው የትግራይ ዴሞክረሲያዊ ሪፑብሊክ ለመመስረት መታገል እንደሆነ በ68 ማኒፌስቶ በይፋ አውጀው የነበሩት አቶ መለስና ግብረ አበሮቻቸው የኢትዮጵያ አንድነት ራእይ አልነበራቸውም፡፡

የምእተ ዓመቱ የልማት ግቦችና የብዙ ኢትዮጵያውን የልማት ራእይ

ልማት የሁሉም ያገራቸውን ሁኔታ የሚከታተሉ ኢትየጵያውያን ራእይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በከፋ ደረጃ ተደጋግሞ የተከስተውና እስካሁን ማስወገድ ያልተቻለው ራሃብ የብዙ ወገኖቻችን ህይወት ቀጭቷል፤ ህዝብን አሰቃይቷል፤ ለልመናና ሃፍረት አጋልጧል፤ ዘውዳዊውንና የደርግን መንግስታትን እንዲወድቁ አሰተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ስለዚህ በዚህ ችግር ያለፉና ይህን ችግር የሚያውቁ ኢትዮጵያውያን ችግሩን ማስወገድ ይፈልጋሉ፡፡

ሁዋላ ቀርነትን የማስወገድ ራእይ ዓለም አቀፍ ራእይም ስለሆነ የምእተ ዓመቱ የልማት ግቦች በ1993 ዓ/ም ሚስተር ኮፊ አናን የዓለም የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ በነበሩበት ጊዜ በ193 አገሮችና ብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለልማት ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ስለተስማሙ በ1994 የሚከተሉት የልማት ግቦች እስከ 2015 (2007 በኢትዮጵያ አቆጣጠር) እንዲሟሉ ተስማምቷል፡፡
1.ከመጠን ያለፈ ድህነትንና ራሃብን ማጥፋት
2.የ1ኛ ደረጃ ትምህርትን ለሁሉም ማዳረስ
3.የፆታ እኩልነትን ማሳደግና የሴቶችን የመወሰን መብት ማስከበር
4.የህፃናት መሞትን መቀነስ
5.የእናቶችን ጤንነት ማሻሻል
6.ኤይድስን፣ ወባንና ሌሎች በሽታዎችን መታገል
7.ያየር ንብረት ዘላቂነትን ማረጋገጥ
8.የልማት ግቦቹን ለማሳካት ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከር

ስምንተኛው የልማት ግብ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያም የልማት ግቦቹን ለማሳካት ከሃብታም አገሮች እርዳታ ታገኛለች፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብም ልማት የግለ-ሰብ ራእይ፣ ማለትም የመለስ ራእይ ተደርጎ ከሚነገረው፣ ልማት ዓለም አቀፍ የጋራ ራእይ መሆኑ ማወቁ ግልፅነት ላለው አሰራር ይጠቅማል፡፡

„የመለስን ራእይ“ ከመከተል መወገድ ያለባቸው አቋሞችና ድርጊቶች

የግለ-ሰብ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነንነት፡

የግለ-ሰብ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነንነት ከድህነትም ከማሃይምነትም የባሰ የሁዋላ ቀርነት መገለጫ ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት አምባገነንነት በህዝብ ላይ ግፍ እንደሚፈፀም በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፤ በአምባገነንነት የኢኮኖሚ እድገት እንደሚመጣ ግን ዋስትና እንደሌለ በብዙ የአፍሪካ አገሮች አምባገነኖች ተረጋግጧል፡፡ ስለዚህ አቶ ሃይለማርያም በኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አመባገነን ያልሆኑ መሪ ቢሆኑ መሠረታዊ የሆነ ታሪካዊ ለውጥ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ የጋራ አመራር የሚል አገላለፅ በአቶ መለስ ስር እንደነበረው ዓይነት ከሆነ እውነት እንዳልነበረ ግልፅ ስለሆነ የጋራ አመራሩ በቅንነት መተግበር አለበት፡፡

የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመከበር

በአቶ መለስ አገዛዝ ስር የኢህአዴግ አባሎችና ብዙ ባለስልጣኖች እንኳንና ተራው ዜጋ እነሱም ራሳቸው ነፃ ዜጎች እንዳልነበሩ ነፃነት እንዳልነበራቸውም ደፍረው መናገር እንዳልቻሉ ያውቃሉ፡፡ የግዲያ ወንጀሎች ከፈፀሙትና በሙስና ከተዘፈቁት የኢህአዴግ ባለስልጣኖች በስተቀር ግን ሌሎቹ አባላት ነፃነት፣ ግልፅነትና ፍትህ የማይፈልጉበት ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ የኢህአዴግ አባላት ነፃነት ቢፈልጉም በተገዥነት ተሸማቅቀውና እርስ በርሳቸው እንዳይተማመኑ ተደርገው ስለቆዩ ለመብቶቻቸው መታገል መቻላቸው ያጠራጥራል፡፡ ኢህአዴግ በስልጣን እስካለ ድረስ የራሱ አባላት ነፃ ሳይሆኑ ሌሎች ዜጎች ነፃ ሊሆኑ ስለማይችሉ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣናቸውን ተጠቅመው ለድርጅታቸው አባላት ነፃነት ቢያጎናፅፉ ለሁሉም ይጠቅማል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሌላቸው አቋም ማውገዝ

