ህዳር ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከዓለማችን በሕዝብ ቁጥር ከቀደሚዎቹ 15 ሐገራት ውስጥ የምትገኘው ኢትዮጵያ በማህበራዊ ሚዲያ በ88ኛ ደረጃ ላይ መገኘትዋን አንድ ጥናት አረጋገጠ ።
ሶሻል ቤከርስ የተባለ ተቐም ይፋ ባደረገው መረጃ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ከማህበራዊ መገናኛ ማለትም ፌስ ቡክ የሚጠቀሙ ከ1 በመቶ በታች 0.95 በመቶ ሲሆኑ በቁጥር ሲቀመጥ 839 ሺህ 580 ኢትዮጵያውያን የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው ።
ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃጸር 27.4 በመቶ መጨመሩንም ከወጣው ጥናት መረዳት ተችሎአል። ይህም በአንድ አመት ውስጥ ተጨማሪ 180 ሺህ 800 ኢትዮጵያውያን የፌስ ቡክ ተጠቃሚ መሆናቸውን ያስረዳል። በህዝብ ቁጥር ከኢትዮጵያ በግማሽ የምታንሰው ኬንያ በፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከኢትዮጵያ በዕጥፍ እንደምትበልጥ ከጥናቱ መረዳት ተችሎዋል።
አንድ ነጥብ 9 ሚሊዮን ኬንያውያን የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ሲሆኑ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር በ327ሺህ 440 ጨምሮ ተገኝቶዋል ። የኬንያውያን የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር አሁንም በመጨመር ላይ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ብቻ የተመዘገበው ዕድገት 4.78 መድረሱ ጠቐሚ ሆንዋል። ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ዕድገት 0.95 ከመቶ ነው።
No comments:
Post a Comment