ህዳር ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አቃቢ ህግ በእነ ኡስታዝ አቡበክር አህመድ መዝገብ በሽብርተኝነት በተከሰሱት የድምጻችን ይሰማ የኮሚቴ አባላት ላይ ያቀረበው ክስ ህገመንግስቱን የጣሰ ና በርካታ የህግ ድንጋጌዎች ግድፈት ያለበት መሆኑን በዝርዝር በመጥቀስ ነው፣ የተከሳሾች ጠበቆች ተቃውሞአቸውን ለፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረቡት።
ጠበቆቹ 7 ገጾች ያሉት ህገመንግስቱን የተመለከቱና 24 ገጾች ያሉት ዝርዝር መቃወሚያዎችን አቅርበዋል።
በተከሳሾች ላይ የቀረበው ክስ ህግ ህገ-መንግስታዊ ባለመሆኑ ክሱም የማያስከስስ ግልፅ ያልሆነ እና ተከሳሾች በዚህ ሁኔታ ክሱን አውቀውት ሊከላከሉ የማይችሉ መሆኑን ጠበቆች በተቃውሞአቸው ገልጸዋል።
በዝርዝር ባቀረቡት መቃወሚያ ደግሞ ” ተከሳሾች በአንቀጽ 3 እና 4 በአንድ ላይ ሊከሰሱ አይገባም፣ የአቃቢ ህግ የክስ አቀራረብ በአንዱ መክሰስ ባይሳካ በሌላው ይሳካ ይሆናል በሚል የተሳሳተ ግምት በግልጽ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ሥነስርአትን፣ የወንጀል ህግ መርህን እና ህገመንግስትን የሚጥስና ክሱም ከህግ ውጪ የቀረበ ነው።” በማለት ገልጸዋል።
አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ አግባብነት ባላቸው የወንጀል ህጎች እና የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ተከትሎ ያልቀረበ በመሆኑ እና በዚሁ ክስም የተገለጹት ድርጊቶች በወንጀል የማያስጠይቁ በህግ የተፈቀዱ መብቶች እና ተግባራት በመሆናቸው ተከሳሾችን ለመክስ የሚያበቃ በቂ ምክንያት የለም ሲሉም ጠበቆች ተቃውመዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ተከሳሾች በሽብር ተግባር ላይ መሰማራታቸውን የሚያመለክት ጠንካራ ማስረጃ ሊያቀርብ አለማቻሉን ተከትሎ፣ እስረኞችን እንዲፈታ አለማቀፍ ጫናው በዝቶበታል።
No comments:
Post a Comment