የልማት ጥያቄ ሲነሳ ለአገራችን ልማት በጣም እንደሚያሰፈልጋት ባሏቸው አቋሞች በኢህአዴግና በቂ የህዝብ ተቀባይነት ባላቸው ተቃዋሚ ድርጅቶች ማኽል መሠረታዊ ልዩነት የለም፡፡ ርሃብ በኢትዮጵያ እንዲጠፋ፣ ተቃዋሚዎችም መንግስት በኢኮኖሚው በጥናት ላይ የተመሰረተ ሚና እንዲኖሮው እንደሚፈልጉ ይገልፃሉ፤ ለነፃ ገበያ ብቻ የቆሙ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ በተቃዋሚዎቹ ላይ ኒዮ ሊበራሊዝምን ለጥፎ ባገር ውስጥ ከሌለ ሃሳብ ጋር ከሚከራከር፤ ተቀዋሚዎቹ የራሳቸውን አቋም ራሳቸው ቢገልፁ ይሻላል፡፡

እንደዚሁም የሚከተሉትን ልመዶችና አሰራሮች ማስወገድና የሚስተካከሉትን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡

- የአንድ ፓርቲ አገዛዝን ማስፈንና በአውራ ፓርቲ ስም ማጭበርበር፣

- ዜጎችን በፖለቲካ ምክንያት በውሸት ማሳሰር፣ ማስከሰስ፣ ማስፈረድ፣ ማሰቃየት፣ የውሸት ሽምግልና መላክ፣ ተከሳሾች ራሳቸውን እንዲወነጅሉና ተሸማቅቀው ይቅርታ እንዲጠይቁ ማድርግ፣

- ለብሄር/ብሄረ ሰብ ልዩነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ፤ ባደረጃጀት( የነገድ ድርጅቶች መፈልፈል)፣ ባጠራር (የኢትዮጵያ ህዝብ በማለት ፈንታ በተንዛዛ „ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝቦች የሚል አጠራር መጠቀም) ህዝብን መከፋፈል

- የፖለቲካ ሙስና> ጉልበትን በመጠቀም ምርጫን ማጭበርበር፣ የፍርድ ተቋምን፣ የመገናኛ ብዙሃንን፣ የምርጫ ቦርድን፣ የሰራዊትንና የፀጥታ ሃይሎችን ገለልተኛ ሆነው ህዝቡን በእኩልነት እንዳያገለግሉ መከልከልና የስልጣን መሳሪያ ማድረግ

- የኢኮኖሚ ሙስና

- በህገ መንግስቱ የተዘረዘሩትን መብቶችና ሕጎች አለመተግበርና ዜጎችን ለማሰቃየት አጣምሞ መተርጎም

- ዜጎችን በጉልበት ማፈናቀልና መሬት ለውጭ ኩባኒያዎች ማከራየት

- በርካሽ የውጭ ዕቃዎች ገበያውን በማጥለቅለቅ የአገር ፋብሪካዎች እንዳያድጉ ወይም እንዲጠፉ ማድረግ፣

- ጥሬ ምርቶች እንደነ ሰሊጥና ኑግ ባገር ውስጥ ፋብሪካዎች እንዲሰሩ በማድረግ ፈንታ ለውጭ ገበያ መላክ፣ ባገር ውስጥ በፋብሪካ እንዳይሰሩ ማድረግ

አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣን ከተረከቡ ቀን ጀምሮ ነጋ ጠባ ያቶ መለስን ራእይ እከተላለሁ ሲሉ ቢደመጡም አቶ መለስ የፈጠሩት ሁኔታ ለጥቂቶቹ ገነት ለሚሊዮኖቹ ሲኦል እንደሆነ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት እስከሌለና በሃገር ገዳይ ላይ ትችት ማቅረብ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ወሕኒ ቤት የሚያስወርድ እስከሆነ ድረስ አቶ ሃይለማርያምና ጥቂቶቹ ባለደረቦቻቸው የዚህ በሽተኛ ራእይ እስረኞች ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ የአንድ አምባገነን ፓርቲ አገዛዝ ያንድ ግለ-ሰብ ፈላጭ ቆራጭነትና ባንድ ግለ-ሰብ አምልኮ መጠመድን እንዳስከተለው ሁሉ፣ በድህነትና ባፈና የሚማቅቁት ሚሊዮኖች ሲነሱበት አገዛዙ ይደመሰሳል፡፡

የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች ካለ ቅድመ ሁኔታና አሁን ይፈቱ!!

No comments:

Post a Comment